መስከረም 16 ቀን 2014 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ፣ወወልድ፣ወመንፈስ ቅዱስ፣አሐዱ አምላክ፤

“መስቀል መልዕልተ ኲሉ ነገር
መስቀል ከሁሉም ነገር በላይ ነው፤”
(ቅዱስ ያሬድ)

ስለ ቅዱስ መስቀል ምሥጢራዊ ትርጒም በምናስተውልበት ጊዜ በውስጡ ሰፊና ጥልቅ የሆነ ምሥጢረ መለኮት ይዞ እናገኘዋለን። ይሁንና በአጭር አገላለጽ ስናስቀምጠው መስቀል ከመርገም ተነሥቶ፣በመሥዋዕትነት ተራምዶ፣ ሰላምንና ዕርቅን ያስገኘ፣ የመጨረሻ ተግባሩንም ሰውን በማዳን ያጠናቀቀ የነገረ ድነት ጠቅላይ ነገር ነው። ቅዱስ ያሬድ መስቀል ከሁሉም ነገር በላይ ነው ሲል የተናገረው ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰውን ከኀጢአትና ከሞት ለማዳን በተገለጠ ጊዜ፣ከዕለተ ፅንሰቱ አንሥቶ እስከ ዕለተ ስቅለቱ ያከናወነው ግብረ አድኖ ሁሉ የነገረ መስቀሉ አካል ነው&በሌላ አባባል የጌታችን ተግባር ሁሉ የማዳን ተግባር ነው ማለት ነው። መዳን ሲነሣ ከሱ በፊት ጕዳት እንዳለ መገንዘብ አያዳግትም&በመሆኑም በግብረ ኀጢአት የወደቀው የሰው ልጅ ከበደሉ የተነሣ እሱና የሚኖርባት ምድር በጽኑ መረገማቸው ቅዱስ መጽሐፍ ይነግረናል። ጉዳቱ ይህ ነበር፤ ክርስቶስ አምላካችንም በዚህ ዓለም የተገለጸው የዚህ መርገም ተሸካሚ በሆንነው በእኛ ፈንታ መርገማችንን ተሸክሞ በመስቀል ላይ በመሰቀል ሊያድነን ነው። ከቅዱስ መጽሐፍ አስተምህሮ እንደምንረዳው ከዘመነ ክርስቶስ በፊት “በመስቀል ተሰቅሎ የሚሞት ሁሉ የተረገመ ነው” ተብሎ ተጽፎል፤ ከዚህ አንጻር በመስቀል ላይ መሰቀል የነበረበት ያው መርገመ ኀጢአት ያለበት የሰው ልጅ እንደሆነ ግልጽ ነው፡፡

ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በማይነገር ምሕረቱና ፍቅሩ ሰውን ከፍዳ መርገም ሊታደገው ሲፈልግ፣ መርገም ሳይኖርበት በርግማን ፈንታ ቤዛ ሆኖ በመስቀል ላይ በመሰቀል ሰውን እንዲያድን አንድ ልጁን ወደ እኛ ላከ፤ እሱም ይህንን በመስቀል ላይ በተግባር ፈጸመ፤ በዚህም ምክንያት የመርገመ አዳም ፋይል ስለተዘጋ በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ዕርቅ ወረደ& ሰላምም ሰፈነ&ሰውም ከፍዳ መርገም ዳነ፤ ምክንያቱም ድነት ወይም ደንነት የዕርቅና የሰላም ውጤት ነውና፤ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን በተመለከተ“ወገብረ ሰላመ በደመ መስቀሉ ለዘበሰማይ ወለዘበምድር፤ &በመስቀል ላይ ባፈሰሰው ደሙ በሰማይና በምድር ላሉት ሰላምን አደረገ” ሲል ያበሥራል፤ በዚህም ክርስቶሳዊ ቤዛነት ሰው ፍጹም ይቅርታና ምሕረት አግኝቶ ወደ አባቱ ወደ እግዚአብሔር ሊቀርብ ቻለ፤ ከእግዚአብሔር ጋር የነበረው ሱታፌም እንደገና ሊቀጥል በቃ፤ በመሆኑም በዚህ አምላካዊ ምስጢር ሰው ወደ ቀደመ ቦታው ወደ ገነት ገባ&ይህ እጅግ ታላቅና አስገራሚ ፍቅር የተገኘው በመስቀል በመሰቀል ነውና መስቀል ከሁሉም ነገር በላይ ነው ሊባል ችሏል፡፡ የመስቀል ዕርቀ ሰላምና አድኖ በዕለተ ስቅለቱ ብቻ ተሠርቶ ያለቀና የተጠናቀቀ አይደለም፤ በዚያ የተጠናቀቀው የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ አድኖ ነው&የእኛ ሰላምና ዕርቅ ግን ዕለት ዕለት በየጊዜው ያለማቋረጥ ልንፈጽመው የሚገባ የቤት ሥራ ነው&በልብሳችን ያሳተምነው&በአካላችን ያስነቀስነው ትእምርተ መስቀል ለጌጥ ወይም ለመመጻደቅ ከሆነ ተሳስተናል፤ ይልቁንም የመስቀል ትርጒም ሰላምና ዕርቅ ስለሆነ በእግዚአብሔርና በእኛ መካከል&በእኛና በእኛ መካከል፣ በእኛና በሥነ ፍጥረት መካከል ያለውን ሰላምና ዕርቅ ልንጠብቅበት ይገባል፤ በምድራችንም ሆነ በዓለማችን ፍጹም ሰላም አለ ብለን ደፍረን መናገር የምንችለው እኛ ከእግዚአብሔር፣ ከሰውና ከሥነ ፍጥረት ጋር ሰላምና ዕርቅ ሲኖረን ነው& መዳን የምንችለውም ይህንን ስንከተል ነው፤ በልብሳችንና በአካላችን አንቈጥቊጠን የምናሳየው ትእምርተ መስቀል ሰላምና ዕርቅ እስከ ውስጣዊው አካላችን ሠርፆ እንዲገባ ሊያሳስበን፤ ሊያስታውሰንና ሊቀሰቅሰን እንጂ ለሌላ አይደለም፤ ስለሆነም የሰው ልጅ ሁሉ በተለይም ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ዓለም የሰላምና ዕርቅ አምባሳደር ሆኖ እንዲሠራ በእግዚአብሔር የተሾመ መሆኑን ሊያስተውል ይገባል፡፡

