32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ ዓመታዊ ጉባኤ ከጥቅምት 4 እስከ 11 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡
“ከሁሉ በፊት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና በቤተ ክርስቲያናችን የአመራር አካላት በሙሉ እንደተለመደው ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ አክብራችሁ እንኳን በደኅና መጣችሁ፡፡
ይህ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ጉባኤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ርእሰ ከተማ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር በዓመት አንድ ጊዜ እየተሰበሰብን በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በአጠቃላይም በሁለንተናዊ እድገት ላይ እየተወያየን የሚጠበቅብንን ግዳጅ ስንወጣ እነሆ! ዛሬ ለሠላሳ ሁለተኛው መደበኛ ስብሰባ ለመድረስ በቅተናል፡፡
በቃለ ዐዋዲው የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ እየታገዘ ሰበካ ጉባኤ አስተዳዳር ከሚሠራው የስብከተ ወንጌል ክፍል አንዱ አካል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያናችን የደም ሥር የሆነውን የስብከተ ወንጌሉን ተግባር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማሳደግ ይጠበቅብናል፣ ለማስረጃም ያህል አንድ ሰው ሕይወት የምትሰጠው ነፍሱ ከተለየች በዓለም ላይ የመኖር ተስፋ ስለሌለው የሚጠብቀው ዕድል ወደ ዐፈርነት መለወጥ ብቻ ነው፡፡
እንደዚሁ ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችን ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ ባለው መዋቅር በስብከተ ወንጌል ካልተጠናከረች የሚጠበቅባትን ያህል አበርክታለች ለማለት አያስደፍርም፣ እንግዲህ ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲጠብቅ እንደቆየ ሁሉ አሁንም የስብከተ ወንጌሉን ተግባር ለማጠናከር መቀጠል አለበት ስንል ቢያንስ ሦስት ዐበይት ነጥቦችን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡
ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ፡- የስብከተ ወንጌል ሠራተኞች ብቃት ባላቸውና በሠለጠኑ መምህራን በተደገፈ የወንጌል ትምህርት መሠልጠን አለባቸው፡፡ እነዚህ ለተልእኮ የሚፋጠኑ አስተማሪዎች የቈራጥነት መንፈስ ያልተለያቸው፣ የተቈርቋሪነት ባሕርይ ያደረባቸው መሆን አለባቸው፡፡
የገንዘብ (ፋይናንስ) አስተዳደር ሁኔታን በተመለከተ፡- የፋይናንስ ዐቅምን ማጠናከር የስብከተ ወንጌሉን ተግባር በበለጠ ማፋጠን ያስችላል፡፡ የፋይንስ ዐቅም ባልጎለበተበት ሁኔታ የሥራውን ድኅንነት ለመቈጣጠርም ሆነ ሂደቱን ለማፋጠን አስቸጋሪ እንደሚሆን ስለሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በአሠራር እየቀደሙ የሚታዩት ተከታዮቻቸው የሚከፍሉትን የአስተዋፅኦ ገንዘብ በማጎልበት እንደሆነ ከጉባኤው አመለካከት ይሠወራል ብለን ባንገምትም በበኩላችንም ሕዝበ ክርስቲያኑን ጠንክረን ማስተማርና ማስተባበር ይጠበቅብናል፡፡
መልካም አስተዳደርን በሚመለከት፡- ኀላፊነት ሐቀኝነትና ተጠያቂነት የተሞላበት መልካም አስተዳደር ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ እንዲሰፍን ማድረግ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ መልካም አስተዳደር ከሌለ ሁሉም ነገር ከንቱ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በቅዱስ መጽሐፋችንም ሲነገር የኖረ አሁንም እየተነገረ ያለ ስለሆነ ለመልካም አስተዳዳር መስፈን ምዕራፍ ከፋች በሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ልናደርገው የሚገባንን ምግባረ ሠናይ ሁሉ በመፈጸምና በማስፈጸም ለቤተ ክርስቲያናችን ያለንን ደጀንነት መግለጽ ይጠበቅበናል፡፡
ስለዚህ በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁት፡- የየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች፣ የየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ በአጠቃላይም የጉባኤው ተሳታፊዎች ሁላችሁ ይህ ዓመታዊ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ለግብ እንዲበቃ፣ የምታደርጉት ጥረት እንዲሳካ እንጸልያለን፡፡
እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ፡፡”