ከግንቦት 05 ቀን እስከ ግንቦት 06 ቀን 2012 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 ድንጋጌ መሠረት ከግንቦት 4 እስከ ግንቦት 6 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ውሳኔዎች፤
1. በዓለማችንና በሀገራችን በኢትዮጵያ ጭምር ከቅርብ ወራት ወዲህ የተከሠተው የኮረና ቫይረስ (ኮቪድ-19) ወረርሽኝ እስከ አሁን በብዙ ሚሊየን የሚቈጠሩ ሰዎችን በመያዙና ከመቶ ሺሕዎች ላላነሱ ሰዎች ሕይወት መጥፋት ምክንያት በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን በእጅጉ ያሳዘነ ሲሆን ጉባኤው፣ በቫይረሱ የተጠቁትን ምሕረት እንዲሰጥልን እስከ አሁን በቫይረሱ ያልተጠቁትንም እንዲጠብቅልን ተማሕፅኖውን ለእግዚአብሔር አቅርቧል፡፡
2. ይኸው ተላላፊና የሰው ልጆችን በሞት እየነጠቀ ያለውን ቫይረስ እግዚአብሔር አምላክ በምሕረቱ እንዲያጠፋልን ምእመናን እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ በመሆን እንዲጸልዩ ተይዞ የነበረውን የሱባዔ ጊዜ በአግባቡ መከናወኑን ጉባኤው ተገንዝቦ ለወደፊቱም ካህናትም ሆኑ ምእመናን ወደ እግዚአብሔር የሚያደርጉትን ጸሎት በቤተ ክርስቲያንም ሆነ በቤታቸው አጠናክረው እንዲቀጥሉ ጉባኤው አበክሮ አሳስቧል፡፡
3. በዚሁ ወረርሽኝ መከሠት ምክንያት በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ የሚሰጠው መንፈሳዊ አገልግሎት መቋረጡ በምእመናን ሕይወት ላይ ችግር እየፈጠረ መሆኑና ምእመናን ከቤተ ክርስቲያን ተለይተው መኖር ስለማይችሉ በቀጣይም የሕዝቡን ጤና መጠበቅ በሚያረጋግጥ መልኩ የሚመለከታቸው የሃይማኖት አባቶች እና የጤና ባለሙያዎች በሚሰጡት ሙያዊ ምክርና መንግሥትም በሚሰጠው መመሪያ መሠረት አሁንም የአካላዊ ርቀትና ንጽሕና አጠባበቅ ከምንጊዜውም በላይ ትኵረት ተሰጥቶት፣ ለዚሁ ተግባር በየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናቱ በተመደቡ የሰንበት ት/ቤት ወጣቶች አስተናጋጅነት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲከናወን፣
4. ሀገራችን ኢትዮጵያ ሀገረ እግዚአብሔር፣ ሕዝቧም ሕዝበ እግዚአብሔር እየተባለ እንደሚጠራ ይታወቃል፡፡ መጠራትም ብቻ ሳይሆን ሕዝባችን በፈሪሀ እግዚአብሔር ተከባብሮ እንኳን የራሱ የሆነውን ወገኑን ቀርቶ ሌላውን እንደራሱ አድርጎ የሚወድ፣ ያለው ከሌለው ጋር የሚካፈልና በደግነቱ የሚታወቅ ሕዝብ መሆኑን ዓለም የሚመሰክረው ነው፡፡ በመሆኑም ይህ የደግነት ምሳሌነታችን በተለይም በዚህ የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ በጸናበትና ሁሉም ወገን የችግሩ ተጋላጭ ሆኖ በተገኘበት በአሁኑ ጊዜ ያለውን ለሌለው በማካፈል ይበልጥ ደግነታችን ጐልቶ እንዲታይ የሚያስፈልግበት ወቅት ላይ እንደምንገኝ የተገነዘበው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሁላችንም ባለን ነገር ሁሉ በመረዳዳት ይህን ፈታኝ ጊዜ እንድናልፈው ጥሪውን ያቀርባል፡፡
5. ከዚህም ጋር ዜጋው እንደ ሀገር በሁለት እግሩ ቁሞ ህልውናው ተጠብቆ ሊኖር የሚችለውና ሀገራዊ ልማትም ሆነ ሕዝባዊ እድገት ሊመጣ የሚችለው በሁሉም ዘንድ ሰላምና አንድነት መግባባትም ጭምር ሲኖር እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ በሀገራችን በፖለቲካ ድርጅቶች መካከል እየታየ ያለው አለመግባባትና የቃላት መወራወር በአጭሩ ካልተገታና ወደ መግባባት በመምጣት መፍትሔ ካልተበጀለት ተጨማሪ ሀገራዊ ቀውስ ሊያስከትል፣ ከፍተኛም ዋጋ ሊያስከፍል እንደሚችል በመገንዘብ የሚመለከታችሁ የፖለቲካ ድርጅቶች ሁሉ ለሀገራዊ ሰላምና ለሕዝባዊ አንድነቱ በጋራ እንድትቆሙ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
6. ሀገራችን ኢትዮጵያን ለከፍተኛ እድገት ያበቃል ሕዝባችንን ከድህነት አረንቋ ያወጣል በሚል እምነት ከረጅም ጊዜ አንሥቶ ሕዝባችን ትኵረት ሰጥቶ ምንም ሳይኖረው ጦሙን እያደረ አስተዋፅኦ በማድረግ እዚህ ደረጃ ላይ ያደረሰው የሕዳሴ ግድባችን አብዛኛው የግድቡ ሥራ እየተጠናቀቀና ወደ ፍጻሜውም እየደረሰ መሆኑን ስለተገለጸ ጉባኤው በከፍተኛ አድናቆት ተመልክቶታል፡፡ በቀጣይም የግድቡን ፍጻሜ ለማየት፣ የመላውን ሕዝባችን ርብርብ እንደሚጠይቅ ግንዛቤ የተወሰደ በመሆኑ እንደአባቶቻችን ለትውልድ የሚተርፍ ታሪክ ለመሥራት ሕዝባዊ አንድነቱና ተሳትፎው እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም ከግንቦት 4-6 ቀናት በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ፣ እንዲሁም ሀገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲነጋገር የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ተጠናቅቆ በዛሬው ቀን በጸሎት ተዘግቷል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!