ከጥቅምት 12 ቀን እስከ 21 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉባኤው ከጥቅምት 6 ቀን 201ዐ ዓ.ም. ጀምሮ የመንበረ ፓትርያርኩን አጠቃለይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና ዓመታዊውን የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ለ15 ቀናት ወሳኝ በሆኑ የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡

1. ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በጉባኤው መክፈቻ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ሕይወት የቃኘ፣ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን እድገትንና የሰላም አስፈላጊነትን በስፋት የገለጸ በመሆኑ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡
2. የሠላሳ ስድስተኛውን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ አንዳንድ ማሻሻያ በማድረግ የጋራ መግለጫው የ2010 በጀት ዓመት ተግባር ሆኖ ያገለግል ዘንድ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
3. የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ እስከ አሁን ድረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደኖረ ሁሉ አሁንም ከመንበረ ፓርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡
4. በመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሒሳብና በጀት መምሪያ ተዘጋጅቶ የቀረበው የ2010 ዓ.ም. በጀት የክፍያው ጣሪያ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
5. የአንድ ሀገር እድገትና መሠረታዊ ፍላጎት ግቡን ሊመታ የሚችለው የሃይማኖቱና የሞራል ስሜቱ የማይወቅሠውን በሚሠራ፣ በመልካም ሥነ ምግባር በታነጸ፣ የሥራን ክቡርነት በተረዳና እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ መሆኑን ባስተዋለ ትውልድ ተደግፎ ሲገኝ ስለሆነ፣ ኅብረተሰቡ ይህንኑ በመረዳት፣ በትዕግሥትና በመቻቻል፣ በመከባበርና በመናበብ፣ በመደማመጥና በመግባባት መንፈስ በአንድነት ተባብሮ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
6. የነገድ፣ የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት ሳይኖር ለጋራ ህልውና ለጋራ ልማትና ለጋራ ብልጽግና ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለጎረቤት አህጉር ብሩህ ተስፋ ሠንቆ እንደሚመጣ የተነገረለት የዐባይ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊነቱን እያስመሰከረ ስለመጣ አሁንም የፕሮጀክቱ ሥራ ተጠናክሮ ለውጤት እስከሚበቃ ድረስ ሁሎችም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ድጋፍ በመለገስ እንዲተባበሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
7. ትውልድ ሁሉ የሙያና የሥነ አእምሮ ብቃቱን አሳድጎ ሥራ የመፍጠር ክሂሎቱን እንዲያረጋግጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
