ጥር 11 ቀን 2009 ዓ.ም. በበዓለ ጥምቀት የተላለፈ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር ሆናችሁ ይህንን ታላቅ በዓል በማክበር ላይ የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፤

በተጠምቆቱ ለዳግም ልደትና ለሐዲስ ሥርዐት ያበቃን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ጥምቀቱ አደረሳችሁ።

“ወይርአይ ኵሉ ዘነፍስ አድኅኖቶ ለእግዚአብሔር
ነፍስ ሁሉ የእግዚአብሔርን ማዳን ይይ።”
(ሉቃ. 3፥6)

ከዚህ ሕያው ቃል መገንዘብ እንደሚቻለው ዓለም ወይም ሥጋ የለበሰ ነፍስ ሁሉ በጽኑ ደዌ ኀጢአት ተይዞ እንደነበረ ነው፣ ያ ባይሆን ኖሮ ስለ መዳን ማንሣቱ ወይም ማውራቱ ተገቢ አይሆንም ነበርና ነው፡፡ በቅዱስ መጽሐፍ በስፋት ተጽፎ እንደምናገኘው፣ በቅዱስ ትውፊትም እንደተረዳነው፣ ከመጀመሪያው ሰው ከአዳም ጀምሮ እስከ ዘመነ ክርስቶስ ድረስ በኀጢአተ-አዳም ምክንያት ደዌ ኀጢአት ሥጋ በለበሰ ሁሉ ላይ ተሰራጭቶአል፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን እውነታ ሲያረጋግጥ እንዲህ ይላል፡- “ሁሉም ኀጢአትን ሠርተዋልና የእግዚአብሔር ክብር ጐድሎአቸዋል” (ሮሜ 3፥23)፡፡

የኀጢአትም ደመወዝ ሞት በመሆኑ በተሰራጨው ደዌ ኀጢአት ምክንያት ሞት በሰው ሁሉ ላይ እንደተዳረሰ ለማንም ግልጽ ነው (ሮሜ 6፥23፤ 5፥12)፡፡ በመሆኑም ከቀዳማዊ አዳም ጀምሮ እስከ ዳግማዊ አዳም እስከ ክርስቶስ ድረስ የሰው ልጅ በአጠቃላይ በኀጢአት፣ በሞትና በመቃብር ቊጥጥር ሥር ዋለ፡፡ ያ ዘመን የሰው ልጅ ስቃይና መከራ የተሞላ ሕይወትን ያሳለፈበት መራራ ዘመን በመሆኑ፣ ዓመተ ፍዳ፣ ዓመተ መርገም፣ ዓመተ ኵነኔ ተብሎ ተሰይሞአል (ሮሜ 5፥12-21)፡፡ ይሁን እንጂ በዚህ ድቅድቅ የጨለማ ዘመንም ቢሆን፣ መሓሪውና ርኅሩኁ አምላካችን እግዚአብሔር የመዳን ተስፋ እንደሚመጣ በቅዱሳን ነቢያት አማካኝነት ተስፋውን በተደጋጋሚ ይገልጽ ነበር፡፡ በተለይም የሞትና የመቃብር ዋና መልእክተኛ ሆኖ ሰውን ሁሉ ለከባድ ጕዳት የዳረገው ደዌ ኀጢአት በጥምቀተ ማይና በልደተ መንፈስ እንደሚወገድ እግዚአብሔር በሚከተለው አገላለጽ አስታውቆ ነበር፡፡ እንዲህ ብሎ “እነዝኀክሙ በማይ ንጹሕ ወትነጽሑ እምርኵሰክሙ፤ በንጹሕ ውኃ እረጫችኋለሁ ከርኵሰታችሁም ትነፃላችሁ”፤ (ሕዝ. 36፥25)፤ “ወእሰውጥ መንፈስየ ዲበ ኵሉ ዘሥጋ፤ መንፈሴን በሥጋ ለባሽ ሁሉ ላይ አፈስሳለሁ” (ኢዩ. 2፥28)፡፡ ኀጢአት ወንድ ሴት፣ ሕፃን ሽማግሌ፣ ቀለም ዘር ሳይለይ የሰው ዘር የሆነውን ሁሉ በጅምላ ያሰቃየ ክፉ በሽታ ቢሆንም፣ ከጊዜ በኋላ አስተማማኝ የሆነ መድኀኒት እንደሚገኝለት ተስፋውን በዚህ ሁኔታ ሲገልጽ የቆየው መሓሪው አባታችን እግዚአብሔር አምላክ በመድኀኒትነቱ ይፈውሰን ዘንድ፣ የባህሕርይ ልጁ የሆነውን ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስን በሥጋ-ሰብእ ወደ እኛ ላከው፡፡ ጌታችንም ወደኛ መጥቶ በሰው ፈንታ ለሰው ሁሉ ቤዛ ሆኖ በመሞት የድኅነት በሩን ከፈተልን፡፡

ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁንና ዛሬ የመዳን ዘመን ሆኖልናል፡፡ ዘመናችን በሃይማኖት፣ በንስሐና በጥምቀት ምሕረት በገፍ የሚታፈስበት ስለሆነ “ ዓመተ ምሕረት፣ መዋዕለ ንስሓ፣ ዘመነ ሥጋዌ” እየተባለ ይጠራል፤ ዛሬ ደዌ ኀጢአትን በሃይማኖት፣ በንስሓና በጥምቀት ማስወገድ ይቻላል፡፡ ታዲያ ይህ ሁሉ የሆነው የእግዚአብሔር የማዳን ኀይል በሆነው በጌታችን በኢየሱስ ክርስቶስ ነውና ሰው ሁሉ ይህንን የማዳን ኀይል እንዲመለከትና እንዲፈወስ የእግዚአብሔር መንግሥት ማእከል የሆነች ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ዛሬም እመኑ፣ ንስሓም ግቡ፣ መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና እያለች ድምፅዋን ከፍ አድርጋ ትጣራለች፡፡ የጥምቀተ ክርስቶስን በዓል የምናከብርበት ዐቢይ ምክንያት ይህንን የመዳን ጥሪ በማስተጋባት ሰውን ከደዌ ኀጢአት ለማዳን ነው፡፡ በዓለ ጥምቀትን ስናከብር እግዚአብሔር ወልድ በፈለገ ዮርዳኖስ ሲጠመቅ፣ እግዚአብሔር መንፈስ ቅዱስ በርግብ አምሳል ሲወርድ፣ እግዚአብሔር አብ በደመና ሆኖ ድምፁን ሲያሰማ፣ እግዚአብሔር በአካል ሦስት በባሕርይና በህልውና አንድ መሆኑን እናውቃለን፡፡ በዓለ ጥምቀትን ስናከብር አብ በደመና ሆኖ “ይህ የምወደው ልጄ ነው ብሎ ሲመሰክር፣ መንፈስ ቅዱስም በርግብ አምሳል በክርስቶስ ላይ ሲቀመጥ አይተን፣ በዚሁ ጥምቀተ ክርስትና ከደዌ ኀጢአት ድነን የእግዚአብሔር ልጆች፣ የመንፈስ ቅዱስ ማደሪዎች የመሆን ትልቅ ጸጋ የምንቀዳጅ መሆናችንን እንገነዘባለን፡፡

