ጥር 11 ቀን 2012 ዓ.ም የጥምቀት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

“ሀለወክሙ ትትወለዱ ዳግመ
ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል፤”
(ዮሐ. 3፥7)

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ዳግም ልደትንና አስፈላጊነቱን አስመልክቶ ያስተማረው ተቀዳሚ ትምህርት በዚህ ምዕራፍ ተጽፎ ይገኛል፡፡ ጌታችን በዚህ ትምህርቱ የልደት ዐይነት ሁለት እንደሆኑ እነሱም ሥጋዊና መንፈሳዊ ልደት እንደሚባሉ በአጽንዖት አስተምሮአል፡፡ ሥጋዊ ልደት ሰው ሁሉ ከእናቱና ከአባቱ በግዘፍ የሚወለደው ነው፤ ይህ ሁሉም የሚያየውና የሚያውቀው ስለሆነ ተጨማሪ ማብራርያ አያስፈልገውም፤ መንፈሳዊ ልደትን በምንመለከትበት ጊዜ ግን እንደ ስሙ መንፈሳዊ ወይም ረቂቅ ስለሆነ ማስተዋልን በእምነት መነጽር መመልከትን ይጠይቃል፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ አስተምህሮው ሰው ሁሉ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት የሚገባበትን ምሥጢር ገልጾአል፤ ቅዱስ መጽሐፍ ደጋግሞ እንደሚያስተምረን ሰው ለክብር የተፈጠረ ታላቅ ፍጡር ነው፤ ይህንንም ማስተዋል የምንችለው ከሰው በቀር በእግዚአብሔር መልክና አምሳል የተፈጠረ ፍጡር በሰማይም ሆነ በምድር የሌለ በመሆኑ ነው፤ ይህ መልክና አምሳል ውጫዊውን የመልክ ገጽታ ብቻ የሚያሳይ ሳይሆን በእግዚአብሔርና በሰው መካከል ያለውን ጥብቅ ግንኙነት የሚያመለክት ነው፤ ይህ ግንኙነት በቅዱስ መጽሐፍ ውስጥ በአባትና በልጅ፣ በባልና በሚስት፣ በወይን ግንድና በቅርንጫፍ ወ.ዘ.ተ… ምሳሌነት ተገልጾአል፡፡ እግዚአብሔር ሰውን አክብሮና ከራሱ ጋር አስተሳስሮ የፍጡራን ሁሉ አዛዥና አስተናባሪ አድርጎ እንደዚሁም በምድር ላይ ብቸኛ የእግዚአብሔር ምስለኔና እንደራሴ አድርጎ መሾሙ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎአል፡፡

ይሁን እንጂ ይህ ግንኙነት በምክረ ሰይጣን ስለተቋረጠ ሰው በጣም አሳዛኝ በሆነ ሁኔታ ወደቀ፤ በዚህም ውድቀት የሰው ሁለንተና ሕይወቱ ተናጋ፤ ሥጋዊ ሕይወቱ በመከራ አረም ሙሉ በሙሉ ከመዋጡም ሌላ፣ ንጹሕ አእምሮው ተቃወሰ፤ ከሁሉም በላይ ደግሞ መውጫውንና መግቢያውን ትንፋሹንም ጭምር ከያዘና ሁሉን ከሚችል ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ልጅነት ተገለለ፤ ህላዌው ሁሉ በጨለማ የተዋጠ ሆነ፤ ሰው በዚህ ዓለም የሚቆይበት ሕይወት ተጠናቅቆ ሥጋው ወደ መቃብር ሲወርድ ነፍሱ ደግሞ ወደ መከራና ሥቃይ ቦታ ወደ ሲኦል ጒድጓድ መጣል ዕጣ ፈንታው ሆነ፡፡ ይህ ሁሉ አሰቃቂ ሕይወት ሊከሠት የቻለው ሰው የእግዚአብሔርን ምክር ንቆና ትቶ፣ የሰይጣንን ምክር አምኖና ተቀብሎ በፈጸመው ስሕተት ጠንቅ ነው፤ የበደለን መቅጣት፣ የታመነን መሸለም በፍጡር የማይጣስ ሕገ መለኮት ነውና ጥፋተኛ የሆነው የሰው ልጅ ከመቀጣት በቀር የሚያገኘው ሽልማት አልነበረውም፤ ሰውም ያለውድ በግድ ቅጣቱን ተቀብሎ መራራ ኑሮውን በሰማይም በምድርም ቀጠለ፤ ይህ ሁኔታ ጌታችን በሞቱ እስኪያስወግደው ድረስ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመናት ያህል ዘልቆአል፤ ከጌታችን ሞት በኋላ ግን ለሰው ልጆች እንደገና አዲስ ጒዞ ተጀምሮአል፤ እሱም በጌታችን ደም የሰው ልጅ በደል በመሠረዙ ምክንያት ከሞት በኋላ የሰው ነፍስ ጒዞ ወደ ሲኦል ጉድጓድ ሳይሆን ወደ ገነት ሆኖአል፤ ይህንንም ጌታችን በመስቀል ላይ ሳለ አምኖ ንስሐ ለገባው ወንበዴ “ ዛሬውኑ ከኔ ጋር በገነት ትኖራለህ” ባለው የማይሻር ቃሉ አረጋገጠው፤ በገነት መኖር ማለት አዳም ከመውደቁ በፊት ወደ ነበረው ጣዕመ ሕይወትና ቦታ እንደገና መመለስ ማለት ነው፡፡

