ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በአባቶች መካከል በተፈጠረው ልዩነት የተላለፈው ቃለ ውግዘት ተነሣ
ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በአባቶች መካከል በተፈጠረው ልዩነት የተላለፈው ቃለ ውግዘት ተነሣ ይኽንኑ አስምልከተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቅዱስ ሲኖዶስ ወሳኔ በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል፡፡
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅም የታሪክ ዘመኗ አንድነቷን ጠብቃ፤ የሀገሪቱንም አንድነትና ነፃነት በማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅ ስታደርግ ኑራለች፤ አሁንም ከማድረግ የተቈጠበችበት ጊዜ የለም፡፡
ይህች ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ከብዙ ዘመን በኋላ ከራስዋ ሊቃውንት መካከል መርጣ ከኤጲስ ቆጶስነት እስከ ፓትርያርክነት ለመሾም የበቃች ቢሆንም ከሁለት ዐሥርት ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ አላስፈላጊ ምክንያት ያልተጠበቁ ችግሮች መከሠታቸው አልቀረም፤ እነዚህን ችግሮች በውይይት፤ በሰላምና በፍቅር በማስተካከል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በጋራ ማስጠበቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ ከውድ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ወጥተው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ውሳኔን አሳልፎአል፡፡
ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ልኡካንን ለአምስተኛ ጊዜ ወደ ሰሜን አሜሪካ እንዲሄዱ በማድረግ፤ ልኡካኑ በቦታው ተገኝተው፤ ተገቢውን ውይይት አካሂደው፤ ለውጤት የሚበቃ ነጥብ መዝግበው የተደረሰበትን የሚያስረዳ መግለጫን አቅርበዋል፡፡
ከቀረበው የዕርቀ ሰላሙ የጋራ ስምምነት ሰነድ ላይ መረዳት እንደተቻለው፦
ሀ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ሆኖ፤ በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ቦታ ተዘጋጅቶ፤ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ በክብር እንዲቀመጡ፤ የሥራ ድርሻን በተመለከተም፤ ጸሎትና ቡራኬን በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን በተመለከተም በሕገ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ መሠረት የአስተዳደር ሥራን እየሠሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ ሆኖ፤ የሁለቱም ፓትርያርኮች ስም የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ቦታ ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሣ የሚሉትና የመሳሰሉት ዐበይት ነጥቦች በልኡካኑ መግለጫ ተመዝግበው እንደሚገኙ ምልአተ ጉባኤው ተገንዝቧል፤ ከዚህ ግንዛቤ በመነሣት በፊደል ተራ ቁጥር ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፤
1. በውጭ ሀገር በሚኖሩ አባቶችና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል የነበረው መለያየት ለውግዘት በሚዳርግ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ አሁን ግን ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር ነውና ብዙ ጊዜ ሲደከምበት የቆየው ታሪካዊው ዕርቀ ሰላም ለሠመረ ውጤት በመብቃቱ በጋራ ስምምነቱ መሠረት ጳጒሜን 2 ቀን 1984 ዓ.ም.፤ መስከረም 15 ቀን 1985 ዓ.ም. እና ጥር 25 ቀን 1999 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቃለ ውግዘቱ ተነሥቶአል፡፡
2. ከልዩነት በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትም በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት በቅዱስ ሲኖዶ ውሳኔ ተመድበው እንዲያገለግሉ ሆኖ፤ ከልዩነት በኋላ የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትን፤ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተም ስያሜያቸው እንዳለ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉረ ስብከት ተመድበው ይሠሩ ዘንድ ምልአተ ጉባኤው ተቀብሎአቸዋል፡፡
3. በአጠቃላይም በልኡካኑ የጋራ መግለጫ በተዘረዘሩት ነጥቦች ጥልቅ ውይይት በማካሄድ የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት በበለጠ እንዲጠናከር፤ የሀገራችን ሰላምና መረጋጋት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችል ሁኔታ ላይ የበኩሉን ድርሻ መፈጸም እንዳለበት በማመን በመግለጫው ከ1-6 ተራ ቊጥር የተዘረዘሩትን ምልአተ ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
4. በመጨረሻም ይህ የቤተ ክርስቲያናችን አሳሳቢ ጉዳይ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሲከታተሉ የቆዩትን የተለያዩ የኮሚቴ አባላትን፤ ማኅበረ ካህናቱንና ማኅበረ ምእመናንን በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል የተከሠተው መለያየት የሀገሪቱ ችግር ጭምር መሆኑን በመገንዘብና ትኵረት በመስጠት ውድ የሀገር መሪነት ጊዜያቸውን ሠውተው ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው በታሪካዊው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ላይ በመገኘት አስተጋባኢና አሰባሳቢ የሆነ መመሪያን በመስጠት ብዙ ዘመን የተደከመበት ጉዳይ ፈጣን መፍትሔን እንዲያገኝ ላደረጉት ለኤፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍ ያለ ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