በዓለ ጥምቀትን ስናከብር “ሰማያት ሲከፈቱ ተመልክተን ጥንት በግብረ ኀጢአት መነሻነት ከገነተ ተድላ የተባረርን እኛ፣ ጌታችን በእኛ ፈንታ ቤዛ ሆኖ በከፈለልን መሥዋዕትነት ምክንያት፣ ከምሥጢረ ጥምቀት ከምናገኘው ጸጋ የተነሣ ከኀጢአት ነጽተን የእግዚአብሔር ልጆችና የመንፈስ ቅዱስ ማደሪያዎች ስንሆን፣ መንግሥተ ሰማያት ለእኛ ክፍት መሆኗን እናስተውላለን፡፡ በዓለ ጥምቀት ይህን ሁሉ የመዳን ጸጋና ምሥጢር የምንማርበትና የምናውቅበት፣ እንደዚሁም በሃይማኖት፣ በንስሓና በጥምቀት የመዳን ቍልፉን እጅ የምናደርግበት ልዩ፣ ታላቅና ቅዱስ በዓል በመሆኑ በታላቅ ድምቀት ማክበራችን ተገቢ ብቻ ሳይሆን ከተገቢም በላይ ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ መጥምቅ ከእግዚአብሔር ተልኮ እንደነገረን ይህንን ታላቅ በዓል ከላይ የተገለጸውን የእግዚአብሔር የማዳን ኀይል ብቻ በመመልከት በዓሉን ማክበር አለብን፡፡ በሌላ በኩል በዓለ ጥምቀትን ስናከብር ማየት ያለብን የመዳን ገጽታውን ብቻ አይደለም፤ በማኅበራዊ ገጽታውም ትልቅ ፋይዳ ያለው በዓል እንደሆነ ማስተዋል አለብን፡፡ በዓሉ ዛሬ የሀገራችንም ሆነ የዓለማችን የልማት ዕንቅፋት እንደሆነ በስፋት የሚነገርለት የራስ ያልሆነውን ሀብት በተለያየ መንገድ የራስ ለማድረግ የሚደረገውን አዝማሚያ በመቃወም “በማንም ላይ ግፍ አትሥሩ፤ ደመወዛችሁ ይብቃችሁ፤ ከታዘዘላችሁ በላይ አብዝታችሁ አትውሰዱ” ብሎ የሚያስተምር ስለሆነ ሙስናን ከሁሉ ቀደሞ ያወገዘ በዓል ነው፡፡ ይህ በዓል ሁሉም ተጋግዞ፣ ተረዳድቶና ተዛዝኖ በሰላም፣ በፍቅር፣ በስምምነት፣ በአንድነት፣ በእኩልነት፣ በመከባበርና በመተማመን ይኖር ዘንድ “ሁለት ልብስ ያለው ለሌለው ያካፍል፤ ምግብ ያለውም እንዲሁ ለሌለው ያካፍል፤ ማንም ሰው ወገኑን በሐሰት አይክሰስ፤” በማለት መጨካከንን ያስቀረ በዓል ነው፡፡ የእገሌ ልጆች ነን እያሉ አባትን በመጥራትና የዘር ሐረግን በመምዘዝ መመካትን ያወገዘ፤ ይልቁንም ከዚህ በተለየ መልኩ መልካም የሥራ ፍሬን በማሳየት የሃይማኖትና የሥራ ታታሪ መሆንን የሚያስተምር ልማታዊ በዓል ነው (ሉቃ. 3፥8-14)፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የበዓለ ጥምቀትን አከባበር ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ አስተምህሮን አጒልቶ ሊያሳይ በሚያስችል መልኩ በየጎዳናው፣ በየመንደሩ፣ በየወንዙ ቅዱስ የሆነውን የእግዚአብሔር ቃል ኪዳን ታቦት ይዛ እግዚአብሔርን በመዝሙር፣ በጭብጨባ፣ በሆታ፣ በዕልልታ፣ በውዳሴ፣ በማሕሌት፣ በቅኔ፣ በስብከተ ወንጌል ፣ በጸሎት የከበረውን ውኃ ባርኮ በመርጨት ልዩና ደማቅ በሆነ የአምልኮ ጒዞ እንዲከበር በማድረጓ ለኢትዮጵያ ሀገራችን ልዩ የሆነ መለኮታዊ ግርማ ሞገስን አጎናጽፋ ትገኛለች፡፡ መላ የሀገሪቱ ሕዝብ በነፃነት፣ በአንድነት በደስታና በፍቅር ከቤተ ክርስቲያኑ አንሥቶ እስከ ባሕረ ጥምቀቱ፣ ከባሕረ ጥምቀቱ እስከ ቤተ ክርስቲያኑ ድረስ እንደ ዐባይ ወንዝ እየተመመ ምንም መለያየት ሳይኖር፣ ጥላቻ ሳያጋጥም፣ ከኃምሳ ሚሊየን በላይ የሚሆን ሕዝብ በየቋንቋው፣ በየባህሉ ፈጣሪውን እያመሰገነ ሕብረ ብዙ የሆነ የእግዚአብሔር ሠራዊት ሆኖ ከዳር እስከ ዳር ሲተም በፊቱ ከደስታ ሌላ የሚታይ ነገር ሳይኖር ማክበር ማለት፣ ይህ ሁሉን የሚገዛ የእግዚአብሔር ኀይል መገለጫ ነው ከማለት ሌላ ሊገልጸው የሚችል አገላለጽ አይኖርም፡፡ ይህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የቅድስና ሕይወትና የሥራ ፍሬ ምን ያህል ታላቅ እንደሆነ የሚያረጋግጥ ሕያው ምስክር ነው፡፡

