ነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም የ2012 ዓ.ም የጾመ ፍልሰታ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና በውጭ የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ!

የይቅርታ ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለድንግል ማርያም ጾመ ፍልሰታ በሰላም አደረሳችሁ!!
“ወሣህሉኒ ለትውልደ ትውልድ ለእለ ይፈርኅዎ
ይቅርታው ለሚፈሩት ለልጅ ልጅ ነው፤”
(ሉቃ. 1፥49)
ይህ ኀይለ ቃል የቅዱስ መጽሐፍ ቀዋሚ ምሰሶ ሆኖ በብዙ ቦታ የሚገኝ ነው፤ ቃሉ እግዚአብሔር ለሚፈሩት የሚያጐናጽፋቸውን የምሕረት ቃል ኪዳን በውስጡ ይዞአል፤ ማኅደረ መንፈስ ቅዱስ የሆነችው ቅድስት ድንገል ማርያምም እግዚአብሔርን ባመሰገነችበት የምስጋና መዝሙር ይህንን ኀይለ ቃል ተናግራዋለች ፡፡በዚህ ኀይለ ቃል የእግዚአብሔር ይቅርታ ምን ጊዜም የተከበረና እንደተስፋ ቃሉ የሚፈጸም መሆኑ፣ ያም ሊሆን የሚችለው ለሚፈሩት ሰዎች መሆኑ በሚገባ ተገልጾአል ፡፡ የእግዚአብሔር ይቅርታ አጭርና ቀጭን ሳይሆን ለልጅ ልጅ እንደሚሆንም ተብራርቶአል ፡፡
ይህ አባባል እውነት እንደሆነ ለመረዳት ከኛ ከሰዎች የበለጠ ሌላ ምስክር ሊኖር አይችልም፡፡ ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ “ሣህሉ ለእግዚአብሔር መልአ ምድረ፣ የእግዚአብሔር ይቅርታ ምድርን መላ” ብሎ እንዳስተማረን ይቅርታው በየጊዜው በዝቶ ባይደረግልን ኖሮ ውሎ ማደሩ የሚቻል አልነበረም፡፡ እግዚአብሔር በነገሩ ሁሉ ኀጢአትን፣ ክፋትን፣ ርኵሰትንና ክሕደትን የሚጠላ አምላክ ነው፤ እኛ ደግሞ ከነኚህ ስሕተቶች ለአንድ ደቂቃ ስንኳ ጸድተን አናውቅም፤ ይሁን እንጂ እግዚአብሔር በቅጣት ፈንታ ምሕረትንና ይቅርታውን እያበዛልን በምሕረቱ ተጠልለን እንኖራለን፡፡ ቅድስት ድንግል ማርያምን በመውደድ፣ አስተብቍዖቷን፣ ጸሎቷንና ልመናዋን በመሻት ይህንን ጾም ስንጾም በመንፈስ ተሞልታ ያስተማረችንን ፈሪሀ እግዚአብሔር ገንዘብ በማድረግ መሆን አለበት፤ እንደ ተስፋ ቃሉም ለቃሉ በመታዘዝ መሆን አለበት፤ ቃሉ ይቅር እንድትባሉ ይቅርበሉ፣ ሰላምንና አንድነትን አጽንታችሁ ያዙ ይለናልና፡፡
ይህን ይቅርታ ለማግኘት የተጠየቅነው ዋናው ነገር እግዚአብሔርን መፍራት ነው፤ እግዚአብሔርን በእውነት የምንፈራ ከሆነ ይቅርታ ለመስጠትም ሆነ ለመቀበል ዳገት አያግደንምና ነው፤ እግዚአብሔርን መፍራት ማለት በምንሠራው ሥራ፣ በምንናገረው ቃል፣ በምናስበው ሐሳብና ምኞት ሁሉ እግዚአብሔር ያውቅብናል፣ ያየናል፣ ይፈርድብናል፣ የሚል አስተሳሰብ በውስጣችን ኖሮ ክፉ ድርጊትን ከማድረግ እንድንቈጠብ መሆን ማለት ነው ፡፡
ሰው ሁሉ እግዚአብሔርን ከእርሱ ውጪ እንዳለ ሳይሆን በአጠገቡና በመንፈሱ ውስጥ ሆኖ እንደሚያውቅበት ተገንዝቦ እግዚአብሔርን መፍራት አለበት፣ የሰላምና አንድነት መሠረት ከፈሪሀ እግዚአብሔር መነሣት ሲችል ዘላቂና ጠቃሚ ይሆናል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤
ዘንድሮ የምንጾመው ጾመ ማርያም ሀገራችንና ሕዝባችን በሰው ሰራሽና በተፈጥሮ አደጋ ውስጥ ተከብበው ባሉበት ወቅት ነው፤ የተጋረጡብን ፈተናዎች እግዚአብሔርን ይዘን ካልሆነ በቀር ብቻችን ሆነን የምንወጣቸው አይደሉም፤ በእግዚአብሔር ከለላነት እነዚህን ፈተናዎች ልናልፋቸው ከሆነ እርሱን በመፍራት ከክፋታችን መመለስና ንስሓ መግባት አለብን፤ በነገው ዕለት የምንጀምረው የጾመ ማርያም ሱባዔም ዋና ዐላማው በንስሓ ወደ እግዚአብሔር ለመመለስና እሱን በመፍራት ለእሱ ተገዢዎች ለመሆን ነው፡፡
ሁሉም እንደሚያውቀው ንስሓ በይቅርታና በዕርቅ መታጀብ ይገባዋል፤ ችግሮቻችን ምን ያህል ቢበዙም ለእግዚአብሔር ብለን በምንፈጽመው ይቅርታና ዕርቅ፣ በምናረጋግጠው ሰላምና አንድነት ተሸናፊዎች ናቸው፡፡ ስለዚህ ችግሮችን ለማሸነፍ ብሎም ለማስወገድ ከይቅርታና ዕርቅ፣ ከሰላምና አንድነት የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ልሂቃኖቻችንም ሆኑ ሕዝቦቻችን በውል መገንዘብ አለባቸው ፡፡
ኢትዮጵያ የምትባለው ሀገር የዚህ ትውልድ ሀገር ብቻ አይደለችም፤ ያለፉ አባቶች፣ የሚመጡ ትውልዶችም የኢትዮጵያ ባለቤቶች ናቸው ፡፡ እኛ በክብ ጠረጴዛ ተገናኝተን ተወቃቅሠንና ተመካክረን ችግራችንን በተሸንፎ ማሸነፍ ጥበብ ማረም ካቃተን ቢያንስ ኢትዮጵያን ባለችበት ሁናቴ ለባለ መብቱ መጪው ትውልድ የማስተላለፍ ግዴታ እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፤ ነገሮችን ሁሉ በትዕግሥት፣ በአርቆ አስተዋይነትና በሰላማዊ ሁኔታ ለማስተናገድ ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይገባናል፤ በመሆኑም ኢትዮጵያ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ ተቋቍማ በአሸናፊነት መሻገር የምትችለው እግዚአብሔርን በመፍራት ለይቅርታና ለዕርቅ ስንዘጋጅ ነው፤ ስለዚህ ይህ ግንዛቤ ተወስዶ ለኢትዮጵያና ለኢትዮጵያውያን ቆመናል የሚሉ የፖለቲካ ተፎካካሪ ወገኖች ሁሉ አንድ ላይ ተገናኝተውና በክብ ጠረጴዛ ሆነው በመወያየት የሀገሪቱን አንድነት፣ ሰላምና ልማት እንዲያስቀጥሉ በዚህ አጋጣሚ በእግዚአብሔር ስም እንማፀናለን ፡፡
በመጨረሻም፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ የጾም ሱባዔ በኮረና ቫይረስ እንዳይጎዳ ጥንቃቄ በማድረግ የሱባኤውን ወቅት ስለሀገር ሰላምና አንድነት በኀዘን፣ በምሕላ፣ በጸሎት፣ በንስሓና በፍቅር፣ የተቸገሩትንም በመርዳት እግዚአብሔርን በመፍራት እንዲያሳልፍ አባታዊና መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን ፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፤ አሜን!