እንግዲህ በአሁኑ ጊዜ የሰው ልጅ ሁሉ ትልቁ ጥያቄ ይህንን ገነታዊ ጣዕመ ሕይወት እንዴት እናግኝ የሚል ነው፤ ጥያቄው ትክክለኛና የአስተዋይ ሰው ሁሉ ጥያቄ ነው፤ ነገር ግን ጥያቄው የዛሬ ሁለት ሺሕ ዓመት በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ አስተምህሮ አጥጋቢና እውነተኛ መልስ ያገኘ በመሆኑ እሱን በሚገባ መረዳትና መፈጸም ያሻል፡፡ ጌታችን አንድ የአይሁድ መምህርና ዐዋቂ፣ ሊቅና አስተዋይ ካቀረበው ጥያቄ ተነሥቶ ሲመልስ፡-“ እውነት እውነት እልሃለሁ፡- ዳግመኛ ያልተወለደ የእግዚአብሔርን መንግሥት አያያትም” ብሎአል፤ ጌታችን በዚህ ትምህርቱ የእግዚአብሔር መንግሥት በማለት የገለጸው ቦታ፣ ቃል ሊገልጸው ከሚችል በላይ ለኑሮ በጣም ምቹ የሆነና ራሱ በመስቀል ላይ ሳለ ገነት በሚል ስያሜ የጠራው ቦታ ነው፤ ማንኛውም ሰው ወደዚህ ቦታ ለመግባት ከሁሉ በፊት ዳግመኛ መወለድ ያስፈልገዋል፡፡ ዳግመኛ ካልተወለደ ግን መግባት ይቅርና በዐይን አሻግሮ ማየት እንኳ አይችልም፤ ጌታችን አያያትም ብሎአልና፡፡ ከዚህ አንጻር ወደ እግዚአብሔር መንግሥት መግባት የሚቻለው እንዴት ነው ለሚለው ጥያቄ መልሱ “ዳግመኛ በመወለድ ነው” የሚል መልስ ከጌታችን ተሰጥቶአል፤ ነገር ግን አእምሮው ውሱን የሆነው የሰው ልጅ አሁንም ጥያቄውን በማራዘም ሰው ካደገ በኋላ እንደገና ተመልሶ ወደ እናቱ ማሕፀን ሊገባና ዳግመኛ ሊወለድ እንዴት ይችላል በማለት ጠይቆአል፤ነገር ግን ጌታችን ለዚህም ሰፊ ማብራሪያና መልስ ጥልቅ ትምህርትም ሰጥቶአል፡፡ ጌታችን ይህንን አስመልክቶ በሰጠው ትምህርት ሰው ዳግመኛ ለመወለድ እንደገና ወደ እናት ማሕፀን መግባት አያስፈልገውም፤ ዳግመኛ መወለድ የሚቻለው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ነው ብሎአል፡፡