8. ዕቅድን በተግባር ለማረጋገጥ፣ ሠርቶ ለማግኘት፣ ውሎ ለመግባት፣ አድሮ ለመነሣት፣ ዘርቶ ለማምረት፣ ነግዶ ለማትረፍና በነፃነት ለመኖር ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር የነፃነት ምልክት እንደሆነች ሁሉ የሰላምና የጸጥታም ምልክት መሆን አለባት፤ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በወገኖቻችን መካከል የተከሠተው ግጭት ተወግዶ ሙሉ ሰላምን የማስፈኑ ሥርዐት ተፋጥኖ እንዲረጋገጥ፣ ከዚህም ጋር በግጭቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቻችን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ባለው መዋቅር ብር 6,000,000 (ስድስት ሚሊዮን) የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ፡፡ እንዲሁም ከጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት ለሁለት ሱባኤ ማለትም ለ14 ቀናት ያህል ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
9. በውጭ ሀገር ከሚኖሩት አባቶች ጋር ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን አሳልፎአል፡፡
10. በቃለ ዐዋዲው የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች የሆኑት ወጣቶች በየአጥቢያ ቤተ ክርስያናቸው በሰንበት ትምህርት ቤት ተደራጅተው በየሰበካ ጉባኤው አመራር ሰጭነት እንዲማሩ ምልአተ ጉባኤው አመራርን ሰጥቷል፡፡
11. በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ወደ ኮሌጅ ደረጃ ማደግ ያስችለው ዘንድ ከክፍሉ ሊቀ ጳጳስ የቀረበውን ፕሮፖዛል ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
12. በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ ማሠልጠኛ አቋቁመው ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ማኅበራት የሚያገለግል እስካሁን ድረስ የተዘጋጀ የማኅበራት ማደራጃ ደንብ የሌለ በመሆኑ ለወደፊቱ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑንና ቃለ ዓዋዲውን መሠረት ያደረገ የማኅበራት ማደራጃ ደንብ በሕግ ባለሙያዎች እንዲዘጋጅ ጉባኤው ተስማምቶ ወስኗል፡፡
13. በጋሻው ደሳለኝ የተባለ ግለሰብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ለምእመናን ሲያስተላልፍ የነበረው የክህደት ትምህርት በመረጃ ተሰብስቦ ችግሩ ለቅዱስ ኖዶስ ከቀረበ በኀላ ከ15/02/2010 ዓ.ም. ጀምሮ የክሕደት ትምህርቱን በማውገዝ ከቤተ ክርስቲያናችን እንዲለይ ተደርጓል፣ በቤተ ክርስቲያችንም ስም እንዳያስተምር ተወግዟል፡፡
14. በተመሳሳይ መልኩም በአሜሪካን ሀገር በዋሺንግተን ዲ.ሲ. የሚያገለግሉት አባ መዓዛ ክርስቶስ በየነ እያስተማሩ ያለው የክሕደት ትምህርት ለቅዱስ ሲኖዶስ በመረጃ ቀርቦ የተረጋገጠባቸው ስለሆነ ሥልጣነ ክህነታቸው ተይዟል፤ ያሉበትን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በማናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል፡፡
15. ወልደ አብ በሚል ርእስ፤ ገብረ መድኅን በተባለ ግለሰብ የተጻፈው የክህደትና የኑፋቄ ትምህርት የቅብዐትንና የጸጋን የክሕደት ትምህርት የሚያስፋፋ በመሆኑ ካህናትን ከካህናት ምእመናንን ከምእመናን የሚያጋጭ ከመሆኑ ጋር፤ ከቤተ ክርስቲያንም አልፎ በሀገራችን ሁከት ለማስነሣት ታስቦ የተዘጋጀ ሆኖ ስለተገኘ፣ መጽሐፉ ከማናቸውም አገልግሎት እንዲለይ ተወግዟል፡፡
16. ለገዳማት መተዳደሪያ እንዲሆን የተዘጋጀው ደንብ ረቂቁ ተስተካክሎ የቀረበ በመሆኑ በሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
17. ተሐድሶ እየተባለ የሚጠራው የኑፋቄ እምነት ማኀበር ራሱን ኦርቶዶክሳዊ በማስመሰል የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና እየተፈታተነ ከማስቸገሩ የተነሣ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ በየአህጉረ ስብከቱ ተቋቁሞ የመከላከልና ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅ ሥራ እንዲያከናውን ውሳኔን መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

