ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ.ም የኤጲስ ቆጶሳት ሥርዐተ ሢመት በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል በታላቅ ክብርና ሥነ ሥርዐት ተፈጽሟል፡፡

ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የካህናት አስተዳደር መምሪያ በወጣው ዝርዝር መርሐ ግብር መሠረት ሐምሌ 9 ቀን 2009 ዓ.ም ከሌሊቱ 10፡00 ሰዓት ጀምሮ እስከ ጠዋቱ 2፡30 ድረስ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት መሪነት በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ተራዳኢነት የሥርዓተ ሢመቱና የቅዳሴው ሥነ ሥርዐት ተከናውኗል፡፡

ከዚያም ጥሪ የተደረገላቸው የክብር እንግዶች፣ የአድባራት አስተዳዳሪዎችና የገዳማት አበምኔቶች፣ በርካታ ካህናትና ምእመናን በተገኙበት የበዓሉ ሥነ ሥርዐት በዐውደ ምሕረቱ ቀጥሎ መርሐ ግብሩ በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ጸሎተ ቡራኬ ከተከፈተ በኋላ በደብረ አሚን አቡነ ተክለ ሃይማኖት ካህናትና ሊቃውንት ለበዓሉ የተዘጋጀው ጸሎተ ወንጌልና መዝሙር እንደተጠናቀቀ በሰንበት ትምህርት ቤት ዘማርያን ለበዓሉ ተስማሚ የሆነ ያሬዳዊ መዝሙር ቀርቧል፡፡ ቀጥሎም ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ በክልል ትግራይ ደቡባዊ ዞን ማይጨው ደቡባዊ ምሥራቅ ትግራይና የምሥራቃዊ ዞን ዓዲግራት አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በዓሉን አስመልክተው በገጽ 4 የሰፈረውን መግለጫ ሰጥተዋል፡፡ ከዚሁ በማያያዝ በአጫብር ሊቃውንት ለበዓሉ ተገቢ የሆነው ወረብ ከቀረበ በኋላ ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊና የደቡብ ምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ስለ ሥርዓተ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት አፈጻጸም መግለጫ አቀረቡ፡፡

ከዚያም ተሿሚዎቹ ኤጲስቆጶሳት በብፁዕነታቸው አማካይነት ቃለ መሐላ አደረጉ፡፡ ከዚህ በኋላ የኢፊዲሪን መንግሥት በመወከል በበዓሉ ላይ የክብር እንግዳ ሆነው የተገኙት ክቡር አቶ ካሳ ተክለ ብርሃን “ይህች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን በኪነ ጥበብና በትምህርት ዘርፍ ያበረከተችው አስተዋፅኦ ዘመን ተሻጋሪ በመሆኑ አሁንም እነዚህንና ጥንታዊ ቅርሶችን በክብር ጠብቃ ለትውልድ የማስተላለፍ ኀላፊነት አለባት፤ ቤተ ክርስቲያንዋ በመንፈሳዊ አገልግሎትዋ በኩል ለምእመኖቿ እያበረከተችው ካለው አስተዋፅኦ በተጨማሪ ለአገራችን እድገትና ልማት መሳካ ትም እያደረገችው ያለ እንቅስቅሴ የሚበረታታ ነው፡፡ በቀጣይነትም ለእድገታችን መሠረት የሆነውን ሰላም በማስጠበቅ ሐዋርያዊ ተግባርዋን በማጠናከር ለሀገራችን ብሎም ለዓለም ሰላም መስፈን ድርሻዋን ልትወጣ ይገባል” በማለት ሲያስገነዝቡ “አገራችን ታላቅ ነበርን፣ ታላቅም እንሆናለን” በሚል ወኔ በመነሣሣት የታሪክ ቀደምትነትዋን ለማስጠበቅና ከድህነት ለመውጣት እያከናወነቻቸው ባሉ ባለፈርጀ ብዙ ተግባራት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተገቢ ድርሻዋን እንድ ትወጣ ጥሪዬን እያቀረብኩ አዲሶች ተሿሚ አባቶች በምትሰማሩበት ሐዋርያዊ ተልእኮአችሁን ለማሳካት የምታደርጉት እንቅስቃሴ ሁሉ የተሳካ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እየገለጽኩ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ›› በማለት አቶ ተክለብርሃን ካሳ ንግግራቸውን ፈጽመዋል፡፡

