ከሚያዝያ 24 ቀን እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አምስት ንኡስ አንቀጽ 164 በተደነገገው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ የዘንድሮውን የርክበ ካህናት ጉባኤ በማስመልከት የስብሰባው መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአንድ ሱባኤ ያህል ባደረገው ስብሰባ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚበጁ ጠቀሜታ ያላቸውን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ለጉባኤው በቀረበው አጀንዳ ተራ ቊጥር 1 የተገለጸውን በተመለከተ፤ የጉባኤው መክፈቻ ንግግር፣ ትምህርትና መመሪያ የቤተ ክርስቲያኒቱንና የሀገሪቱን ሁለተናዊ ገጽታ የዳሰሰ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎትን የሚገነባ ተልዕኮ ያለው በመሆኑ ምልአተ ጉባኤው በበሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል።
2. ከግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. እስከ ሚያስዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ የተላለፉ ውሳኔዎች በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ አማካይነት ቀርበው ምልአተ ጉባኤው በአፈጻጸማቸው ዙሪያ ከተወያየ በኋላ አስፈላጊውን መመሪያ በመስጠት ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
3. በተለያየ ምክንያት የሥራ ዝውውር እንዲደረግላቸው ጥያቄ ያቀረቡ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳትና ጳጳሳት የጥያቄያቸው አስፈላጊነት በቅዱስ ሲኖዶስ ከተጠና በኋላ ዝውውሩ ተፈጽሞላቸዋል፤
4. እናት አባታቸው ሙተውባቸው ሰብሳቢ ያጡ ሕፃናትን እያሳደገና እያስተማረ ለቁም ነገር ያበቃ ዘንድ ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያኒቱ ያቋቋመችው የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ርዳታ ለጋሾች ጋር ያለውን የቅርብ ግንኙነት በበለጠ እያጠናከረ ሥራውን ይቀጥል ዘንድ ምልአተ ጉባኤው መመሪያን ሰጥቷል፤
5. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከተሠየሙበት ጊዜ ጀምሮ እያደረጉት ያለው ታሪካዊ ንግግር፣ ሀገራዊ አንድነትን፣ ፍቅርና ትሕትናን የሚያስተምር፣ ሰላምንና መረጋጋትን የሚያበሥር፣ የሩቁንና የቅርቡን የሚያስተባብር መንግሥታዊ ኀላፊነት የተሞላበት መልእክት በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአክብሮት ተቀብሎታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየክልሉ እየተዘዋወሩ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የተፈጠረው መቃቃር ይቅርታ ባልተለየው መንፈስ ተወግዶ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መመሪያ ከመስጠት ጋር እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ልብ ደግፎታል፤ የጥረቱም አካል በመሆን የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
6. ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡት ክቡር የእስራኤል ሀገር ፕሬዚዳንት ሪቨን ሪቢሊን የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በሚጀመርበት ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓትርያርኬቱ ተገኝተው ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ስለ ዴር ሡልጣን ገዳማችን ሁኔታ ለ30 ደቂቃ ያህል የጋራ ውይይት ካደረግን በኋላ በኢየሩሳሌም ያሉት ገዳማት በሙሉ እንደሚታደሱ፣ በተለይም አሁን በቅርቡ የመፍረስ አደጋ የደረሰበት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ እንደሚታደስ የቃል ተስፋ በመስጠት አረጋግጠውልናል፡፡
7. እግዚአብሔርን መፍራት የመጀመሪያው ጥበብ እንደሆነ እየተገነዘበ የመጣው ወጣቱ ትውልድ፤ ሀገሩንና ሃይማኖቱን፣ ባህሉንና ቋንቋውን፣ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ከመጠበቅ ጋር ሥራ የመፍጠር ክሂሎቱን በበለጠ አጎልብቶ ሀገሩን እንዲያለማ ቅዱስ ሲኖዶስ አደራውን ጥሎበታል፡፡
8. የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን የግንባታው ሥራ ማከናወኛ የሚሆን ገንዘብ እንዲያዋጣ ሕዝቡን ከማስተባበር ደረጃ ጀምሮ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ሁሉ ከመለገስ ወደኋላ ያለችበት ጊዜ እንደሌለ ቢታወቅም፣ የማጠናቀቂያው የደወል ድምፅ እስካልተሰማ ድረስ የማስተባበሩ ሥራም ሆነ የእርዳታ ገንዘብ አሰባሰቡ ተግባር እንዲቀጥል ማድረግ ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን ትገነዘባለች፡፡

