ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በአባቶች መካከል በተፈጠረው ልዩነት የተላለፈው ቃለ ውግዘት ተነሣ

ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም በአባቶች መካከል በተፈጠረው ልዩነት የተላለፈው ቃለ ውግዘት ተነሣ ይኽንኑ አስምልከተው ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የቅዱስ ሲኖዶስ ወሳኔ በመገናኛ ብዙኃን አስተላልፈዋል፡፡

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

ሐዋርያዊት፣ ጥንታዊትና ታሪካዊት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅም የታሪክ ዘመኗ አንድነቷን ጠብቃ፤ የሀገሪቱንም አንድነትና ነፃነት በማስጠበቅ ከፍተኛ አስተዋፅ ስታደርግ ኑራለች፤ አሁንም ከማድረግ የተቈጠበችበት ጊዜ የለም፡፡

ይህች ታላቅ ቤተ ክርስቲያን ከብዙ ዘመን በኋላ ከራስዋ ሊቃውንት መካከል መርጣ ከኤጲስ ቆጶስነት እስከ ፓትርያርክነት ለመሾም የበቃች ቢሆንም ከሁለት ዐሥርት ዓመታት ወዲህ በአንዳንድ አላስፈላጊ ምክንያት ያልተጠበቁ ችግሮች መከሠታቸው አልቀረም፤ እነዚህን ችግሮች በውይይት፤ በሰላምና በፍቅር በማስተካከል የቤተ ክርስቲያንን አንድነት በጋራ ማስጠበቅ በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ቅዱስ ሲኖዶስ ተወያይቶ ከውድ እናት ሀገራቸው ኢትዮጵያ ወጥተው በሰሜን አሜሪካ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች ወደ ሀገራቸው እንዲመለሱ ውሳኔን አሳልፎአል፡፡

ከዚህ በኋላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ከርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ልኡካንን ለአምስተኛ ጊዜ ወደ ሰሜን አሜሪካ እንዲሄዱ በማድረግ፤ ልኡካኑ በቦታው ተገኝተው፤ ተገቢውን ውይይት አካሂደው፤ ለውጤት የሚበቃ ነጥብ መዝግበው የተደረሰበትን የሚያስረዳ መግለጫን አቅርበዋል፡፡
ከቀረበው የዕርቀ ሰላሙ የጋራ ስምምነት ሰነድ ላይ መረዳት እንደተቻለው፦

ሀ/ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ ፓትርያርክ ወደ ቅድስት ሀገር ኢትዮጵያ እንዲመለሱ ሆኖ፤ በመንበረ ፓትርያርኩ ግቢ ውስጥ ደረጃውን የጠበቀ ቦታ ተዘጋጅቶ፤ የሚያስፈልጋቸው ሁሉ ተሟልቶ በክብር እንዲቀመጡ፤ የሥራ ድርሻን በተመለከተም፤ ጸሎትና ቡራኬን በማድረግ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲያገለግሉ፤
ለ/ ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ አቡነ ማትያስን በተመለከተም በሕገ ቤተ ክርስቲያን ድንጋጌ መሠረት የአስተዳደር ሥራን እየሠሩ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንን እንዲመሩ ሆኖ፤ የሁለቱም ፓትርያርኮች ስም የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ባለችበት ቦታ ሁሉ ዘወትር በጸሎት እንዲነሣ የሚሉትና የመሳሰሉት ዐበይት ነጥቦች በልኡካኑ መግለጫ ተመዝግበው እንደሚገኙ ምልአተ ጉባኤው ተገንዝቧል፤ ከዚህ ግንዛቤ በመነሣት በፊደል ተራ ቁጥር ‹‹ሀ›› እና ‹‹ለ›› የተጠቀሰው እንደተጠበቀ ሆኖ፤