የቅዱስነታቸው ሐዋርያዊ መመሪያ፣ ቃለ በረከት ቃለ ምዕዳን

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የኤጲስ ቆጶሳቱን ሢመት አስመልክተው ያስተላለፉትን ቃለ በረከት ሙሉ መልእክት የሚከተለው ነው፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣ ክቡራን ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ክቡራን የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የመምሪያና የድርጅት ኀላፊዎች፣ የገዳማትና የአድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ካህናት፣ ዲያቆናት፣ የሰንበት ት/ቤት ተማሪዎች፣ ክቡራን ምእመናንና ምእመናት፣ በአጠቃላይ በዚህ በዓለ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ላይ የተገኛችሁ ክቡራንና ክቡራት

በአምላካዊ ጸጋው መንፈሳውያንና ሥጋውያን መሪዎችን እየሾመ ፍጥረቱን የሚያስተዳድር እግዚአብሔር አምላክ ከኅሊና በላይ በሆነ አጠራሩ አርዑተ መስቀሉን ሊሸከሙ በጠራቸው ኤጲስ ቆጶሳት በዓለ ሢመት ላይ ተገኝተን ስሙን በመጥራት እንድናመሰግን ስለፈቀደልን እግዚአብሔር አምላካችንን እናመሰግነዋለን፡፡

“አኮ አንትሙ ዘኀረይክሙኒ አላ አነ ኀረይኩክሙ ወሤምኩክሙ ከመ ትሑሩ ወፍሬ ትፍረዩ፤ እኔ መረጥኋችሁ እንጂ እናንተ አልመረጣችሁኝም፤ አብ በስሜ የምትለምኑትን እንዲሰጣችሁ፣ ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ፣ ፍሬአችሁም ሊኖር ሾምኋችሁ”፡፡ (ዮሐ 15፡16)

ከዚህ ኀይለ ቃል መረዳት እንደሚቻለው በሕዝበ እግዚአብሔር ላይ ለአገልግሎት ወይም ለተልእኮ የሚሾመው ሥዩም በእግዚአብሔር ምርጫ የሚሾም መሆኑን ነው፡፡ ይልቁንም ለሃይማኖታዊ አገልግሎትና ተልእኮ የሚሾም ዐቢይ ኖላዊ እንደሌሎች ሥዩማን በተዘዋዋሪ መንገድ ሳይሆን፣ በቀጥታ በእግዚአብሔር ምርጫ የሚሾም መሆኑን ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን የመረጠበትንና የሾመበትን ሂደት ማየት ይቻላል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ቅዱሳን ሐዋርያትን መርጦ ሲሾም ዐቢይ ዓላማና ግብ ነበረው፤ ይኸውም ሐዋርያትእሱ በደሙ የዋጀውን የሰው ልጅ አስተምረውና አሳምነው፣ በሃይማኖትና በመልካም ሥነ ምግባር ገንብተው፣ ለእግዚአብሔር መንግሥት ብቁ የሆኑ ክርስቲያኖችን ለማብዛት ተግተው እንዲሠሩ ነው፡፡

በጌታችን ትምህርት መሠረተ ሐሳብ ይህ ድርጊት “መሄድና ፍሬ ማፍራት” ተብሎ ተጠቅሶአል፡፡ በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው ሹመት ማለት የሥራ መገልገያ መሣሪያ እንጂ የግል መገልገያ አይደለም፤ ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ይህንን አስመልክቶ ሲያስተምር “እስመ ኢመጽአ ወልደ ዕጓለ እመሕያው ከመ ይትለአክዎ ዘእንበለ ዳእሙ ከመ ይትለአክ ወየሀብ ነፍሶ ቤዛ ብዙኃን — የሰው ልጅ ሊያገለግሉት አልመጣም፤ ነፍሱን የብዙዎች ቤዛ አድርጎ በመስጠት ሊያገለግል እንጂ” ብሎአል፤ ሁላችንም እንደምንገነዘበው የአገልግሎት ሥራ ብዙ መሄድን ይጠይቃል፤ መውጣትን፣ መውረድን፣ መንገላታትን፣ ድካምን፣ ከዚያም አልፎ መሥዋዕትነትን ይጠይቃል፡፡

