የካቲት 16 ቀን 2012 ዓ.ም የዐቢይ ፆም መግቢያ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና በተለያዩ የውጭ ሀገር ክፍለ ዓለማት የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናንና ምእመናት፣ እንዲሁም ኢትዮጵያውያን የሆናችሁ ወገኖቻችን በሙሉ፡፡ በጾምና በጸሎት፣ በሰላምና በፍቅር የሚቀርብለትን የምእመናን ተማኅፅኖ ተቀብሎ ምሕረትንና ይቅርታን ለሕዝቡ የሚያድል እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሁለት ዓመተ ምሕረት የጾመ ኢየሱስ ሱባዔ በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ፤ ወኢይትኀፈር ገጽክሙ
ወደ እርሱ ቅረቡ፤ ያበራላችሁማል፣ ፊታችሁም አያፍርም።”
(መዝ. 34፥5)

አምላካችን እግዚአብሔር የምልአተ ዓለም የበላይ ጠባቂና አስተዳዳሪ፣ መጋቢና መሪ፣ ውሳኔ ሰጭና ተቈጣጣሪ ነው፤ እግዚአብሔር በምልአተ ዓለም ውስጥና ከዚያም በላይ በምልአትና በርቀት ያለ ነውና ሁሉንም ማድረግ የሚቻለውና የሚሳነው ነገር የሌለ የኀያላን ኀያል፣ የጥበበኞች ጥበብ፣ የልዑላን ልዑል ነው፡፡ የፍጡራን ችግሮች በሙሉ ሊቀረፉ የሚችሉት በእሱ ፈቃድና ጥበብ ብቻ ነው፤ እኛ ፍጡራን የእርሱ ፈቃድ ማስፈጸሚያ እንሆን እንደሆነ እንጂ በራሳችን ዕውቀትና ጒልበት ብቻ የምናከናውነው ሥራ፣ የምናርቀው መከራ የለም፤ ይህንን ማድረግ የሚያስችል ዐቅም ቢኖረን ኖሮ ዓለማችን ሁሌ በሥጋት ተወጥራ ለመኖር አትገደድም ነበር፡፡

እግዚአብሔር በዳኝነቱ ኰናኒ በርትዕ፣ ፈታሒ በጽድቅ ነውና በበደላችን ከመፍረድ ወደኋላ ስለማይል ኰናኒ በርትዕ ይባላል፤ ንስሓ ገብተን፣ በጾምና በጸሎት ልባችንን ሰብረን፣ ወደእርሱ ከተመለስን ደግሞ፣ ምሕረቱንና ይቅርታውን ለመስጠት ጊዜ የማይወስድ ነውና ፈታሒ በጽድቅ ይባላል፡፡ ‹‹እስከ ሺሕ ትውልድ ቸርነትን የሚጠብቅ፣ አበሳንና መተላለፍን፣ ኀጢአትንም ይቅር የሚል፣ በደለኛውን ግን ከቶ የማያነፃ ነው›› የሚለው፣ የእግዚአብሔር ቃልም ይህንን ያረጋግጣል፤ ይህም ማለት ንስሓ ገብቶ በጾምና በጸሎት ለሚቀርብ ይቅር የሚል፣ ንስሓ ሳይገባ በበደሉ ጸንቶ ለሚኖር ግን ይቅር የማይል እውነተኛ ዳኛ ነው ማለት ነው፡፡ እንግዲህ ችግርንና ጭንቀትን የማስወገድ ፍጹምና ወሳኝ ኀይል ያለው እግዚአብሔር ብቻ ከሆነ በዓለማችንም ሆነ በሀገራችን እንደዚሁም በየግላችን ከሚያጋጥሙን ፈተናዎች እንዲታደገን ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ግዴታችን ይሆናል፤ ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ ደግሞ የተሰበረ ልብ ሊኖረን ይገባል፤ የተሰበረ ልብ ማለት በበደሉ እጅግ የተጸጸተና ዳግም ኀጢአትን ላለመፈጸም በቍርጥ የወሰነ ማለት ነው፤ ከዚህ አንጻር ጾም የኅሊና ጸጸትን ከፍ በማድረግ ለእግዚብሔር እንድንታዘዝ የሚያደርገን ፍቱን መሣሪያ ነው፤ ስለሆነም ወደ እግዚአብሔር ቀርበን ለመለመንና ለመሰማት፣ ወደ ንስሓም ለመገሥገሥ ጾምና ጸሎት አስፈላጊዎቻችን ናቸው ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