ጌታችን ዳግመኛ መወለድ የሚቻለው ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ነው ሲል፣ በውኃና በመንፈስ ቅዱስ በመጠመቅ ዳግመኛ መወለድ ይቻላል ማለቱ እንደሆነ ግልጽ ነው፤ እግዚአብሔር በጌታችን ሞት መነሻነት በዘረጋው ሰዎችን የማዳን አሠራር ሰዎች በፍጹም ልባቸው ሲያምኑ፣ በውኃ ሲጠመቁና በመንፈስ ቅዱስ ሲቀቡ ዳግመኛ ተወለዱ ማለት ነው፤ ዳግመኛ ልደት የሚፈጸመው በዚህ አኳኋን ነው፤ ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ዳግመኛ መወለድ ለምን አስፈለገ የሚል ጥያቄ ቢነሣ፣ ከሁሉ በፊት ሰው ወደ እግዚአብሔር መንግሥት ለመግባት ከኀጢአት መንጻት አለበት፤ ከዚያም በመንፈስ ቅዱስ ከብሮ መታተም አለበት፤ይህ ሲፈጸም እግዚአብሔር ተጠማቂውን ሰው በልጅነት ይቀበለዋል፤ከዚህ ጊዜ ጀምሮ ተጠማቂው ሰው የእግዚአብሔር ልጅና የእግዚአብሔር የሆነውን ሁሉ ወራሽ ነው ማለትም የእግዚአብሔር የሆነውን መንግሥተ ሰማያትንና በውስጡ የሚገኙ ሕይወታዊ ስጦታዎችን ሁሉ ያገኛል፤ ይወርሳልም፤ በአንጻሩ ደግሞ ማንኛውም ከውኃና ከመንፈስ ቅዱስ ያልተወለደ ሰው የእግዚአብሔር ልጅ መሆን አይችልም፤ በመንግሥተ ሰማያትና በውስጡ ያሉትን ስጦታዎችም ሊያገኝ አይችልም፤ ምክንያቱም ሰውየው ከሥጋ ብቻ የተወለደ ሥጋዊ እንጂ ከመንፈስ ያልተወለደ ነው፤ ከመንፈስ ሳይወለድም የመንፈስ የሆነውን ነገር ሊያገኝ አይችልም፤ ምክንያቱም ከሥጋ፣ የተወለደ ሥጋ፣ ከመንፈስም የተወለደ መንፈስ ነውና የመንፈስ የሆነውን ነገር ለማግኘት ከመንፈስ መወለድ የግድ ስለሆነ ነው፤ በዚህ ምክንያት ከውኃና ከመንፈስ መወለድ ግድ በመሆኑ ጌታችን ትምህርቱን ሲያጠቃልል “ዳግመኛ ልትወለዱ ያስፈልጋችኋል” ብሎ አትሞአል፡፡

ሰው በጥምቀት የሚያገኘው ሰማያዊ ሀብተ ርስት ይህን ያህል ታላቅና ለሰው ልጅ ሁሉ አስፈላጊ በመሆኑ ጌታችን ራሱ ለሁላችን መሪና አርኣያ በመሆን በእደ ዮሐንስ፣ በፈለገ ዮርዳኖስ ተጠምቋል፡፡ ጌታችን በዮርዳኖስ ወንዝ በተጠመቀ ጊዜ ሰማይ ተከፍቶአል፤ መንፈስ ቅዱስም በነጭ ርግብ አምሳል ከሰማየ ሰማያት ወርዶ በላዩ ተቀምጦአል፤ አብም በደመና ሆኖ “ይህ የምወደው ልጄ ነው” ሲል መስክሮአል፡፡ ይህ ክሥተት በእግዚአብሔር ማንነትና በሰው ልጅነት ምሥጢር ላይ ያነጣጠረ እውነታ እንደሚያንጸባርቅ ከድርጊቱ መረዳት ይቻላል፤ ይኸውም ከእግዚአብሔር ማንነት አንጻር ሲታይ እግዚአብሔር ሦስት አካላት እንዳሉት፣ የአካላት አስማትም አብ ወልድ መንፈስ ቅዱስ እንደ ሚባሉ፣ በእግዚአብሔር ዘንድ አባት፣ ልጅ፣ መንፈስ፣ የሚባሉ ሦስት ህልዋን አካላት እንዳሉ ግልጽ ሆኖአል፡፡ ከሰው ልጅነት አንጻር ሲታይ ደግሞ ሰው አምኖ ሲጠመቅ እግዚአብሔር በልጅነት እንደሚቀበለው፣ ሰማያዊ በሩንም ከፍቶ ወደ ዘለዓለማዊ መንግሥቱ እንደሚያስገባው ክሥተቱ ያመለክታል፤ በመሆኑም የእግዚአብሔር ማንነት ማለትም አንድነቱ እና ሦስትነቱ የተገለጸበት፣ የጌታችንም የልጅነቱ ክዋኔ የተረጋገጠበት፣ በዚያው አንጻርም የሰው መንፈሳዊ ልደት የተመሠጠረበት ዕለት በመሆኑ በዓለ ጥምቀት በግሪክ ቋንቋ ኤጲፋንያ፣ በግእዝ አስተርእዮ፣ በአማርኛ መገለጥ ይባላል፡፡ ምክንያቱም በዓለ ጥምቀተ ክርስቶስ እግዚአብሔር ስለራሱ ማንነት፣ ስለክርስቶስ አምላክነት እንደዚሁም ስለ ሰው ልጅ ልጅነት የተገለጠበትና እግዚአብሔር ወሳኝ መልእክቱን ያስተላለፈበት ዕለት ነውና፡፡