አሁንም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር እስከ አህጉረ ስብከት ባለው መዋቅር የተቋቋመው ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ ተጠናክሮ የመከላከሉን ሥራ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጥቷል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ከዚህ በላይ በተገለጹትና በሌሎችም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አስፈላጊውን መመሪያ ከሰጠ በኋላ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቆአል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ለሕዝባችን ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

ጥቅምት 12 ቀን 2010 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ወኤጲስ ቆጶሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
እግዚአብሔር አምላካችን በተለመደው ቸርነቱ ከየመንበረ ጵጵስናችሁ በሰላም አሰባስቦ በዚህ ዐቢይ ዓመታዊ ስብሰባ ተገናኝተን ስለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን አንድነት፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በስሙ እንድንመካከር ለፈቀደልን ለእርሱ ምስጋና ከአምልኮት ጋር እናቀርባለን፡፡ እናንተም ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳትና ኤጲስ ቆጶሳት እንኳን በደኅና መጣችሁ፡፡ እንኳንም ለዚህ ሐዋርያዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖደስ ዓመታዊ ጉባኤ በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ፡፡

“ወዘንተ ባሕቱ አእምር ከመ በደኃረ መዋዕል ይመጽኣ ዓመታት እኩያት ወይከውኑ ሰብእ መፍቀርያነ ርእሶሙ፡፡ ነገር ግን በኋለኞቹ ዓመታት ሰዎች ራሳቸውን የሚወዱበት ክፉ ዘመን እንደሚመጣ ዕወቅ” (2ኛ ጢሞ.9.1) ይህ መልእክት ቅዱስ ጳውሎስ ለሚወደው ደቀ መዝሙሩ ለጢሞቴዎስ ያስተላለፈው ምክር አዘል ትምህርት ነው፡፡

በቤተ ክርስቱያን ታሪክ እንደሚታወቀው ዐይነቱ ስልቱና መጠኑ ይለያይ እንደሆነ ነው እንጂ ከሆነ ጊዜ ጀምሮ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ከፈተና ተለይታ አታውቅም፡፡ ይሁን እንጂ ወደ መጨረሻው ዘመን አካባቢ የሚሆነው መከራ ግን ከሁሉ የባሰ እንደሚሆን በቅዱሳት መጻሕፍት በተደጋጋሚ የተገለጸ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ ቅዱስ ጳውሎስ ተማሪውን ጢሞቴዎስን ሊያስገነዝበው የፈለገው ነገር በመጨረሻ ዘመን የሚከሠተውን ፈተና ምእመናን ዐውቀው ጥንቃቄ ያደርጉ ዘንድ እንዲያስተምር ነው፡፡ ለወደፊት የሚሆነውን ነገር አስቀድሞ ማሳወቅና ወዳጆቹን የማስጠበቅ ኩነት ከጥንት ጀምሮ የነበረ የእግዚአብሔር አሠራር ነው፡፡ በዚህም ቅዱስ ጳውሎስ ለተከታዩ ትውልድ ስለመጨረሻው ዘመን ሁናቴ የማሳወቅ ሥራን ሲሠራ እናስታውላለን፡፡

በተጠቀሰው ክፍለ ምንባብ ላይ የመጨረሻው ዘመን ገጽታ ምን እንደሚመስል በዝርዝር ተገልጾአል፡፡ ይዘቱን ጠቅለል አድርገን ስንመለከተው በመጨረሸው ዘመን አካባቢ ነገሩ ሁሉ የተመሰቃቀለ እንጂ አንዳች የሚያስደስት ነገር እንደሌለው ነው፤ በተለይም በጥቅሱ ላይ እንደሚታየው የመጨረሻው ዘመን ሰዎች ከምንም በላይ ራሳቸውን የሚወዱበት ጊዜ መሆኑ ተነግሮአል፡፡ ይህ ዐይነቱ አመለካከት ቃለ ቅዱስ ወንጌልን ሙሉ በሙሉ የሚጻረር ነው፡፡

ጌታችን ለተከታዮቹ ያስተማረው “የኔ ሊሆን የሚወድ ሁሉ ራሱን ይካድ” የሚል ነው፡፡ ይህም ማለት የኋለኛው ትውልድ ራስን የሚወድ ከሆነ ጌታ የሚያዘው ደግሞ ራሱን መውደድ ሳይሆን ራስን መካድ ከሆነ ነገሩ “ሆድና ጀርባ” ሆኖአል ማለት ነው፡፡ ከዚህ አንጻር የዘመናችን ክሥተት በዚህ ፈተና ላይ ያለ እንደሆነ በግልጽ ማየት ይቻላል፡፡

ዛሬ የመንፈስ እናታቸው ብቻ ሳትሆን የማንነታቸውና የታሪካቸው ጭምር ማኅደር ከሆነች እናት ኦርቶዶክሳዊት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እያፈተለኩና እየኮበለሉ የሚገኙት በርካታ ወገኖች ራሱን ከመውደድ የተነሣ ካልሆነ በቀር ሌላ ትርጒም ሊሰጠው አይችልም፡፡