ይህ በዓል የኢትዮጵያውያን ቅዱሳን አበው የማይፈርስ ጽኑ ግንብ ነው፡፡ ይህ በዓል የኢትዮጵያና የእግዚአብሔር የሆነ ጽኑ የቃል ኪዳን ትስስር የሚያረጋግጥ ማስረጃ ነው፡፡ ኢትዮጵያውያን ይህንን ጸጋ እግዚአብሔር እስከ መጨረሻው ሊጠብቁትና ሊንከባከቡት፣ ሊያሳድጉትና ሊያበለጽጉት እንደዚሁም በተባበሩት መንግሥታት የባህል የሳይንስና የትምህርት ድርጅት በማስመዝገብ ፣ ለዓለም ሊያስተዋውቁትና የማኅበራዊነት ጸጋ ሊያስተምሩበት ይገባል፤ በዓለ ጥምቀት መተኪያ የማይገኘለት የኢትዮጵያውያን ታላቁና ግርማ ሞገስ የተሞላ በዓላችን ነው፤ በዓሉን ልዩ የሚያደርገው ሕዝቡ አንድ ሆኖ ከእግዚአብሔር ጋር የሚጓዝበት ቀን በመሆኑ ነው፡፡ ከእግዚአብሔር ጋር የሚጓዝ ሕዝብ ግርማ ሞገሱ ይህ ነው ተብሎ አይነገርም፤ ከቋንቋ በላይ ነውና፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መላ የኢትዮጵያ ሕዝቦችን በእኩልነት ተቀብላ የምታስተናግድ የሁሉም ሕዝቦች ቅን አገልጋይና እናት መሆኗን በተጨባጭ የሚመሰክር ይህ የጥምቀት በዓላችን ነው፡፡ በዓሉ የኢትዮጵያ ሕዝብን በአንድነት አስተሳስሮ የሚኖር፣ የሁሉም ሕዝቦች ቋንቋና ባህል በእኩልነት አስተናግዶ በመከባበር፣ በመተማመንና በወንድማማችነት ስሜት ጠብቆ ሕዝቡን እርስበርስ የሚያቀራርብና የሚያስተሳስር በመሆኑ ከዚህ የበለጠ የነበረ፣ ያለና የሚኖር በዓል ይኖራል ተብሎ አይገመትም፡፡ በመሆኑም በዓለ ጥምቀትን ማክበር ማለት ኢትዮጵያ ያላትን ሰማያዊና ምድራዊ ገጽታ ምን እንደሚመስል በሚገባ ማየት ማለት ነው፡፡ በዓለ ጥምቀት ማለት የኢትዮጵያን ግርማ ሞገስ ኀይልና ክብር በትክክል መገንዘብ መቻል ማለት ነው፡፡ በዓለ ጥምቀት የኢትዮጵያን ሕዝቦች አንድነት መጠበቂያ ጠንካራ ኀይል እንደሆነ በተግባር የሚያሳይ ሃይማኖታዊ ዕሴት ነው፡፡

በመጨረሻም፡ የቀደሙት ኢትዮጵያውያን አበው የበዓለ ጥምቀትን ሃይማኖታዊ ማኅበራዊና ሥነ ምግባራዊ ጠቀሜታ ግምት ውስጥ በማስገባት “ለጥምቀት ያልሆነ ቀሚስ ይበጣጠስ” ብለው ሃይማኖታዊ ማኅበራዊና ባህላዊ ጸጋቸውንና ክብራቸውን እንዳወረሱን፤ እኛም የእግዚአብሔርን ማዳን በመመልከት እንደዚሁም የኢትዮጵያ ግርማ ሞገስ የሆነውን ይህን በዓል በማክበርና በመጠበቅ ሕዝባችንም ኑሮውን በፍቅር፣ በአንድነት፣ በስምምነት፣ በእኩልነትና በሰላም እየቃኘ እንደጀመረው ለልማትና ለእድገት እንዲተጋ በማነሣሣት ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ተልእኮአችንን እንድንወጣ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡ መልካም የጥምቀት በዓል ያድርግልን፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡

ታኅሣሥ 29 ቀን 2009 ዓ.ም የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

እኛን ለማዳን በለበሰው ሥጋ በቤተ ልሔም ተወልዶ በመካከላችን የተገኘው፣ በመለኮታዊ ባሕርዩ የማይወሰነው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

“ወበዘርዕከ ይትባረኩ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር
የምድር አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።”
(ዘፍ 22፥18)

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው በረከት የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ነው፤ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት ለሰው ልጅ የሰጠው የመጀመሪያው ጸጋ ብዝኀ በረከት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላል “እግዚአብሔርም ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሣዎችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው” ይላል፤ (ዘፍ. 1፥28)፡፡ ለሰው የተሰጠው በረከት በኀጢአት ምክንያት መሰናክል ቢገጥመውም፣ እግዚአብሔር በፍጡሩ ጨርሶ አይጨክንምና ሙሉና ፍጹም የሆነው በረከት እንደገና ተመልሶ ለሰው ልጅ እንዴት እንደሚሰጥ ለበረከት በጠራቸውና በመረጣቸው ቅዱሳን አበው አማካይነት ሲያስታውቅ ኖሮአል፡፡ በተለይም የበረከት አባት ተብሎ በሚታወቀው በአብርሃም ዘር በኩል መጻኢው በረከት እውን እንደሚሆን “በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ” ተብሎ በእግዚአብሔር አንደበት በማያሻማ ሁኔታ ተነግሮ ነበር፡፡ ከእውነተኛው በረከት ተራቊታ የቆየችው ዓለመ – ሰብእ፣ እግዚአብሔር በራሱ ቃል የገባላት ዘላቂውና እውነተኛው በረከት እስኪመለስላት ድረስ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በተስፋ ስትጠባበቅ ቆይታለች፡፡

የተናገረውን የማያስቀር እግዚአብሔር በረከቱን ለሕዝቡ የሚያድልበት ጊዜ ሲደርስ ቅዱስ መንፈሱን ባሳደረባት ቅድስት እናት በኤልሳቤጥ አንደበት የበረከቱ ሙዳይ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በረከቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑንና በረከቱን ለምድር አሕዛብ ሁሉ ሊያድል እንደመጣ “ከሴቶች ሁሉ ተለይተሸ አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማሕፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው” ሲል የምሥራቹን ለዓለም አሰማ (ሉቃ 1፥41-43)፡፡ ቀዳማዊ የሆነ እግዚአብሔር ወልድ በድንግል ማርያም ማሕፀን ውስጥ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በፅንስ ቆይቶ የዛሬ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን በቤተ ልሔም ተወለደ ጌታችን በተወለደ ጊዜ የሰማይ ሠራዊት ማለትም መላእክትና የመላእክት አለቆች “ወናሁ ተወልደ ለክሙ መድኅን ዘውእቱ እግዚእ ቡሩክ — እነሆ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ የሆነ ጌታ ነው” በማለት የሕፃኑን ማንነት ከገለጹ በኋላ “በሰማያት ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም ሰላም ይሁን፤ ለሰውም በጎ ፈቃዱ ይደረግለት” እያሉ የተወለደው ሕፃን ለሰው ልጅ የሚያስገኘውን ሰላምና መልካም በረከት በመግለጽ ደስታቸውን በቃለ መዝሙር በቤተ ልሔም ዙሪያ አስተጋብተዋል፡፡

ከሰው ወገንም ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከእርስዋ ጋር የነበሩ ወገኖች፣ እንደዚሁም በአካባቢው የነበሩ የከብት እረኞች በመላእክት የምስጋና መዝሙር ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ (ሉቃ. 2፥8-20) እንግዲህ ከጥንት ጀምሮ በአበው ሲነገርና ሲጠበቅ የነበረው የበረከት ተስፋ በቃልም፣ በመልእክትም፣ በሐሳብም፣ በምሥጢርም ተፋልሶ ሳያጋጥመው፣ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ፍሰቱና ምሥጢሩ ተጠብቆ በተነገረው መሠረት ተፈጽሞ መገኘቱ፣ የክርስትና ሃይማኖት ምን ያህል አምላካዊ የሆነ ጽኑ መሠረት እንዳለው ያረጋግጣል ፡፡ የክርስትና ሃይማኖት መሠረቱ “ባርኮ እባርከከ፤ መባረክን እባርክሃለሁ” ከሚል ተነሥቶ፣ “የአባቴ ቡሩካን መንግሥተ ሰማያትን ትወርሱ ዘንድ ወደኔ ኑ!” በሚል የሚጠናቀቅ፣ መነሻውና መድረሻው በረከት የሆነ ሃይማኖት ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት “ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም” ከሚል ተነሥቶ “በምድርም ሰላም ይሁን” በሚል ተንደርድሮ፣ በምስጋና፣ በክብርና በሰላም፣ በማያልፍም ሕይወት ዘለዓለማዊነቱን የሚያውጅ ሃይማኖት ነው፡፡

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዕለት ከወደላይ የተላለፈው ዐቢይ መልእክት ሰላምና በረከት በምድር ላይ ሆነ የሚል እንደሆነ ማስተዋል አለብን፡፡ ታላቁ ሊቅና ኢትዮጵያዊው አባት ቅዱስ ያሬድ ስለዚህ በረከት ሲናገር “ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት፤ ወማየ ባሕርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ፤ ማለትም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራሮች የሕይወት እንጀራ ሆኑ፤ የበረሓ ዛፎችም የበረከት እሸትን አፈሩ፤ የባሕር ውኃም ወተትና ማር ሆነች” ይላል፡፡ የቅዱስ ያሬድ ቃለ ዝማሬ ሕያዋኑም ግዑዛኑም ሁሉ በልደተ ክርስቶስ ምክንያት በበረከት እንደ ተንበሸበሹ ይመሰክራል፡፡ ከዚህ አኳያ በበዓለ ልደተ ክርስቶስ የሚበላ እንጀራና የሚጠጣ ውኃ አጥቶ በረኃብና በጥም ተጐሳቊሎ የዋለ አልነበረም ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራውም ወተቱም ማሩም ፍጥረቱ ሁሉ እንደ ፈለገው እየተመገበ በሰላምና በደስታ ቀኑን ሁሉ ማሳለፉን እንገነዘባለን፡፡ የልደተ ክርስቶስ በረከት ገደብ የለሽ መሆኑን ያወቅን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን የምንል ክርስቲያኖች በዚህ ቀን ርቦትና ጠምቶት፣ አዝኖና ተክዞ የሚውል ሰው እንዳይኖር ያለውን በማካፈልና በጋራ በመመገብ የታረዘውን በማልበስ የታመመውን በመጠየቅ የበዓሉን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ገጽታ መጠበቅና ማስጠበቅ ይኖርብናል፡፡ በዓለ ልደተ ክርስቶስ የበረከት ቀን ከመሆኑም ሌላ የዕርቅ፣ የእኩልነትና የአንድነት በዓልም ነው፡፡ ከብዙ ጊዜ መለያየትና መራራቅ በኋላ፣ ፈጣሪ የሰዎችን ሥጋ አካሉ አድርጎ በሰዎች መካከል በአካል መገኘት ከዕርቅ ሁሉ የበለጠ ዕርቅ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ በዕለተ ልደተ ክርስቶስ መላእክትና ሰዎች ፈጣሪያቸው በተወለደበት ዙሪያ ተሰባስበው በእኩልነትና በአንድነት ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ ማየትና መስማትም የፍጡራንን እኩልነትና አንድነት ያረጋገጠ ሌላው ክሥተት ነበረ፡፡