በሌላ በኩል ጥምቀት ለሰው ልጆች ድኅነት በጣም ወሳኝ ነገር መሆኑን ከምናውቅባቸው ዐበይት ነገሮች መካከል፣ ጥምቀት ለጌታችን ትምህርት መነሻና መድረሻ ወይም ርእስና መደምደሚያ ሆኖ መሰጠቱ ነው፤ ጌታችን የማዳን ትምህርቱንና ሥራውን የጀመረው በዕለተ ጥምቀት፣ በፈለገ ዮርዳኖስ በፈጸመው ድርጊት ነው፤ ያጠናቀቀውም ሊያርግ ሲል በአስተላለፈው ገዢ የጥምቀት ትምህርት ነው፤ ይኸውም ጌታችን ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ወደ ሰማይ የሚያርግበት ቀን ሲቀርብ፣ ለደቀ መዛሙርቱ ያስተላለፈው የመጨረሻ ትእዛዝና ትምህርት “አሕዛብን ሁሉ አስተምሩ፤ በአብ በወልድ በመንፈስ ቅዱስ ስምም አጥምቋቸው፤ ያመነ የተጠመቀ ይድናል፤ ያላመነ ግን ይፈረድበታል” የሚል ነው፤ ስለሆነም ጌታችን ትምህርቱን የጀመረና ያጠናቀቀ በነገረ ጥምቀት መሆኑን ስናስተውል፣ ጥምቀት ለድኅነታችን ያለው ቦታ ከፍተኛ መሆኑን እንገነዘባለን፡፡ እንግዲህ ጥምቀት የድኅነታችን ቊልፍ ምስጢር መሆኑን ካየን ከእኛስ ምን ይጠበቃል የሚለውን ማየት ይኖርብናል፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን የሰው ልጅ ድኅነት የሁለትዮሽ ውጤት ነው፤ ይህም ማለት በእግዚአብሔርና በሰው ጥምር ተግባር የሚከናወን ነው ማለት ነው፤ ሰዎች ወደዱም ጠሉም፣ ተቀበሉም አልተቀበሉም ይህ የእግዚአብሔር መለኮታዊ አሠራር ነው፤ ጌታችን ሰዎችን ከልዩ ልዩ በሽታ ሲፈውስ በራሱ ፈቃድ ብቻ አልነበረም፤ የበሽተኛው ፈቃድም የተጠበቀ ነበረ እንጂ፤ ለመዳን በሽተኛው ቢያንስ ፍላጎቱን ወይም ዝንባሌውን ማሳየትና መግለጽ ይጠበቅበታል፡፡ ለዚህም ነው ጌታችን ልትድን ትወዳለህን ? ይህንን እንደማደርግ ታምናለህን? ምን ላደርግልህ ትወዳለህ? እያለ ሰዎችን ሲጠይቅ የምናየው፤ ጌታችን ይህንን የሚያደርገው እውን ሰዎች የሚፈልጉትን የማያውቅ ሆኖ ነውን? ወይስ የሚጠቅማቸው ምን እንደሆነ ያውቅ የለምን? ለምን ይጠይቃቸዋል ተብሎ ቢጠየቅ መልሱ ያውቃል ነው፤ ነገር ግን በእርሱ ዘንድ የሰው ኅሊናዊ ነፃነት የተጠበቀ መሆኑንና ምርጫው የግለሰቡ መሆኑን፣ መዳን ቢሆንም ከምርጫው ውጭ በግድ መፈጸም አግባብ አለመሆኑን ለማሳየት እየጠየቀና እያስፈቀደ ያድን ነበረ፡፡