ክርስቶስ ሌላ አዲስ ክርስቲያን የፈጠረ ይመስል ክርስቲያን የሆነውን ሰው በተለያየ አባባል ወደሌላ የክርስቲያን ጎራ እንዲኮበልል መጣጣር አስኮብላይም ኮብላይም ራስን ከመውደድ የተነሣ የሚያደርጉት ነው እንጂ አንዳች የሚጨበጥ ክርስቲያናዊ ትርጒም የለውም፡፡

ራስን በመውደድ የሚታወቀው የዘመናችን ባሕርየ ሰብእ በዚህ ብቻ ሳይወሰን በትምህርትም በሐሳብም በአስተያየትም በሥራም ወዘተ የሚገለጸው ራስን ከፍ ከፍ የማድረግና የኔ ከሁሉ ይበልጣል እያሉ ሌላውን የማንኳሰስ አባዜ የሃይማኖት መዐዛ ምግባርን እየበከለው ይገኛል፡፡

ከዚህም የተነሣ የእኔ ዐውቅልሃለሁ ባይነት ዝንባሌ ሥር እየሰደደ ትሕትናና ፈሪሀ እግዚአብሔር የራቀው ትውልድ እየተበራከተ ይገኛል፡፡ ዛሬ እንደትናንቱ አበው ባሉት እንመራ፣ እንታዘዝ፣ አበውን እናዳምጥ የሚል ትውልድ ሳይሆን ከእናንተ ይልቅ እኛ እናውቃለንና እኛ የምንላችሁን ተቀበሉ በማለት ወደ ላይ አንጋጦ የሚናገር ራስ ወዳድ የሆነ መታዘዝን የሚጠላ ከሃይማኖታዊነት ይልቅ አመክንዮታዊነትን የሚያመልክ ትውልድ እየመጣ ነው፡፡ ይህ ራስ ወዳድ አስተሳሰብ የሚመነጨው ዘመኑ ካፈራው የሥነ ልቡና ፍልስፍና እንጂ ራሱን በመንፈስ ድሀ አድርጎና ሌላው ከእርሱ እንደሚሻል አድርጎ ከሚያስተምር በመንፈሰ እግዚአብሔር ከተጻፈው ከቅዱስ መጽሐፍ የመነጨ አይደለም፡፡
ቤተ ክርስቱያን ደግሞ መመሪያዋ በመንፈሰ እግዚአብሔር የተጻፈ ቅዱስ መጽሐፍ እንጂ በሰዎች ውሱን ጥበብ የተቀነባበረ ሰው ሠራሽ ፍልስፍናና ዘመን አመጣሽ ስልት አይደለም፡፡ በመሆኑም ቤተ ክርስቲያን ስትጠብቀው የኖረች ለወደፊም የምትጠብቀው በመንፈሰ እግዚአብሔር በታጀበ ጥበብና ስልት እንጂ ከፍልስፍና ብቻ በተገኘ የተውሶ ዕውቀት ሊሆን አይችልምና ሁሉም ሊያስብበት ይገባል፡፡

ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንን ለሁለት ሺሕ ዓመታት ያህል በአንድነትና በጥንካሬ ጠብቆ ያቆየ ጥበብ ኦርቶዶክሳዊና ሲኖዶሳዊ የሆነ የውሉደ ክህነት አመራር ጥበብ እንጂ የምዕራባውያንና የሉትራውያን ምክር ቤታዊና ዘመን አመጣሽ ፍልስፍና አይደለም የቤተ ክርስቲያናችን መርሕ እንደዚያ ቢሆን ኖሮ ዛሬ የምናያት አንዲት ሐዋርያዊትና ኀያል ቤተ ክርስቲያን ሳትሆን የተበታተነች የደከመችና መዐዛ ሐዋርያት የሌላትና የተለያች ቤተ ክርስቲያን ነበር የምናየው፡፡

