ሚያዝያ 16 ቀን 2014 ዓ.ም ቅዱስነታቸው የትንሣኤ በዓል በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤
እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ሁሉ፤
እንኳን ለ2014 ዓ.ም የጌታችን የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡
“ወይእኅዝዎ ለወልደ ዕጓለ እመሕያው ወይሰቅልዎ፣ ወይቀትልዎ ወአመ ሣልስት ዕለት ይትነሣእ፡- የሰውን ልጅ ይይዙታል፤ ይሰቅሉታል፤ ይገድሉታል፤ በሦስተኛውም ቀን ይነሣል” (ማቴ.፳፮፥፪ ፤ ማር. ፰፥ ፴፩)።
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቅ ክርስቶስ በዚህ ዓለም ሲገለጥ እስከ ሞት የሚያደርስ መከራ እንደሚቀበል፣ ከመከራ በኋላም ሞትን ድል አድርጎ እንደሚነሣ ኦሪትም ነቢያትም፣ መዝሙራትም በተለያየ አገላለጽ አሳውቀዋል፡፡ ቀደምት ሊቃውንትም ይህንን እውነታ ሲያረጋግጡ “ኦሪት ወነቢያት ሰበኩ በክርስቶስ፤ ማለትም ኦሪትና ነቢያት ክርስቶስን ሰበኩ” በማለት አመሥጥረዋል፡፡
እሱ ራሱም በምድረ እስራኤል እየተዘዋወረ ወንጌለ መንግሥተ ሰማያትን ሲያስተምር፣ በተነገረው ትንቢት መሠረት እንደሚያዝ፣ እንደሚሰቀልና እንደሚገደል፣ በሦስተኛው ቀን ግን እንደሚነሣ ለደቀ መዛምርቱ ደጋግሞ አስረድቶአል፡፡ እንግዲህ እኛ ሰዎች ይህንን አምላካዊ ድርጊት ስናይ ለምን እንደዚህ መሆን አስፈለገ? ብለን እንጠይቅ ይሆናል፤ ቅዱስ መጽሐፍ ለዚህ ጥያቄ ግልጽና የማያሻማ መልስ አለው፡፡
ይኸውም ቅዱስ መጽሐፍ ዳር እስከ ዳር እንደ ኀብለ ሰረሰር እርስ በርስ እየተናበበ ሲያውጅ የሚገኘው እግዚአብሔር በክርስቶስ ቤዛነት ትዝምደ ሰብእን ለማዳን ቃል መግባቱን ነው፡፡ በመሆኑም ቅዱስ መጽሐፍ ለተጠየቀው ጥያቄ መልስ ሲሰጥ ክርስቶስ በመከራ እንዲያልፍ ያስፈለገበት ዋና ምክንያት በእግዚአብሔር ትክክለኛ ፍርድ ፊት ለኀጢአት ቅጣት በተጋለጡ ሰዎች ፈንታ ቤዛ ሆኖ በመሞት ሰዎችን ለማዳን ነው ይለናል፡፡
ከዚህ አኳያ ይህ አድራጎት እግዚአብሔር ሰውን ብቻ ሳይሆን በኀጢአት የተበከለውን ምልአተ ዓለም በሙሉ ንጹሕ በሆነ ደመ ክርስቶስ ለማንጻትና ለመቀደስ የመረጠው መለኮታዊ አሠራር መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ እንደ ፈቃዱም እንሆ ዛሬ ዓለምንና በውስጡ የሚገኙትን በሙሉ በደሙ አንጽቶአል፤ በዚህም አድራጎቱ በእርሱ በኩል ስለ ድኅነተ ዓለም ሊደረግና ሊከፈል የሚገባው የዕዳ ኀጢአት ካሳ ከፍሎአል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
እግዚአብሔር በሕግ ፈጥሮ፣ በሕግ የሚያስተዳድር አምላክ እንጂ ከኔ በላይ ማንም ስለሌለ እንደፈለግሁት ማድረግ እችላለሁ የማይል እውነተኛ ዳኛ መሆኑን በውል መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ በመሆኑም ሕግ የሚጠይቀውን የኀጢአተኝነት ቅጣት የሚሸከም ወይም ኀላፊነት ወስዶ በኀጢአተኞች ፈንታ የሚቀጣ ሳይኖር ኀጢአተኛን ያለ ቅጣት አይተውም፤ ለዚህም ነው “በደለኛውን ከቶ የማያነፃ” በማለት የማይለወጥ ትክክለኛ ፍርዱን ያሳወቀው፡፡
ነገር ግን እግዚአብሔር በትክክል የሚፈርድ ዳኛ ብቻ ሳይሆን ምሕረትና ይቅርታ በማድረግም ርኅሩኅነቱን ደጋግሞ ያሳወቀ አምላክ ነው፡፡ ይህንን የአምላክ ምሕረትና ይቅርታ ተጠቃሚ ለመሆን እሱን ማመና ንስሓ መግባት ያስፈልጋል፡፡
በመሆኑም መሓሪው አምላካችን በአንድ በኩል ትክክለኛው ፍርዱን ሳይተው በሌላው በኩል ደግሞ ሕግ የሚጠይቀውን ቅጣት ራሱ በመቀበል በኀጢአታችን ከመጣብን የኀጢአት ቅጣት ማለትም ከዘለዓለማዊ ሞተ ነፍስ ነፃ አደረገን፡፡
ለዚህም ነው “ክርስቶስ መድኀኒነ መጽአ ወሐመ በእንቲኣነ ወበሕማማቲሁ አድኀነነ፤ መድኀኒታችን ክርስቶስ መጣ፤ በኛ ፈንታም መከራ መስቀልን ተቀበለ፤ በመስቀል ላይ በተቀበለው መከራም አዳነን” ተብሎ የተነገረን፡፡ ከዚህ አንጻር በቤዛነት የተመሠረተ የማዳን አሠራር በሕግ ፊት ተቀባይነት ያለው በመሆኑ የእርሱ ቤዛችን ሆኖ መሞት እኛን ከሞተ ነፍስ ማዳን ችሎአል፡፡