ይህንን የመሳሰለው ሁሉ ችለውና ታግሠው መንገዳቸውን የሚቀጥሉ ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን ብዙ ፍሬ ማፍራታቸው እንደማይቀር ልትሄዱና ፍሬ ልታፈሩ ሾምኋችሁ የሚለው የጌታችን ቃል አስረጅ ነው፡፡

ዛሬ በቤተ ክርስቲያናችን የተፈጸመው ሥርዐተ ሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ከላይ የተጠቀሰውን ትምህርተ ክርስቶስ መሠረት አድርጎ የተፈጸመ ነው፡፡ እግዚአብሔር ገና ከጥንቱ ከጠዋቱ ጀምሮ ሰውን መርጦ በከፍተኛ ኀላፊነት እንዳስቀመጠ በመጽሐፈ ፍጥረት የምንገነዘበው ነው፡፡ እግዚአብሔር ፍጥረቱን ያለ መሪ ወይም ያለ አገልጋይ የተወበት ጊዜም ፈጽሞ የለም፤ የቤተ ክርስቲያናችን ትልቅና ዕውቅ ሊቅ ቅዱስ ያሬድ ይህንን አስመልክቶ ሲናገር “ኢኀደጋ ለምድር እምቅድመ ዓለም ወእስከ ለዓለም እንበለ ካህናት ወዲያቆናት፤ ከዓለም አስቀድሞ፣ እስከ ዓለም ፍጸሜም ድረስ፣ ያለ ካህናትና ዲያቆናት ምድርን እንዲሁ አልተዋትም ” በማለት ያረጋግጣል፡፡

ይህ እውነት በፅንሰ ሐሳብ ታስቦ ወይም በቃል ብቻ ተነግሮ የቀረ ሳይሆን ዛሬም በዓለም ዙሪያ ሁሉ በየቀኑ እየተፈጸመ የሚገኝ ትዕይንት ነው፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ሥነ ጥበብ ለሦስት ሺሕና ከዚያም በላይ ስትገነባ የነበረችው ሀገራችን ኢትዮጵያም የዚህ መንፈሳዊ ጸጋ ባለቤት ናት፤ በሀገሪቱ ውስጥ የሚገኙ፣ የሚታዩና የማይታዩ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ፣ ባህላዊና ሥነ ምግባራዊ ዕሴቶች ሁሉ፣ ከቤተ ክርስቲያናችን እየተመዘዙና እየተመለመሉ በተሾሙ ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን ቅን አገልግሎት የተከናወኑ አኵሪ ሥራዎች እንደሆኑ የማይካድ ነው፡፡

አባቶቻችን ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን ይህንን የግንባታ ፍሬ በመላ ኢትዮጵያ ማፍራት የቻሉት የጌታችን ትምህርት መሪና ኀይል ሆኖአቸው ከምሥራቅ ወደ ምዕራብ፣ ከሰሜን ወደ ደቡብ ያለ ዕረፍት በመመላለስ፣ በመጓዝና በመሄድ እንደሆነ በምድሪቱ ገጽታ እንደ ኔት ወርክ ወይም እንደመረብ የተዘረጋው የቅዱስ ፍሬምናጦስ አቡነ ሰላማ፣ የቅዱሳን ነገሥታት አብርሀ ወአጽብሐ፣ የቅዱስ ያሬድ፣ የጻድቁ አቡነ ተክለ ሃይማኖትና የሌሎች ቅዱሳን አበው ታሪክና የቅድስና ተግባር ዐቢይ ማስረጃችን ነው፡፡