ይሁን እንጂ አባቶቻችን ካህናት መሪዎች ሕዝቡ ተመሪ ሆኖ በአንድ የእዝ ሰንሰለት እየተደማመጠ ካህኑ ተናገረ ማለት እግዚአብሔር ተናገረ ማለት ነው በሚል ቅንና ትሕትና የተመላ ታዛዥነት እንደዚሁም በውሉደ ክህነት አመራር ሰጪነት የቤተ ክርስቲያናችን አንድነት እስከዛሬ ድረስ ተጠብቆ ቆይቷል፡፡

አሁን ግን ይህ ቀርቶ በአባቶች ላይ ተደራቢ አመራር ሰጪ በአባቶች ላይ የስድብ ናዳ አውራጅ ትውልድ መበራከቱን ካየንና ከሰማን ውለን አድረናል፡፡ ይህ ሁሉ ሲሆን ከጎናችን ሳይሆኑ ከጎናችሁ አለን የሚሉ ወገኖችም ስለ ድርጊቱ አፍራሽነት በተመለከተ አንድ ቀንስንኳ የተቃውሞ ሐሳብ አለመሰንዘራቸው በስተጀርባው እነርሱ ራሳቸው ያሉበት እንደሆነ የሚያመለክት መስሎ አሳይቶባቸዋል፡፡

አሁን ዋናው ጥያቄ ይህ ራስ ወዳድ የሆነውን አመለካከት ተቀብሎ የሚመጣውን ጥፋት ማስተናገድ ይሻላል ወይስ ራስን መካድ የሚለውን የጌታ ትምህርት አሥርጾ ነገሮች ሁሉ በንስሓ ወደነበሩበት መመለስ ምርጫው ለዚህ ዐቢይ ጉባኤ አቅርበነዋል፡፡

በሌላ በኩል ቤተ ክርስቲያናችን ያላትን መንፈሳዊና ማኅበራዊ ተልእኮ በሚገባ ለማከናወን ግልጽነታችንና ታማኝነትን በማረጋገጥ መልካም አስተዳደርን ማስፈን ለነገ የማይባል የቤተ ክርስቲያኒቱን ዐቢይ አጀንዳ ሆኖ ይገኛል፡፡ ከዚህ አኳያ የቤተ ክርስቲያናችንን ዙሪያ መለስ ምጣኔ ሀብት በሚገባ ለመያዝና ለማሳደግ እንዲሁም የሰው ኀይላችንን በአግባቡ ለመጠቀም የዘመኑን አሠራር መከተል የግድ ያስፈልገዋል፡፡

ሌላው በሀገራችን እየተመዘገበ ያለውን የልማትና የእድገት ግንባታ በአስተማማኝ ለማስቀጠል የሕዝቡን አንድነትና ሰላም ማረጋገጥ ወሳኝነት አለው ፣ ቤተ ክርስቲያናችን ከሆነ ጀምሮ የኢትዮጵያ ሕዝብ የሰላም እናት ሆና ሕዝቡን በማስተማር ያስመዘገበችው ጒልህ ታሪክ ዛሬም ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ ሁላችንም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ኀላፊነታችንን እንድንወጣ በዚህ አጋጣሚ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ ቅዱስ ጉባኤ የቤተ ክርስቲያኒቱን አንኳርና ዐበይት ጉዳዮችን በጥልቀት በመመርመርና በማጥናት ለቤተ ክርስቲያናችን ሊጠቅሙ የሚችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ጉባኤው እንዲቀጥል እያሳሰብን ዓመታዊው የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ መከፈቱን በእግዚአብሔር ስም እናበስራለን፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ ይቀድስ ሀገራችንንም ይባርክ ይቀድስ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!