1. በውጭ ሀገር በሚኖሩ አባቶችና በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል የነበረው መለያየት ለውግዘት በሚዳርግ ደረጃ ላይ ደርሶ እንደነበር የታወቀ ነው፡፡ አሁን ግን ጊዜ ገቢር ለእግዚአብሔር ነውና ብዙ ጊዜ ሲደከምበት የቆየው ታሪካዊው ዕርቀ ሰላም ለሠመረ ውጤት በመብቃቱ በጋራ ስምምነቱ መሠረት ጳጒሜን 2 ቀን 1984 ዓ.ም.፤ መስከረም 15 ቀን 1985 ዓ.ም. እና ጥር 25 ቀን 1999 ዓ.ም. በቅዱስ ሲኖዶስ የተላለፈው ቃለ ውግዘት ይህ ውሳኔ ከተላለፈበት ሐምሌ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ ቃለ ውግዘቱ ተነሥቶአል፡፡
2. ከልዩነት በፊት የተሾሙ ነባር ሊቃነ ጳጳሳትም በውጭ ሀገርም ሆነ በሀገር ቤት በቅዱስ ሲኖዶ ውሳኔ ተመድበው እንዲያገለግሉ ሆኖ፤ ከልዩነት በኋላ የተሾሙ ሊቃነ ጳጳሳትን፤ ጳጳሳትንና ኤጲስ ቆጶሳትን በተመለከተም ስያሜያቸው እንዳለ እንደተጠበቀ ሆኖ ፤ በሀገር ውስጥና በውጭ አህጉረ ስብከት ተመድበው ይሠሩ ዘንድ ምልአተ ጉባኤው ተቀብሎአቸዋል፡፡
3. በአጠቃላይም በልኡካኑ የጋራ መግለጫ በተዘረዘሩት ነጥቦች ጥልቅ ውይይት በማካሄድ የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት በበለጠ እንዲጠናከር፤ የሀገራችን ሰላምና መረጋጋት ተጠናክሮ እንዲቀጥል በሚያስችል ሁኔታ ላይ የበኩሉን ድርሻ መፈጸም እንዳለበት በማመን በመግለጫው ከ1-6 ተራ ቊጥር የተዘረዘሩትን ምልአተ ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
4. በመጨረሻም ይህ የቤተ ክርስቲያናችን አሳሳቢ ጉዳይ ተጀምሮ እስከሚጠናቀቅ ድረስ ሲከታተሉ የቆዩትን የተለያዩ የኮሚቴ አባላትን፤ ማኅበረ ካህናቱንና ማኅበረ ምእመናንን በተለይም በኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ አባላት መካከል የተከሠተው መለያየት የሀገሪቱ ችግር ጭምር መሆኑን በመገንዘብና ትኵረት በመስጠት ውድ የሀገር መሪነት ጊዜያቸውን ሠውተው ሰኔ 19 ቀን 2010 ዓ.ም. በአሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ በተካሄደው በታሪካዊው የዕርቀ ሰላም ጉባኤ ላይ በመገኘት አስተጋባኢና አሰባሳቢ የሆነ መመሪያን በመስጠት ብዙ ዘመን የተደከመበት ጉዳይ ፈጣን መፍትሔን እንዲያገኝ ላደረጉት ለኤፌድሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ለክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ቅዱስ ሲኖዶስ ከፍ ያለ ልባዊ ምስጋናውን ያቀርባል፡፡

የቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ልኡካን ሽኝት ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም

ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶስክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አሜሪካ ለሚጓዙ የዕርቀ ሰላም ልኡካን ሽኝት አድርጓል፡፡

በሽኝቱ መርሐ-ግብር ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አባታዊ መልእክትና መመሪያን ሰጥተዋል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ዕርቀ ሰላም ሂደት የበኩሏን ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰው ዛሬም ቅዱስ ሲኖዶስ በሁሉም መንገድ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀው የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ወደ ፍጻሜ ማምራት እንዳለበት አበክረው አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በአባቶች መካከል መከፋፈል ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ሰላምና አንድነት አስታውሰው “ሰላምና ፍቅር ለሁሉም ጥሩ ነው” ካሉ በኋላ “ያለፈውን ሁሉ ረስተን ወደ ጥንት አንድነታችንና ወደ ጥንት ፍቅራችን፣ ወደ ጥንት መንፈሳዊ ሕይወታችን እንድንመለስ እግዚአብሔር ይርዳን” በማለት ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል።