ይህ ሁሉ የሚያስገነዝበን ነገር ቢኖር መዳን በዳኑና በአዳኙ የጋራ ፈቃድ የሚከናወን መሆኑን ነው፡፡
ይህም ማለት ፍላጎት፣ ዝንባሌ፣ ተነሳሽነት፣ ታዛዥነትና በእምነት ራስን ለእግዚአብሔር ንጹሕ መሥዋዕት አድርጎ ማቅረብ ከሰው ይፈለጋል፤ በይቅርታና በምሕረት ተቀብሎ ማንጻት ማክበርና ተጠማቂውን በልጅነት መቀበል ደግሞ ከእግዚአብሔር ይጠበቃል፤ እነዚህ አንድ ላይ ተጣምረው ሰውን ለድኅነት ያበቁታል ማለት ነው፤ እንግዲህ የድኅነት መንገድ ይህ ከሆነ እያንዳንዳችን ክርስቲያኖች እኔስ የት ነው ያለሁ ብለን ራሳችንን በራሳችን መጠየቅና ያለንበትን ተጨባጭ ሕይወት የት እንደሆነ ማወቅ ይገባናል፤ ሕይወታችንን በዚህ አቅጣጫ ካየነው ያለንበትን ሁኔታ በትክክል እንድናውቅ ያደርገናል፤ ማወቅ ብቻም ሳይሆን በንስሐ እየታደስን ለእግዚአብሔር ልጅነታችን በሚመጥን ሃይማኖትና ሥነ ምግባር ጸንተን እንድንኖር ያስችለናል፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የጥምቀትን በዓል በየዓመቱ በታላቅ ሥነ ሥርዐት የምታከብረው ይህንን የመዳን አስተምህሮ እንዳይረሳና የሰው ልጆች ወደ አጥፊ ጎዳና እንዳይጓዙ ለማድረግ ነው፤ ስለሆነም የጥምቀትን በዓል ስናከብር የመዳናችንን ነገር በማሰብ፣ በእሱ ለመጠቀምም የኅሊና ዝግጅት በማድረግና እሱን ለመተግበር ቁርጥ ውሳኔ በማሳለፍ እንጂ ሥነ በዓሉ ስለማረከን፣ ወይም ባህላዊ ገጽታው ስለሚስብ፣ ወይም ሆታውና እልልታው፣ መዝሙሩና ግብዣው ስለናፈቀን መሆን የለበትም፤ የእግዚአብሔር ፈቃድ አንድ ስንኳ እንዳይጠፋ ነውና እንደፈቃዱ መኖር ይገባናል፤ የፈቃዱ ተጋሪዎች በመሆንም ራሳችንን ከጥፋት ለማዳን ዘወትር መትጋት ይኖርብናል፡፡

መልካም የጥምቀት በዓል እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

ታኅሣሥ 28 ቀን 2012 ዓ.ም፡ የበዓለ ልደት ቃለ በረከት አስተላልፈዋል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤ በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ በልደቱ “ሰላም በምድር ይሁን” የሚል የሰላም መዝሙርን ያሰማን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሁለተኛው ዓመት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ !!

‹‹ተወልደ እምአመቱ ወሰላመ ገብረ በልደቱ፤
ከአገልጋዩ ተወለደ፤ በልደቱም ሰላምን አደረገ።››
(ቅዱስ ያሬድ)