በዛሬው ዕለት በእግዚአብሔር ፈቃድ የተከናወነው የሢመተ ኤጲስ ቆጶሳት ዓላማም ይህንን ከእግዚአብሔር የተረከብነውን ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ጸጋ፣ በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ከዳር እስከ ዳር በማቀጣጠል፣ መላ ሀገራችንን ከዚያም አልፎ ዐቅም በፈቀደ መጠን መላ ዓለምን በትምህርተ ወንጌል ለማጥለቅለቅ ነው፤ ይህ ዐቢይ ተልእኮ ድንበር የለሽ የሆነ የእግዚአብሔር ሕገ መንግሥት እንደመሆኑ መጠን ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ መላው ዓለምን በትምህርተ ወንጌል እያዳረሰች ትገኛለች፤

በመሆኑም ቤተ ክርስቲያናችን በደረሰችባቸውና ለወደፊቱ በምትደርስባቸው ሀገሮች ሁሉ ተልእኮውን የሚፈጽሙ ዐበይት ልኡካን ማለትም በሐዋርያቱ እግር የሚተኩ ብፁዓን አባቶች ማስፈለጉ የግድ ነውና በዚህ እሳቤ በዛሬው ዕለት የዐሥራ አምስት ኤጲስ ቆጶሳት ሢመተ ሐዋርያነትን እውን አድርጋለች፤ በዚህም እግዚአብሔር ለሠራልን ሥራ ደስታችን ወደር የለውም፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስትነጻጸር በሁሉም መስክ ማለትም በምእመናን ብዛት፣ በጽንዐ ሃይማኖት፣ በሐዋርያዊ ትውፊት፣ በአበው ቀኖና፣ በተቀደሰ ሃይማኖታዊ ባህልና በሥርዐተ አምልኮ አፈጻጸም ቀዳሚውን ስፍራ ይዛ የምትገኝ ቤተ ክርስቲያን ስለመሆኗ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በአበው ሐዋርያዊ ተጋድሎ ጠብቃ ያቆየችውን ይህን ሀብተ መንፈስ ቅዱስ እንዳለ ጠብቆ ለመጪው ትውልድ ለማስተላለፍ ብቃትና ተነሣሽነት ያላቸው ኤጲስ ቆጶሳት በመሾም ወደ ሥራ ማሰማራት ለነገ የማይባል የቤተ ክርስቲያናችን ተቀዳሚ ተግባር ነው፡፡

ስለሆነም በዛሬው ዕለት የተፈጸመው የኤጲስ ቆጶሳት ሹመት ይህንን ሐዋርያዊ ተልእኮ በማስፋፋትና በማጠናከር ረገድ የበኩሉን ሚና ይጫወታል ተብሎ ታምኖበታል፡፡ ከዚህም ጋር በአሁኑ ጊዜ የሃይማኖትና የሥነ ምግባር ጉዳይ እጅግ ትኵረት የሚያስፈልገው ከመሆኑ አኳያ፣ የዘመኑ ትውልድ በሃይማኖት የጸና፣ በሥነ ምግባር የቀና፣ ለሀገርና ለወገን ክብር የቆመ እንዲሆን፣ የቤተ ክርስቲያን አባቶች አስተምህሮና አርኣያነት በጣም አስፈላጊ በመሆኑ ለችግሩ መቃለል ይበጃል ተብሎ የተፈጸመ ነው፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅኝት የተቀረጸ ሕዝብ ባለቤት በመሆኗ፣ ለሃይማኖት፣ ለሥነ ምግባር፣ ለብልጽግና፣ ለልማትና ለአንድነት የተመቸ ሕዝብ አላት፤ ይህን የተቀደሰ ባህልና ሥነ ምግባር ለመጠበቅ ከቤተ ክርስቲያን አባቶች ብዙ ይጠበቃል፤ በተለይም ብፁዓን ሊቃ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት የመጨረሻውን የቤተ ክርስቲያን መዓርገ ሥልጣን የተረከቡ በመሆናቸው ካህናቱን፣ ሕዝቡንና ሌላውን ኢትዮጵያዊ ወገን በፍቅርና በአባትነት መንፈስ በማቅረብ ሁሉም በሰላም፣ በወንድማማችነት፣ በመከባበር፣ በመተማመንና በመቻቻል አብሮ እንዲኖር፣ በዓለም የተደነቀውን የሕዝባችን አንድነትና ነፃነት በልማት ኀይል እየተጠናከረ ትውልዱ እንደ አባቶቹ ደማቅ ታሪክ ሠርቶ እንዲያልፍ ያልተቈጠበ ጥረት ማድረግ ይኖርባቸዋል፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን በሃይማኖት አስተምህሮና ይዘት፣ በቀኖና ቤተ ክርስቲያንና በሐዋርያዊ ትውፊት፣ በሥርዐተ አምልኮ አፈጻጸምና በቅዱስ ባህል ግንባታ እንከን የለሽ ብትሆንም፣ በአስተዳደር፣ በፋይናንስና በንብረት አያያዝ፣ በምእመናን እንክብካቤና በሐዋርያዊ ተልእኮ ክንውን፣ በእናቶችና በወጣቶች አያያዝ ከዘመኑ ጋር መራመድ አለመቻልዋ የወቅቱ የቤተ ክርስቲያናችን ተግዳሮት ሆኖ ይገኛል፡፡