በ36ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ አሰተዳደር ጉባኤ ከጥቅምት 6-9 ቀን 2010 ዓ.ም አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

መጋቤ ኵሉ ወመሴስየ ኵሉ የሆነው አምላካችን እግዚአብሔር ከያለንበት ሰብስቦ በዚህ የሠላሳ ስድስተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ተገኝተን ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ለመወያየት ስለተሰበሰብን በቅድሚያ አምላካችንን እናመሰግናለን፡፡ እናንተም እንኳን አደረሳችሁ እንኳንም በደኅና መጣችሁ እንላለን!!

“መኑ እንጋ ገብር ምእመን ወጠቢብ ዘይሠይሞ እግዚኡ ውስተ ቤቱ ከመ የሀቦሙ ሲሳዮሙ በበጊዜሁ — ምግባቸውን በየጊዜው ይሰጣቸው ዘንድ ጌታው በቤተ ሰቦዎቹ ላይ የሚሾመው ታማኝና መልካም አገልጋይ ማን ነው” (ማቴ. 24፥45)

ይህ አረፍተ ነገር ጌታ በቤተሰቡ ላይ የሚሾመውን ታማኝ አገልጋይ አስመልክቶ በትእምርተ ጥያቄ ያስተማረው ትምህርት ነው፡፡ የትምህርቱ ይዘት በጥያቄ መልክ የቀረበ እንደመሆኑ መጠን ከእያንዳንዳችን መልስ የሚያስፈልገው እንደሆነም በግልጽ ይታያል፡፡ በዚህ ትምህርት መሠረተ ሐሳብ የክርስቶስ ተከታዮች የሆኑ ምእመናን በአጠቃላይ የጌታ ቤተሰብ እንደሆኑ በሚገባ ተቀምጦአል፤ በጌታና በቤተሰቡ መካከል ያለው ግንኙነት ምን ያህል ጥብቅ እንደሆነ ሁላችንም እናውቃለን፤ ጌታ ለሚወዳቸውና ለሚያስብላቸው ቤተ ሰቦቹ እጅግ ታማኝና መልካም አገልጋይ ሲፈልግ መገኘቱ ቤተ ሰቡን እጅግ የሚወድና ለቤተሰቡ የሚቈረቈር፥ የሚያስብና የሚጠነቀቅ መሆኑን የሚያመለክት ማስረጃ ነው፡፡

በመሆኑም በጌታ በቤተ ሰቡና በአገልጋዩ መካከል ያለው ግንኙነት አስተማማኝና እጅግ በጣም ጤናማ ሆኖ እንዲቀጥል የጌታ ጽኑ ፍላጎት ነው፤ ጌታ ጥንቃቄ ማድረግ የፈለገው አገልጋዩን መሾም ላይ ነው ምክንያቱም ለቤተሰቡ የተቃና እድገትና ኑሮ ወሳኝ ሚና የሚጫወተው አገልጋዩ ነውና ነው፡፡ አገልጋዩ ታማኝና መልካም ከሆነ ቤተሰቡም በሥነ ምግባር፣ በዕውቀት፣ በጥሩ ሰብእና፣ በመልካም ኑሮ የመኖር ዕድል ይኖራቸዋል፤ አገልጋዩ ግድ የለሽና ምግባሩ ያልቀና ከሆነ ግን ቤተሰቡም በተመሳሳይ ታማኝነት የሌላቸው፣ ምግባራቸው ያልቀና፣ ለጌታቸው ሸክም የሆኑ፣ በገቡበትና በሄዱበት ሁሉ መለያየትና መናቈርን የሚወዱ፣ መልካም ሰብእና የጎደላቸው፣ ጌታቸውን ጭምር የሚያስነቅፉ፣ ወላጆቻቸውን የሚያስረግሙ ይሆናሉ፤ ጌታ ለቤተሰቡ የሚሆን መልካም ታማኝ አገልጋይ የመፈለጉና የመሾሙ ነገር በጣም ሲጠነቀቅበት የሚታየው በቤተሰቡ እንዲህ ያለው ችግር እንዳይደርስ ነው፡፡ ይህ አማናዊ የሆነ የወልደ እግዚአብሔር ክርስቶስ ትምህርት መልካምና ታማኝ የሆኑ ካህናትንና ምእመናነ ክርስቶስን በመመገብ ረገድ ያላቸው ኀላፊነት ምን ያህል ታላቅና ጥንቃቄ የሚያስፈልገው እንደሆነ የሚያሳይ ነው፤ እንደ ጌታቸን አስተምህሮ የምእመናን ሕይወት መቃናት አለመቃናት በካህናት እጅ የወደቀ ነው፤ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ጥሩ ያልሆነ ሕይወትና ሥርዐት አልበኝነት እየሰፋ ሄደ ማለት፣ ካህናት ምእመናንን በትምህርተ ወንጌል በአግባቡ መመገብ አለመቻላቸውን የሚያመለክት ነው፤ በአንጻሩ ደግሞ በቤተ ክርስቲያን ውስጥ የተስተካከለና እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ የሚኖር ሕይወት ከተስፋፋ፣ አንድነት፣ ታዛዥነት፣ ትሕትና፣ ፍጹም ፍቅርና ስምምነት መልካም ሥነ ምግባርና በሥርዐተ አበው መመራት ካለ ካህናት ምእመናኑን በሚገባ እየመገቡ መሆናቸውን የሚያስረግጥ ነው፡፡

