የካቲት 12 ቀን 2009 ዓ.ም የዐቢይ ጾም መግቢያ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገር ውስጥና በመላው ክፍላተ ዓለም የምትገኙ የእግዚአብሔር ቤተሰቦች ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት በሙሉ፤

ፍጥረቱን በምሕረት፣ በይቅርታና በርኅራኄ የሚጠብቅ፣ የሚመግብና የሚያስተዳድር፣ ከሁሉ በላይ የሆነ ኀያሉ አምላካችን እግዚአብሔር እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት መዋዕለ ጾም ዐቢይ በሰላም አደረሳችሁ።

“ቅረቡ ኀቤሁ ወያበርህ ለክሙ፣ ወኢይትኀፈር ገጽክሙ
ወደ እርሱ ቅረቡ ያበራላችኋልም፤ ፊታችሁም አያፍርም”፡፡”
(መዝ. 34፥5)

የሰው ልጅ ከአራቱ ባሕርያተ ፍጥረት በተገኘ ሥጋዊ ሕይወቱ፣ የአራቱ ባሕርያት ውጤት የሆኑትን ማለትም እህልን ውኃን፣ ነፋስንና እሳትን የመሻት ፍላጎቱ የላቀ እንደሆነ ሁሉ፣ ከእግዚአብሔር በተገኘ መንፈሳዊ ሕይወቱም እግዚአብሔርን የመሻት ፍላጎቱ ከፍተኛ ነው፤ ከእግዚአብሔር የተገኘው ይህ ሀብተ ተፈጥሮ ከሰው ባሕርይ መለየት የማይቻል በመሆኑ ሰብኣዊ ፍጡር ሁሉ ከፈጣሪው ጋር ግንኙነት ለማድረግ ይጓጓል፡፡

ሰው ወደ ፈጣሪው ለመቅረብ ከሚፈልገው በላይ፣ ፈጣሪም ሰውን በእጅጉ ሊቀርበውና ማደርያው ሊያደርገው ይፈልጋል፤ በመሆኑም ሁለቱም ተፈላላጊ መሆናቸውን በሕገ ተፈጥሮም ሆነ በቅዱስ መጽሐፍ የታወቀ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሁለቱም እንዳይቀራረቡ የሚያደርጉ መሠረታውያን ነገሮች እንዳሉ ሁሉ እንዲቀራረቡ የሚያደርጓቸውም አሉ፤ ሁለቱንም ሊያቀራርቡ ከሚችሉት መካከል አንዱ ጾም ነው፡፡ እግዚአብሔር በሁለመናው ንጹሕ ቅዱስ ፍጹምና ክቡር በመሆኑ ለባሕርዩ ከማይስማሙ ድርጊቶችና ከአድራጊዎቻቸው ጋር ግንኙነት ሊያደርግ አይፈቅድም፤ ሆኖም ንስሓ ሲገቡና ጥፋታቸውን አምነው ሲፀፀቱ በይቅርታ የሚቀበል ርኅሩኅ መሓሪና ይቅር ባይ አምላክ ነው፤ ከዚህ አኳያ በሰውና በእግዚአብሔር መካከል የሚፈጠረውን ክፍተት ለማጥበብ ብሎም ለመዝጋት ንስሓ ጾምና ጸሎት ቊልፍ መሣሪዎች ናቸው፤ እኛ ክርስቲያኖችም ጾምን የምንጾምበት ዋና ምክንያት ይኸው ነው፡፡

ወደ እግዚአብሔር ለመቅረብ መንፈሳዊ ኀይል ያስፈልጋል፤ መንፈሳዊ ኀይል የሚገኘው ደግሞ ሥጋዊ ኀይል ሲገታ ነው፡፡ ጾም ይህንን በማድረግ ከፍተኛ ሚና ይጫወታል፡፡ ጾም ኀይለ ሥጋን በመግራት ኀይለ መንፈስ እንዲበረታ ያደርጋል፣ ጾም ራሳችንን ዝቅ አድርገን ለእግዚአብሔር እንድንገዛና ለቃሉ ታዛዥ እንድንሆን ያስችለናል፤ ጾም ሰከን ብለን ስለበደላችን እንድናስብና ለንስሓ እንድንፈጥን ያደርገናል፣ ጾም የእግዚአብሔርን ቸርነት በማሰብ ፍቅሩን እንድናውቅና እንድናመልከው፣ ለሰውም ጥሩ የሆነውን ብቻ እንድናስብ ያደርገናል፡፡ እነዚህ ነገሮች በሕይወታችን ውስጥ ሥርጸት ሲያገኙ ወደ እግዚአብሔር የመቅረቡና የመገናኘቱ ዕድል ሰፊ ይሆናል፡፡ በዚህ ሕይወት ውስጥ ሆነን ስለምንሻው ነገር እግዚአብሔርን ብንጠይቅ መልሱ ፈጣን ይሆናል፤ ከዚህ አንጻር የነነዌ ጾም ያስገኘው ፈጣን መልስ ማስረጃችን ነው፤ በጾም ኀይል አማካኝነት ከፈጣሪ ጋር የተገናኙ እነ ሊቀ ነቢያት ሙሴ፣ ነቢዩ ዳንኤልና ዕዝራም በዚህ ተጠቃሽ መምህሮቻችን ናቸው፡፡ ርኵስ መንፈስን ድል ለማድረግ፣ ሊጀመር የታሰበውን ዐቢይ ተግባር በስኬት ለማጠናቀቅ በጾም ረድኤተ እግዚአብሔርን መጠየቅ አስፈላጊ መሆኑን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተገባርና በትምህርት አሳይቶናል፡፡ ቅዱሳን ሐዋርያትም ይህንን በተግባርና በትምህርት ፈጽመውታል፤ ከዚህ አኳያ ጾምና ሃይማኖት የማይለያዩ የአንድ ሣንቲም ሁለት ገጽታዎች መሆናቸውን መገንዘብ አያዳግትም፡፡ በመሆኑም ጾም ራሳችንን ለመቈጣጠር፣ የእግዚአብሔር ታዛዥ ለመሆን፤ ለጥያቄአችን ፈጣን መልስ ለማግኘት፤ ርኵስ መንፈስን ድል ለማድረግ፤ ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት የሚያገለግለን ሃይማኖታዊና መንፈሳዊ መሣሪያ ነው፡፡