ከዚህ አንጻር የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ ሁሉም ኅብረተሰብ የጋራ ኀላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብና በውል በመረዳት የርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከዚህ በላይ በተገለጹትና በሌሎችም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ አስፈላጊዎቹን በመወሰን ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡

ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት፤ ብፁዓን ኤጲስ ቆጶሳት፣ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት በሙሉ
እግዚአብሔር አምላካችን ለዚህ ዓመታዊ የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስላደረሰን እንደዚሁም ከየሀገረ ስብከታችን አሰባስቦ አንድ ላይ ስላገናኘን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡

“ዘይሁብ መርሐ ርቱዐ ለቤተ ክርስቲያን” ለቤተ ክርስቲያን የተስተካከለ መርሕን የሚሰጥ እግዚአብሔር አምላክ ነው› (መጽሐፈ ኪዳን)፡፡

ሁላችንም እንደምንገነዘበው መርሕ ወይም ሕግ ካለ ባለቤት አለ፤ ሕጉን የሚያስፈጽም አገልጋይም አለ፤ የሕጉ ባለቤት ቤተ ክርስቲያንን በደሙ የመሠረተ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ሰማያዊ አምላክ እንደመሆኑ መጠን ለቤተ ክርስቲያን የሰጠው መርሕም ሰማያዊ ነው፡፡ ይህም ማለት የመጨረሻ መዳረሻው ሰማየ ሰማያት መሆኑን የሚያመለክተን እንጂ በጌታችን የተሰጠው መርሕ መነሻው በምድር ሳሉ የሚተገበር ነው፡፡ መርሑ በምድር ላይ መተግበር ስለነበረበትም ትግበራውን ሊከታተሉና ሊያስፈጽሙ ለቅዱስ ሲኖዶስ አባላት የውክልና ሥልጣን በሀብተ ክህነት ተሰጥቷል፡፡

በጌታችን የተሰጠው መርሕ ቅዱስ ወንጌል እንደሆነ ሁላችንም የምናውቀው ነው፤ የቅዱስ ወንጌል መልእክትም በአጭር አባባል ሲገለጽ ሰውን አስተምሩ፣ ሰውን ጠብቁ፣ ሰውን ለድኅነት አብቁ የሚል ነው፤ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትም ውክልና የተሰጠን ይህንን መርሕ ለማስፈጸም ነው፡፡ ይህንም ስንፈጽም ብቻችን እንዳይደለን እርሱ ባለቤቱ ቀጥሎ ቀጥሎ በሚደረግ ተአምርና ሙሉ ጥበቃ ቃሉን እያጸና በሥራችን ሁሉ ዘወትር ከኛ ጋር እንደሆነ በማይታበል ቃሉ አረጋግጦልናል፡፡

በዚህ ሕያውና አምላካዊ ቃል ኪዳን መሠረት ቤተ ክርስቲያን ቃሉን ለዓለም ሁሉ ማድረስ ችላለች፡፡ በሁሉም ያለች፣ ሐዋርያዊት፣ አንዲትና ቅድስት የሆነች ቤተ ክርስቲያናችንም በእግዚአብሔር ፈቃድ ዛሬ እግሯ ያልረገጠው ክፍለ ዓለም የለም፤ ከዚህ አኳያ ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ ብሔራዊት ብቻ ሳትሆን ዓለም ዐቀፋዊት ሆና የወጣችበት ዘመን ሆኖ ይገኛል፡፡ እግዚአብሔር በልዩ ጥበቡ ይህንን የሐዋርያነት ጸጋ ስላደለን ቤተ ክርስቲያናችን በገባችበትና እግር በተከለችበት ሁሉ የተደራጀ የተጠናከረና በስልታዊ ጥበብ የታቀደ ሥራን በመሥራት ይበልጥ እንዲሰፋ ማድረግ ከዚህ ዐቢይ ጉባኤ ቀና ትብብርና ተነሣሽነት ያስፈልጋል፡፡