በተጨማሪም “ሰላም በእጃችን ሳለች አትታወቅም ከእጃችን ከወጣች በኋላ እንጂ” በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው “ቤተ ክርስቲያን የሰላም ቤት ናት፣ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ምንጭ ናት፣ ቤተ ክርስቲያን የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያት አይደለችም” በማለት በአባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ አለመሆኑን በአጽንዖት ገልጸዋል። አያይዘውም “የቤተ ክርስቲያን ሥራ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መመሥረት ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል፣ አገርን መጠበቅና ትምህርት ማስተማር ነው” በማለት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባቶች ካህናትና ምእመናን ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት እንዲሠሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም በቅዱስ ፓትርያርኩ የተላለፈውን መልእክት በመጋራት ቅዱስነታቸው አስቀድሞ ጀምረውት የነበረው ዕርቀ ሰላም ዛሬም በቅዱስነታቸው ዘመን ለፍጻሜ መቅረቡ ዕደለኛነታቸውን ጠቅሰው በየራሳቸው እይታ ዕርቀ ሰላሙ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ ዕውን ሊሆን የሚችልበት ወቅት ላይ መድረሱን ገልጸዋል። ልኡካኑም ይህ የዕርቀ ሰላም ሂደት በጥሩ መንገድ እየተጓዘ የመጣ መሆኑን በማስታወስ ከፍጻሜ ላይ ደርሶ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና የአባቶችን አንድነት በቅርቡ ማየት እንድንችል የቅዱስነታቸውና የብፁዓን አባቶች ድጋፍና ጸሎት እንዳይለያቸው ተማጽነዋል።

የዕርቀ ሰላም ኮሚቴ አባላትም ላቀረቡት የዕርቀ ሰላም ጥያቄ ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከቅዱስ ሲኖዶስ ላገኙት አዎንታዊ መልስና ቀና ትብብር ምስጋናቸውን ገልጸው የተጀመረው ዕርቀ ሰላም በመልካም ፍጻሜ እንዲቋጭ አሁንም ድጋፋቸውና ጸሎታቸው እንዳይለያቸው ተማጽነዋል።

ሐምሌ 4 ቀን 2010 ዓ.ም. ቅዱስ ሲኖዶስ ልዩ አስቸኳይ ጉባኤ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ ለ2000 ዓመታት አንድነቷን፣ ዶግማዋንና ቀኖናዋን ጠብቃ የቆየች ጥንታዊት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በተለያዩ ዘመናት የውጭና የውስጥ ፈተናዎች ቢፈራረቁባትም ፈተናዎቹን በመቋቋም፣ እምነቷን በማጽናት፣ ቀኖናዋንና ትውፊቷን በመጠበቅ፣ ተከታዮቿን በመምከርና በማስተማር ሀገርን ሰላም እያደረገች ኖራለች፡፡

ሆኖም በ1984 ዓ.ም. የነበሩት 4ኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ፓትርያርክ መንበራቸውን መልቀቃቸውን ተከትሎ ከተወሰኑ አባቶች ጋር ከአገር በመውጣታቸው ምክንያት በቤተ ክርስቲያናችን ለ26 ዓመታት ተከታዮቿ ምእመናን እያዘኑ በከፍተኛ የሰላም ዕጦት ውስጥ አሳልፋለች።

ይህ ቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ የጠፋውን ሰላም ወደነበረበት እንዲመለስ ለማድረግ ከችግሩ መፈጠር መነሻ ማግስት እና ከ2003 ዓ.ም. ጀምሮ ቅዱስ ሲኖዶስ በአራት የተለያዩ የስብሰባ ጊዜያት ዕርቀ ሰላሙን ለማምጣት ሊቃነ ጳጳሳትን መድቦ አሜሪካ ድረስ በመላክ ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ ከዚህ በተጨማሪ ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት በሚያደርጋቸው ጉባኤያት የሰላሙ በር ክፍት መሆኑን በመግለጽ የሰላም ጥሪ ሲያስተላልፍ ቆይቷል፡፡

