ግንቦት 2 ቀን 2009 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

“ወይእዜኒ ዕቀቡ ርእሰክሙ ወኵሎ መራዕየ ዘሀሎ ኀቤክሙ፤ አሁንም ራሳችሁንና በእናንተ ሥር ያለውን መንጋ ሁሉ ጠብቁ፤”(የሐዋ.ሥራ 20፡28)

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

መዋዕለ ጾሙን በሰላም አስፈጽሞና ከበዓለ ትንሣኤው አድርሶ፣እንደዚሁም ሁላችንን ከየሀገረ ስብከታችን አሰባስቦ በዚህ ዓመታዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ በአንድነት ስለሰበሰበን እግዚአብሔር አምላካችን ስሙ የተመሰገነ ይሁን፤ እናንተም እንኳን ደኅና መጣችሁ፡፡

ከላይ የተጠቀሰው ኀይለ ቃል የመንጋው እረኞች የሆን ሁሉ በቃለ እግዚአብሔር ጎልብተን በመንፈስ ቅዱስ ኀይል ተቃኝተን ራሳችንንና ምእመናንን እንዴት መጠበቅ እንዳለብን የሚያመለክት የእግዚአብሔር ታላቅ የጥሪ ቃል ነው፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትና፣ ቀደምት ቅዱሳን አበው የሥልጣነ ክህነትና የመንበረ ሐዋርያት ወራሽ የሆነው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ በቋሚነትና በመደበኛነት እንደዚሁም ለቤተ ክርስቲያን ጉዳይ አስፈላጊ ሆኖ በተገኘ ጊዜ ሁሉ እየተሰበሰበ የቤተ ክርስቲያንን ጉዳይ እንዲገመግም፣ እንዲያጠና እና መፍትሔ እንዲሰጥ መደንገጋቸው ያለምክንያት አልነበረም፡፡

የጉባኤው መሠረታዊ ዓላማ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶሰ አስቀድሞ እንደተናገረው ከመጀመሪያ አንሥቶ ልዩ ልዩ ፈተና ተለይቶአት የማያውቅ ቤተ ክርስቲያን በመከራው ጽናት ተሠቅቃ ወይም ተስፋ ቈርጣ ዓላማዋን እንዳትስት እስከ ሕይወት መሥዋዕትነት ሊዘልቅ የሚችል ጥብቅ ክትትልና ጥበቃ ለማድረግ እንዲቻል ነው፡፡ ይህም በመሆኑ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ አማካኝነት ነገራተ ቤተ ክርስቲያንን በጥልቀትና በአስተዋይነት እየተረጐመች፣ እንደዚሁም መንፈስ ቅዱስን መሪ በማድረግና አስፈላጊው መሥዋዕትነትን እየከፈለች፣ በመክፈል ከውጭና ከውስጥ የሚሰነዘሩባትን ጥቃቶችን እየተቋቋመች እነሆ በአሸናፊነት ከዘመናችን ደርሳለች፡፡

ይህም ሊሆን የቻለው በመንፈስ ቅዱስ ኀይል የተቃኙ ቅዱሳን አበው በፈጸሙት ተጋደሎና ወደር የለሽ መሥዋዕትነት እንደሆነ አይዘነጋም፡፡ የመንፈሳዊ ጥበቃና ክትትል ተግባር በቤተ ክርስቲያናችን ሥርዐተ ቀኖና መሠረት በቤተሰብ ደረጃ በነፍስ ወከፍ ጠባቂ ካህን ወይም የነፍስ አባት እንዲኖር የተደረገበት ዐቢይ ምክንያትም የጥበቃውና የክትትሉ ተግባር አስተማማኘና ዘላቂ ለማድረግ ነው፡፡ የተግባሩ መነሻም የጌታችን ትምህርትና ትእዛዝ ነው፡፡

እኛ የቤተ ክርስቲያን መሪዎችና አገልጋዮች ሕፃኑንም ወጣቱንም ጎልማሳውና ሽማግሌውንም አንድ አድርገን እንድንጠብቅና እንድናሰማራ ጌታችን በባሕረ ጥብርያዶስ ግልገሎቼን ጠብቅ፣ ጠቦቶቼን ጠብቅ፣ በጎቼን ጠብቅ፤ በማለት ለቅዱስ ጴጥሮስ በሰጠው ትእዛዝ መሠረት አዞናል፤ (ዮሐ. 21፥15-17)፡፡ እኛም ትእዛዙንና ኀላፊነቱንም ወደንና ፈቅደን ተቀብለናል፡፡ ከበዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን የሚካሄደውና ርክበ ካህናት ተብሎ የሚታወቀው በዛሬው ዕለት የምንጀምረው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤም መሠረቱ ይህ የባሕረ ጥብርያዶስ የጥበቃ ትእዛዝና ትምህርት እንደሆነ ይታወቃል፡፡