ሰማያውያንና ምድራውያን ለሰው ልጅ ህልውና ወሳኝ የሆነውን ‹‹ ሰላም በምድር ይሁን›› እያሉ በአንድ ቃል መዘመራቸውም ለሰማያውያኑም ሆነ ለምድራውያኑ ከሰላም የበለጠ ትልቅ ጸጋ የሌለ መሆኑ የሚያስገነዝብ ነበረ፡፡ እንዲህም ስለሆነ ከልደተ ክርስቶስ ያልተማርነው ትምርት የለም ማለት ይቻላል። እግዚአብሔር በልደተ ክርስቶስ ዕለት ያስተማረን ብቻ አጥብቀን ብንይዝና ይህንኑ ብንፈጽም ከበቂ በላይ ነው ቢባል ፍጹም እውነት ነው፡፡ ተራራው ሁሉ የሕይወት እንጀራ ሆነ፤ የበረሓ ዛፍ ሁሉ የበረከት እሸት ሆነ፤ የባሕር ውኃም ማርና ወተት ሆነች ተብሎ ሲነገር በዓለ ልደተ ክርስቶስ የልማት፣ የእድገትና፣ የብልጽግና አስተማሪ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ከዚህ አንጻር ዛሬም ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ተራራው ይልማ፣በረሓው በደን ይሸፈን፣ ውኃው ከብክለት ድኖ ለምግብነት የሚያገለግሉ ሕይወታውያን ፍጡራን በብዛት ይኑሩበት የሚለው በልማትና በበረከት የተሞላው የልደተ ክርስቶስ አስተምህሮ ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን አምላካዊ አስተምህሮ በምልአት ተቀብሎ ወደ ልማት ከተሰማራ በዚያው መጠን በረከቱን በገፍ ያፍሳል፡፡ ከዚህም ጋር “የሺሕ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ›› እንደሚባለው የሁሉም ማሰሪያ ሰላም ስለሆነ የድሮ ነጋዴ ለንግድ ሲወጣ ሥንቁን በትከሻው ተሸክሞ እንደሚጓዝ ሁሉ፣ ዛሬም የልማት ነጋዴ ሕዝባችን ሰላምን በልቡ ቋጥሮ መጓዝ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ችግሮች ከሰላም በታች መሆናቸውን ሁሉም ማኅበረሰባችን መገንዘብ አለበት፤ ሁሉም ለአንድነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕ፣ ለወንድማማችነት፣ ለመተማመንና ለመከባበር መስፈን የማያወላውል አቋም ሊይዝ ይገባል፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ታላቅ ሀገር እንድትሆን ያበቋት አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ ስለሠሩ ነው፤ ያለ አንድነት ታላቅነትም፣ ኀያልነትም፣ ልማትና እድገትም፣ ፈጽሞ እንደማይገኝ ሳይታለም የተፈታ ነውና ሕዝባችን ይህንን በውል ማጤን ይኖርበታል፡፡

በመጨረሻም፡ ከላይ ለመግለ,, እንደተሞከረው የክርስቶስ መወለድ ዋና ዐላማ መለያየትና መቃቃርን፣ መነታረክንና፣ በጥላቻ ዐይን መተያየትን አስወግዶ በምትኩ ዕርቅን፣ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን በሰው ሁሉ አእምሮ ውስጥ ማስፈን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በመሆኑም ይህ ነገረ ሕይወት ከተሰበከባቸው የዓለማችን ሀገራት ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ በእግዚአብሔር ከተሰጣት የቅድሚያ ኀላፊነት አንጻር በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃም ሁሉ፣ እንደ ድሮው ደማቁ የአንድነት ታሪኳና ተደናቂው ሥልጣኔዋ፣ እንደዚሁም ጽኑ ሰላምዋና ልማቷ ጠብቃ በማስጠበቅ አስተማሪነትዋ ጎልቶ እንዲወጣ “ችግሮች ሁሉ ከሰላም በታች ናቸው” የሚለውን ጠንካራ የሰላም አስተሳሰብ መርሕ በማድረግ ሁሉም በአንድነት፣ በኀላፊነት፣ በቅንነትና በተቈርቋሪነት ሀገሩን እንዲጠብቅና እንዲያለማ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የልደት በዓል ያድርግልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክልን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