በዛሬው ዕለት የምናከብረው በዓለ መስቀል የእግዚአብሔርን ሰላምና ዕርቅ ፈልጋ በብርቱ የተንቀሳቀሳችው ታላቋ ክርስቲያናዊት ንግሥት ዕሌኒ የፈጸመችውን የቅድስና ተግባርና ያስገኘችውን ሃይማኖታዊ ስኬት መነሻ አድርገን ከእግዚአብሔር ጋር ለመታረቅ ነው፤ በዚህ አጋጣሚ በዛሬው ዕለት ለመላው የዓለም ማበረሰብም ሆነ ለኢትዮጵያ ሕዝብ የምናስተላልፈው መልእክት “እባካችሁ የመስቀሉን ሰላምና ዕርቅ እናክብር” የሚለውን ነው፡፡ ስለ ሰላምና ዕርቅ ሲነገረን ጆሮአችንን አንድፈን፣ ዐይናችንን አንጨፍን፣ ፊታችንን አናዙር፣ በራችንን አንዝጋ፣ሰላምና ዕርቅ እኮ ፍቱን የሆነ የሕይወትና የንብረት የዋስትና መድኀኒት ነው፤ ሰላምና ዕርቅ የእድገት፣ የጤና እና የልማት ጒዞ ነው፤ ሰላምና ዕርቅ እኮ አሸናፊነትን እንጂ ተሸናፊነትን አያስከትልም፣ ሰላምና ዕርቅ እኮ ወደ እግዚአብሔር በሞገስና በክብር የሚያቀርብ መለኮታዊ ፈውስ ነው፤ ከዚህ አኳያ ስለ ሰላምና ዕርቅ አስመልክቶ የሚሰማው ድምፅ ከሰው የመጣ ድምፅ ሳይሆን ከእግዚአብሔር የመጣ ድምፅ መሆኑን አውቀን መልሳችን አዎንታዊ ሊሆን ይገባል፤ ሌላው ሁሉ ከዚያ በኋላ ይሆናል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ በድርድር፣በውይይት፣በሰጥቶ መቀበልና በይቅርታ የማይፈታ ችግር ከቶ የለም፤ እነዚህን እንዳናደርግ ማን ከለከለን? ከነዚህስ በቀር የሚጠቅመን ሌላ ምን ነገር አለ? የችግር ሁሉ መቋጯስ ውይይት ካልሆነ ሌላ ምን ሊሆን ይችላል?ታድያ ይህ የተሻለ አማራጭ እያለ ለምን ሕይወት ይጠፋል? ለምንስ ንብረት ይወድማል? ወንድምስ በወንድሙ ላይ ለምን ይጨክናል? አሁንስ ሄዶ ሄዶ ወደ ውይይት መግባቱ መቼ ይቀራል; ነገር ግን ከዚህ ሳይደረስ ቢደረግ መልካም ነበረ፤ ለሰላምና ዕርቅ ዋጋ ሳንሰጥ የመስቀሉን በዓል ማክበር ብቻ ትርጒም ይኖረዋል ብለን የምናስብ ከሆነ የመስቀሉን ምሥጢር በቅጡ አልተረዳነውም ማለት ነው፣እግዚአብሔር ከሁሉ በላይ አብልጦ የሚመለከተው እኛን እንጂ የመስቀሉን በዓል አይደለም፤ እኛ እየተጣላን በዓለ መስቀሉን ብናከብር፣ እግዚአብሔር የማይቀበለው መሥዋዕት እንደሆነ እንወቅ፡፡ ከዚህ አንጻር ታላላቅ የሃይማኖት መሪዎችና ሊቃውንት፣ አሉ የተባሉ የሀገር ሽማግሌዎች፣ እጅግ የተራቀቁ ምሁራን እንደዚሁም የበሰሉ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች በሚገኙባት በታላቋ ሀገር በኢትዮጵያ የተከሠተው ክሥተት ለሕዝባችን የሚመጥን አይደለም፤ ከሃይማኖታችንና ከታሪካችን ጋርም አብሮ የሚሄድ አይደለም፤ ይህ በብርቱ ሊታሰብበት ይገባል፤ ከእንግዲህ ወዲህ የእስካሁኑ በቅቶን ሌላውም ሁሉ ለጊዜው አቆይተን፣እንደ መስቀል መርሕ በሰላምና ዕርቅ ጥበብ የሕይወት አድን ሥራን በቁርጥ እንድንሠራ ማለትም በማናቸውም ምክንያት የሰው ሕይወት እንዳይጠፋ ጠንካራ ሥራ እንድንሠራ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዓለ መስቀል።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር።