በዓለ ልደተ ክርስቶስን ባነሣን ቊጥር በኅሊናችን ፈጥኖ የሚታወሰን ትልቅ ትዝታ፣ መላእክትና እረኞች በቤተልሔም ተገኝተው ‹‹‹ ሰላም በምድር ይሁን›› በማለት በአንድነት የዘመሩትን መዝሙር ነው፤በእርግጥም ይህ መዝሙር ጌታችን ሰው ሆኖ ከቅድስት ድንግል ማርያም በመወለድ በዚህ ዓለም የተገለጠበትን ምሥጢር የሚተረጕም ነው፡፡ ሁሉም እንደሚገነዘበው የሰላም ዋጋና ጣዕም በሰማይም ሆነ በምድር መተኪያ የማይገኝለት ነው፤በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰውና በመላእክት እንደዚሁም በሰውና በሰው መካከል ተገድግዶ የነበረው የጥል ግድግዳ ለሰው ብቻ ሳይሆን ለመላእክት ተልእኮም ዕንቅፋት መሆኑ አልቀረም፤ ምክንያቱም መላእክት በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረው ሰው ከቅድስና ስፍራ ተባርሮ በጐስቋላ ሕይወት ኑሮውን ሲገፋ ባዩ ቊጥር ደስታቸው ፍጹም አልነበረምና ነው፡፡ የቅዱሳን መላእክት ደስታ ፍጹም የሚሆነው ሰዎች በተመደበላቸው የክብር ስፍራ ሲገኙ እንደሆነ “በአንድ ሰው ንስሓ መግባት በሰማይ ታላቅ ደስታ ይሆናል” ተብሎ የተነገረው አምላካዊ ቃል በቂ ማስረጃ ነው፡፡ በልደተ ክርስቶስ ቀን ግን ከዚህም አልፎ በጐስቋላ ይሕወት ይማቅቅ የነበረው ሰው በተዋሕዶተ መለኮት በመንበረ ጸባኦት ዙፋን ተቀምጦ አይተዋል፤ከዚህም በመነሣት እግዚአብሔር ሰውን ከመታረቁና ከመሙደዱም በላይ በተዋሕዶ የሰው አካልና ባሕርይን የራሱ አካልና ባሕርይ ማድረጉን አስተውለዋል፡፡ በዚህ ጊዜ ነበር የሆነው ድርጊት በትክክል ሊገልጥ በሚችል አገላለጽ ‹‹እግዚአብሔር ሰውን በእጅጉ ወደደው በሰላምም ጐበኘው፤ ይህንንም ስላደረገ ከፍ ያለ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይገባል›› በማለት መላእክትና ሰዎች የዘመሩት፣ መዝሙር በደማቅ ብርሃን የታጀበ ሰማያውያን ሠራዊትና ሰዎች በአንድነት የተሳተፉበት ድንቅ የሆነ የሰላም መዝሙር ነበር፡፡

ሰላም ለምድራውያን ብቻ ሳይሆን ለሰማያውያንም ውድና በጣም ተፈላጊ ስለ መሆኗ በልደተ ክርስቶስ ዕለት የተፈጸመው ሁናቴ ትልቅ መምህራችን ነው፤ያለ ሰላም ሃይማኖታዊ ሥርዐትን በአግባቡ ማካሄድ አይቻልም፤ ትምህርተ ሃይማኖትን አስተምሮ ማሳመንም አይቻልም፤ ሰላም ሳይኖር በልቶ፣ ጠጥቶና አጊጦ መኖር አይቻልም፤ ሰላም ሳይኖር ተምሮ መመረቅ፣ነግዶ ማትረፍ፣ አርሶ ማምረት፣ወልዶ ማሳደግ፣ድሮ መኳል የለም፤ሰላም ከደፈረሰ የኅብረተሰብ ኑሮ ይናጋል፤ ልማት ይቆማል፣ ድህነትና ችግር ይንሰራፋል፤ በመሆኑም የሰላም ጥያቄ የህልውና ቊጥር አንድ ጥያቄ መሆኑን ተገንዝበን ትልቁም ትንሹም፣ ሕዝብም መንግሥትም ከምንም በላይ ለሰላም ያለመታከት መሥራት አለብን፡፡ በዛሬው ዕለት የምናከብረው በዓለ ልደተ ክርስቶስም ለሰላም ተብሎ የሚከበር በዓል መሆኑን ማጤን ተገቢ ነው፤ይህ በዓል አካላዊ ቃል የሆነው እግዚአብሔር ወልድ አካላችንን አካል እስከ ማድረግ ደርሶ ምሕረትንና ይቅርታን ለሁላችን ማድረጉን በማስተማር የሚከበር በዓል ነው፡፡ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በልደቱ ሰላምን የሰበከልን፣ለሰው ልጆች በዚህም ሆነ በወዲያኛው ዓለም ከሰላም የበለጠ አስፈላጊ ነገር እንደሌለ ስለሚያውቅ ነው፤ሰላም ካለ ሌላው ሁሉ በሰላም ውስጥ ይገኛልና፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፡ ዛሬ በዓለም ዙሪያ ሁሉ የሚስተዋለው የጦርነት ሥጋት፣ የበሽታዎች መዛመት፣ የስደተኞች ንረት፣ የፍትሕና የእኩልነት መዛባት ምንጫቸው የሰላም ዕጦት እንደሆነ አንስተውም፤ የሰው ኅሊና በሰላም አየር የተሞላ ቢሆን ኖሮ ሥጋቱ ይቀርና ለአጥፊ መሣሪያና ለመሳሰለው የሚወጣው ወጪ ለልማትና ለድሆች ድጋፍ ይውል ነበር፣ የዓለማችንን ችግር ለማስወገድ ለጦርነት የሚወጣው ወጭ ከበቂም በላይ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ እግዚአብሔር በሀብተ ጸጋ የተሞላች ምድር ቢሰጠንም በራሳችን ደካማ አያያዝና የተሳሳተ አመለካከት ወደ ድህነት እየቀየርናት ነው፤ለሰው ልጆች ሰላምና ደግነት መጠበቂያ የሆነው ትምህርተ ሃይማኖትም ለነገር ትንኮሳና ለጠብ መጫሪያነት መጠቀም የተለመደ ሆኖአል፤ ነገር ግን የሃይማኖት ትንኮሳ ሌላውን ሳይሆን ተመልሶ ራስን ለባሰ አደጋ የሚያጋልጥ መሆኑን ሃይማኖታውያን ሁሉ በውል መገንዘብ ይኖርብናል፡፡

