የካቲት 29 ቀን 2008 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሁለት ቀናት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፏል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
«ኅሡ ሰላማ ለብሔር እስመ በሰላመ ዚኣሃ ይከውን ሰላምክሙ፤
የአገርን ሰላም ሹ ፈልጉ የአገራችሁ ሰላም የእናንተ ሰላም ነውና።
የሀገርና የወገን ፍቅር ያለው ሕዝብ ሰላም ከእግዚአብሔር መሆኑን ያውቃል፣ ሰላም ለሰው ልጆች ከማናቸውም መሠረታውያን ፍላጎቶች በላይ ተቀዳሚ ጉዳይ ነው፡፡ ኢትዮጵያ ሀገራችን የተለያዩ ሃይማኖቶች፣ ብሔር፣ ብሔረሰቦች ተቻችለውና ተረዳድተው የሚኖሩባት የዓለም ምሳሌ ናት፡፡ ይህን ዓለምን የሚያስደንቅ ገጽታችንን ማንኛውም ኢትዮጵያዊ እንዲከተለው ጥሪያችንን እናቀርባለን፡፡
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት! ኢትዮጵያ አህጉረ ሰላም (የሰላም ሀገሮች) ከሚባሉት ከዓለም ሀገሮች አንዷ ስትሆን በአሁኑ ጊዜ በአንዳንድ ከተሞች የሚታየው አለመረጋጋት ሁሉንም የሚያሳስብ ሆኖ አግኝተነዋል፡፡ ከዚህም ጋር ባሳለፍናቸው ሳምንታት በተከሠተው ያልተጠበቀ ችግር፡-
1. በአንዳንድ አካባቢ የሰው ሕይወት ሲጠፋ፣ ትምህርት ቤቶች ሲዘጉ፣ የንግድ ተቋማት፣ የሕዝብና የመንግሥት ንብረት፣ የእምነት ተቋማት ሲወድም የሕዝባችን የዕለት ከዕለት ኑሮ ሲናጋ ሁሉም ኅብረተሰብ የችግሩ ተጠቂ ሆኗል፣ የዚህ ዐይነቱ ድርጊት በዚህ ሁኔታ የሕዝባችን ህልውና የትውልዱም የወደፊት ዕድል አደጋ ላይ ሊወድቅ ይችላል፡፡
2. ባሳለፍናቸው ሳምንታት በተከሠተው ሁኔታ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖች በመሪር ኀዘንና ጸሎት እናስባቸዋለን፡፡ ስለዚህ ሁላችሁም ልጆቻችን መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ወንድ፣ ሴት፣ ወጣት፣ ሽማግሌ ሳትሉ ችግራችሁን ሰላማዊ በሆነ መንገድ ለሚመለከተው እንድታቀርቡ መንግሥትም የሕዝቡን ችግር እና ሰላማዊ ጥያቄ በመገንዘብ መፍትሔ በመስጠትና ሰላም ለማምጣት እያደረገ ያለውን የዕለት ከዕለት ጥረት እንዲቀጥልበት በቤተ ክርስቲያናችን ስም እናሳስባለን፡፡
3. ሕዝባችንና ሀገራችን በረኃብ፣ በድኅነትና በበሽታ ቸነፈር በተቸገረበት ወቅት የኢትዮጵያ ሕዝብ በአንድነት መሠረታዊ ወደሆነው ልማት የሰላምና የድርቅ ጉዳይ በማተኮር መልስ ሰጭ መሆን ይገባዋል ብለን በጽኑ እናምናለን፡፡
4. ወገኖቻችን ሆይ በአሁኑ ጊዜ የወቅቱ የኤሌክትሮኒክስ መገናኛ (ብሎጎችና የፌስ ቡክ) ተጠቃሚዎች በሙሉ ኢትዮጵያውያን ከሙያችሁ ከዕውቀታችሁ ተጠቃሚዎች የመሆን ምኞታቸው የላቀ ነው፡፡ ሆኖም መልካሙንና ለእድገት የሚያግዛቸውን ዕውቀት እንጂ ኅብረተሰቡን የሚለያይና የሚያራርቅ መረጃ (ኢንፎርሜሽን) ዕለት ዕለት ብታስነብቡት ትርፉ መራራቅን እንጂ መቀራረብን፣ መለያየትን እንጂ መግባባትን አያመጣም፣ ከዚህ አንጻር የእናንተም ጥረትና ድካም ከንቱ ሆኖ ይቀራል፡፡ በመሆኑም የተከበረ ዕውቀታችሁን ሙያችሁን ለሕዝባችን ፍቅርና አንድነት፣ ለሀገራችን ሰላምና እድገት እንድታውሉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አጥብቃ ትጠይቃለች፡፡
የተወደዳችሁ ኢትዮጵያውያን፡ ተቻችሎና ተረዳድቶ የመኖር የተቀደሰ ነባር ባህላችንን የሚያጎድፍ ማናቸውንም አስተሳሰብና እንቅስቃሴ በአንድነት መቋቋም እንደሚገባ አበክረን እየገለጽን፣ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት ወገኖቻችን በሙሉ በተለይም አገር ተረካቢ ትውልድ የሆናችሁ ወጣቶች ሁከትና ብጥብጥን ከሚያስከትሉ መጥፎ ድርጊቶች እንድትቈጠቡ ለአገር ልማትና ሰላም ጠንክራችሁ እንድትቆሙ በልዑል እግዚአብሔር ስም አጥብቀን እያሳሰብን በተፈጠረው ሁከትና ብጥብጥ ሕይወታቸውን ላጡ ወገኖቻችን የሀብትና፣ የንብረት ውድመት፣ በተለይም የሕዝብ መገልገያ የሆኑ የእምነት ተቋማት መቃጠል የተሰማንን ኀዘን እንገልጻለን፡፡ ይልቁንም ከሁሉም በላይ ሁሉን ማድረግ የሚችል እግዚአብሔር አምላካችን ለኢትዮጵያ ለሀገራችን ሕዝቦች ሰላሙን፣ ፍቅሩን አንድነቱን ይሰጥልን ዘንድ፣ ድርቁን ረኀቡን አስታግሦ መጪው ጊዜ ዝናመ በረከቱን ይሰጠን ዘንድ በያዝነው በዐቢይ ጾም ሱባኤ ጸሎተ ምሕላ በመላ ሀገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት የገጠር አብያተ ክርስቲያናት እንዲደረግ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡
እግዚአብሔር አምላክ ኢትዮጵያን ይባርክ!