ግንቦት 10 ቀን 2014 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ብፁዕ አቡነ ያሬድ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የምሥራቅ ጎጃምና የአርሲ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ እንዲሁም የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኀላፊ፤
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣ የሲዳማ፣ የጌድኦ፣ የአማሮና ጉርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
በአጠቃላይ በዚህ ታላቅ ቅዱስ ጉባኤ የተገኛችሁ በሙሉ፦
በዓለም ውስጥ የሰላምና የአንድነት ማእከል ሆና ታገለግል ዘንድ ቤተ ክርስቲያንን በክቡር ደሙ ቀድሶ የሰጠን ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አራት ዓ.ም የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ አደረሳችሁ!
“ወሩጹ ኀበ ሰላም ምስለ ኵሉ
— ከሁሉ ጋር ወደ ሰላም ሩጡ።”
(ዕብ. 12፥14)
ሁላችንም እንደ ምንገነዘበው የቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ዓለም መመሥረት ዋና ዐላማ ሕዝብንና አሕዛብን በክርስቶስ ትምህርተ ሰላም፣ አገናኝታ፣ አቀራርባና አንድ አድርጋ በሃይማኖት ለእግዚአብሔር መንግሥት ንጹሕ ወገንን ማቅረብ ነው፡፡ ለዚህ ለተቀደሰ መለኮታዊ ዐላማ እውን መሆን ሲባል ከራሱ ከባለ ቤቱ ከጌታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ አንሥቶ ብዙ ቅዱሳን አበው የደም ዋጋ ከፍለዋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በዚህ ክቡር ደም አማካኝነት ድል በድል እየተሻገረችና እየተራመደች እስካሁን ደርሳለች ዛሬ በክብር የተቀመጥንበት ወንበርም የዚህ ደም ውጤት እንደ ሆነ አሳምረን እናውቃለን፡፡ በየጊዜው በኀላፊነት የተቀመጡ ቅዱሳን አበው መከራ መስቀሉን ፈርተውና ተሠቅቀው ቢያፈገፍጉ ኖሮ ይህ እኛ ዛሬ የተሰየምንበት ክብረ መንግሥተ እግዚአብሔር የሚገኝ አልነበረም፡፡ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን ጒዞ አንድ ተብሎ ሲጀመር በፍኖተ መስቀል ስለ ሆነ ፍኖተ መስቀሉ ተቋርጦ አያውቅም፤ ለወደፊትም ይቋረጣል ተብሎ አይጠበቅም፡፡
በዚህ ፍኖት የሚጓዙ ቅዱሳንም አይታጡም ብቻ ሳይሆን እጅግ በጣም ብዙ ናቸው፤ ፍኖተ መስቀል በልዩ ልዩ ዕንቅፋቶችና መሰናክሎች የተሞላ፣ አባጣ ጐርባጣ፣ ወጣ ገባ ቢሆንም መጨረሻው ስኬትና ድል ነውና ለፍጹም ዘለዓለማዊ ሰላምና አንድነት ሲባል የሚጓዙበት መንገድ ነው፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
የዘመናችን ፍኖተ መስቀልም መሰናክሉንና ዕንቅፋቱን በሀገራችን፣ በቤተ ክርስቲያናችንና በምእመናን ልጆቻችን ጫናው እያበረታ እንደ ሆነ መጠራጠር ያለብን አይመስለንም፡፡ የምእመናን፣ የካህናትና የአብያተ ክርስቲያናት ጒዳት አሁንም ገዝፎና ሰፍቶ እየቀጠለ ነው፡፡ ስጋትና ጭንቀት፣ አለመተማመንና ቀቢጸ ተስፋ ተንሰራፍቶአል፤ አብሮ ተከባብሮ፣ ከመኖር ይልቅ ሌላውን ጥሎ ኮርቻ ላይ ለመውጣት የሚደረገው እሽቅድምድም በሰፊው እየተሠራበት እንደሆነ እየታዘብን ነው፡፡
ይህንን አደገኛ አካሄድ ለማሳካት ሲባል የሚደረገው ያልነበረ ልማድም ቤተ ክርስቲያናችንን እየተጋፋ ነው፤ ምእመናንንም እያሳዘነ ነው፤ ቤተ ክርስቲያናችን በሃይማኖት ነፃነት መከበር ችግር ባይኖርባትም በአጒል ፉክክር የሚደረጉ፣ ካሁን በፊት ያልነበሩ የሥርዓተ ሃይማኖታችን አደባባዮችን ለመቀራመት የሚደረገው አካሄድ ተገቢ ነው አንልም፡፡
ይህ ሁኔታ ለሁሉም በሚበጅና ሁሉም በየራሱ የሚስተናገድበት የየራሱ የሆነ ክቡር ስፍራ አግኝቶ ሊስተናገድ የሚችልበት ሁኔታ ካልተፈጠረ ጥሩ ሊሆን አይችልም፤ ችግሩም በግልጽ እየታየ ስለ ሆነ የሚመለከተው አካል ፈጣን መፍትሔ ሊያበጅበት ይገባል፡፡ ከታሪክ፣ ከነባር ባህል ጥበቃ፣ ከሃይማኖት ክብርና መብት ባሻገር በአንድ ስፍራ ሁለት የተለያዩ ሃይማኖታውያን እንዲገለገሉ የሚደረግ ከሆነ ሁለት የተለያየ እምነት ያላቸው ሃይማኖታውያን በዓላቸው በአንድ ቀን ቢውል ምን ሊፈጠር እንደሚችል መገመት አያስቸግርም፡፡ ሃይማኖታውያንም ለራሳቸው ሲሉ ይህንን ችግር ራሳቸው የመፍትሔ አካል መሆን ይኖርባቸዋል፤ የሰላም ጠበቆች መሆናቸውንም በዚህ ሊያሳዩ ይገባል፡፡
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት !!
