መስከረም 16 ቀን 2011 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል ሐዋርያዊ መልእክት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
የጥል ግድግዳን በመስቀሉ አፍርሶ ሁላችንንም በፍቅርና በይቅርታ አንድ አድርጎ ወደ እርሱ ያቀረበን አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ አንድ ዓመተ ምሕረት በዓለ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ።
«ወወሀበነ ሰላመ ለርሑቃን ወሰላመ ለቅሩባን በመስቀሉ
በመስቀሉ ርቀው ለነበሩትም፥ ቀርበን ለነበርነውም ሰላምን ሰጠን።»
(ኤፌ. 2፥17)
የእግዚአብሔር ቃል እዚህ ላይ እንደሚነግረን ስሕተት ባመጣው ኀጢአት ምክንያት ሰዎች በአንድ ወቅት በመንፈስ ተለያይተውና ተራርቀው እንደ ነበሩ ነው። በእርግጥም የቀደመው ሰው በመስሐቲ ፍጡር ተገፋፍቶ ስሕተትን በመፈጸሙ ለኀጢአት ተዳርጎ ከእግዚአብሔር ተለይቶ፥ ከገነትም ወጥቶ ወደ ምድረ ፍዳ እንደተሰደደ እናውቃለን። በምድረ ፍዳ መኖርን አንድ ብሎ የጀመረው የሰው ልጅ ንጽሐ ባሕርዩ ስለአደፈበት በስሕተት ላይ ስሕተት እየፈጸመ በመቀጠሉ የእርስ በርስ መለያየትና መራራቅ እያሰፋ የጨለማ ሕይወትን ማስተናገድ ቀጠለ። ሰዎች በመለያየትና በመራራቅ የኖሩበት ያ ዘመን የጨለማና የሞት ጥላ ዘመን እንደነበረ ቅዱስ መጽሐፍ ‘በጨለማና በሞት ጥላ የሚኖር ሕዝብ’ እያለ ይገልጸዋል። በዚያን ወቅት ሰዎች ከሰማያውያን ፍጡራን ብቻ ሳይሆን እርስ በርሳቸውም ተለያይተውና ተራርቀው የኖሩበት፥ ከሁሉም በላይ ደግሞ ሕይወት፥ መድኀኒት ከሆነው ከእውነተኛው አምላክ ከእግዚአብሔር ተለይተውና ርቀው፥ በባዕድ አምልኮ ተዘፍቀው የኖሩበት ያ የፍዳ፥ የመርገም፥ የኵነኔ፥ የመለያየትና የመራራቅ ዘመን እውነትም የጨለማና የሞት ጥላ ተምሳሌት ነበረ። ሆኖም የሰው ድኅነቱን እንጂ ጥፋቱን የማይሻ እግዚአብሔር አምላካችን በፍጹም ፍቅሩ እኛን ሊታረቀንና ወደራሱ ሊያቀርበን ቍርጥ ፈቃዱ እንደሆነ በቅዱሳን ነቢያት ደጋግሞ ገለጸልን። ጊዜው ሲደርስም ራሱ በሥጋ ተገልጾ በመስቀል ላይ በፈጸመው ቤዛነት ፍጹም ይቅርታን ሰጥቶ፥ በሩቅም በቅርብም ያለነውን አንድ ላይ አገናኝቶ የአንዲት መንግሥቱ ዜጎች አድርጎናል።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
የመስቀልን በዓል በየዓመቱ በታላቅ ድምቀት የምናከብርበት ዋና ምክንያት ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የራቁትንና የቀረቡትን አሰባስቦ አንድ ያደረገበትን ምሥጢር ተረስቶና ተዳፍኖ እንዳይቀር ሲባል የተካሄደውን መንፈሳዊ ተጋድሎ ለማስታወስና በትምህርተ መስቀል ውስጥ ያለውን የሰላም ጸጋ በምእመናን ልቡና ውስጥ ለማሠረጽ ነው። ከመስቀሉ የምንሰማው እጅግ በጣም ላዕላዊ አስተምህሮ «እየተበደሉም ቢሆን ለበዳዮች ይቅርታ መስጠት፥ በፍቅርም መቀበል» ነው። ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በደል ሳይኖረው በዐመፅና በአድማ ተነሣሥተው በችንካር እጁንና እግሩን ቸንክረው፥ በገመድ አስረው ለሰቀሉት ሰዎች በዚያችው ሰዓት በመስቀል ላይ እያለ «የሚያደርጉትን አያውቁምና ይቅር በላቸው» ብሎ ይቅርታ መስጠቱ፥ በመስቀሉ ላይ የተገነባው የይቅርታ፥ የምሕረትና የፍቅር ከፍታ ምን ያህል አስገራሚ እንደሆነ በአድናቆትና በተመስጦ እንድናየው ያስገድደናል። በመሆኑም ከዚህ ዐቢይ በዓል ልንወስደው የሚገባን ዐቢይ አስተምህሮ ፍቅርን፥ ይቅርታንና አንድነትን እንደ ልዩ የሕይወት ጸጋ አድርጎ መያዝ ለዘላቂ ሰላም ዋስትና አለው የሚለው ነው።
ጌታችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰውን ጥፋትና በደል በምልአት የሚያውቅ አምላክ ሆኖ ሳለ በመዋዕለ ሥጋዌው ሁሉን በፍቅር እየተቀበለ ይቅር ተብለሃል፥ ይቅር ተብለሻል ከማለት በስተቀር በአንድ ሰው እንኳ አልፈረደም። ታዲያ የተደረገውንና የተነገረውን ብቻ ሳይሆን በልብ የታሰበውንም ሳይቀር የሚያውቅ አምላክ ሁሉንም በፍቅር፥ በይቅርታና በምሕረት የሚቀበል ከሆነ የራሳችንን እንጂ የሌላውን በደል በአግባቡ የማናውቅ፥ በዚያውም ላይ ሌላውን ከምንተችበት በደል ነፃ ሳንሆን ለመፍረድ እንዴት እንደፍራለን? ምክንያቱም መፍረድ በራሱ ኀጢአት እንደሆነ «በማንም ላይ አትፍረዱ» ተብሎ ተነግሮናልና ነው። የመስቀል አስተምህሮ አንድነትና አንድነት ብቻ እንደሆነ የምንገነዘበው ለበደለኞች በተደረገው ይቅርታ ነው። በደለኞች ይቅርታ ከተደረገላቸው ይቅርታ የተደረገላቸው በደለኞችና ያልበደሉ ወገኖች አንድ ላይ ይውላሉ ማለት ነው፤ ታዲያ አንድነት ማለት ይህ አይደለምን? ቅድስት ዕሌኒ ከብዙ ሠራዊቷ ጋር ረጅም ጒዞ የተጓዘችው የፍቅር፥ የይቅርታና የአንድነት አስተምህሮ ዋና መገለጫ የሆነው ዕፀ መስቀል ተቀብሮ፥ ተዳፍኖና ተረስቶ መቅረት የለበትም፥ ዓለምና ትውልዶች ሊማሩበት፥ ሊያውቁትና ሊመሩበት ይገባል በሚል ጽኑ መለኮታዊ እምነት እንደነበረ ጥርጥር የለውም። በመሆኑም ህልምዋና ጥረትዋ ተሳክቶ እነሆ በዛሬው ዕለት በደመረችው ጢሰ ዕጣን አመልካችነት መስቀሉ የተቀበረበትን ለማወቅ ችላለች። ባደረገችውም ቊፋሮ መጋቢት 10 ቀን እውነተኛውን መስቀል ለማውጣት ችላለች። ወዲያውኑም ቤተ ክርስቲያኑን ማሠራት ጀምራ መስከረም 17 ቀን ቅዳሴ ቤቱን በማክበር መስከረም 21 ቀን ዕፀ መስቀሉን በጎልጎታ ባሠራችው ቤተ ክርስቲያን አስገብታለች። እኛም በዓለ መስቀሉን በየዓመቱ የምናከብረው ከዚህ ሃይማኖታዊ ትውፊት በመነሣት ነው።
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
የደመራን በዓል ስናከብር ደመራ ማለት የተበታተኑትንና ተራርቀው የነበሩትን ዕንጨቶች አንድ ላይ ማሰባሰብ ማለት እንደሆነ አንዘነጋውም። ታዲያ ዕንጨቶችን ሰብስቦ አንድ ላይ በመደመር አንድነትንና እውነተኛነትን ያስተማረ ቅዱስ መስቀል አይደለምን? እኛስ ከመስቀል ባገኘነው መሠረታዊ አስተምህሮ ደመራን በመደመር መስቀሉን ለማክበር የተሰበሰብነው አንድነታችንን ለማረጋገጥ አይደለምን? ይህንን ተገንዝበን በዓለ መስቀሉን እያከበርን ከሆነ የመስቀሉ ትምህርት በሚገባ ገብቶናል ማለት ነው። መስቀል ማለት ወዳጅን ብቻ ሳይሆን ጠላትንም ጭምር እንደራስ አድርጎ መውደድ ነው፤ መስቀል ማለት ለወዳጅ ብቻ ሳይሆን ለበዳይም ጭምር ይቅርታን መጸለይ ነው፤ መስቀል ማለት ከወዳጅ ጋር ብቻ ሳይሆን ከባላጋራም ጋር ታርቆና ተቻችሎ በአንድነት መኖር ነው። ይህ ዐይነቱ ሕይወት ሰዎችን ወደ ፍጹም ፍቅር ያደርሳቸዋል። ፍቅርና ይቅርታ ሲጠቅሙ እንጂ ሲጎዱ ታይተው አያውቁም። ለዚህም ነው ሕዝባችን በየዓመቱ በመላ ሀገራችን በሚከበረው በዓለ መስቀል የተጣላው ታርቆና ይቅር ይቅር ተባብሎ በየሰፈሩ በአንድነት ተቀምጦ እግዚአብሔር የሰጠውን በረከተ ማእድ በኅብረት እየተቋደሰ አንድነቱንና ፍቅሩን የሚያድሰው። ቅዱስ መስቀል ያወረሰንን ይህንን ባህል እናክብረው፥ እንጠብቀው፥ እንመራበት።
በመጨረሻም፤ በዛሬው ዕለት ለመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት የምናስተላልፈው የእግዚአብሔር መልእክት ገና ያልሰከኑ የሚመስሉ የጥላቻ፥ የመጠራጠር፥ የመለያየትና ያለመተማመን፥ ራስን የመውደድና የመሳሰሉ ዝንባሌዎች እንዲገቱ፥ ሁሉም ኢትዮጵያውያን የኢትዮጵያ አንድነት ከሁሉም በላይ እንደሆነ እንዲገነዘቡ፤ ኀይልና ጒልበት፥ እድገትና ብልጽግና፥ መከበርና መታፈር፥ መወደድና መፈራት በአስተማማኝ ሁኔታ የሚገኘው ከአንድነት ብቻ እንደሆነ በአጽንዖት እንዲያስተውሉ፤ ከእኛ ውስጥ አንድ ስንኳ ሳይጠፋ በሰላም ዘመኑን የይቅርታና የአንድነት ዘመን አድርገው እንዲቀበሉና ይህንንም እንዲጠብቁ በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን።
በዓለ መስቀሉን የሰላም የፍቅርና የአንድነት በዓል ያድርግልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር። አሜን።