መስከረም 1 ቀን 2014 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ዘመን መለወጫ በዓል አስመልከቶ የሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትገኙ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

ሰማይንና ምድርን፣ በውስጣቸው የሚገኙ ፍጥረታትን የሚታዩትንና የማይታዩትን የፈጠረ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ከዘመነ ማቴዎስ 2013 ዓመተ ምሕረት ወደ ዘመነ ማርቆስ ወንጌላዊ 2014 ዓመተ ምሕረት በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡
“ዘይሔድሳ ለምድር በበረከቱ
እግዚአብሔር አምላክ ምድርን በበረከቱ ያድሳታል።”
(ድጓ)

ቅዱሳት መጻሕፍት እንደሚነግሩን እኛም እንደምንገነዘበው እግዚአብሔር አምላክ በፍጡራን አእምሮ ሊመጠን በማይችል በረከቱ ምድርንና በውስጧ ያሉትን ፍጥረታት ሁሉ በማያቋርጥ ሂደት እያደሰ ይኖራል ፡፡እግዚአብሔር አምላክ፥ ፍጥረታት እየታደሱ እንዲተካኩ በማድረጉ የቀደመው ሲያልፍ አዲሱ ሲተካ የሕይወት ጒዞ የማያቋርጥ ሆኖ እንዲቀጥል አድርጎአል ፡፡ከጌታችን ከአምላካችን ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ልደት በፊት የነበረው አሮጌ ዘመን ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ ኩነኔ፣ በእርሱ መሥዋዕትነት ሲያሳልፍ ከልደተ ክርስቶስ ጀምሮ ያለውንም የምሕረት ዘመን ብሎ አድሶታል ፡፡ወደፊትም በዳግም ምጽአቱ ሰማይንና ምድርን በማሳለፍ የተሻለ ሕይወት ለሰው ልጆች መስጠቱ የእግዚአብሔር ፈቃድ መሆኑን ከቅዱስ ወንጌል ተምረናል (ማቴ. 24-25)። በመሆኑም ፍጥረታትን የማሳለፉ ተግባር የእግዚአብሔር ቀዋሚ ሥራ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን በባሕርዩ ማርጀትና ኅልፈት የሌለበት ነው፤ በመጻኢው ዓለም ለሰው ልጆች ያዘጋጀው ሕይወትም ማርጀትና ኅልፈት የሌለበት፣ ሁል ጊዜ ሐዲስ ሆኖ የሚኖር ነው፡፡የሃይማኖታችን ጽኑ ተስፋም በአዲሱ ዓለም ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ይሁንና ወደ አዲሱ ዓለም ለመድረስ በየዘመኑ አዳዲስ ሥራዎችን በመሥራት እግዚአብሔርንና ፍጡራኑን በትጋት ማገልገል ያስፈለጋል፡፡ በዚህ ዓለም በፍጡራን ዐቅም ሊታደስ የማይችል ነገር ቢኖር ሃይማኖት ብቻ ነው፡፡ ከሃይማኖት በቀር ሌላው ሁሉ ለሰው ልጅ በሚጠቅም መንገድ ሊሻሻል፣ ሊስተካከልና ይበልጥ ሊጠቅም የሚችልበትን ዘዴ ተከትሎ ማሻሻል ተገቢ ይሆናል ፡፡
ዓለም ከተፈጠረ፣ ዘመን ከተቈጠረ አንሥቶ እስካሁን ባለበት ብቻ ቆሞ የኖረበት ዘመን የለም፤ በየጊዜው አዳዲስ የአሠራር ስልቶች እየተፈጠሩ፣ በቀጣይም በሌላ አዲስ ስልት እየተተኩ ይኖራሉ፤ ይህም ቀዋሚ የሆነ የእግዚአብሔር ጸጋ ነው ፡፡ከዚህ አኳያ በተሰናባቹ በ2013 ዓመተ ምሕረት ማብቂያና በአዲሱ 2014 ዓ.ም. መግቢያ ላይ ቆም ብለን ልናስበው የሚገባ ነገር አለ ፡፡ይኸውም በተሰናባቹ ዓመት የነበረንን አጠቃለይ ሥጋዊና መንፈሳዊ ተግባር መመርመር ሲሆን ያልሠራንባቸው አጋጣሚዎች ካሉም በአዲሱ ዘመን አካክሰን በመሥራት ያመለጠንን ሁሉ በእጥፍ ሠርቶ ለመተካት ጠንክሮ መሥራት ያስፈለጋል ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅድስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

አዲሱ ዓመት ሲመጣ የደስታና የተሐድሶ ልቡና ዘመን እንዲሆንልን ከመመኘቱ ጋር በብሩህ ተስፋ መቀበላችን መልካም ነው፤ ይሁንና የሰላምና የእድገት ምኞታችን ወደ ተጨባጭ ፍሬ ሊደርስ የሚችለው በሥራ ብቻ ነው ፡፡በዓለማችን፣ እንዲሁም በአካባቢያችን የምናያቸው ውብና ድንቅ ነገሮች ሁሉ የሥራ ውጤት መሆናቸውን ለአንድ አፍታ እንኳ ቢሆን ልንዘነጋው አይገባም ፡፡ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረ እንድንሠራ እንጂ እንድንተኛ አይደለም፤ በሥራ ላይ ቸልተኛነትን የምናሳይ ከሆነ የኑሮአችን መመሰቃቀል ብቻ ሳይሆን በእግዚአብሔር ፊት መክሊት ቀባሪ ተብሎ መጠየቅም እንዳለ ማሰብ ይገባናል ፡፡ እንደሚባለውም ‹‹ሰው ለመብላት አይኖርም፤ ለመኖር ይበላል እንጂ፡፡ ለሥራ ክብርን አለመስጠት፣ እግዚአብሔር እኛን የፈጠረበትን ዐላማ እንደመዘንጋት የሚያስቆጥር ይሆናል፤ ይህ ደግሞ ለእኛ የሚበጅ አይደለም (ዘፍ. 1፥3)። እግዚአብሔር ከበረከቱ ያጎደለብን አንዳችም ነገር የለም፤ በየጊዜው አዲስ የሆነ ራእይ፣ አዲስ የሆነ አሠራር፣ አዲስ የሆነ ጥበብ፣ አዲስ የሆነ ዘመን፣ አዲስ የሆነ ጤንነት ወዘተርፈ ከመስጠት ያቋረጠበት ጊዜ የለም ፡፡ ይሁንና እርሱ የሰጠንን አዲስ የዘመን ስጦታ በአዲስ አስተሳሰብና አሠራር ተቀብለን ካልተጠቀምንበት አዲስ ዘመን ማለቱ ብቻ ከምኞትና ከቃላት ያለፈ ትርጒም ሊኖረው አይችልም፡፡ ዘመኑ አዲስ ሊሆን የሚችለው እኛ በምናበረክተው ሥራ እንጂ ዘመን በራሱ አዲስ ሊሆን አይችልምና እግዚአብሔር አምላክ የሚወዳችሁና እግዚአብሔርን የምትወዱ ልጆቻችንና ወገኖቻችን በሙሉ አዳዲስ ሥራዎችንና አሠራሮችን በመፍጠር አዲሱን ዓመት በሁለመናው አዲስ አድርገን እናክብረው ፡፡እግዚአብሔር አምላካችን በዓሉን የደስታና የጤና፣ዘመኑን የምሕረትና የሰላም ያድርግልን፡፡
ለሀገራችንና ለመላው ዓለም ሰላምን ይስጥልን፡፡ሕዝባችንን በፍቅርና በአንድነት ያጽናልን፡፡የተዘራውን ዘር፣ የተተከለውን ተክል ይባርክልን፡፡የተወለዱትን ሕፃናት ያሳድግልን፡፡

መልካም የሥራ ዘመን ያድርግልን፤
እግዚአብሔር አምላካችን ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።