ጾም ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጀምሮ የቀደምት አበው፣ የነቢያት፣ የጌታችን የኢየሱስ ክርስቶስና የሐዋርያት፣ እንደዚሁም የሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን ቀዋሚ ሕግ ነው፤ ውጤቱም ምሕረትና ይቅርታ፣ ሰላምና መዳን እንደሆነ በነነዌ የሆነውን ታሪክ ማስረጃችን ነው፡፡ ጾም የኀጢአትና የበደል አበጋዝ የሆነው ዲያብሎስን ድል ለማድረግም ዐቢይ መሣሪያ ነው፤ ዲያብሎስ በአዳም ያስለመደውን በመብል አሳስቶ የመጣል ስልት፣ ጌታችን በጾም ኀይል አሳፍሮና ድል አድርጎ እንደመለሰው ከቅዱስ ወንጌል እንማራለን፤ በዚህም ጾም ፈቃደ እግዚአብሔር በፈቃደ ዲያብሎስ ላይ የበላይነትን እንዲጐናጸፍ የሚያደርግ ረቂቅ ኀይል እንደሆነ እንገነዘባለን፤ እኛ ክርስቲያኖች ጾምን የምንጾመው ከዚህ በላይ በተጠቀሰው መሠረታዊ አስተምህሮ ነው፡፡

ጾም የሚያስገኘው መንፈሳዊ ኀይል ብዙ እንደሆነ ሁሉ፣ ሠራዊቱም ብዙ ነው፤ ጾም ሲባል ብዙ ጊዜ ወደ ሰዎች አእምሮ የሚመጣው የእንስሳት ውጤት ከሆኑ ምግቦች መከልከልና ሰዓታትን ጠብቆ መመገብ የሚለው ነው፤ ነገር ግን የጾም ዐላማ በንስሓ ወደ እግዚአብሔር መቅረብ ነውና ከምግብ መከልከል ብቻ ወደ እግዚአብሔር እንድንቀርብና መልስ እንድናገኝ የሚያስችለን አይደለም፤ ወደ እግዚአብሔር ስንቀርብ በፍጹም ሓሳባችን፣ በፍጹም ልባችን፣ በፍጹም ነፍሳችን ነውና በአካላችንና በመንፈሳችን ሁሉ ለእግዚአብሔር ሙሉ በሙሉ ለመታዘዝ ዝግጁ በመሆን ልንጾም ይገባል፡፡ በመሆኑም በጾም ወቅት ከጥላቻና ከዛቻ፣ ፍትሕን ከማጕደልና ሰውን ከመበደል፣ ከቂምና ከበቀል ርቀን፣ እጃችንም፣ እግራችንም፣ አፋችንም፣ ዓይናችንም፣ ጆሮአችንም፣ ውስጣችንም፣ ውጫችንም ሁሉ በመልካም ሥነ ምግባርና በመንፈሳዊ ሕይወት አሸብርቀን መጾም ይገባናል፤ በዚህ ወቅት መስማትና ማዳመጥ ያለብን እግዚአብሔርና እግዚአብሔርን ብቻ ነው፤ የእግዚአብሔር ድምፅ ፍቅርና ሰላም፣ አንድነትና ስምምነት፣ ዕርቅና ይቅርታ፣ ምሕረትና ቸርነት፣ ርኅራኄና ኀዘኔታ፣ ጸሎትና ምፅዋት፣ ፍትሕና እውነት፣ እኩልነትና ኅብረት ነው፡፡ እነዚህን በሥራ በመተርጐም እየጾምን ወደ እግዚአብሔር ከቀረብን የጨለመብንን ሁሉ ያበራልናል፤ በፊቱም ሳናፍር የፈለግነውን ሁሉ አግኝተን እንመለሳለን ፡፡

በመጨረሻም፤ ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ ከገጠማት ሥጋትና ጭንቀት ለመገላገል በጾምና በጸሎት ወደ እግዚአብሔር በመቅረብ ከመማፀን የተሻለ አማራጭ ሊኖር አይችልምና ሕዝበ ክርስቲያኑ የተቸገሩትን በመርዳት፣ በጾም፣ በጸሎት፣ በሰቂለ ኅሊና፣ በተመሥጦ ልቡና፣ ጽሙድ እንደ በሬ፣ ቅኑት እንደ ገበሬ ሆኖ ስለ ሀገር ሰላም፣ ስለሕዝቦች አንድነትና እኩልነት መጠበቅ፣ ወደ እግዚአብሔር በምሕላ እንዲያመለክት በእግዚአብሔር ስም መንፈሳዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ወርኀ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን፤ እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

የካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የእነ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን ሥልጣነ ክህነት በውሳኔ ማገዱን ቅዱስነታቸው እንደሚከተለው ገልጸዋል፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያኒቱና በምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር አስመልክቶ ከየካቲት 9 -11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለሦስት ተከታታይ ቀናት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ተነጋግሮ በቤተ ክርስቲያናችን በተለያዩ ገዳማትና አብያተ ክርስቲያናት እንዲሁም የቤተ ክርስቲያናችን ተከታይ የሆኑ ምእመናን ላይ እየደረሰ ያለውን ችግር አስመልክቶ በመነጋገር እና ውሳኔ በማሳለፍ የሚከተለውን መግለጫ አውጥቷል፡፡

1. በቦሌ ክፍለ ከተማ ወረዳ 4 እና 5 በቀድሞው ቀበሌ 24/18/16 እና 15 ነዋሪዎች ለቅዱስ ሲኖዶስ ባቀረቡት አቤቱታ እንደተገለጸው በ24/5/2012 ዓ.ም. ለ25 አጥቢያ በውድቅት ሌሊት በቦሌ ቅዱስ ገብርኤል እና ቅድስት አርሴማ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሆኑ ምእመናን በምሕላና በጸሎት ላይ እያሉ በተኵስና አስለቃሽ የመርዝ ጋዝ ጭስ በመጠቀም በጥይትና በዱላ በርካታ ሰዎች ላይ የአካል ጉዳት መድረሱ ሁለት የቤተ ክርስቲያናችን አማንያን ወጣቶች መገደላቸውን ቤተ ክርስቲያኑ ፈርሶ ክቡር የሆነውና በአባቶች ተባርኮ የነበረው የቃል ኪዳን ጽላት መወሰዱ፣ የቤተ ክርስቲያኑ ንዋያተ ቅድሳት መዘረፋቸውን የሰማው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በድርጊቱ እጅግ ከማዘኑም በላይ ይህን ክፉና ጭካኔ የተመላበት ድርጊት አውግዟል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችንም ላይ እንዲህ ዐይነት ክፉ ድርጊት የፈጸሙ አካላት ላይ መንግሥት ጥብቅ ምርመራ በማድረግ ወንጀለኞቹ ለፍርድ እንዲቀርቡና ውጤቱ ለምእመናኖቻችን በሚዲያ እንዲገለጽ እንጠይቃለን፡፡
2. የቤተ ክርስቲያኒቱን ቦታ በተመለከተ ቤተ ክርስቲያናችን ከአራት ዓመታት በፊት ጀምሮ ቦታው ለአካባቢው ምእመናን ማምለኪያ እንዲሆን ከመንግሥት በመነጋገርና በመጻጻፍ የቆየችበት ከታቦተ ሕጉ ጀምሮ ንዋያተ ቅድሳት የከበሩበት ከመሆኑም ባሻገር ሁለቱ የቤተ ክርስቲያናችን አማንያን ወጣቶች በግፍ ጨለማን ተገን ባደረጉ የመንግሥት ፀጥታ አስከባሪዎች ደማቸው የፈሰሰበትና ሕይወታቸው ያለፈበት ቅዱስ ቦታ እንደመሆኑ መጠን ወደ ቀደመ ክብሩ ተመልሶ ሕንጻ ቤተ ክርስቲያን ተሠርቶ ምእመናን በሰላም መንገድ አምልኮአቸውን እንዲፈጽሙ የሚመለከተው የመንግሥት አካል የበኩሉን መመሪያ እንዲሰጥልን ቅዱስ ሲኖዶስ ይጠይቃል፡፡
3. ይህ ደም የማፍሰስና ሕይወትን የማጥፋት ተልእኮ አልበቃ ብሎ በየምክንያቱ የታሰሩ ካህናትና ምእመናን ወጣቶችም ጭምር በእስር ላይ መሆናቸው ስለሚታወቅ ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከእስራት እንዲፈቱ እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ይጠይቃል፡፡
4. ሀ. ከቤተ ክርስቲያኒቱ ሕግና ደንብ ውጭ በመነሳሳት የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት እናቋቁማለን በማለት በሕገ ወጥ መንገድ የሚንቀሳቀሱ እንዲሁም በቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ ጽላት ተሰጥቶናል በሚል በምድረ አሜሪካ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም ቤተ ክርስቲያን አቋቁመናል የሚሉት፡- (1) ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኮንን (2) አባ ገ/ማርያም ነጋሳ (3) መምህር ኀ/ሚካኤል ታደሰ (4) ቄስ በዳሳ ቶላ፣ እነዚህ ግለሰቦች ቤተ ክርስቲያናችን በማታውቀው መንገድ በዐመፅ በመነሳሳት ምእመናንን ግራ እያጋቡና እያሳሳቱ መሆኑን እንዲሁም ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አስተምህሮ ውጭ የክህደት ትምህርት ማስተማራቸው በመረጃ ተደግፎ ለቅዱስ ሲኖዶሱ ጉባኤ የቀረበ በመሆኑ እነዚሁ ከላይ ስማቸው የተጠቀሰ የኦሮምያ ቤተ ክህነት አደራጆች ነን የሚሉ ከድርጊታቸው ተቈጥበው በንስሓ እስኪመለሱ ድረስ ከየካቲት 11 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ ከቤተ ክርስቲያናችን የተሰጣቸው ክህነት ተይዟል፡፡ በቤተ ክርስቲናያናችንም ስም ምንም ዐይነት እንቅስቃሴ እንዳያደርጉና መንፈሳዊ አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል፡፡ ግለሰቦቹ ከጥፋት ድርጊታቸው ተፀፅተው ለመመለስ ከፈቀዱ ጉዳያቸው በድጋሚ እንዲታይ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡
ለ. እነዚሁ ካህናት ነን የሚሉ ግለሰቦች በቅዱስ ሲኖዶስ ተባርኮ የተሰጠን ጽላት አለ በሚል ምእመናንን እያደናገሩ ቢሆንም እንደ ቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐትና ደንብ መሠረት ጽላት እንዲሰጣቸው ያልጠየቁ ከቤተ ክርስቲያናችንም የሰጣቸውም አካል አለመኖሩ በጉባኤው የተረጋገጠ በመሆኑ ምእምናን ከእንደዚህ ዐይነት ተሳስተው ከሚያሳስቱ ግለሰቦች ራሳቸውን ሃይማኖታቸውንና የቤተ ክርስቲያን ሥርዓታቸውን ከምንጊዜውም በላይ እንዲጠብቁ ጉባኤው አሳስቧል፡፡
5. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በርካታ ቅዱሳንና መናንያን ለአገርና ለወገን የሚጸልዩባቸው ታላላቅ ገዳማት እንዳሏት ይታወቃል፡፡ ሆኖም ከጥቂት ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ ገዳማት ላይ ግለሰቦች እያደረሱ ያለው ፈተናና ችግር ያለ መሆኑ ሲታወቅ በተለይም በአሁኑ ጊዜ፡-
ሀ. በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት በሊበን ዝቋላ ወረዳ የሚገኘው የዝቋላ ደብረ ከዋክብት አቡነ ገብረ መንፈስ ቅዱስ ገዳም፣
ለ. በሰላሌ ሀገረ ስብከት በታላቁ ደብረ ሊባኖስ ገዳም ሆን ተብሎ በአንዳንድ ግለሰቦችና ቡድኖች አማካኝነት እየደረሰ ያለው ችግር እና ታሪክን የማጠልሸት ሂደታቸው በአስቸኳይ እንዲቆም የሚመለከተውም የመንግሥት አካል ለጉዳዩ ትኵረት ሰጥቶ ችግር ፈጣሪዎችን እንዲያስቈም ለገዳማቱም የአገር ቅርስ እንደመሆናቸው ሁሉ አስፈላጊውን ጥበቃ እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነውን ውሳኔ መንግሥት እንዲያስፈጽምልን እንጠይቃለን፡፡