ይህ የምእመናን ልጆቻችን የሰላም ጥማትና የዘወትር ጸሎት የቅዱስ ሲኖዶስ የዕለት ከዕለት የሰላም ጥረት ቅድመ እግዚአብሔር ደርሶ ሰላሙ መቋጫ ወደሚያገኝበት ደረጃ እንዲደርስ የ2010 የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ተከትሎ በራሱ ተነሳሽነት ከካህናትና ምእመናን የተውጣጣ የሰላም ኮሚቴ ያቀረበውን የዕርቀ ሰላም ጥያቄ በአዎንታ ተቀብሎት ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ሂደት ተጠናክሮ እንዲቀጥልና የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሦስት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትን ሰይሟል፡፡

በዚሁ መሠረት ከሐምሌ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በአባቶች መካከል የሚካሄደው የዕርቀ ሰላም ሂደት ፍጻሜ የሚያገኝበት በውጭ አገር የሚገኙ አባቶች ወደ አገር ቤት የሚገቡበት ፍጹም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት የሚመለስበት እንዲሆን በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማትና አድባራት ካህናትና ምእመናን በጸሎት እንድትተጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡

አገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ በአዲስ መንፈስ እየሄደችበት ያለው የሕዝቡን ሰላምና አንድነት ማረጋገጥ ውጤታማ እየሆነ መጥቷል፡፡ ከዚሁ ጋር ለዘመናት አንድነትና ቤተሰባዊነት የነበራቸው የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች ወደ ፍጹም ሰላም እንዲመጡ እየተከናወነ ያለው ጅምር ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ የምትደግፈውና ለመጨረሻውም ግብ የበኩሏን አስተዋፅኦ የምታደርግበት ይሆናል፡፡

ቤተ ክርስቲየናችን በአሁኑ ጊዜ በውስጧ የሚገኙ ችግሮቿን ከጥንት ጀምሮ ይዛው በቆየችው ትዕግሥትና የሰላም ሂደት በቀኖናዋ መሠረት የምትፈታው ሲሆን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎቷን በብቃት የምታከናውንበት አቅጣጫ ቅዱስ ሲኖዶስ አስቀምጧል፡፡

በቀጣይ ወቅቱንና ዘመኑን በዋጀ መልኩ መልካም አስተዳደርን በቤተ ክርስቲያናችን ካለፈው በበለጠ ማስፈን እንዲቻል የቤተ ክርስቲያኒቱን ችግሮች ሊፈታ ያስችላል በሚል በባለሙያዎች የተዘጋጀውን መሪ ዕቅድና ከአሁን በፊት የተጠኑ ጥናቶች በተግባር ማዋል እንዲቻል ጥናቶቹ ለ2011 ዓ.ም. የጥቅምቱ ምልአተ ጉባኤ ዋና የመነጋገሪያ አጀንዳ ሆኖ እንዲቀርብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

አሁን በቤተ ክርስቲያናችን አባቶች መካከል የተጀመረው ዕርቀ ሰላም ያለምንም መሰናከል ለውጤት ይበቃ ዘንድ ዕርቀ ሰላሙን አስመልክቶ ቅዱስ ሲኖዶስ ፈቃድ ከሰጠው አካል በስተቀር መግለጫ መስጠት ጠቃሚ አለመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡

በዕርቀ ሰላሙ ሂደት በሚደረገው ማንኛውም ውይይት የነበረውንና ቤተ ክርስቲያናችን ይዛው የቆየችው ቀኖና በተመለከተ ውይይቱም ሆነ ዕይታው በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ ብቻ የሚታይ ይሆናል፡፡

አሁን ለተጀመረው የዕርቀ ሰላምና የአንድነት መገኘት የቅዱስ ሲኖዶሱን ውክልና ይዘው ወደ አሜሪካ የሚጓዙ ብፁዓን አባቶች ጒዞአቸው የተቃናና የተሳካ ሆኖ ችግሩ የመጨረሻ እልባት እንዲያገኝ ሁላችንም ተባብረን እንድንሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለአገራችንና ለሕዝባችን ሰላሙን ይስጥልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ፡፡