መስከረም 16 ቀን 2012 ዓ.ም በመስቀል ደመራ በዓል ላይ የተላለፈ መልእክት

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ከመስቀሉና ከቃሉ የተነሣ አባቶቻችንን በክብርና በዘለዓለማዊ ሕይወት ከፍ ከፍ ያደረገ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!!

“በመስቀሉ ወበቃሉ አዕበዮሙ ለአበዊነ፤
በመስቀሉና በቃሉ አባቶቻችንን ከፍ ከፍ አደረጋቸው።”
(ቅዱስ ያሬድ)

የክርስትና ሃይማኖት እምነትና አስተምህሮ መሠረታዊ ይዘት ድኅነተ ዓለም በክርስቶስ መስቀል ተፈጽሞአል፤ ወደፊትም ይፈጸማል የሚል እንደሆነ ሁሉም የሚያውቀው ነው፡፡ የጌታችን ግብረ አድኅኖ ፍጹም እንደመሆኑ መጠን ወደኋላም ወደፊትም ያሉትን ሁሉ ያካተተ እንደሆነ በቅዱስ መጽሐፍ ተረጋገጦአል፡፡ በፍዳ ኀጢአት ተግዘው ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዘመናት በግዞት ይማቅቁ የነበሩ ነፍሳተ አበው በአጠቃላይ በመስቀል ላይ በተፈጸመው የቤዛነት መሥዋዕት ምክንያት ነፃነትን አግኝተው ወደቀድሞው የክብር ቦታቸው እንደገቡ “ወሖረ ኀበ እለ ሙቅሕታ ትነብር ነፍሶሙ ወሰበከ ሎሙ ግዕዛነ፤ ተግዘው ወደነበሩት ነፍሳት ሄዶ ነፃነትን ሰበከላቸው ወይም አወጀላቸው” በማለት ሐዋርያው ቅዱስ ጴጥሮስ የምሥራቹን ያስረዳናል፡፡ ከዚህ እውነታ በመነሣት ኢትዮጵያዊው ነባቤ መለኮት ቅዱስ ያሬድ በዜማ መጽሐፉ የአባቶቻችን ክብር የተረጋገጠው በቅዱስ ወንጌል በተነገረውና በቅዱስ መስቀል በተፈጸመው የቤዛነት መሥዋዕት እንደሆነ በጣዕመ ዜማው ይነግረናል፡፡

ቅዱስ መጽሐፍም እንደሚያስረዳን በመስቀሉና በቃሉ የከበሩ ከክርስቶስ በፊት የነበሩ ቀደምት አበው ብቻ አይደሉም፤ ከዘመነ ክርስቶስ ጀምሮ እስካሁን ያሉት ሕዝበ ክርስቲያንም በመስቀሉና በቃሉ ከብረዋል እንጂ ይለናል፡፡ ከዚህ አንጻር በዚህ ዘመን የምንገኘውም ሆን እስከ ዕለተ ምጽአት የሚነሣው ትውልድ ሁሉ የክብር ክብርና የዘለዓለም ሕይወት የሚያገኘው በመስቀሉና በቃሉ መሆኑን ያሳየናል፡፡

ጌታችን ወደዚህ ዓለም በመጣ ጊዜ ያከናወናቸው ተግባራት ሁሉ በሁለት ዐበይት ነገሮች የሚጠቃለሉ ናቸው፤ እነሱም፡- አንደኛው እግዚአብሔርንና መንግሥቱን ፈቃዱንም ጭምር ለሰው ልጆች መግለፁ ነው፤ ይኸውም በቅዱስ ወንጌል ተጽፎ የምናገኘው ቅዱስ ቃሉ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ በሰው ልጆች ፈንታ እሱ ራሱ በመስቀል ላይ መሥዋዕት በመሆን የሰው ልጆችን ማዳኑ ነው፡፡ ጌታችን በእነዚህ ሁለት ዐበይት ነገሮች ትዝምደ ሰብእን ወይም የሰው ዘርን አድኖአል፤ ስለሆነም መዳናችን ቃሉ በተመዘገበበት በቅዱስ ወንጌልና የቤዛነት አዳኝነቱ በተከናወነበት በቅዱስ መስቀል ላይ የተፈጸመ በመሆኑ ቅዱስ መስቀልንና ቅዱስ ወንጌልን በከፍተኛ ደረጃ ማክበራችን ተገቢ ብቻ ሳይሆን ከተገቢም በላይ ሆኖ እናገኘዋለን፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ክቡራንና ክቡራት የበዓለ መስቀሉ ተሳታፊዎች፡- የፍቅረ መስቀሉ መንፈሳዊ ተመሥጦ ያደረባት የታላቁ ቈስጠንጢኖስ እናት ቅድስት ዕሌኒ መስቀሉን ለመፈለግ ከዛሬዋ የቱርክ ሀገር እስከ ኢየሩሳሌም ድረስ የተጓዘችው መስቀሉ የክብሯ ምንጭና የዘለዓለማዊ ሕይወቷ መገኛ መሆኑን ከቃሉ በመረዳትዋ፣ በተግባርም በማየቷ እንደሆነ መገንዘቡ አይከብድም፡፡ ቅድስት ዕሌኒ በዛሬው ዕለት የልቧ ምኞት በእግዚአብሔር ፈቃድ ተሳክቶ ዕጣንና ዕንጨት አንድ ላይ ደምራ በማቃጠል በጢሱ አማካኝነት መስቀሉ የተቀበረበትን ቦታ ያወቀችበት ዕለት በመሆኑ በዚህ ምክንያት ይህንን ቀን ቤተ ክርስቲያናችን በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት ታከብረዋለች፡፡ እንደ እውነቱ ከሆነ የሰው ልጆች ድኅነት በምልአት የተፈጸመበት ቅዱስ መስቀል ከምንም በላይ ሊከበርና ሊደመጥ ይገባል፡፡ የመስቀል ነገረ ድኅነት በአንድ ጊዜ ተከናውኖ የተጠናቀቀ አይደለም፤ ዛሬም ነገረ መስቀሉ በየሰከንዱ ብዙዎችን ያድናል፡፡ ነገረ መስቀሉ የተለያዩትን አሰባስቦ አንድ የሚያደርግ ነው፤ ነገረ መስቀሉ የተጣሉትን አስታርቆ በአንድ ማእድ የሚያስቀምጥ ነው፡፡ ነገረ መስቀሉ ቂምንና በቀልን ከሥሩ መንግሎ የሚጥል፣ በምትኩም ሰላምንና ፍቅርን የሚያድል አምላካዊ ምሥጢር ነው፡፡ ነገረ መስቀሉ ኀጢአትን በደልንና መርገምን ደምስሶ ነፃነትን፣ ጽድቅን፣ ሕይወትንና ክብርን የሚያጐናጽፍ ነው፤ ግን ይህ ሁሉ እውን ሊሆን የሚችለው ነገረ መስቀሉ በትክክል ሲደመጥና ሲከተሉት እንደሆነ መዘንጋት የለብንም፡፡ ቀደምት ኢትዮጵያውያን አበው ነገረ መስቀሉን በትክክል አዳምጠውና ተከትለው በነፃነት፣ በአንድነት፣ በወንድማማችነት፣ በይቅር ባይነትና በሰላም ኖረዋል፡፡

አባቶቻችን በዓለም ብቸኛ የሆነ የሀገር ነፃነትና አንድነት ጠብቀው ለእኛ ሊያስረክቡ የቻሉት የነገረ መስቀሉን አስተምህሮ ብቻ በመከተላቸው እንደሆነ ማስተዋል ይገባናል፤ ይህንን እውነት የማንገነዘብና የማናስተውል ኢትዮጵያውያን ካለን ራሳችንን አላወቅንም ማለት ነው፡፡ ደግሞስ አብያተ ክርስቲያናትን እየተዳፈሩና እያቃጠሉ፣ እየዘረፉና እየገደሉ፣ ሰላምንና አንድነትን፣ ፍቅርንና ልማትን ማምጣት ይቻላል ወይ? እንደዚህ ዐይነቱ አጒል አስተሳሰብና ድፍረት በእግዚአብሔርና በሕዝበ ክርስቲያኑ ላይ እየተፈጸመ ያለ ክፉና አጥፊ ድርጊት መሆኑ ታውቆ በአስቸኳይ መቆም አለበት፤ እስከ መጨረሻውም መገታት አለበት፤ በዚህ ዙሪያ በሚሆነው ነገር ሁሉ በጭራሽ መግባባት አይኖርም፡፡ ኢትዮጵያውያን አበው መስቀልን ይሳለሙታል እንጂ አያቃጥሉትም፤ ኢትዮጵያውያን አበው መስቀልን የአክብሮት ስግደት ይሰግዱለታል እንጂ አይረግጡትም፣ ኢትዮጵያውያን አበው መስቀልን ያከብሩታል እንጅ አያዋርዱትም፤ ምክንያቱም በመስቀሉና በቃሉ ክብራቸውንና ድኅነታቸውን እንዳገኙ አሳምረው ያውቃሉና ነው፡፡ ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ “ትመኛላችሁ፤ ለእናንተም አይሆንም፣ ትገድላላችሁ፣ በብርቱም ትፈልጋላችሁ፣ ልታገኙም አትችሉም፣ ትጣላላችሁ፣ ትዋጉማላችሁ፣ ነገር ግን አትለምኑምና ለእናንተ አይሆንም” እንዳለው ምኞታችን ሁሉ ሊሳካ ያልቻለው ከመስቀሉ እየራቅን ስለሄድን ነው፤ ልመናችንም ወደ እግዚአብሔር ለማቅረብና በፈቃዱ ለመኖር እንደ አሳፋሪ ነገር ስለቈጠርን ነው፡፡

ይህም በመሆኑ እግዚአብሔር በነቢዩ በኢሳይያስ በኩል “አንትሙኒ ተሐውሩ ግድመ ግድመ፤ ወአነኒ አሐውር ግድመ ግድመ፤ እናንተም ዳር ዳሩን ትሄዳላችሁ፤ እኔም ዳር ዳሩን እሄዳለሁ” ያለውን በኢትዮጵያ ላይ እየተፈጸመ ይገኛል፡፡ ኢትዮጵያውያን መሪዎችና ልሂቃን ከኃምሣ ዓመታት ላላነሱዘመናት ከእግዚአብሔር ርቀዋል፡፡ ከመስቀሉ ሥርም ጠፍተዋል፡፡ ይህ ዐይነቱ አመለካከት በኢትዮጵያ ውስጥ አያስኬድም፣ እንደማያስኬድም በግልጽ እያታየ ነው፡፡ ከእንግዲህ ወዲህ ተዉ ወደ እግዚአብሔር እንመለስ፤ እንደ ቀደምት አባቶቻችን ከቤተ ክርስቲያን ዐጸድና ከመስቀል ሥር እንገኝ፡፡ የጎደለንን ፍቅርና ሰላም፣ አንድነትና እኩልነት፣ ፍትሕና ወንድማማችነት በመስቀሉ ውስጥ ተትረፍርፎ እናገኘዋለን፡፡ ይቅርታና መተባበር፣ መከባበርና መተማመን በመስቀሉ ውስጥ ሞልቶአል፡፡ የኢትዮጵያ ፈውስ ከመስቀሉ ሥር እንደሆነ ሁላችንም እንወቅ፤ እንደ አባቶቹ በመስቀሉና በቃሉ ለመክበር የሚፈልግ ትውልድ ወደ መስቀሉና ወደቃሉ ሊመለስ ግድ ይለዋል፤ ያለዚያ ግን ምኞቱ ሁሉ ቅዠት ከሚሆን በቀር ሊሳካ አይችልም፡፡

በመጨረሻም፤ የመስቀል ትሩፋት ግኝት የሆነው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከሁሉም በላይ እኩልነትን ከአንድነት ጋር፣ ነፃነትን ከወንድማማችነት ጋር አጥብቆ እንደሚወድ፣ ይህንንም ከመስቀሉ ቃል ያገኘው ዕሴት እንደሆነ ዐውቃችሁ፣ የሀገሪቱ ምሁራን፣ ፓለቲከኞች፣ ልኂቃንና አክቲቭስቶች ከጥላቻና ከመወራረፍ፣ ከስድብና ከመጠላለፍ፣ ከመፎካከርና ከመዘለዓለፍ ተቈጥባችሁ በቅንነት፣ በአርቆ አስተዋይነት፣ በይቅርታና በፍቅር ይህንን ታላቅ ሕዝብ በእኩልነት እንድናገለግል፣ አንድነታችንንና ሰላማችንንም የጋራ ሀብት አድርገን እንድንጠብቅ አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡ መልካም የመስቀል በዓል ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

መስከረም 1 ቀን 2012 ዓ.ም. የዘመን መለወጫ በዓልን ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣

ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፣

የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣

በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጰያውያንና ኢትዮጵያውያት፡፤

የዘመናትና የዓመታት ባለቤት የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን የሁለት ሺሕ ዐሥራ አንድ ዓመተ ምሕረት ዘመነ ሉቃስን በሰላም አስፈጽሞ ወደ ሁለት ሺሕ ዐሥራ ሁለት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ዮሐንስ እንኳን በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ!!

“አመ ርእሰ ሳብዕ ወርኅ ግበሩ መጥቅዐ፤ በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን ዕረፍት፣ በመለከት ድምፅ መታሰቢያ የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ” (ዘሌ. 2324)፡፡

የኢትዮጵያ የዘመን አቈጣጠር ሥር መሠረቱ ቀመረ አዳም፣ ቀመረ ኖኅ እንደሆነ ቅዱስ መጽሐፍ ያስረዳል፡፡ ይህም አቈጣጠር እስከ ዘመነ ሙሴ በመካከለኛው ምሥራቅ ሕዝቦች ሁሉ ጥቅም ላይ የዋለ ነበረ፡፡ በሊቀ ነቢያት ሙሴ ዘመን ግን በእግዚአብሔር ኀይል የሕዝበ እስራኤል ከግብጽ ባርነት መውጣትና ነፃነት ማግኘት ጋር በተያያዘ ወርኀ ሚያዝያ የወር መጀመሪያ እንዲሆን እግዚአብሔር ትእዛዝ መስጠቱ በቅዱስ መጽሐፍ ተመዝግቦአል፡፡ ይሁንና የወር መጀመሪያ እንጂ የዓመት መጀመሪያ ከመስከረም እንዳልተፋለሰ ‹‹በሰባተኛው ወር በመጀመሪያው ቀን በድምፀ መለከት የተቀደሰ ጉባኤ ይሁንላችሁ›› ተብሎ ከእግዚአብሔር ለሙሴ በተሰጠው ትእዛዝ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም ሕዝበ እስራኤል ዛሬም ድረስ በጨረቃ አቈጣጠር ቢሆንም የዘመን መለወጫ ዐውደ ዓመታቸውን የሚያከብሩት መስከረም ላይ ነው፡፡ ወደ ኢትዮጵያ ሀገራችን ቀመረ ዘመን አጠቃቀም የተመለከትን እንደሆነ የኖኅ አቈጣጠርን በትክክል የተከተለ ሆኖ ይገኛል፡፡ ይኸውም የቀኑም የወሩም የዓመቱም መጀመሪያ አንድ ላይ መስከረም አንድ ቀን መሆኑ ነው፤ የኖኅ ቀመር የሚቈጠረው በፀሓይ አቈጣጠር ሆኖ ከጳጉሜን በቀር ሁሉም ወሮች በሠላሳ ቀናት የተመደቡ መሆናቸውን መጽሐፍ ቅዱስ ‹‹በሁለተኛው ወር፤ በዐሥራ ሰባተኛው ቀን የጥፋት ውኃ መዝነብ መጀመሩን ገልጾ፣ ከመቶ ኃምሣ ቀን በኋላ ደግሞ በመጀመሪያው ወር በመጀመሪያው ቀን ውኃው ከምድር ላይ ደረቀ›› ይላል፤ ይህም በጥቅል ሲገለጽ አምስት ወር እንደሆነ ያሳያል፤ በዚህ ስሌት መሠረት ወሮቹ በሠላሳ ቀናት የተመደቡ መሆናቸውን በግልጽ ያመለክታል ፡፡ በመሆኑም ኢትዮጵያ ሀገራችን እንዲህ ያለውን በእግዚአብሔር ትእዛዝና በአበው ትውፊት ከጥንት ከዘመነ አዳም ወኖኅ ጀምሮ የነበረውን የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት እስከ ዛሬ ድረስ ጠብቃ ማቈየቷ ለኢትዮጵያ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ለመላው ዓለም የሚያኮራ ነው፡፡

ዛሬ የምንጠቀምበት የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት ጥንት የብዙ ሀገሮች ዘመን መለወጫ የነበረ ቢሆንም ሌሎቹ በተለያየ ሰው ሠራሽ ምክንያት ሌላ ቀመር በመፍጠር የነበረውን ትተው በሌላ እየተጠቀሙ እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ ክብር ለእግዚአብሔር ይግባውና እኛ ኢትዮጵያውያን ብቻ በተሟላ ሁኔታ የጥንታውያን አበው ማለትም የአዳምና የኖኅ ሐሳበ ቀመር ይዘን መዝለቃችን ለእግዚአብሔርና ለቀደምት አበው ያለን ታማኝነት ምን ያህል ጠንካራ እንደሆነ ያሳያል፡፡ ይህ በራስ ሃይማኖት ትውፊትና ባህል ኮርቶ በልበ ሙሉነት የመኖር ጸጋችን የሀገርን ነፃነትና የሕዝብን አንድነት ለመጠበቅም ጒልህ ሚና እንደተጫወተ በደምብ መገንዘብ ያስፈልጋል ፡፡ የኢትዮጵያ ዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት ከሌሎች የዘመን መለወጫ በዓል ልዩ የሚያደርገው፤ በእግዚአብሔር የታዘዘ በአርእስተ አበው ዘመን የነበረ መሆኑ ብቻ አይደለም፤ ከነገረ ክርስቶስና ከሥነ ፍጥረትም በእጅጉ የተቈራኘ ምሥጢር አለው፡፡ ከነገረ ክርስቶስ አንጻር የክርሰቶስ መንገድ ጠራጊ የሆነው ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ የብሉይ ኪዳን ማብቂያና የሐዲስ ኪዳን መግቢያ መሆንና መስከረም አንድ ቀንም የአሮጌው ዓመት ማብቂያና የሐዲስ ዘመን መነሻ መሆን ተመሳሳይነት ስላላቸው የሁለቱን ንጽጽር በማገናኘት የዮሐንስ መታሰቢያ በዓል በርእሰ ዐውደ ዓመት እንዲከበር መደረጉ ነው፤ በተጨማሪም ይህ ንጽጽር ክርሰቶስ አሮጌውን ዓለም የሚያሳልፍ የሐዲስ ሰማይና የሐዲስ ምድር ጌታና ንጉሠ ነገሥት እንደሆነ የሚገልጽ ምሥጢር አለው፡፡ ከሥነ ፍጥረት አንጻር ሲታይ ደግሞ የክረምቱ የዝናም ውሽንፍር፣ የደመናው፣ የመብረቁ፣ የነጐድጓዱ፣ የጭፍናውና የጎርፉ ጋጋታ ሁሉ አልፎ ምድር በልምላሜና በአበባ ባሸበረቀችበት፣ ውኃው በየፏፏቴው በየሸለቈውና በየወንዙ ጥርት፣ ኮለል ብሎ በሚታይበት አዲስ እሸት በደረሰበት እንስሳቱም አእዋፉም በዝማሬና በደስታ በሚቦርቁበት ሰውም ከመልክዐ ምድር ውበት የተነሣ ልቡ በተስፋና በኃሤት በሚሞላበት የሚከበር የዘመን መለወጫ ርእሰ ዐውደ ዓመት መሆኑ ልዩ ያደርገዋል ፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

ይህ የዘመን መለወጫ በዓል በሁለመና ገጽታው ፍጹም መታደስን የሚያበስር ርእሰ ዐውደ ዓመት እንደሆነ በእግዚአብሔር ቃልም በሥነ ፍጥረትም ጭምር የተረጋገጠ መሆኑን በኅሊናችንም፣ በዐይናችንም የምናየው ሐቅ ነው፡፡ በመሆኑም ይህ ሁሉ የሆነው ለማን ተብሎ እንደሆነ መገንዘብና መጠቀም ከፍጡራን ይጠበቃል፡፡ እግዚአብሔር የፍጥረታት መታደስን የሚወድ አምላክ እንደሆነ በሥነ – ፍጥረት ብቻ የገለጸ አምላክ አይደለም፤ በቅዱስ ቃሉም ‹‹በልባችሁ መታደስ ተለወጡ›› በማለት ሁሉም መታደስ እንዳለበት አስተምሮናል እንጂ፡፡ አዲስ የዘመን መለወጫ ብለን የምንናገርለት ይህ ዕለት አዲስ ሊሆን የሚችለው በዋናነት የኛ ልቡና ሲታደስ ነው፡፡ እግዚአብሔር ቃል ኪዳኑን ጠብቆ እነሆ ምድራችንን በልምላሜ፣ በአበባ፣ በፍሬ፣ በምርት በሁሉም ነገር አስውቦ አዲስ አድርጎአታል፡፡ እኛ ሰዎችም በተመሳሳይ በአስተሳሰብ በሥራ በአኗኗር ሁሉ ከልብ የሆነ መታደስ ሊኖረን ይገባል፡፡ ‹‹የኢትዮጵያ ሕዳሴን እናበሥራለን›› የሚለው መልካም ምኞታችን ከቃላት አልፎ ተግባራዊ እንዲሆን ከሁሉም በፊት ይቅርታና እውነተኛ መግባባት በሁሉም ወገኖች መከናወን አለበት፤ አንድ መቀበል ያለብን እውነት በሐሳብ መቀራረብና በሰጥቶ መቀበል መርሕ እየተቻቻሉ መሄድ እንደ አዋጭ ባህል አድርገን መጓዝ ካልቻልን መቼም ቢሆን ለችግራችን መፍትሔ አናገኝም፤ ምክንያቱም በታሪክ የሁሉም ሐሳብ አንድ ዐይነት ሆኖ የተገኘበት ጊዜ የለምና ነው፡፡ ያለን ብቸኛ አማራጭ የተወሰነውን በመተው፣ የተወሰነውን በመቀበል፣ የተወሰነውን ደግሞ በመስጠት ወደ አንድነት መምጣትና ሀገርንና ወገንን ማሳደግ ነው፡፡ ይህ ዐይነቱ መቻቻል በሀገራችን ውስጥ ባለመዳበሩ ሕዝባችን ለመከራ ተጋልጦአል ፡፡

ይህ ዐይነቱ ክሥተት ከአሮጌው ዘመን ጋር አብሮ ማክተም አለበት፤ መለያየት፣ መገዳደል፣ ወገንን ማፈናቀል፣ አብያተ ሃይማኖትን መዳፈር፣ የእርጅና ምልክቶች ናቸውና ከአሮጌው ዓመት ጋር አብረው ማለፋቸውን በአዲሱ ዓመት እናብሥር፤ በምትኩም ለአንድነት፤ ለመፈቃቀር ለመተዛዘን፣ ለመቻቻል፣ ለመከባበር፣ ለመተማመንና ለአብሮነት መበልጸግ ከዛሬዋ ቀን ጀምረን በአዲስ ልብ በአዲስ መንፈስ መነሣት ይኖርብናል፡ ይህን ስናደርግ ዘመኑም፣ ሥነ ፍጥረቱም፣ እኛም በትክክል በሕዳሴ መንገድ መጓዝ ጀምረናል ማለት እንችላለን፡፡ የእግዚአብሔር በረከት በሕዝቦች አንድነት ውስጥ አለ፡፡ የነፃነትና የኀያልነት መንፈስ በሕዝቦች አንድነት ውስጥ አለ፡፡ ችግሮችን ሁሉ በብቃት ተቋቁሞ በአሸናፊነት መወጣት በሕዝቦች አንድነት ውስጥ አለ፡፡ አንድነት ከሌለ ጒልበት የለም፤ ችግሮችን መቋቋምም አይቻልም፤ በባዕዳን መደፈርም ሊከተል ይችላል፤ እግዚአብሐሔርም ፊቱን ያዞራል፡፡ ስለዚህ ይህ ታላቅና ባለታሪክ ሕዝብ ለዘመናት ተንከባክቦ ያቆየው ሃይማኖቱን፣ ታሪኩን፣ ባህሉንና አንድነቱን ይፈልጋልና አሁንም፣ ነገም፣ ከነገ በኋላም የሕዝቡን አንድነት እንጠብቅ፤ ለግል ፍላጎት ስንል በሕዝቡ አንድነትና እኩልነት መሰናክል አናብዛ፤ በምናደርገውም ሁሉ በእግዚአብሔርና በታሪክ ፊት በደል እንዳንፈጽም እንጠንቀቅ ፡፡

በመጨረሻም፡ አዲሱ ዓመት የሰላም፣ የፍቅር፣ የአንድነት፣ የስምምነትና የይቅርታ ዘመን ማድረግ የምንችለው ከእግዚአብሔር በታች እኛው ነን፤ ስለሆነም በይቅርታና በሰጥቶ መቀበል መርሕ ሁሉንም ልዩነቶች ወደ መቀራረብ ብሎም ወደ ፍጹም መተማመን በማምጣት ሀገሪቱንና ሕዝቦችዋን ወደ አንድነትና ወደ ላቀ ሕዳሴ እንድናሸጋግር አደራ ጭምር መንፈሳዊና አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዘኢብሔር አሜን፡፡

ጳጒሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም.የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ሊቀ አእላፍ በላይ መኮንን የኦሮሚያ ቤተ ክህነት ለመክፈት ባዘጋጀው ቡድናዊ አሠራር መሠረት አሽቸኳይ ምልአተ ጉባኤ ጠርቶ ለሦስት ቀናት ዝግ ጉባኤ አድርጎ ውሳኔ አስተላለፈ፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ መግለጫ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በንባብ በመገናኛ ብዙኃን የተላለፈ ሲሆን ሙሉ መልእክቱ የሚከተለው ነው፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በወቅታዊ የቤተ ክርስቲያኒቱ ጉዳዮች ላይ የተሰጠ የአቋም መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊት፣ ታሪካዊትና ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን እንደመሆኗ መጠን አገራችን ኢትዮጵያ አሁን ከደረሰችበት የሥልጣኔና የእድገት ደረጃ ከመድረሷ በፊት ብራና ዳምጣ፣ ቀለም በጥብጣና ፊደል ቀርጻ ትምህርትና ሥልጣኔን ያስጀመረች፣ የመጀመሪያው ዩኒቨርሲቲና የትምህርት ሚኒስቴር፣ የፍትሕ ሥርዐቱ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ መዋቅራዊ አደረጃጀት ገና ሳይኖረው ፍርድ እንዳይጓደልና ደሃ እንዳይበደል በማሰብ የፍትሐ-ነገሥት መምህራኖቿን በዳኝነት መድባ የፍትሕ ሥርዐትን የመሠረተች፣ ዜጎችን በሥነ-ምግባርና በግብረ-ገብነት ትምህርት ኰትኩታ በማሳደግ ሀገር ወዳድ ትውልድ በማፍራት መሠረት የጣለች፣ በውጭ ወራሪ ኀይል የሀገር ሉዓላዊነት በተደፈረ ወቅት የእምነቱ ተከታይ ምእመናኖቿና አገልጋይ ካህናቶቿ እንዲሁም ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የእምነታችን መገለጫ የሆነውን የቃልኪዳኑን ታቦት ይዘው በየጦር ግንባሩ በመሰለፍና በመሠዋት እንኳንስ ሕዝቦቿ ምድሪቱም ለወራሪ ጠላት እንዳትገዛ በማውገዝ የሀገር ሉዓላዊነት ያስከበረችና ኢትዮጵያ ሀገራችን ከሌሎች አፍሪካ አገራት በብቸኝነት ቅኝ ገዥዎች ያልደፈሯት አገር ተብላ በታሪክ ድርሳናት እንድትመዘገብ ግንባር ቀደም ሚና የተጫወተች የሀገር ባለውለታ እናት ቤተ ክርስቲያን መሆኗን እንኳንስ እኛ ልጆቿ ይቅርና የታሪክ ምሁራን ዘወትር በየአደባባዩ የሚመሰክሩት በብዕር ሳይሆን ለነፃነት በተከፈለ በአበው አባቶቻችን ደም የተጻፈ አኲሪ ታሪካችን ነው፡፡