6. በዐረብ ኤምሬቶችና በዱባይ በስደት የሚኖሩ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያን ወገኖቻችን ከፈጣሪያቸው ጋር የሚገናኙበት እግዚአብሔርን የሚያመልኩበት ቤተ ክርስቲያን ለመሥራት የአገሪቱ መንግሥት ከቤተ ክርስቲያናችን የቦታ ጥያቄ እየቀረበለት ምላሽ ሳናገኝ እስከአሁን ቆይተን ነበር፡፡ በአሁኑ ጊዜ ግን የአገራችን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በዐረብ ኤምሬቶች ባደረጉት የሥራ ጒብኝት በዚያ የሚገኙ ኢትዮጵያውያን ዜጎቻቸውን ከማነጋገርና ከማጽናናት ባሻገር ከሀገሪቱ መንግሥት በመነጋገር ለክርስቲያን ወገኖቻችን የማምለኪያ ቤተ ክርስቲያን መሥሪያ ቦታ በማስፈቀዳቸው ከዚህም ጋር በዐረቡ ዓለም በስደት ይኖሩ የነበሩ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ከስደት እንዲመለሱና ለአገራቸው እንዲበቁ በማድረጋቸው ስደተኛ የሆኑ ክርስቲያን ወገኖቻችን በእጅጉ ያስደሰተና ቤተ ክርስቲያናችንም ሐዋርያዊ ተልእኮዋን እንድታስፋፋ የሚያግዝ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በእጅጉ ከመደሰቱም በላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ወደዚህ ሀገራዊ መንበረ ሥልጣን ከተጠሩበት ጊዜ ጀምሮ የቤተ ክርስቲያናችንን ጉዳይ ጉዳያቸው አድርገው እየፈጸሙት ያለ አኵሪ መንፈሳዊ ተግባር ሁኖ ስላገኘው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የከበረ ምስጋናውን አቅርቧል፡፡
7. በኢትዮጵያ ብሮድካስት ባለሥልጣን፡- በ“OMN”፣ በ“LTV”፣ በ“OBS” ቴሌቪዥን ጣቢያዎች ከጥቂት ጊዜያት ወዲህ በጥንታዊትና ሐዋርያዊት በሆነችዋ ለአገርና ለወገን ባለውለታና ባለ ታሪክ በሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን የከፈቱት የስም ማጥፋት ዘመቻ ማካሄዳቸው ታሪክን እያበላሹ የተሳሳተ መረጃ ለሕዝብ ማስተላለፋቸው ከዚህም የተነሣ ከ60 ሚሊዮን ያላነሰ ተከታይ ያላትን ቤተ ክርስቲያን ክብሯንና ልዕልናዋን ዝቅ ባደረገ መልኩ የሚያስተላልፉት የተሳሳተ መረጃ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ ብቻ ሳይሆን አገራዊ ቀውስ ለማምጣት እየተደረገ ያለ ጥረት በመሆኑ የሚመለከተው የመንግሥት አካል አስፈላጊውን ማጣራት በማድረግ የጣቢያዎቹ ኀላፊዎች ከብዙኃን መገናኛ ሕግ እና ደንብ አኳያ በሕግ እንዲጠየቁ ለወደፊቱም ከእንዲህ ዐይነት ሕገ ወጥ ድርጊት እንዲታቀቡ መንግሥትም በዚሁ ላይ አስፈላጊውን ውሳኔ እንዲያሳልፍልን ቅዱስ ሲኖዶስ ጠይቋል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከየካቲት 9-11 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ለ3 ተከታታይ ቀናት ባደረገው አስቸኳይ ስብሰባ ከዚህ በላይ በተገለጹት ነጥቦች ላይ ከመከረና ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ በኢትዮጵያ አገራችን በመንግሥትና በሕዝቡ ጭምር እየተከናወኑ ያሉ ተግባራት ማለትም ሕዝባዊ አንድነት እንዲጐለብት፣ ማኅበራዊና ልማታዊ ተግባራት እንዲፋጠኑ፣ በአጠቃላይ በአገራችን ሰላምና አንድነት ሰፍኖ አገራችን ኢትዮጵያ መላው ዜጋ ከሚመኝላት የእድገት ጫፍ እንድትደርስ እንደ አንድ ልብ መካሪና እንደ አንድ ቃል ተናጋሪ ሆኖ ለሀገሩና ለሕዝባዊ አንድነቱ ጸንቶ እንዲቆም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥሪውን በማስተላለፍ ጉባኤውን በዛሬው ዕለት በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር ሀገራችንን ኢትዮጵያን ይባርክ ቤተ ክርስቲያናችንን ይጠብቅ ለሕዝባችንም አንድነቱንና ሰላሙን ይስጥልን፣አሜን፤