ከጌታችን በተሰጠው መርሕ መሠረት ቤተ ክርስቲያናችን ምእመናንን ለማስተማር፣ ለመጠበቅና ለድኅነት ለማብቃት ከሁለት ሺሕ ዓመታት በላይ ባደረገችው ተጋድሎ ስፍር ቍጥር የሌላቸው አማንያንንና ቅዱሳንን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ማብቃቷ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡ አሁን ባለንበት የፈተና ዘመንም ቤተ ክርስቲያናችን ምእመናንን በየደረጃቸው በቃለ ዐዋዲ አደራጅታ እያስተማረች፣ እየጠበቀችና ለመንግሥተ እግዚአብሔር እያበቃች ትገኛለች፡፡ ከሃያኛው ክፍለ ዘመን ጀምሮ በቃለ ዐዋዲ አደረጃጀት ባደረገችው የሥራ እንቅስቃሴ ልምድ ሙሉ በሙሉ ወደተሻለ የጥበቃ ሥራ ሊያሸጋግራት የሚችል ዐቅም መፍጠር እንደምትችል በተጨባጭ አይተናል፤ ምእመናን በአጠቃላይ በተለይም ወጣቶች ቤተ ክርስቲያንን ለመደገፍና ለመጠበቅ ብሎም የመንግሥተ እግዚአብሔርን ዜጎች ለመሆን የሚያደርጉት እሽቅድድም እጅግ አስደሳች ሆኖ ተገኝቷል፡፡

ይህም የቃለ ዐዋዲ አደረጃጀት ያስገኘው ጸጋ እንደሆነ የማንስተው ነው፤ ቃለ ዐዋዲው ያላቀፈው የክርስቲያን ማኅበረ ሰብ በአሁኑ ጊዜ የለም፤ ካለማወቅ የሚቀር ባይጠፋም ዕድሉ ግን ለሁሉም ክፍት አድርጎ ሰጥቷል፤ ስለሆነም የቃለ ዐዋዲ መዋቅር የቤተ ክርስቲያናችን የአንድነቷ፣ የሀብቷና የሃይማኖቷ መጠበቂያና የምእመናን ዋስትና ስለሆነ ልንጠብቀው ይገባል፡፡ ቀረ የሚባል ካለም በጥናት ላይ በተመሠረተ አሠራር በቃለ ዐዋዲው እያካተቱ ከመሥራት ውጭ የተሻለ ጠቃሚ ነገር አይኖርም፡፡

በቤተ ክርስቲያናችን የሚከናወነው መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ አሠራር እንደማንኛውም ሰብኣዊ ሥራ የራሱ የሆነ ጥንካሬና ድክመት እንዳለው ሁላችንም እንገነዘባለን፤ ቀድሞውኑም ይህ ሊኖር እንደሚችል ታሳቢ ተደርጎ ነው የቀደሙት ቅዱሳን አበው በዓመት ሁለት ጊዜ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ እንዲኖር በቀኖና የደነገጉት፤ ስለሆነም የመሰብሰባችን ዐቢይ ዓላማ የቤተ ክርስቲያናችንን ጠቅላላ ሥራ በመገምገም ጥንካሬያችንን ይበልጥ አጎልብተን ለመቀጠል ድክመታችንን ደግሞ በፍጥነት አርመን ለሕዝበ ክርስቲያኑ የተሻለ አስተምህሮና የተጠናከረ ጥበቃ በማድረግ ለእግዚአብሔር መንግሥት ለማብቃት ነው፡፡ ከዚህ አኳያ ባለፉት ወራት የነበረው የሀገራችን ሁኔታ ፈታኝና ከሃይማኖት አባቶች ብዙ ሥራ መሥራትን የሚጠይቅ እንደሆነ አስተውለናል፤ ይሁንና አሁን ባለው ሁኔታ አንጻራዊ መረጋጋት የሚታይበት ጊዜ እግዚአብሔር በቸርነቱ ሰጥቶናል፡፡ ይህም በሕዝቡ በተለይም በወጣቱ ትውልድ ይበልጥ ሥርጸት እንዲያገኝ ከእኛ ከሃይማኖት አባቶች ባለመታከት ቀን ከሌሊት ተግቶ የማስተማርና የመጠበቅ ሥራ መሥራት ያስፈልጋል፡፡

