ከግንቦት 17 ቀን እስከ ግንቦት 23 ቀን 2013 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዐተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከግንቦት 17 ቀን 2013ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ግንቦት 20 ቀን 2013ዓ.ም. ድረስ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
1. የ2013 ዓ.ም. ግንቦት ርክበ ካህናት የጉባኤ መክፈቻ በሀገራችን ወቅታዊ ሁኔታዎች ማለትም፡-
• ስለ ሀገር ደኅንነትና ስለ ሕዝቦች አንድነት፣
• ከቀያቸው ስለተፈናቀሉና ለስደት ስለተዳረጉ ወገኖች፣
• በተለያዩ አካባቢዎች እየታዩ ስለአሉ አለመግባባቶች የሚያመላክት እና ይህንንም በመግባባት በውይይት በይቅርታ መፍታት እንደሚገባ ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ምሕረት መጠየቅ እንደሚያስፈልግ የሚገልጽ በመሆኑ ጉባኤው ተቀብሎ በተግባር ላይ እንዲውል ተስማምቷል፡፡
2. ሀገራዊ ሰላምን አስመልክቶ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶች ምክንያት የጠፋው የሰው ሕይወት የታረዱና ከቀያቸው የተፈናቀሉ ወገኖች በችግሩ ምክንያት የወደመ ንብረት በዐይነትና በቊጥር ተለይቶ በየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ እንዲቀርብ ተወስኗል፡፡
3. የቤተ ክርስቲያን የአምልኮ ሥፍራ ስምና እስከዛሬ ተጠብቆ የቆየ ክብሯ እንዲሁም በካህናትና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለ ሞት፣ ስደት የመሳሰለው ከየአህጉረ ስብከቱ ተጣርቶ ሪፖሪት እንዲቀርብ መንግሥትም አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
4. ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በሀገራችን የነበረውንና የቆየውን ታሪካዊ ሂደት ለመቀየር በዚህም አጋጣሚ የኖረውንና ዓለም የሚያውቀውን በዓለም ዐቀፍ ደረጃ በዩኒስኮ የተመዘገበ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የመስቀል አደባባይና የባሕረ ጥምቀት ቦታዎች እንዲሁም የአምልኮ ሥፍራዎችን ምክንያት በመፍጠር አንዳንድ ወገኖች የግጭትና የትንኮሳ ተግባር እየፈጸሙ መሆኑ ጉባኤውን በእጅጉ አሳዝኗል፡፡በመሆኑም ይህ በቤተ ክርስቲያናችን ስም የቆየው የዘመናት ታሪክ ሀገራዊ ታሪክ ተደርጎ ልዩ ጥበቃና ክብካቤ ሊደረግለት ስለሚገባ አሁንም መንግሥት ለጉዳዩ ትኵረት በመስጠት የኖረው የቤተ ክርስቲያኒቱና የሀገሪቱ ታሪክ ክብሩ ከነማንነቱ ተጠብቆ እንዲኖር የበኩሉን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት አሳስቧል፡፡
5. ሀገራችን ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ እንደሚታወቀው ዳር ድንበሯን ጠብቃና አስጠብቃ ያለ ቅኝ ግዛት ያለ ማንም ጣልቃ ገብነት በሀገር ወዳድ መሪዎቿ አንድነቷን ጠብቃ የቆየች መሆኗ ዓለም የሚያውቀው ነው፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ አንዳንድ የውጭ ሀገራት ከሩቅና ከቅርብ ግንባር በመፍጠር በሀገራችን ህልውና ላይ እያደረጉት ያለው ጣልቃ ገብነት፣
• ሀገራዊ የመልማት ፍላጎታችንን ለመግታት
• ዳር ድንበራችንን ለመድፈር እያደረጉ ያለውን ሙከራ ጐረቤት ሀገራት ጭምር በጠላትነት እንዲነሣሡብን እያደረጉ ያለው ቅስቀሳ ተዘዋዋሪ ቅኝ ግዛት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ተቃውሞአል ሕዝባችንም ከምንጊዜውም በተለየ መልኩ ሀገራዊ አንድነቱን በመጠበቅ ሀገሪቱን ከውጭ ወራሪ በመከላከል ሀገራዊ ልማትን በማፋጠን የበኩሉን እንዲወጣ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
6. ሀገራችን ኢትዮጵያ በልማት እንድታድግ ሌሎች ሀገራት ከደረሱበት ደረጃ ለማድረስ በዚህም ዜጎችን ከጨለማ ወደ ብርሃን ለማውጣት ታስቦ እየተገነባ ያለው ሕዳሴ ግድባችን ወደ መጨረሻው ምዕራፍ እየተቃረበ እና ለኢትዮጵያውያን ሁሉ የአንድነታችን ማሳያ እየሆነ በመምጣቱ አሁንም ለግንባታው ፍጻሜ መላው ኢትዮጵያዊ እንዲረባረብ ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡
7. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በዘመናት ታሪኳ የአብያተ ክርስቲያናትን ዐጸድ በመትከል አረንጓዴ ልምላሜን በማስፋፋት ጠብቃ የቆየች ሲሆን በአሁኑ ጊዜ ደግሞ መንግሥታችን በየዓመቱ በቢሊየን የሚቈጠር ችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር ማዘጋጀቱ ለአየር ጥበቃና በምግብ ራስን ለመቻል እየተደረገ ያለው ሀገራዊ ጥረት የሚደገፍ በመሆኑ በዘንድሮውም የችግኝ ተከላ መርሐ-ግብር መላው ዜጋ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
8. ከአንድ ዓመት በፊት በመላው ዓለም ተከሥቶ ብዙዎችን ለኅልፈተ ሕይወት የዳረገው ኮቪድ 19 ተላላፊ በሽታ በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በመስፋፋቱ ብዙዎች ወገኖቻችንን ለሞት እየዳረገ የሚገኝ በመሆኑ መላው ሕዝባችን ከምንግዜውም በበለጠ በአሁኑ ጊዜ ከጤና ባለሙያዎች የሚሰጠውን ምክረ ሐሳብ በመቀበል ራሱን ከወረርሽኙ እንዲጠብቅ ጉባኤው አሳስቧል፣
9. በሀገራችን በተለያዩ አካባቢዎች በተፈጠረው አለመግባባት ምክንያት ከቤት ንብረታቸው የተፈናቀሉ ያለመጠለያ የሚገኙ እና በዚሁ ተላላፊ በሽታ ምክንያት ችግር ላይ የወደቁ ወገኖቻችንን በተለመደውና በኖረው የመረዳዳትና የመተሳሰብ ባህላችን ከምንጊዜው በላይ አሁን ለችግራቸው እንድንደርስላቸው ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡
10. ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በሽግግር ላይ የምትገኝ በቀጣይም ሕዝባዊ ምርጫ ለማካሄድ በከፍተኛ ዝግጅት ላይ መሆኗ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ገዥው ፓርቲም ሆነ ተፎካካሪዎች ለሀገራችንና ለሕዝባችን የሚጠቅመውን ሰላማዊ መንገድ እንዲከተሉ መላው ሕዝባችንም ለሀገርና ለወገን ይጠቅማሉ የሚባሉትን በመምረጥ ሁሉም አካል ውጤቱን በጸጋ በመቀበል ኢትዮጵያዊ ጨዋነትን የምናስመሰክርበት ምርጫ እንዲሆን ጉባኤው የሰላም ጥሪውን አቅርቧል፡፡
11. በምሥራቅ ጎጃም ሀገረ ስብከት በጐንቻ ሲሶ እነሴ ወረዳ በምስካበ ቅዱሳን ቆጋ ኪዳነ ምሕረት በሕገ ወጥ መንገድ ዶግማና ቀኖና ቤተ ክርስቲያንን በጣሰ መልኩ ራሳቸውን በራሳቸው ጳጳስና ፓትርያርክ አድርገው የሾሙ፡-
1. መምህር ሄኖክ ፈንታ
2. መምህር አባ ኪዳነ ማርያም
3. መሪጌታ ሙሉ
ከግንቦት 19 ቀን 2013ዓ.ም. ጀምሮ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተወግዘዋል፡፡ የገዳሙንም ሀብትና ንብረት አስረክበው ከገዳሙ እንዲወጡ ተወስኗል፡፡ የዚህ ተባባሪ የነበሩ መነኮሳት ካህናትና ዲያቆናትም የተወገዙ ሲሆን በዚህ የዶግማና የቀኖና ጥሰት ምክንያት በማወቅም ይሁን ባለማወቅ ተሳስተው ድጋፍ ሲሰጡና ሲከተሏቸው የነበሩ ምእመናን ንስሓ እየገቡ ይቅርታ እንዲደረግላቸው ጉባኤው ወስኗል፡፡
12. በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው፡-
• የእርስ በርስ አለመግባባት እንዲቆም ፣
• ሞትና ስደት እንዲያበቃ ፣
• ተላላፊ በሽታ ከምድራችን ጠፍቶ ሰዎች በጤንነት እንዲኖሩ ፣
• መጪው ሀገራዊ ምርጫ በኢትዮጵያዊ ጨዋነት በአንድነትና በሰላም እንዲጠናቀቅ ፣
ለዚሁ ሁሉን ቻይና ሁሉን አድራጊ የሰላም አምላክ እግዚአብሔር ሀገራችንና ሕዝባችንን በሰላምና በምሕረቱ እንዲጐበኝ ሁላችንንም ይቅር እንዲለን ከአሁን ጀምሮ በግልም ሆነ በማህበር ጸሎት በማድረግና ችግረኞችን በመርዳት እንድንተባበር ሆኖ ከምርጫው ሰኔ 14 ቀን 2013ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሐምሌ 4 ቀን 2013ዓ.ም. ድረስ በመላው ሀገራችንና በውጭም ባለችው ቤተ ክርስቲያን ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከግንቦት 17 እስከ ግንቦት 23 ለስድስት ቀናት ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ አጠናቅቆ በጸሎት ዘግቷል፡፡
እግዚአብሔር ሀገራችንን ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይጠብቅ፡፡