የጾም አስፈላጊነትና ውጤታማነት ከጥንት ጀምሮ በነቢያትና በሐዋርያት የታወቀ፣ ከሁሉ በላይ ደግሞ እግዚአብሔር ራሱ “በፍጹም ልባችሁ፣ በጾም፣ በልቅሶና በዋይታ ወደ እኔ ተመለሱ፣ ልባችሁን እንጂ ልብሳችሁን አትቅደዱ፤ አምላካችሁ እግዚአብሔር ቸርና መሓሪ ነው፤ ቊጣው የዘገየ ምሕረቱ የበዛ ለክፋትም የተፀፀተ ነውና ወደ እርሱ ተመለሱ፤ በጽዮን መለከትን ንፉ፤ ጾምንም ቀድሱ (ለዩ) ጉባኤውንም አውጁ፤ ሕዝቡንም አከማቹ፤ ማኅበሩንም ቀድሱ” ብሎ ጾምን በአዋጅ እንድንጾም አዞናል (ኢዩ. 2፥12-18)፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስም ርኵስ መንፈስ ሊሸነፍና ድል ሊሆን የሚችለው በጾምና በጸሎት እንደሆነ አስረግጦ አስተምሮናል፤(ማቴ. 17፥14-21) ይሁንና ጾም በእግዚአብሔር ዘንድ ዋጋም፣ መልስም፣ ኀይልም ሊያሰጥ የሚችለው እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ ማለትም እግዚአብሔር ባዘዘው ትእዛዝ መሠረት ሲከናወን መሆኑን መገንዘብ ያስፈልጋል፤ እግዚአብሔር የሚፈልገው ጾም እንዴት ያለ እንደሆነ እርሱ ራሱ እንዲህ ብሎናል “እኔ የመረጥሁት ጾም ይህ አይደለምን? የበደልን እስራት ትፈቱ ዘንድ፣ የቀንበርን ጠፍር ትለቁ ዘንድ፣ የተገፉትን አርነት ትሰዱ ዘንድ፣ ቀንበሩን ሁሉ ትሰብሩ ዘንድ አይደለምን ? እንጀራህን ለተራበ ትቈርስ ዘንድ፣ ስደተኞቹ ድሆችን ወደቤትህ ታገባ ዘንድ፣ የተራቈተውን ብታይ ታለብሰው ዘንድ፣ ከሥጋ ዘመድህ እንዳትሸሸግ አይደለምን? የዚያን ጊዜ ብርሃንህ እንደ ንጋት ያበራል ፈውስህም ፈጥኖ ይበቅላል፤ ጽድቅህም በፊትህ ይሄዳል፤ የእግዚአብሔርም ክብር በላይህ ሆኖ ይጠብቅሃል” ብሎ ፈቃዱን ነግሮናል፡፡ (ኢሳ. 58፥6-8)

የጾም ዐቢይ ዐላማ ለእግዚአብሔር የሚታዘዝና የተሰበረን ልብ መፍጠር፣ በጾም በጸሎት በንስሓ በስግደት በተመሰጦ፣ በአንቃዕድዎ ለእርሱ መታዘዝና መገዛት እርሱንም ማምለክ ነው፡፡ ከዚህም ጋር ጥልን በይቅርታ ማስወገድ፣ ሰላምን በማረጋገጥ ፍቅረ ቢጽን ገንዘብ ማድረግ፣ ራስን መቈጣጠርና መግዛት፣ ኀይለ ሥጋን መመከት፣ ኀይለ ነፍስን ማጎልበት፣ የእግዚአብሔርን እንጂ የሰውን አለማየት፣ የርኩሳን መናፍስትን ግፊት በመቋቋም ክፉ ምኞትን ድል ማድረግ፣ ቅዱስ ቊርባንን መቀበል፤ ኅሊናን ለእግዚአብሔር መስጠት፣ ያለንን ለነዳያን ከፍለን መመጽወት የመሳሰሉትን ሁሉ ዕለታዊ ተግባራችን በማድረግ ጾሙን ልንጾም ይገባል፡፡

በመጨረሻም፡ የጾም ዋና ዐላማ ለእግዚአብሔር መታዘዝ እንደ መሆኑ መጠን ምድርን እንድናበጃትና እንድናለማት ያዘዘንን ትእዛዝ ተቀብለን አካቢያችንን በማልማት ሀገራችንን ውብና ለኑሮ የተመቸች በማድረግ እንደዚሁም ከኀጢአት መከላከያዎች መካከል ዋናውና አንዱ ያለ ዕረፍት በሥራ መጠመድ ነውና ሕዝቡ ሥራ ሳይፈታ ፈጣሪውን በጾም እያመለከ፣ የተቸገረ ወገኑን ካለው ከፍሎ እየረዳ፣ ልማትንም እያፋጠነ የሀገሩን ሰላምና ፀጥታ እየጠበቀ መዋዕለ ጾሙን እንዲያሳልፍ በእግዚአብሔር ስም መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

ወርኀ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፣ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