ከዚህ አኳያ በቤተ ክርስቲያናችን ውሰጥ በአሁኑ ጊዜ እየተስተዋለ ያለው ከሁለቱ የትኛው ነው የሚለውን መገምገሙ ብልህነት እንጂ ሌላ ሊሆን አይችልም፤ ሥራን ገምግሞ ለንሥሓ መዘጋጀትና ለተሻለ ሥራ እንደገና መነሣት የእግዚአብሔር ፈቃድና የጻድቃን ምርጥ የሕይወት ጒዞ ነው፤ ስለዚህ እኛም የተሻለ የምእመናን ምግብና ልናሰፍን የምንጥር ከሆነ ከወቅቱ ተጨባጭ ሁኔታ በመነሣት ያለውን እውነታ ገምግመን ማወቅ በቅድሚያ ያስፈልጋል፤ ከዚያም ቀጥለን ክፍተቶቻችንን በመዝጋት፣ ዐቅዶና አልሞ በአዲስ መንፈስ በመሥራት ውጤትን ማስመዝገብ የግድ ይላል፡፡

ልዩ ልዩ የቊጥር ዘገባዎችና መረጃዎች እንደሚያሳዩት በአሁኑ ጊዜ በመካከለኛውና በደቡቡ የሀገራችን ክፍል የሚገኙ ምእመናን በቂ የካህናት ምግብና ባለማግኘታቸው በተኵላዎች በከፍተኛ ደረጃ እየተነጠቁ መሆናቸውን ነው፤ እንደዚህ ያለው ክሥተት ገዝፎ በሚታይበት በአሁኑ ጊዜ የካህናት አገልግሎት በታማኝነትና በመልካም ሁኔታ እየተከናወነ ነው ብለን የምናስብ ከሆነ ሌላውን ሳይሆን ራስን ማታለል ነው የሚሆነው፤ በሌላ በኩል መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “መንጋው አንድ እረኛው አንድ” ብሎ የመሠረታት አበው ሠለስቱ ምእትም “በአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን እናምናለን” ብለው ያጸኗትን የአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን አንድነት ለመከፋፈልና ለማዳከም በውስጥም በውጭም የሚሯሯጡ ቢጽ ሐሳውያን እየተበራከቱ መምጣታቸው በግልጽ እየታየ ነው፤ የእነዚህ ሁሉ ድምር ውጤት ዞሮ ዞሮ የካህናት ምግብና እጥረት ከመሆን አያልፍም፡፡