እናት ቤተ ክርስቲያን ከላይ በአጭሩ የተጠቀሱትን ዘመናት የማይሽሩት ታሪካዊ ውለታዎችን ለሀገር ያበረከተች ቤተ ክርስቲያን ብትሆንም አንዳንድ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎችና የጥፋት ኀይሎች በተለያዩ ጊዜያት በቤተ ክርስቲያናችን ላይ የሚፈጽሙት ከፍተኛ የሆነ አስተዳደራዊ በደልና የተቀናጀ ጥቃት እያደረሰብን ያለውን መከራና ችግር ቤተ ክርስቲያናችን ባላት ሀገራዊ ኀላፊነት ችግሩን በትዕግሥት አሳለፈችው እንጂ እየተፈጸመባት ካለው ግፍና በደል አንጻር ይከሠት የነበረው ችግርና ሀገራዊ ቀውስ በቀላሉ የሚታለፍ ባልሆነም ነበር፡፡

ይህ በእንዲህ እንዳለ እየደረሰብን ያለውን በደልና መከራ ከዛሬ ነገ ይሻላል በማለት ታግሠን ብንችለውም እያደር እየባሰና የችግሩም አድማስ እየሰፋ ሊሄድ ችሏል፡፡ ምንም እንኳን በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለው በደል ዘመናትን ያስቀጠረ ቢሆንም ቅሉ በተለይ በአሁኑ ወቅት መልኩን እየቀያየረ እና ለዘመናት የቆየ አንድነቷን በማፈራረስ ከቤተ ክርስቲያኒቱም አልፎ ሀገራዊ ቀውስና አለመረጋጋት የሚያስከትል የጥፋት አጀንዳን ባነገቡ ግለሰቦች በቤተ ክርስቲያኒቱ ስም የጀመሩት እንቅስቃሴ ወደከፋ ደረጃ ከመድረሱ በፊት የቤተ ክርስቲያኒቱ የበላይ እና የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ አካል የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በጉዳዩ ላይ አስቸኳይ ስብሰባ በማድረግ በስፋት ከተወያየ የሚከተለውንየአቋም መግለጫ አውጥቷል፡-

1. አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኀላፊዎች ሥልጣናቸውን መከታ በማድረግ እና ለጥፋት ለተደራጁ ቡድኖች ፖለቲካዊ ሽፋን በመስጠት በልዩ ልዩ ክልሎች የተፈጸሙት የአብያተ ክርስቲያናት መቃጠል፣ የአገልጋይ ካህናት እና ምእመናን መገደል፣ ዘመን የማይተካቸው የሀገር መገለጫ የሆኑትን ጥንታውያን እና ታሪካውያን ቅርሶችን በማቃጠል ሀገሪቱ እና ሕዝቦቿን ታሪክ እና ቅርስ አልባ በማድረግ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየተፈጸሙ ያሉትን በደሎች እና ግፎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል፤
2. ቤተ ክርስቲያኒቱ ባህል፣ ቀለም፣ ቋንቋ እና ብሔር ሳትለይ በአንድነት እና በአቃፊነት ለሀገር ውለታ ያበረከተች መሆኗ ተዘንግቶ በእምነት ሽፋን የቤተ ክርስቲያኒቱ አማኞች የሆኑ ምእመናን ካደጉበትና ሀብት እና ንብረት ካፈሩበት ቀያቸው እንዲፈናቀሉ መደረጉ፣ በእምነታቸው ብቻ ተገድደው በመደፈር እና ልዩ ልዩ የሥነ ልቡና ጥቃት እንዲደርስባቸው በማድረግ እንዲሁም በድብደባ እና በዛቻ ሃይማኖታቸውን እንዲቀይሩ እየተደረገ ያለውን ሕገ ወጥ አድራጎትን ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ ያወግዛል
3. ለባለውለታዋ እናት ቤተ ክርስቲያን በማይመጥን እና ኢፍትሓዊ በሆነ መንገድ ሕጋዊ ይዞታዋን እና የአምልኮት ቦታዎቿን በመንጠቅ መንግሥታዊ ሥልጣናቸውን እንደ ሽፋን በመጠቀም በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ በደል እና ግፍ የሚፈጽሙ አንዳንድ የመንግሥት ባለሥልጣናት እና ሥራ ኀላፊዎችን ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ አድራጎታቸው እንዲታቀቡ በጥብቅ ያሳስባል
4. እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ በሀገራዊ የኀላፊነት ስሜት ታግሦና ችሎ ሞቱ፣ እስራቱ፣ ዛቻው፣ ስደቱ እና እንግልቱ ሳይበግረው ሀገር በአንድነት እና በፍቅር እንዲሁም በመተሳሰብ እንድትቀጥል ታሪክ የማይረሳው መሥዋዕትነት እየከፈሉ ያሉትን አገልጋይ ካህናት እና መላውን ምእመናንን እንዲሁም ወጣት የሰንበት ትምህርት ቤት አባላት በአጠቃላይ መላው የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ላሳያችሁት ትዕግሥት የተመላበት ሀገራዊ ኀላፊነት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያመሰገነ፤ እንደአሁን ቀደሙ ሁሉ ትዕግሥት የተመላበት ሀገራዊ ኀላፊነታችሁ እንደተጠበቀ ሆኖ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን እና ወደፊትም ሊደርስ የታቀደውን ግፍ እና ጥፋት በአንድነት እና በኅብረት ከእኛ ከመንፈስ ቅዱስ አባቶቻችሁ ጋር በመሰለፍ በጽናት ቤተ ክርስቲያናችሁን እንድትጠብቁ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ጥሪውን ያስተላልፋል፤
5. በቤተ ክርስቲያናችን እምነት እና ቀኖና መሠረት በእምነታቸው ምክንያት በሰይፍ የታረዱ፣ በጥይት የተገደሉት፣ በእሳት የተቃጠሉ፣ ሕይወታቸውን ስለ ቤተ ክርስቲያናቸው የሰጡ ኦርቶዶክሳውያን ሁሉ በሰማዕትነት ክብር እና መዓርግ ዘወትር እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ የወሰነ ሲሆን በሰማዕትነት ሕይወታቸውን የሰጡ አገልጋዮች እና ምእመናን ቤተሰቦች ማኅበራዊ እና መንፈሳዊ ሕይወታቸው እንዳይናጋ በተቻለ ዐቅም ድጋፍ እና እንክብካቤ በማድረግ ሁላችንም ከጎናቸው በመሆን የድርሻችንን እንወጣ ዘንድ ለመላው ኢትዮጵያውያን እና የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ቅዱስ ሲኖዶስ ጽኑ መንፈሳዊ ጥሪውን ያስተላልፋል፤
6. እናት ቤተ ክርስቲያችን በእንግዳ ተቀባይነቷ እና በአቃፊነቷ ዛሬ ለቍጥር አዳጋች የሆኑት ቤተ እምነቶች ሕገ መንግሥታዊ መብታቸው ተከብሮ ሰላማዊ፣ የማምለክ መብታቸው እንዲረጋገጥ የበኩሏን ድርሻ የተወጣች መሆኗን ሁሉም ቤተ እምነቶች በየአደባባዩ የሚመሰክሩት እውነታ እንደመሆኑ መጠን በእናት ኦርቶዶክሳዊት ቤተ ክርስቲያናችን ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና መከራ ሁሉም ቤተ እምነቶች በአንድነት እና በተባበረ ድምፅ በጽናት እንዲያወግዙ እና ለእምነት ተከታዮቻቸውም የቤተ ክርስያናችን ጥፋት እና በደል እንዲወገድ የበኩላቸውን ሚና እንዲወጡ መንፈሳዊ ጥሪያቸውን እንዲያስተላልፉልን በቅድስተ ቤተ ክርስቲያናችን ስም የከበረ ጥሪያችንን እናስተላልፋለልን፣
7. የፍትሕ አካላት ለምሥረታችሁ እና ለእድገታችሁ ውለታ የከፈለችውን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን የቀደመ ውለታዋን ከግምት ውስጥ በማስገባት ሕግ ተጥሶ እና ፍትሕ ተጓድሎ በቤተ ክርስቲያኒቱ ላይ እየደረሰ ያለውን ግፍ እና በደል በጽናት ከማውገዝ በተጨማሪ አጥፊዎችን ለፍትሕ በማቅረብ እና ተመጣጣኝ እና ለሌሎችም አስተማሪ የሆነ ውሳኔ በመስጠት እና በማሰጠት የራስዋ የሆነ ተቋማዊ ህልውና እና መዋቅር ያላት ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ሕጋዊ መብት እና ልዕልና መከበር የበኩላችሁን ድርሻ ትወጡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ጥሪ ያስተላልፋል
8. በሀገሪቱ ሕገ መንግሥት የተከበረውን እና የተረጋገጠውን የእምነት ተቋማት ነፃነት እና ሉዓላዊ ክብር በሚጋፋ ሁኔታ እየተፈጸሙ ያሉት የመብት ጥሰቶች እና የጥፋት በደሎችን የማረም እና ከመፈጸማቸውም በፊት የመከላከል ኀላፊነት ያለባችሁ በየደረጃው የምትገኙ የመንግሥት አካላት በሕገ መንግሥቱ የተጣለባችሁን ሕግን የማስከበር አደራና ኀላፊነት፣ በሀገሪቱ ውስጥ ያሉ ሀገራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ተቋማት መብት የማስጠበቅ ሀገራዊ ኀላፊነት በመወጣት የቤተ ክርስያኒቱን ልዕልና እና ክብር እንድታስጠብቁ በቅድስት ቤተ ክርስያናችን ስም ቅዱስ ሲኖዶስ አደራውን ጥሎባችኋል በማለት በጽኑ ያሳስባል፤