ይህንን ተግዳሮት ከሥር መሠረቱ መንግሎ በመጣል ወደሚፈለገው የልማት፣ የእድገትና የመልካም አስተዳደር ለመሸጋገር የአሁኑ ሥዩማን ኤጶስ ቆጶሳት ከቀደሙት ሊቃነ ጳጳሳት ጋር በመቀናጀት ጒልህ ሚና ትጫወታላችሁ የሚል እምነት በሕዝቡም በብፁዓን አባቶችም ተጥሎባችኋል፡፡

ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በየሀገረ ስብከቱ በመንበራቸው ተገኝተው ለአንድ አፍታ እንኳ ከሕዝቡ ጎን ሳይለዩ ሠርተው የሚያሠሩ፣ ሁሉንም ወገን በእኩል ዐይን የሚያዩና የሚያስተናግዱ፣በሕዝቡ መካከል ሰላምን የሚሰብኩ፣ከማንኛውም ርእዮተ ዓለም ደጋፊነት የተለዩናከጣልቃ ገብነት የጸዱ፣ ከሁሉ በላይ ደሞ ለአንዲት ሉዓላዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት መከበር በጽናት የቆሙ አባቶችን ትሻለች፡፡ ከዚህ አንጻር የአሁኑ ሥዩማን ኤጲስ ቆጶሳት ከማንም ይሁን ከማን በላይ ለቤተ ክርስቲያን ክብርና ሁለንተናዊ አንድነት በጽናት ልትቆሙ በእግዚአብሔር መጠራታችሁን ልትዘነጉ አይገባም፡፡

አባቶቻችሁ ቅዱሳን ሐዋርያት “ናሁ ኀደግነ ኵሎ ወተሎናከ — እነሆ ሁሉን ትተን ተከተልንህ” ብለው የገቡትን ቃል ኪዳን እናንተም እንደገባችሁበትና አርዑተ መስቀሉን እንደተሸከማችሁ አውቃችሁ በተኲላዎች ጫካ ውስጥ በልበ ሙሉነት ማለፍ ይጠበቅባችኋል፡፡

ዓለሙ በበኩሉ ያለና የሌለ ኀይሉን አግበስብሶ እንደሚታገላችሁ አትርሱ፤ ነገር ግን የድል አድራጊው ጌታ ሠራዊት ናችሁና የመጨረሻው ድል የእናንተ መሆኑን አትጠራጠሩ፡፡

