ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ: ሊቀጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ በኢትዮጵያ የጣልያን አምባሳደር ሆነው የተሾሙትን አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ (Sem Fabrizi) በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወእጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በኢትዮጵያ አዲሱ የኢጣልያ አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ በጽሕፈት ቤታቸው ተቀብለው አነጋገሩ።
በውይይቱ ወቅት ቅዱስ ፓትርያርኩ ለአዲሱ ተሿሚ አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ የእንኳን ደህና መጡ መልእክት ካስተላለፉ በኋላ፣ መልካም የሥራ ዘመን እንዲሆንላቸው ተመኝተዋል። ቅዱስነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት መሆኗን ጠቅሰው፣ ከጣልያን ጋር ያሏት ታሪካዊ ግንኙነቶች ይበልጥ ተጠናክረው እንደሚቀጥሉ ገልጸዋል።
ቅዱስነታቸው በውይይቱ ወቅት ባስተላለፉት ጥልቅ የሰላም እና የሰብአዊነት መልእክት፤ ዓለማችን ማንኛውም ፍጡር የሃይማኖት ልዩነት ሳይኖርበት በእኩልነት፣ በመከባበር እና በሰብአዊነት አስተሳሰብ ሊኖርባት የተሰጠች መሆኗን ገልጸዋል። በመሆኑም ሕይወታችንን በሰላማዊ መንገድ መምራት እንደሚገባ ጠቅሰው፤ “እኛ የሃይማኖት አባቶች ሁሌም በትጋት በሀገራችን ብሎም በመላው ዓለም ሰላምና ፍቅር እንዲሰፍን እንጸልያለን” ብለዋል።
አምባሳደር ሴም ፋብሪዚ ከቆይታቸው በኋላ ለብዙኃን መገናኛ ድርጅት ጋዜጠኞች በሰጡት መግለጫ፤ ከቅዱስ ፓትርያርኩ ጋር መወያየታቸው እንዳስደሰታቸው ጠቁመው፣ ውይይቱ በሁለቱ ሀገራት መካከል ያለውን ጥንታዊና ታሪካዊ ግንኙነት ይበልጥ የሚያጠናክር መሆኑን ገልጸዋል።
አምባሳደሩ አክለውም፣ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን በሀገሪቱ ማኅበራዊ ትስስር እና የታሪክ ግንባታ ውስጥ ያላትን ሚና ከፍተኛ ግምት እንደሚሰጡት ተናግረዋል።
እንዲሁም አምባሳደሩ ይህንን የቆየ ግንኙነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ጣሊያን በሰላምና በልማት ዘርፎች ላይ ከቤተክርስቲያኗ ጋር በትብብር ለመስራት ቁርጠኛ መሆኗን ጠቁመዋል። በተለይም ከሀገራቸው መንግሥት ጋር በመሆን በዘላቂ ሰላም ዙሪያ ይበልጥ እንደሚሠሩ አመላክተዋል።

“መልእክተ ቅዱስ ፓትርያርክ”

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ አምላክ
አሜን !!
‹‹ወነአምር ከመ ለእመሂ ተነሥተ ቤተ ማኅደርነ ዘበምድር ዘውእቱ ሥጋ ብነ ሕንጻ በኀበ እግዚአብሔር በሰማያት ዘኢገብሮ እደሰብእ፡-
በምድር ያለው ማደሪያ ቤታችን ቢፈርስም በሰማይ በእግዚአብሔር ዘንድ የሰው እጅ ያልሠራው ዘለዓለማዊ ቤት እንዳለን እናውቃለን፡፡›› (2ቆሮ. 5፡1)
በልዩ ልዩ ጊዜያት ዐረፍተ ዘመን የገታቸውን ወገኖች ልንሸኝ እንችላለን፤ የአንዳንድ ሰዎች ሞት ግን ከልብ ቶሎ የማይወጣ፤ ለዘመናትም በህሊና መዝገብ ላይ የሚቆይ ነው፡፡
በመሆኑም የሚከተሉት ሃይማኖት ወይም መርጠው ያልተወለዱበት አካባቢ እንደበደል ተቆጥሮባቸው ከየአቅጣጫው በሚሰነዘረው ጥቃት በሚገደሉ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች፣ ምእመናን በአጠቃላይ የሰው ልጆች ኀዘን ልባችን በትካዜ ውስጥ በሚገኝበት በዚህ ወቅት በመንፈሳዊ ሕይወቱ እና በትጋቱ ለቤተ ክርስቲያን ተስፋ የነበረው፤ ለበርካታ ዓመታትም በገጠር፣ በከተማ፣ በሀገር ውስጥ እና ከሀገር ውጭ እየተዘዋወረ ወንጌለ መንግሥትን ሲያስተምር የቆየው የመንፈስ ቅዱስ ልጃችን መ/ር ዘለዓለም ወንድሙ ለመንፈሳዊ አገልግሎት በተጓዘባት ሰሜን አሜሪካ ባጋጠመው ሕመም ከዚህ ዓለም ድካም በሥጋ ማረፉን ስንሰማ ታላቅ ድንጋጤ ፈጥሮብናል፡፡
በእርግጥ መምህር ዘለዓለም ወንድሙ ስመ ጥምቀቱ ወልደ ሰማእት በሥጋ ከእኛ ቢለይም ያለዋጋ የተቀበለውን የእግዚአብሔር ቃል ለምእመናን በማስተማር አደራውን በሚገባ ተወጥቶአልና በሰማይ ወደሚጠብቀው ዘለዓለማዊ ስፍራ በክብር እንደሚገባ እናምናለን፡፡
የመልካም ሰዎች መጉደል ለሀገር በተለይም ደግሞ ለቤተ ክርስቲያን የነገ ዕጣ ፈንታ የሚያስጨንቅ ቢሆንም ሁሉን የሚችል አምላክ ተተኪዎችን እንዲያዘጋጅልን በመጸለይ፤ ለመንፈስ ቅዱስ ልጃችን ቤተሰቦች፣ ወዳጅ ዘመዶችና ምእመናን መጽናናትን እየተመኘን አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር አምላክ የአገልጋዩ ወልደ ሰማዕትን ነፍስ በመንግሥቱ ያሳርፍልን፤
“እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ኣሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
የካቲት 30 ቀን 2018 ዓ.ም.
አዲስ አበባ፣ ኢትዮጵያ

ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣ በ13ኛው ዓመት በዓለ ሢመተ ፓትርያርክ በዓል አከበባር ሥነ ሥርዓት ላይ ያስተላለፉት አባታዊ ሙሉ መልእክት

መልእክተ  ቅዱስ ፓትርያርክ
ስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ አምላክ ኣሜን !!

ብፁዕ አቡነ ሳዊሮስ የጠቅላይ ቤተክህነት ጽ/ቤት ዋና ስራ አስኪያጅ፣
የደቡብ ምዕራብ ሸዋና የሸገር ከተማ ኣህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ዲዮስቆሮስ የቅዱስ ሲኖዲስ ዋና ጸሓፊና የራያ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ሕርያቆስ የአዲስ አበባ እና የሓዲያ ስልጤ ኣህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ፣
የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
ክቡራን የመንግሥት ከፍተኛ ባለሥልጣናት፣
ክቡራን ኣምባሳደሮችና የኮር ዲፕሎማቶች፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተክህነት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኃላፊዎች፣
የተከበራችሁ የቤተ ክርስቲያናችን ኣገልጋዮችና ሰራተኞች፣ምእመናንና ምእመናት፣
በኣጠቃላይ በዚህ በዓለ ሢመተ ክህነት የተገኛችሁ በሙሉ፤
ጸጋውን እያበዛልን ከዚህ ዕለት ያደረሰን እግዚአብሔር ኣምላካችን እንኳን ለዓሥራ ሦስተኛው በዓለ ሢመተ ክህነታችን ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
“ወቦቱ ረከብነ ጸጋ ወተሠየምነ ሓዋርያተ ከመ ናስምዖሙ ለኣሕዛብ ወይእመኑ በስሙ፤በስሙ ያምኑ ዘንድ ቃለ ወንጌልን ለኣሕዛብ እንድናሰማ የተሾምንበት ሓዋርያነት ከሱ የተገኘ ጸጋ ነው›› (ሮሜ.፩÷፭)፤
ይህ ጥቅስ ሓዋርያት ተብለን የተሾምንበትን ፍሬ ነገር ይገልጻል፤የተሾምንበትም ዋና ምንክያት ስሙን ለኣሕዛብ ልናስተምር እንደሆነ ያስረዳል፤የማስተማር ውጤት ደግሞ ሰዎች በስሙ ኣምነው እንዲድኑ ማድረግ እንደሆነ ያመለክታል፤የካህናተ እግዚአብሔር ዓቢይ ተልእኮም ይህ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፤
በቤተ ክርስቲያናችን ብዙ የኣገልግሎት ዘርፎች ቢኖሩም፣ መዳረሻቸው ቃለ ወንጌልን ለፍጥረት ሁሉ ማብሰር ነው፤ የክህነት ኣገልግሎታችን በተመደበለት ቦታ ላይ ያለ መሆኑን መመዘን ያለበትም በዚህ መለኪያ ነው፤ ዛሬ የምናከብረው በዓለ ሢመትም ይህንን ተልእኮ ማእከል ያደረገ ነው፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣
ክቡራን እንግዶች!

የዘመናችን ሓዋርያት የሆን ሁላችን ቃለ ወንጌልን በትክክል ለሕዝቡ እንዲደርስ ማድረግ ይጠበቅብናል፤ እሱን በኣግባቡ ማስተላለፍ ከቻልን፣ማኅበረ ሰባችንን ከልዩ ልዩ ተፈናዎች መታደግ እንችላለን፤ ከዚህም ጋር በሀገራችንም ሆነ በዓለማችን በየጊዜው ብቅ ጥልቅ የሚሉ ፈተናዎችን ለመከላከል በንጹህ ልቡና በትሑት ሰብእና ሆነን ወደ እግዚአብሔር እንጸልይ፤እንደዚሁም ከግል ፍላጎትና ኣስተሳሰብ በጸዳ ሁናቴ ቃለ ወንጌል በማስተማር ኅብረተሰቡን በሃይማኖትና በሥነ-ምግባር እንጠብቅ፤ ይህንን በብቃት ለመወጣትም ከሁሉ በፊት ራሳችንን ክደን ለእግዚአብሔር ክብርና ለሰው ልጆች የተሟላ ደኅንነት በጽናት እንቁም፤

በመጨረሻም፡-
ቤተ ክርስቲያን የጣለችብንን ከፍተኛ ኃላፊነት ተገንዝበን የእግዚአብሔር ሠራዊት የሆኑትን ምእመናንንና እግዚአብሔርን በቅንነት እናገልግል በማለት ኣባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፤ በድጋሚ እንኳን ለዓሥራ ሦተኛው በዓለ ሢመተ ክህነት በሰላም ኣደረሳችሁ!

“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
ወስብሐት ለእግዚአብሔር
ኣሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ
ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
የካቲት 24 ቀን 2018 ዓ,ም
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