9. አንድነትን፣ መተሳሰብን፣ መከባበርን፣ ሰላም እና ፍቅርን በመስበክ እና በተግባር በመፈጸም ለሀገር እና ለመላው ዓለም አርኣያ የሆነችውን እናት ቤተ ክርስቲያን ያለ ስሟ ስም፣ ያለ ግብርዋ ግብር በመስጠት በተለይም የተከበረውን እና የቤተ ክርስቲያኒቱን ባለውለታ የሆነውን የኦሮሞን ሕዝብ ቤተ ክርስቲያናችን እንዳገለልችው እና ዐቅዳ እንደበደለቸው ለማስመሰል እና ለማስቈጠር ዐቅደው ቤተ ክርስያኒቱን እና ሀገርን ለመከፋፈል ድብቅ አጀንዳ ይዘው በተነሡ ግለሰቦች እና ቡድኖች አለአግባብ እየተሠራጨ ያለው አፍራሽ እና ከፋፋይ ድርጊት የቤተ ክርስቲያኒቱ አቋም እና ድምፅ ካለመሆኑ በተጨማሪ ትክክለኛው የቤተ ክርስቲያኒቱ ታሪክ እንደሚያስረዳን ሕገ ወጦቹ ግለሰቦች እና ቡድኖች የተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ የሚያገለግለው እና የሚባርከው መንፈሳዊ አባት እንደሌለው ቢገልጹም እንኳንስ ለቤተ ክርስቲያኒቱ አገልግሎት ለሀገር አንድነት፣ ሉዓላዊነት እና ነፃነት ከተከበረው የኦሮሞ ሕዝብ አብራክ የተገኙት እና ለነፍሳቸውን ሳይሳሱ በሰማዕትነት ዋጋ የከፈሉትን የሰማዕቱ ቅዱስ አቡነ ጴጥሮስን ታሪክ የማይረሳውን ውለታ የዘነጋ እና ቤተ ክርስቲያኒቱ በተለያዩ ጊዜያት በመዓርገ ጵጵስና ሹማ በክልሉ ባሉ አህጉረ ስብከት ለሐዋርያ አገልግሎት አሰማርታ መላውን የክልሉን ሕዝበ ክርስቲያን በማገልገል ከቤተ ክርስቲያኒቱ አልፎ ለክልሉ ሰላም እና አንድነት ዋጋ በመክፈል ላይ የሚገኙትን ከኦሮሞ ሕዝብ የተገኙትን አበው ሊቃነ ጳጳሳት ሐዋርያዊ አገልግሎት እና በእነሱ የሚመሩ ከአጥቢያ እስከ ሀገረ ስብከት ያሉ በርካታ ጽ/ቤቶች ከዐሥራ አምስት የሚበልጡ በሊቃነ ጳጳሳት የሚመሩ የቤተ ክህነት ጽሕፈት ቤቶች እና መዋቅሮችን ፈጽሞ የካደ አድራጎት በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ በጽኑ እያወገዘ በዚህ አድራጎት ውስጥ እየተሳተፉ ያሉትን ግለሰቦችን እና ቡድኖችን ከዚህ አድራጎታቸው እንዲቈጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ ያሳስባል፤
10. የተከበራችሁ እና የተወደዳችሁ የኦሮሞ ሕዝብ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን እናት ቤተ ክርስቲያናችሁ እንደ ትናንቱ ሁሉ ባህልን፣ ቀለምን፣ ቋንቋ እና ብሔርን መሠረት ሳታደርግ በተቻላት ዐቅም መንፈሳዊ እና ሐዋርያዊ አገልግሎቷን ተደራሽ ለማድረግ የጸሎት፣ የሥርዐተ አምልኮ መፈጸሚያ እና ሃይማኖታዊ የትምህርት መጻሕፍትን በኦሮምኛ ቋንቋ በመተርገም እና በማዘጋጀት፣ ከአምስት በላይ የካህናት ማሠልጠኛ ተቋማትን፣ አንድ ከፍተኛ መንፈሳዊ ኮሌጅን በጀት መድባ በማቋቋም መላውን የኦሮሞ ብሔር ሕዝበ ክርስቲያን ስታገለገል የቆየችውን እና ያላቸውን ወደ ፊትም ዘመኑን በዋጀ መልኩ አጠናክራ የምታገለግለውን እናት ቤተ ክርስያናችሁ መሆኗን ዐውቃችሁ አንድነታችሁን እና ፍቅረ ቤተ ክርስቲያናችሁን ለመከፋፈል የተነሡትን የጥፋት ኀይሎች በጽናት በመቃወምና አንድነት እና ፍቅራችሁን አጠናክራችሁ ቤተ ክርስያናችሁን እና ሃይማኖታችሁን ከጥፋት ኀይሎች ትጠብቁ እና ትንከባከቡ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፣
11. አዲስ የኦሮምያ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የሚል መዋቅር በራሳቸው ሥልጣን መሥርተው በመገናኛ ብዙኃን መግለጫ የሰጡት ግለሰቦች በአካል ቀርበው ለቅዱስ ሲኖዶስ እንዲያስረዱ በሰጣቸው ዕድል ቀርበው የተወያዩ ሲሆን በውይይቱም ወቅት ጥያቄውን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ከአሁን ቀደም በኮሚቴ ተጠንቶ እንዲቀርብ ውሳኔ ሰጥቶበት እያለ ለጉዳዩ ትኵረት እንዳልሰጠው በማስመሰል ከቅዱስ ሲኖዶስ ዕውቅናና ፈቃድ ውጭ አዲስ መዋቅር ፈጥረው መግለጫ መስጠታቸው አግባብ አለመሆኑን አምነው ይቅርታ ለመጠየቅ ከሌሎች የኮሚቴ አባላት ጋር ተወያይተን እንመለስ ብለው ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ለጳጒሜን 2 ቀን 2011 ዓ.ም. ከጠዋቱ 2፡30 የተቀጠሩ ቢሆንም በዕለቱ የኮሚቴው ዋና ተጠሪ ሊቀ አእላፍ ቀሲስ በላይ መኰንን ያልተገኙ ሲሆን፤ 2 የኮሚቴው አባላት ብቻ ከተሰጣቸው ሰዓት አሳልፈው ከመምጣታቸው በላይ 2ቱ ግለሰቦች በጽሑፍ ባቀረቡት ምላሽ በሕገ ወጥ አቋማቸው የጸኑ መሆናቸውን የገለጹ በመሆኑ የግለሰቦቹ እንቅስቃሴም ሆነ የኦሮሞ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት ተብሎ የተጠቀሰው አደረጃጀት ሕጋዊ ዕውቅና የሌለው መሆኑን ሁላችሁም የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ዐውቃችሁ የግለሰቦቹን ሕገ ወጥ እንቅስቃሴ በመቃወምና በቀደመው አንድነታችሁ ጸንታችሁ ቤተ ክርስቲያናችሁንና ሃይማኖታችሁን ትጠብቁ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡
12. ከዚህ በላይ በተገለጸው መሠረት ምንም ዐይነት ሕጋዊ ውክልናም ሆነ ከሕግ የመነጨ ሥልጣን ሳይኖራቸውና የኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ከሕግ የመነጨ መብት በመጋፋት የቤተ ክርስቲያኒቱን ሎጎ /አርማ/፣ ማኅተምና መጠሪያ ስያሜ መጠቀማቸው ሕገ ወጥ አድራጎት በመሆኑ የሚመለከታችሁ የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ግለሰቦቹ በቤተ ክርስቲያኒቱ ሎጎ /አርማ/ እና ማኅተም እንዲሁም መጠሪያ ስያሜ መጠቀም የማይችሉ መሆኑ ታውቆ አስፈላጊውን አስተዳደራዊ እርምት በመስጠት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ታስከብሩ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት እያሳሰበ፤ የጽ/ቤታችን የሕግ አገልግሎት መምሪያም በሕገወጦች ግለሰቦች ላይ ክስ በመመሥረት የቤተ ክርስቲያኒቱን መብትና ጥቅም ያስከብር ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ በጥብቅ አዟል፡፡ ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በዝርዝር በተገለጹት የአቋም መግለጫዎችና በሌሎችም ዐበይት ጉዳዮች ላይ በመወያየትና ተገቢውን ውሳኔ በመስጠት ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