ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ በቫቲካን በቅድስት መንበር የምሥራቅ አብያተ ክርስቲያናት ክፍል ኃላፉ ብፁዕ ካሪዲናል ክላውዲዮ ጉጀሮቲን በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
ዛሬ ግንቦት 25 ቀን 2018 ዓም ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በቫቲካን በቅድስት መንበር የምሥራቅ ክርስቲያናት ክፍል ኃላፉ ብፁዕ ካሪዲናል ክላውዲዮ ጉጀሮቲን በቢሮአቸው ተቀብለው አነጋገሩ፡፡
ቅዱስነታቸው ልዑካኑን “ወደ ኢትዮጵያ ለጉብኝት እንኳን ደህና መጣችሁ፣ ወደ መንበረ ፓትርያርክ ለመጎብኘት ስለመጣችሁ ደስ ብሎናል፤ መልካም የጉብኝት ወቅት ያድርግላችሁ” በማለት መልካም ምኞታቸውን ለልዑካኑ ገልጸዋል፡፡ .
ብፁዕ ካሪዲናል ክላውዲዮ ጉጀሮቲም እንደተናገሩት “በመጀመሪያ መልእክቴ በፖፕ ሊዮ የተላከ የፍቅር መልእክት ለማድረስ ነው፡፡ ወደዚህች ምስጠራዊ ሀገር፣ የብዙ ሰማዕታት፣ መነኮሳት፣ የብዙ መንፈሳውያን ሀገር ወደ ሆነችው ኢትዮጵያ የመጣሁት” ሲሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ ካርዲናል ክላውዲዮ አያይዘውም “በዓለማችን በክርስቲያኖች ላይ እየተላለፈ ያለው ጥላቻ እየጨመረ መጥቷል፤ በዚህ ጉዳይ በቫቲካን ያለንም ሐሳብ ውስጥ ገብተናል፤ ክርስቲኖችን ለመታደግ በአንድነት አብረን መሥራት አለብን” ሲሉ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡
በመጨረሻም ቅዱስነታቸው እንደተናገሩት “ሁላችንም በችግር ውስጥ ነው ያለነው፤ በዚህ ወቅት በኅብረት መሥራት፣ መነጋገር አስፈላጊም፣ ወቅታዊም ጉዳይ ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች ያለን መሣሪያ ጸሎትና ምህላ ብቻ ነው፡፡” ሲሉ አባታዊ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል፡፡