የሰላም አስፈላጊነት በየቀኑ ብቻ ሳይሆን በእያንዳንዷ ሰከንድ ለሃይማኖታችን መጠበቅና ለሕዝባችን ደኅንነት መረጋገጥ ትልቅ ዋጋ አላት፡፡ ሰላም በደፈረሰ ቍጥር የምናጣው ብዙ ነው፤ እንደ እውነቱ ከሆነ ሰው ሁሉ ከማንም ተግባር በፊት ሰላምን መጠበቅ ላይ ቢሠራና ሰላምን ገንዘብ አድርጎ ቢመላለስ በሁሉም ነገር ስኬታማ መሆን ይችላል፡፡
በተለይም ሕዝብን በኀላፊነት በመምራት የምንገኘው ዓለማውያንም ሆን ሃይማኖታውያን ከማናቸውም ተግባር በፊት ሰላምን ማረጋገጥ ላይ መሥራት ይጠበቅብናል፤ ምክንያቱም ሃይማኖታዊም ሆነ ሀገራዊ ጥቅም ያለ ሰላም በምንም ተኣምር ሊመጣ አይችልምና ነው፡፡
ሰላም ከሞላ ጐደል ፍጥረት ሁሉ የሚፈልጋት ውድ ነገር ብትሆንም መገኛዋን በተመለከተ ግን ብዙ አናውቀውም፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ ግን ሰላም በጕልበት አትገኝም፤ በሀብትም አትገኝም፤ በሥልጣንም ሆነ በነጠላ ዕውቀትም አትገኝም፡፡ እውነተኛዋና ዘላቂነት ያላት ሰላም የምትገኘው “ክፉውን በመልካም እንጂ በክፉ አታሸንፍ” በሚለው ትምህርተ እግዚአብሔር ብቻ ነው፤ ሰው ሌላውን ቸል ብሎ ራሱን ሲያስቀድም የሰላም ፀር ይሆናል፤ ራሱን ሳይሆን ሌላውን ሲያስቀድም ግን የሰላም ጠበቃ ይሆናል፡፡
በሀገራችን ተከሥቶ ሕዝባችንን እያንገላታ የሚታየው ክሥተት ይህ ራስን ማብለጥ ሌላውን ማንጓጠጥ ነው፤ ይህንን በአግባቡ አርመን አንተ ትበልጣለህ አንተ ትሻላለህ ወደ ሚል ፍኖተ ትሕትና ካልተመለስንና ነገሮችን በፍቅር ለመለወጥ ካልጣርን የሕዝባችንን መከራ ማሳጠር አንችልም፡፡ “ዕርቅ ደም ያደርቅ” እንዲሉ የዕርቅን ጥቅም በመቀበል ወደ ተሻለ ነገር መራመድ ጊዜው የሚጠይቀን ተግባር ነው፡፡ ይህንን በማስተማርና በመምከር ሕዝቡን ወደ ዕርቅና ወደ ይቅርታ ማምጣት ደግሞ የኛው የሃይማኖት አባቶች ተቀዳሚ ተግባር ሊሆን ይገባል፤ ምክንያቱም “ወደ ሰላም ሩጡ” ተብለናልና፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት!!
በአሁኑ ጊዜ ከምንም ጊዜ በላይ ቤተ ክርስቲያናችን በፈተና ላይ የምትገኝበት ወቅት መሆኑን መዘንጋት የለብንም፤ ደማቸው በየአቅጣጫው እንደ ጐርፍ እየፈሰሰ ያለው የልጆቻችን ብሎም የወገኖቻችን ደም ነው፡፡በጦርነትና በድርቅ፣ እንደዚሁም በተለያዩ ግጭቶች በረኃብ እየረገፉ ያሉት እኛ አጥምቀን የሥላሴ ልጅነትን አሰጥተን በልጅነት ያከበርናቸው፣ እግዚአብሔር ጥብቅ በሆነ አደራ ያስረከበን የመንፈስ ልጆቻችን ናቸው፡፡የእነሱ ልሳን ሆነን ዛሬ ከጎናቸው ካልቆምን ነገ የኛ አባትነት ጥያቄ ውስጥ የሚከት ነገር ሊመጣ ይችላል፡፡
ስለሆነም ይህ ቅዱስ ጉባኤ፣ ራሱን ከማናቸውም አደረጃጀት ነፃ አድርጎ የሰላም ጥሪን በማሰማት ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ሰላም መረጋገጥ ለሰላም በሰላም መሥራት መጣርና ውጤት ማምጣት ይጠበቅበታል፡፡ በዚህ ዙርያ ይህ ዐቢይ ጉባኤ በስፋት ተወያይቶ አቅጣጫ እንደሚያስቀምጥም ይጠበቃል፤
በመጨረሻም ለሁሉም ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን የምናስተላልፈው መልእክት ሰላምንና አንድነትን ለማረጋገጥ ጕልበትን እንደ አማራጭ መውሰድ አቁመን፣ የተከሠቱብንን ችግሮች በውይይትና በድርድር ለመፍታት ለሚደረገው ጥረት የላቀ ድጋፍ በመስጠት በጦርነትና በረኃብ፣ በድርቅና በበሽታ እያለቁ ያሉ ልጆቻችንንና ወገኖቻችንን እንድንታደግ በእግዚአብሔር ስም በመማፀን መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ፤
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ ፤
ኢትዮጵያንንና ሕዝቦችዋንም ይቀድስ!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን ፤