በተለይም ወጣት ልጆቻችን፣ እርስ በርስ ተፋቀሩ እንጂ ተጣሉ የሚል ሃይማኖት የሌለ መሆኑን፣ ነፍስን አድኑ እንጂ ግደሉ የሚል ሃይማትም እንደሌለ በትክክል ልታውቁ ይገባል፤ የሃይማኖት አስተምህሮ ምን ጊዜም ሰላምና ፍቅር ብቻ ነው፤ይህንን በቅጡ ያልተገነዘቡ ወገኖች ስሕተት ቢፈጽሙ እንኳ ስሕተትን በስሕተት ማረም ፍጽሞ አይቻልም፤ ስሕተት በሕግና በትምህርት ብቻ እንዲታረም ማድረግ እንጂ በስሕተት ላይ ስሕተት፣ በጥፋት ላይ ጥፋት በማከል ችግርን ማስፋፋት መፍትሔ አያመጣም ፡፡ የጐበጠውን ለማቅናት እንጂ የበለጠ እንዲጎብጥ ለማድረግ እግዚአብሔር እኛን አልጠራንምና በተጠራንበት ጥሪ ጸንቶ መኖር ከኛ ይጠበቃል፡፡ እኛ ክርስቲያኖች በዓለ ልደትን ስናከብር ሀገራዊ አንድነታችንንና ሁለንተናዊ ሰላማችንን ለማረጋገጥ ቃል መግባት ከሁላችን ይጠበቃል፡፡ ከዚሁም ጋር በልዩ ልዩ ምክንያት ችግር አጋጥሞአቸው የሚበሉትንና የሚጠጡትን፣ የሚለብሱትንና የሚጠለሉበትን ያጡ ወገኖችቻን ካለን በማካፈል በዓሉን ከኛ ጋር በደስታ እንዲያሳልፉ ማድረግ ይገባናል፡፡ ሕዝበ ክርስቲያኑ በዚህ ሁሉ ሃይማኖታዊ ግዴታውን እንዲወጣ አባታዊ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፤ ያለ ሰላምና መረጋጋት መምረጥም ሆነ መመረጥ፣ መምራትም ሆነ መመራት እንደሌለ ሁላችንም እናውቃለን፤ በመሆኑም ሁሉም የፖለቲካ ተፎካካሪ ፓርቲዎችና የሚድያ ባለሙያዎች የሀገርን ሰላምና አንድነትን ተቀዳሚ አጀንዳ አድርጋችሁ ኀላፊነት ባልተለየው ጥበብ ሥራችሁን እንድታከናውኑ፣ ሕዝቡም በተለይም ወጣቱ ትውልድ ሰላምን ከሚያደፈርሱ ተግባራት ተቈጥቦ፣ በምትኩ ሠርቶ የሚያተርፍበትን አማራጭ በማፈላለግ ለሀገር ልማት እንዲነሣሣ አደራ ጭምር አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዓለ ልደት ያድርግልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ‹‹ወስብሐት ለእግዚአብሔር››