ከዛሬ ጀምሮ ለእናንተ አባት፣ እናት፣ ወንድም፣ እኅት ፣ሀብት፣ ንብረት፣ ዘመድ፣ ወገን የላችሁም፤ በዚያ ምትክ እግዚአብሔር የኢትዮጵያን ሕዝበ ክርስቲያን የእናንተ ልጆች አድርጎ በዛሬው ቀን ማስረከቡን ልብ ብላችሁ አስተውሉ፤ ተቀበሉትም፤

ይህ ወደር የሌለው ታላቅ ስጦታ በሚገባ ሊያዝና ትርፋማ ሊሆን ይገባል፤ምክንያቱም የስጦታው ባለቤት መክሊቱን ከነትርፉ አስረክቡ የሚልበት ጊዜ አለና ነው፡፡ እግዚአብሔር የሰጣችሁን ሕዝብ በቀንም በሌሊትም ከፊቱ ሳትለዩ በሁለንተና ሕይወቱ ባለ ዐቅማችሁ ሁሉ ሳትለግሙ አገልግሉት፤ ከስደት፣ ከእንግልት ተገላግሎ የልማት ኀይል በመሆን ሀገሩን እንዲገነባ፣ ሃይማኖቱንና ባህሉን እንዲጠብቅ፣ ያለመታከት አስተምሩት፡፡

ከቆሎ ትምህርት ቤት ጀምሮ እስከ ኤጲስ ቆጶስነት ድረስ እየመገበና እየተንከባከበ ለታላቅ ክብር ያበቃችሁን ሕዝብ የልቡን ሃይማኖታዊ ትርታ እያዳመጣችሁና በወቅቱ እየደረሳችሁ አስተምሩት አጽናኑት፡፡ ልጆቹን በተኵላዎች ከመነጠቅ አድኑለት፤ ወጣቱ ትውልድ ከሐሽሽ፣ ከአደንዛዥ ዕፅ፣ ከሱሰኝነት፣ ከሥራ ፈትነትና ከመጤ ጎጂ ባህል እንዲላቀቅ አድርጉ፤ የኢትዮጵያ ሕዝበ ክርስቲያን በአሁኑ ጊዜ ከሃይማኖት አባቶች የሚፈልገው ይኸው ነው፡፡

የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ጉዳይ ሁሌ በዐይናችሁ እንደተንጠለጠለ ነገር ፋታ የማይሰጣችሁ ይሁን፤እርግጥ ነው በዚህ ሐዋርያዊ ጒዞአችሁ ብዙ መሰናክሎች እንዳሉ አይዘነጋም፤ ነገር ግን ሁሉም ችግሮች ከሞት በታች እንጂ ከሞት በላይ አይደሉምና ከሐዋርያዊ ተልእኮአችሁ የሚገታ ነገር ምንም አይኖርም፤ ምክንያቱም አሁን የገባችሁት ቃል ኪዳን እስከ ሞት ድረስ ለመጋፈጥ እንደሆነ እናንተው ራሳችሁ ታውቃላችሁና ነው፤ ታድያ ለሞት ያላመነታ አባት ከሞት በታች ለሆኑ ችግሮች መንበርከክ እንዴት ሊሆን ይችላል?

በመጨረሻም፤ በዛሬው ዕለት በሐዋርያዊ ኀላፊነት የተሾማችሁ ኤጲስ ቆጶሳት ከአሁኗ ሰዓት ጀምሮ በተመደባችሁበት ሀገረ ስብከት ተገኝታችሁ ከሚመለከታቸው መንግሥታዊና ሕዝባዊ ድርጅቶች ጋር በመቀናጀትና በመተባበር ደረጃ በደረጃ የሕዝቡን መንፈሳዊ፣ማኅበራዊና ልማታዊ ፍላጎት በማሟላት ተግታችሁ እንድትሠሩ፣ በየዞኑ የምትገኙ መንግሥታዊ እና ሕዝባዊ ድርጅቶች፣ እንደዚሁም ጠቅላላ ሕዝቡ፣ በተለይም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ለአዳዲሶቹ ኤጲስ ቆጶሳት ሙሉ ድጋፍና እገዛ በማድረግ ከጎናቸው እንድትሰለፉ አደራ እያልን መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