በዚህ ምክንያት በሱ መሰቀል ኀጢአትንና ሞትን ማሸነፍ ስለቻልን ቅዱስ ጳውሎስ “ወለእግዚአብሔር አኰቴት ዘወሀበነ ንማእ በእግዚእነ ኢየሱስ ክርስቶስ፤ በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ቤዛነት ሞተ ነፍስን ድል እንድንነሣ ላደረገን ለእግዚአብሔር ምስጋና ይሁን” በማለት በተመሥጦና በአድናቆት የታጀበ ምስጋና ያቀርባል፡፡
ይሁን እንጂ በክርስቶስ ደም መዳን እንችል ዘንድ ማድረግ የሚገባን እንዳለ መድኀኒታችን በቅዱስ ወንጌል በሚገባ ነግሮናል፤ ይኸውም በልጁ ያመነ የዘለዓለም ሕይወት ያገኛል የሚለው ገዢ ቃል ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የሰው ልጅ ሁሉ ከኀጢአት ቅጣት አምልጦ ይህንን የመዳን ድል ለመቀዳጀት ዋናው ቍልፍ ተግባር በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ማመንና ንስሓ መግባት ነው፤
እሱን በምልአት የማመኑ ነገር ከተሟላ ሌላው ሁሉ እሱ ያስተማረውን በምልአት በመቀበል የሚሆን ነው፡፡ ምክንያቱም ጌታችን ያስተማረው ትምህርት በሙሉ እውነት እንደ ሆነ የክርስቶስ ትንሣኤ አረጋግጦአልና ነው፡፡ ክርስቶስ ሲነሣ ብቻውን የተነሣ አይደለም፤ ያስተማረው ትምህርትም ሆነ የሠራው ሥራ ሁሉ እንደዚሁም ስለ እርሱ የተነገረው ትንቢት በሙሉ አብሮት ተነሥቶአል፡፡ ምክንያቱም ትንሣኤው የትምህርቱ እውነተኛነት ምስክር ነውና፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት።
ትንሣኤ ክርስቶስ ለእኛ ለክርስቲያኖች የሃይማኖታችን ሁለንተናዊ ሕይወት ነው፡፡ ትንሣኤው በምድራዊ ሕይወታችንም ሆነ በሰማያዊ ሕይወታችን የላቀ ትርጒም ያለው ነው፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በምድራዊ ሕይወታችን ከግብረ ኀጢአት ርቀን፣ በበጎ ሥራ አሸብርቀን፣ በፍቅርና በአንድነት፣ በስምምነትና በመቻቻል፣ በመተዛዘንና በመተሳሰብ፣ በዕርቅና በሰላም እንድንኖርና የሞራል ትንሣኤ እንዲኖረን ያነሣሣናል፡፡
በመንፈሳዊ ሕይወታችን በኩል ደግሞ ከሞት በኋላ ያለውን ትንሣኤና የማያልቅ ዘለዓለማዊ ሕይወት በሩቅ እንድናይና በተስፋ ተሞልተን በመጽናናት እንድንኖር ያስችለናል፡፡ በመሆኑም ክርስቲያኖች የትንሣኤ ልጆች በመሆናችን ከማንም በላይ የላቀ የሞራል ልዕልና ሊኖረን ይገባናል፡፡
ደገኛው ትንሣኤያችንን በጌታችን ቀን እስክንቀዳጅ ድረስም ትንሣኤ ልቡናን በመነሣት የጨለማው ዓለም ብርሃናት ሆነን ልንመላለስ ይገባናል፡፡ የክርስቶስ ትንሣኤ ጥላቻንና መጠፋፋትን ያስወገደ፣ ሰላምን ያሰፈነ፣ ዕርቅን ያረጋገጠ ነው፡፡ እኛም በዓለ ትንሣኤውን ስናከብር የእርሱ ደቀ መዛሙርት ነንና ከኛ የሚጠበቀው ይኸው ዐይነት ክርስቶሳዊ ሕይወት ነው፡፡
በመጨረሻም፡ ትንሣኤውን በሚመስል ትንሣኤ መተባበር ለሁላችንም ክርስቲያኖች ሃይማኖታዊ ግዴታችን ነውና ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን በትንሣኤው ዕለት ተርበውና ተጠምተው፣ ታርዘውና ተስፋ ቈርጠው መዋል ስለሌለባቸው በልዩ ልዩ ምክንያት መከራ ላይ ለሚገኙ ወገኖቻችን የሚያስፈልጋቸውን በማቅረብ ፋሲካውን አብረናቸው እንድናከብር ነው፡፡
እንደዚሁም የሰላምና የፍቅር፣ የዕርቅና የይቅርታ ኀይሎች ሆነን በመመላለስ ሀገራችንን ከፈተና ሕዝባችንን ከሰቆቃው እንድንታደግ ለኢትዮጵያውያን ሁሉ አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
መልካም የትንሣኤ በዓል ያድርግልን ፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክልን ይቀድስልን!!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