እውነቱን እንናገር ከተባለ እነዚህ ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችን ወልዳ ስመ ክርስትናም ሰጥታ ያሳደገቻቸው በካህናት እጅ የነበሩ ምእመናን ልጆቿ ናቸው፤ ይህ የማንክደው ሐቅ ነው፤ ነገር ግን የእኛ የካህናት እጅ አጥብቆ መያዝና መመገብ ባለመቻሉ ሌላው ከእጃችን ፈልቅቆ ወሰዳቸው፤ በእጃችን አሉ የምንላቸውም ቢሆኑ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሥርዐት በቅጡ በአእምሮአቸው ውስጥ ማሥረጽ ባለመቻሉ በጥቂት አፈ ጮሌዎች፣ አታላዮችና አስመሳዮች ግራ ተጋብተው የሚይዙትና የሚጨብጡት ጠፍቶቸአው የሚባዝኑ ብዙ ሆነው ይታያሉ፤ ይህ ለምን ሆነ ብሎ መጠየቅ የወቅቱ አንገብጋቢ ጥያቄ ነው፤ ይህ ጥያቄ በአፋጣኝ መልስ ማግኝት አለበት፤ መልሱ የመልካምና የታማኝ አገልጋይ ካህን ህልውና ማረጋገጥ ነው፤ መቼም አገልጋይ ማለት ካህን ማለት እንደሆነ፣ ካህን ማለት ደግሞ ከፓትርያርኩ ጀምሮ እስከ ዲያቆኑ ድረስ የሚዘልቅ የወል ስም እንደሆነ አንስተውም፤ ይህም ከሆነ ያጋጠመንን ክፍተት ለመዝጋት ከሁሉ በላይ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያንና ለምእመናንዋ ጥብቅና ብቻ የቆመ ካህን ያሰፈልገናል ማለት ነው ፤ በተለያዩ ስሑታን ቤተ ክርስቲያን ስትከፋፈልና አዛዥዋ ሲበዛ ዝም ብሎ የሚመለከት፤ ከዚያም አልፎ የሚደግፍ ካህን በምንም መመዘኛ ታማኝና መልካም አገልጋይ ሊሆን አይችልም፤ መጋቢ ሆኖ ምእመናንን ማስተዳደርም አይችልም፡፡

ሁላችንም ውሉደ ክህነት ጌታችን በቤተሰቡ ላይ የሾመን ነን በመሆኑም ከተሰጡን መንጎች አንዱ ስንኳ እንዳይጠፋ ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን ማእከል አድርገን በተሳሳተ መንገድ እየተጓዙ ቤተ ክርስቲያንን ለመከፋፍል የሚከጅሉ ልጆቻችንን አንድ ላይ ሆነን ተዉ ንሥሓ ግቡ፣ ታዘዙ፣ የቤተ ክርስቲያንን አንድነትና ሥርዐት ጠብቃችሁ በአበው እግር ዋሉ እንበላቸው፤ ይህ ሲሆን መልካምና ታማኝ እረኛ መሆናችንን እናረጋግጣለን፤ አንዲት ኀያልና ጠንካራ ቤተ ክርስቲያንም ትኖረናለች፤ ይህ ሲሆን የጋራ ጠላት የሆነውን የውጭ ባለጋራ ለመመከት ለምንም ለምን የማይበገር ዐቅም እንፈጥራለን፤ እኛ አንድ ስንሆን እግዚአብሔር ከእኛ ጋር ይሆናል፤ ኀይላችንም የበረታ ይሆናል፡፡

በመጨሻም፡ የሠላሳ ስድስተኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዙሪያ በሰፊው በመወያየት ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ህልውና እና ሉዓላዊ ሥርዐት መከበር በአንድነት እንዲቆም አባታዊና መንፈሳዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡እግዚአብሔር የቤተ ክርስቲያናችንን አንድነት ይጠብቅ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን በማለት መልእክታቸውን ያጠናቀቁ ቅዱስነታቸው የ36ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በዚህ ዙሪያ የተሟላ ግንዛቤ ወስዶ ለአንዲት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ህልውና እና ሉዓላዊ ሥርዐት መከበር በአንድነት እንዲቆም አባታዊና መንፈሳዊ መልእክታቸውን አጠቃልለዋል፡፡