ለቤተ ክርስቲያን አገልግሎትና ለሕዝብ ጥበቃ ከአምላክ ሥልጣነ ክህነትን የተቀበሉ ሁሉ ሀገርን ከቤተ ክርስቲያን፣ ቤተ ክርስቲያንን ከሀገር ነጥለው ማየት የለባቸውም፤ ምክንያቱም ቤተ ክርስቲያን የምትኖረው በሀገር ውስጥ ነው፤ ጠንካራና ዘላቂ እምነቷን የምታስጠብቀውም ሀገር አንድ ስትሆን ነው፤ የሀገር አንድነትና የሕዝቦች ስምምነት ከሌለ የቤተ ክርስቲያን አንድነትም አይኖርም፤ ስለዚህ እኛ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ለሀገር አንድነት የሚበጅ ሥራን በመሥራትና በማስተማር ተምሳሌትና አርኣያነት ያለው ሥራ ለመሥራት መጣር አለብን፤ ዓለሙ በጮኸ ቊጥር የምንጮኽ ሳይሆን ለሃይማኖታችን፣ ለሕዝባችን፣ ለሀገራችንና ለአንድነታችን የሚበጀውን ብቻ በመከተል ሕዝቡን መምራት ይጠበቅብናል፡፡

ዛሬ ዓለማችን ለመንግሥተ እግዚአብሔር ዜጎች እጅግም የማትመች እየሆነች መምጣቷ በግልጽ የሚታይ ነው፤ አስተሳሰቦች በፍጥነት እየተቀያየሩ፤ የሥነ ምግባር ዕሴቶችም በፍጥነት እየተሸረሸሩ፤ አማንያን ወዲያና ወዲህ እየባዘኑ የሚታይበት ጊዜ ነው፤ ከዚህ አኳያ ከተወሰኑ ጊዜያት በኋላ አማንያን ምን ዐይነት ቁመና ይኖራቸው ይሆን; የሚለው ጥያቄ እየገፋ ነው፤ ይህ ፈተና ምዕራባውያንን ባዶአቸውን እያስቀራቸው እንደሆነም በግልጽ እየተሰማ ነው፤ እስካሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ከሌላው ሁሉ የኦርቶዶክሱ ዓለም በጥንካሬ እንደሚገኝ ሁኔታዎች ያሳያሉ፤ ይህም በደምብ ከተሠራበት የኦርቶዶክስ ሃይማኖታዊ አስተምህሮና ቀኖና ፈተናን የመቋቋም ዐቅሙ ከፍ ያለ መሆኑን ስናይ ተስፋችን የላቀ እንዲሆን አድርጎታል፤ በመሆኑም ከኦርቶዶክሱ ዓለም በተለይም ከአኃት አብያተ ክርስቲያናት ጋር ያለውን ሃይማኖታዊ አንድነት እንደተጠበቀ ሆኖ ከራሺያ ቤተ ክርስቲያን ጋር በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ፣ በሰላምና በልማት ተግባራት እንደዚሁም በሁለንተና የሥራ መስክ ሥልጠና በጋራ መሥራት እንደሚያስፈልገን ተገንዝበናል፡፡

በመሆኑም በቋሚ ሲኖዶስ ውሳኔ መሠረት የልኡካን ልውውጥ በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ተካሂደዋል፤ በቀጣይም በከፍተኛ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ተጨማሪ ጒብኝቶች በሁለቱም ሀገሮች ለማድረግና ግንኙነቱን ወደላቀ ደረጃ ለማድረስ በሰፊው እየሠራን ነው፤ ቅዱስ ሲኖዶስም ድጋፉንና ትብብሩን እንዲያክልበት በዚህ አጋጣሚ ለማሳሰብ እንወዳለን፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ ዓመታዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገር አንድነት የሚጠቅሙ መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮችን በዝርዝር በማየት በመገምገምና አቅጣጫ በማስቀመጥ ውጤታማና ሰላማዊ ጉባኤ እንዲሆን በመመኘትና በመጸለይ የ2010 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ የተከፈተ መሆኑን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን ጉባኤያችንን ይባርክ፣ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