የቤተ ክርስቲያን ዐቢይ እና ዋና ተልእኮም ዐቂበ ምእመናን እንደሆነ በቅዱስ ወንጌል በተደጋጋሚ ተጽፏል፡፡ በመሆኑም ቅዱሳን ሐዋርያትም ሆኑ ቅዱሳን አበው ዋነኛ ተግባራቸው ምእመናንን ማስተማር፣ ማሳመን፣ ማጥመቅ፣ ምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያንን ማደል፣ ከዚያም ምእመናንን በዕለት ተዕለት ኑሮአቸው መጠበቅና ክትትል ማድረግ ነበር፡፡

ሐዋርያዊት፣ ህልውተ ኵሉ፣ ወይም በሁሉም ያለች፣ አንዲትና ቅድስት የሆነችው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በረጅሙ የሁለት ሺሕ ዘመናት ጒዞዋ፣ አንድነቷ ሳይናጋ፣ ሐዋርያዊ ተልእኮዋ ሳይቋረጥ ለዘመናት የዘለቀችው ካህናት በነፍስ አባትነት እያንዳንዱን ቤተሰብ በመጠበቃቸው በማስተማራቸውና በመከታተላቸው ነው፡፡

ዛሬም ቢሆን እየተስፋፋ ለመጣው የምእመናን ቅሰጣ ዋና መከላከያው የነፍስ አባትን ተልእኮ ማእከል ያደረገ በቤተሰብ ውስጥ የነፍስ ወከፍ ጥበቃ ሲጠናከር ብቻ እንደሆነ ግንዛቤ ሊወሰድበት ይገባል፡፡ ይህንን የግብረ ኖሎት ሥራ በተፈለገው መጠን ግቡን እንዲመታ በየሀገረ ስብከቱ የካህናት ማሠልጠኛ በማቋቋም፣ ዘመኑን ያገናዘበና በቀላሉ ወደ ተግባር የሚያሻግር የሥልጠና መርሐ ግብር በመንደፍ ካህናቱን ከዳር እስከ ዳር በማነቃነቅ፣ አስተማማኝ ጥበቃ ማረጋገጥ ይኖርብናል፤ ይህንን ተግባር ለማፋጠን የሊቃነ ጳጳሳት ፈቃደኝነትና ተነሳሽነት ከፍተኛውን ድርሻ ይወስዳል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ ዛሬም ለሃይማኖቱ ተቀርቋሪ የሆነ፣ ለእምነቱ አድርግ የተባለውን የሚያደርግ ሕዝብ እግዚአብሔር አልነሳንም፤ በእኛ በኩል ግን የሚቀር ብዙ ሥራ እንዳለ አይካድም፤ ከዚህ አንጻር እየተፈታተነን ያለው የቅን አገልግሎትና የመልካም አስተዳደር ክፍተት በፍጥነት አስተካክለን ወደ ሕዝቡ የጥበቃ ተግባር መሰማራት ወቅቱ የሚጠይቀው ተግባር መሆኑን ማስተዋል አለብን፤ አሁን ባለው የጥበቃና የክትትል ክፍተት ቊጥሩ በርከት ያለ ወጣት እየኮበለለ እንደሆነ ማወቅ አለብን፤ አለሁ የሚለው ወጣትም ቢሆን ኦርቶዶክሳዊ መርሕና ቀኖና በቅጡ ባለማወቁ ሲደናገርና የተቃራኒ አካላት ባህልና ሥርዐትን ሲደበላልቅ ይታያል፤ ይህ ሁሉ ሊሆን የቻለው ጌታችን እንዳስተማረንና እንዳዘዘን ከግልገልነት ዕድሜ ጀምረን ወጣቱን ባለመጠበቃችንና ባለመከታተላችን እንደሆነ ሊሠመርበት ይገባል፡፡

በቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጪነትና የበላይ ተቈጣጣሪነት የሚመራው የግብረ ኖሎት ጥበቃ የምእመናንን ሁለንተናዊ ሕይወት የሚያካልል ሊሆን ይገባል፡፡ ምእመናን ለሃይማኖታቸው የሚታመኑ፣ ለሀገራቸው ዕድገትና ልማት የሚቈረቈሩ፣ በአንድነት፣ በስምምነትና በፍቅር የመኖር ጥቅምን የሚገነዘቡ፣ በማንነታቸውና በባህላቸው፣ በታሪካቸውና በእምነታቸው የሚኮሩ፣ በአጠቃላይ የተስተካከለ መንፈሳዊና ሥነ ልቡናዊ ሰብእና የተላበሱ እንዲሆኑ በርትተን የማስተማር፣ የመጠበቅና የመከታተል ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ኀላፊነት አለብን፤ ይህም በታቀደ፣ በተደራጀ፣ በተጠናከረና ተከታታይነት ባለው የአፈጻጸም ስልት ሊከናወን ይገባል፡፡

በመጨረሻም፡ በዚህ ዓመታዊና ቀኖናዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የቀረቡትን አጀንዳዎች ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት በማስተዋልና ለቤተ ክርስቲያናችን በሚበጅ መልኩ በማጤን፣ እንደዚሁም ለቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ህልውና መጠበቅ የሚያስችሉ ውሳኔዎችን በማሳለፍ ሐዋርያዊ ግዳጁን እንዲወጣ እያሳሰብን የሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት የርክበ ካህናት ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዛሬው ዕለት መጀመሩን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር አምላካችን የተባረከና የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