ነሐሴ1 ቀን 2ዐ13 ዓ.ም ቅዱስነታቸው ጾመ ፍልሰታን ምክያት በማድረግ ስለሀገር ሰላምና አንድነት ጥሪ ያስተላለፉት ቃለ ምዕዳን ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት በሙሉ፤
እንኳን ለ2013 ዓ.ም. የቅድስት ድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላምና በጤና አደረሳችሁ፡፡
«ጾም ልጓም ፍሬሃ ጥዑም፤
ጾም ልጓም ናት፤ ፍሬዋም ጣፋጭ ነው።»
(ቅዱስ ያሬድ)
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በኦርቶዶክሳዊ ቀኖና ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ መሠረት ከምትጾማቸው ሰባት አጽዋማት አንዱ ጾመ ፍልሰታ ለማርያም ነው፡፡ ጾመ ፍልሰታ ማለት ቅድስት ድንግል ማርያም ፈጣሬ ዓለማት በሆነው በልጇ ኀይል ከሞት ተነሥታ ወደ ሰማይ ያረገችበትን በማሰብ የሚጾም ጾም ማለት ነው ፡፡ይህ ጾም የቅድስት ድንግል ማርያምን ቅድስናና ክብር በማስታወስና በተሰጣት ጸጋ በጸሎቷና በአማላጅነቷ ከእግዚአብሔር ዘንድ ለምእመናን የምታሰጠውን በረከትና ረድኤት በማመን የምንጾመው ታላቅ ጾም ነው ፡፡ጾመ ፍልሰታ ከሌሎች አጽዋማት ለየት የሚያደርገው ሽማግሌውም፣ ሕፃኑም፣ ወጣቱም በተለየ ዝግጅት፣ በተመሥጦና በመንፈሳዊ ስሜት የሚጾመው መሆኑ ነው፡፡ይህም ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በመስቀል ላይ ሆኖ #እነኋት እናትህ$ ብሎ የሰጠንን የቅድስት ድንግል ማርያም እናትነት በቅዱሳን ሐዋርያት ስብከትና በሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን ትምህርት በስፋት ተብራርቶና ተገልጾ፣ በአበው ትውፊትም ተጠብቆ እንደኖረው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእምናን ዘንድ አሁንም እንደተጠበቀ መሆኑን የሚያሳይ ነው፡፡
እንደ ቤተክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት የቅድስት ድንግል ማርያም ርኅራኄና አዛኝነት ለሰዎች ብቻ ሳይሆን ለፍጡራን ሁሉ እንደሆነ በቤተ ክርስቲያናችን መጻሕፍት በስፋት ተገልጾ እናገኘዋለን፤ ከዚህም የተነሣ እኛ ኢትዮጵያውያን ቅድስት ድንግል ማርያምን “አዛኝቷ እናታችን” በማለት እንማፀናታለን፡፡ የጾመ ፍልሰታን ጾም በምንጾምበት ጊዜ ቅድስት ድንግል ማርያም በተሰጣት አማላጅነት ለፍጡራን የምታሰጠው በረከት ትምህርት ሆኖን እኛም የተቸገሩትን በመርዳት፣ የተራቡትን በማጒረስና የታረዙትን በማልበስ ለወገኖቻችን ፍጹም ርኅራኄሄና አዛኝነት በማሳየት ልንጾመው ይገባል ፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያም ከእግዚአብሔር በተሰጣት አማላጅነት ለፍጥረቱ ሁሉ እንደምትጸልይ፣ እርሷን በመማፀን ጾሙን የምንጾም ሁላችን በቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የጾም መሣሪያዎች የሆኑ ሰላም፣ ፍቅር፣ ጸሎት፣ ምጽዋትና ትዕግሥትን ገንዘብ በማድረግ፣ የሰው ሰውኛውን ሳይሆን የእግዚአብሔር የሆነውን ብቻ በመምረጥና በመከተል፣ መዋዕለ ጾሙን ልናሳልፍ ይገባል፡፡
በመጨረሻም፤ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ የጾም ሱባዔ በኮረና ቫይረስ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ በማድረግ የሱባዔውን ወቅት ስለ ሀገር ሰላምና አንድነት በምሕላ፣ በጸሎት፣ በንስሓና በፍቅር፣ እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲያሳልፍ አባታዊና መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን !