ጥቅምት 12 ቀን 2008 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
የአማልክት አምላክ፣ የነገሥታት ንጉሥ፣ የአጋእዝት ጌታ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ከተለያዩ የዓለም አህጉርና ከሀገራችን አህጉረ ስብከት አሰባስቦና አንድ ላይ አገናኝቶ በመንፈስ ቅዱስ ስለተሰጠን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለመወያየት ስለሰበሰበን ክብርና ምስጋና ለእርሱ ይሁን፡፡

“ምንተ ይቤ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት፤ መንፈስ ቅዱስ አብያተ ክርስቲያናትን አስመልክቶ ምን አለ?” (ራእ. 2፥7)፡፡

በጌታችን በአምላካችንና በመድኀኒታችን በኢየሱስ ክርስቶስ የተመሠረተችው ክርስቶሳዊት ቤተ ክርስቲያን ከበዓለ ኃምሳ ጀምሮ በመንፈስ ቅዱስ አመራርና ጥበቃ ሥር እንዳለች ይታወቃል፡፡ ቅዱስ መንፈሰ እግዚአብሔር ዓለም በማያየውና በማያውቀው ረቂቅ ጥበቡ በሃይማኖት አማካይነት በልበ ምእመናን አድሮ ቤተ ክርስቲያንን ሲመራ ይኖራል፡፡ ከዚህም ሌላ በሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን አማካይነት ቅዱስ ቃሉንና ቅዱሳት ምሥጢራቱን ለምእመናን ያድላል፡፡ በመሆኑም ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን፤ የቅድስት ቤተ ክርስቲያን መሪ የሆነው መንፈስ ቅዱስ የሚለውንና የሚናገረውን በትክክል አዳምጠውና ተረድተው ምግብናቸውን ማከናወን እንዳለባቸው ለሰባቱ ሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን ዘእስያ የተነገረው ቃለ ተግሣጽ ወምዕዳን በግልጽ ያስተምረናል፡፡

ለተጠቀሱት የቤተ ክርስቲያን ሥዩማን የተላለፈው መልእክት በአጠቃላይ የመንፈስ ቅዱስ ቃል እንደሆነ ለማመልከት ‹‹ምንተ ይቤ መንፈስ ቅዱስ ለአብያተ ክርስቲያናት›› በሚልና ‹‹ዘቦ እዝን ሰሚዐ ለይስማዕ›› በሚል ኀይለ ቃል ሲዘጋ እናያለን፡፡

ለሰብዑ አብያተ ክርስቲያናት ዘእስያና ለአለቆቻቸው የተነገረው ሁሉ ዛሬ ያለችው ቤተ ክርስቲያንና አለቆቿን ጭምር በቀጥታ የሚመለከት እንደሆነ ጥርጥር የለውም፡፡ ከአለቆቹ መካከል የተመሰገኑም፣ በመካከለኛ ደረጃ የሚገኙም፣ እንደዚሁም ጠንከር ያለ ተግሣጽ የደረሰባቸው እንዳሉ እንገነዘባለን፡፡ ዛሬ በቤተ ክርስቲያን የሥራ ኀላፊነት የምንገኝ ሥዩማንም በዚያን ጊዜ በነበረችው ፈታኝ ዓለም ውስጥ የምንገኝ እንደመሆናችን መጠን፤ በዚያን ጊዜ የነበሩ ኩነቶች ሁሉ አሁንም አይኖሩም ማለት አይቻልም፡፡

በየትኛውም ዘመን፣ በየትኛውም ቦታ፣ ክፍተት አይፈጠርም ብሎ ሙሉ በሙሉ ኀላፊነት መውሰድ የሚችል ይገኛል ተብሎም አይጠበቅም፡፡ ነገር ግን የከፋና የባሰ ክፍተት እንዳይፈጠር የተጠናከረ ሥራ በመሥራት መከላከል የሚችሉ በየጊዜው ሁሉ የተነሡ ታላላቅ አበው እንዳሉ እናስተውላለን፡፡ በዚህ ዘመን የምንገኝ ኖሎትም ምንም ቢሆን ከዚህ እውነታ ውጭ መሆን አንችልም፤ መሠረታዊ ችግር ሊሆን የሚችለው ክፍተት ለምን ተፈጠረ የሚለው ሳይሆን ክፍተት መኖሩ እየታወቀ ዝም ብሎ መኖሩ ነው፡፡ በዚህ ዙሪያ ይህ ዐቢይ ጉባኤ ብዙ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡

እንደ እውነቱ ከሆነ በቤተ ክርስቲያናችን መሠራት የነበረባቸው፤ ሆኖም ግን እስካሁን በአጥጋቢ ሁኔታ ያልተሠራባቸው የሥራ መስኮች እንዳሉ ባይካድም ጥሩ ውጤት ያስመዘገብንባቸው ነገሮች እንዳሉም መዘንጋት የለበትም፤ በተለይም ሕዝበ ክርስቲያኑ ባለው ዐቅም ሁሉ ቤተ ክርስቲያኑን ለመደገፍና ለማልማት የሚያደርገው ቀና ትብብር ከመቼውም ጊዜ የበለጠ ተስፋ ሰጪ ሆኖ ይታያል፣ አንዳንድ አህጉረ ስብከትና አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት በሚያስደንቅ ሁኔታ የራስ አገዝ ልማት እያካሄዱ ለቤተ ክርስቲያናችን ተጨማሪ የሚሆን ትልቅ ዐቅም እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡

ከሁሉም በላይ ደግሞ የቤተ ክርስቲያናችንን ሐዋርያዊ ተልእኮ ለማስፋፋት በዓለም ዙሪያ የተደረገው እንቅስቃሴ በአሁኑ ጊዜ ሁሉንም ክፍለ ዓለማት ማለትም ከምዕራብ አሜሪካ እስከ ጃፓን፣ ከአየርላንድ እስከ አውስትራሊያ ቤተ ክርስቲያናችን ክንፎቿዋን የዘረጋችበት ሁኔታ የተፈጠረ በመሆኑ ትልቅ ስኬት ተገኝቶአል ማለት እንችላለን፤ ቤተ ክርስቲያናችንም ዓለም አቀፋዊት ቤተ ክርስቲያን ወደ መሆን አድጋለች ማለት ይቻላል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን ሥራ ሰፊና ዘርፈ ብዙ በመሆኑ አሁንም ቢሆን ትኵረት ተሰጥቶአቸው በቅድሚያ ሊሠሩ የሚገቡ ሥራዎች እንዳሉ ማስታወሱ ተገቢ ነው፤ በመሆኑም፤

• ቤተ ክርስቲያናችን ዘመኑን የዋጀ የአስተዳደር ጥበብ ተከትላ ሀብትዋና ንብረትዋን መጠበቅ የሚያስችሏትን አሠራሮች መቀየስ፤
• በሕገ ቤተ ክርስቲያኑ መሠረት ሊዘጋጁ የሚገቡ ልዩ ልዩ ደንቦች፣ ፖሊሲዎችና መመሪያዎችን በማዘጋጀት ሥራዎች ሁሉ ግልጽነትና ተጠያቂነት እንዲኖራቸው ማድረግ፤
• ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረውንና እስካሁን በይደር የቆየውን የመሪ ዕቅድና የሚድያ ጥናት በዚህ ዓመት በጀት ተይዞለት በአፋጣኝ ሥራ ላይ ማዋል፤
• የምእመናንን ፍልሰት ለማስቆም መልካም አስተዳደርን በማስፈን ስብከተ ወንጌልን ማጠናከር፣
• በውጪ ሀገራት የሚገኙ አድባራት ከእናት ቤተ ክርስቲያን ጋር ያላቸውን ግንኙነትና ትስስር ማጠናከር፤
• በሁሉም አቅጣጫ የልማት ሥራዎችን በማስፋፋት ቤተ ክርስቲያናችንን በኢኮኖሚ የበለጸገች ማድረግ፤
• የነገዋ ቤተ ክርስቲያን ተረካቢ የሆኑ ሕፃናትና ወጣቶች በሰንበት ት/ቤት በስፋት እየተደራጁ በሃይማኖትና በሥነ ምግባር ተገንብተው እንዲያድጉ ማድረግ፤
• ለአብነት ት/ቤቶችና ለገዳማት የሚደረገውን ድጋፍ በማሳደግ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማድረግና በመሳሰሉት ሥራዎች ልዩ ትኲረት ሰጥተን የምንሠራባቸው ሥራዎች ሊሆኑ ይገባል፡፡
• በሌላ በኩል በዚህ ዓመት በሀገራችን በተከሠተው የዝናም እጥረት ምክንያት፣ በተለያዩ የሀገራችን አካባቢዎች ድርቅ እንደተከሠተና የምግብ እጥረትም እንዳጋጠመ፣ በሠላሳ አራተኛው የቤተ ክርስቲያናችን አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በቀረቡ የየአህጉረ ስብከቱ ሪፖርቶች ለመገንዘብ ተችሎአል፡፡
• በመሆኑም ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በተለመደው ሃይማኖታዊና ማኅበራዊ ባህላችን መሠረት፣ ሕዝቡ ካለው እየከፈለ የተጎዱ ወገኖችን እንዲረዳ ከማስተማርና ከማስተባበር በተጨማሪ፣ የሕዝብ እናት የሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በድርቅ ለተጎዱ ወገኖቻችን ዐቅሟ የሚችለውን ሁሉ ታደርግ ዘንድ፣ ይህ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በጉዳዩ መነጋገር አለበት፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ ሐዋርያዊ የቅዱስ ሲኖዶስ ዐቢይ ጉባኤ ሐዋርያዊት፣ ህልውተ ኵሉ፣ አንዲትና ቅድስት የሆነችው ቤተ ክርስቲያናችን በሁሉም አቅጣጫ የተሟላ፤ የተስተካከለና ከክርስቶሳዊ አስተምህሮዋ ጋር የሚጣጣም አሠራር እንዲኖራት ከላይ የተጠቀሱትን ዋና ዋና ጉዳዮች አንሥቶ በመወያየት ጠቃሚ ውሳኔዎችን ያሳልፍ ዘንድ በማሳሰብ በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 164 በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የ2008 ዓ.ም. የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤን ባርከን ከፍተናል፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤችንን ይባርክ፤ይቀድስ አሜን

ወስብሐት ለእግዚአብሔር

34ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ከጥቅምት 8-11 ቀን 2008 ዓ.ም አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ የጠቅላይ ቤተ ክህነት የየመምሪያው ኀላፊዎችና፣ የየድርጅቱ ሥራ አስኪያጆች፤ የየአህጉረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች፣ የገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ የካህናት፣ የምእመናንና የሰንበት ት/ቤት ተወካዮች፣ ክቡራን የዚህ ታላቅ ጉባኤ ተሳታፊዎች፤

ሁሉን ፈጥሮ የሚገዛ አምላካችን እግዚአብሔር ያለፈውን የ2007 ዓ.ም.የሥራ ዘመን በሰላም አስፈጽሞ በአዲሱ የ2008 ዓ.ም. ልንሠራው የሚገባንን ሥራ ለመሥራት አንድ ላይ ስለሰበሰበን ከሁሉ በፊት እርሱን እያመሰገን እንኳን ለሠላሳ አራተኛው ዓመታዊ መደበኛ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ በሰላም አደረሳችሁ እንላለን ፡፡

‹‹ቃለ እግዚብሔር ቃል ንጹሕ — የእግዚአብሔር ቃል ንጹሕ ቃል ነው።›› (መዝ. 11፥6)

ስለ ቃል አንሥተን ስንመረምር በፍጡራን ዘንድ የተለያዩ ቃላት እንዳሉ ከቅዱስ መጽሐፍ እንመለከታለን፡፡ ከእነሱ መካከል የተወሱትን ለመጥቀስ የአዕዋፍን ቃል “ቃለ ማዕነቅ” የውኃን ቃል “ቃለ ማያት ብዙኅ” የደመናትን ቃል “ቃለ ወሀቡ ደመናት” እየተባለ በቅዱስ መጽሐፍ ተጽፎአል፡፡

ከምድራውያን ፍጡራን ሁሉ የተሻለ ቃለ ሰብእም እንዳለ ሁላችን የምናውቀው ጉዳይ ነው፡፡ ነገር ግን ከዚህ ሁሉ የበለጠና ሕያው የሆነው ቃል የእግዚአብሔር ቃል ነው፤ ቃለ እግዚአብሔር በሰማይም ሆነ በምድር ያሉትን ማለትም የሚታዩትንና የማይታዩትን ሁሉ የፈጠረ፤ ኀይላተ ሰማያት ወምድር ጸንተው የሚኖሩበት፣ ሁሉን የሚያሳልፍ እንጂ እርሱ የማያልፍ ቃል ነው፤ የእግዚአብሔር ቃል እውነት እንጂ ሐሰት የማይቀላቀልበት፤ ኀይል እንጂ ድካም የማይፈራረቅበት በመሆኑ ንጹሕ ቃል ይባላል፡፡

በዚህ ዓለምም ሆነ በወዲያኛው ዓለም የእግዚአብሔር ቃል ያልተናገረለት ፍጡር የለም፤ ይሁን እንጂ የእግዚአብሔር ቃል ከሁሉም በላይ አብዝቶ የተናገረላት ብትኖር ቤተ ክርስቲያን ብቻ ናት፣ በተለያየ ሕብረ ትንቢት ወአምሳል፣ በተለያየ ኊልቈ ሱባዔ ወቀመር ተጽፎ የሚገኘው ቃለ እግዚአብሔር የመጨረሻ መዳረሻው ቤተ ክርስቲያን ናት፤ ቤተ ክርስቲያን በጥንተ ፍጥረት ከመጀመሪያ ጀምሮ ነበረች፤ ከዓለም ፍጻሜ በኋላም የእግዚአብሔር መንግሥት ርእሰ ከተማ ሆና ማኅለቅት በሌለው ኊልቈ ዘመን ትቀጥላለች፡፡

የእግዚአብሔር ቃል በብሉይ ኪዳን ስለ ቤተ ክርስቲያን ሲናገር “ይሰግዱ ለኪ ኵሎሙ ነገሥታተ ምድር ወይልሕሱ ጸበለ እግርኪ፤ ወትሰመይ ጽዮንሃ ሀገረ እግዚአብሔር፤ ወአስተጋብኦሙ ለውሉድኪ በውስቴትኪ፣ ያመጽኡ አምኃኪ እምርሑቅ ብሔር ወነገሥት ክብረ ሊባኖስ” ብሎአል፡፡ ይህም ማለት ሁሉም የምድር ነገሥታት ላንቺ ይሰግዳሉ፤ የእግርሽንም ትቢያ ይልሳሉ፤ አንቺ የእግዚአብሔር ከተማ ጽዮን ነሽ ትባያለሽ፤ ልጆችሽን በአንቺ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ፤ መባውን፣ ቀዳምያቱን፣ ዐሥራቱን፣ በኵራቱን ከሩቅ አገር ይዘውልሽ ይመጣሉ፤ ነገሥታትም የሊባኖስን ክብር ያመጡልሻል ማለት ነው ፡፡ (ኢሳ. 49፡23)

በውስጧ ሆነው ሲያገለግሉ የሚኖሩ ልጆችዋም ‹‹ወይትወሀውሁ በአዝማን ዘአልቦ ኊልቁ፤ ፍጻሜ በሌላቸው አዝማነ መንግሥተ ሰማያት ሲመላለሱ ይኖራሉ›› ተብሎ (በመጽ ምሥ.) በተነገረላቸው ቃል መሠረት ማኅለቅትና ፍጻሜ በሌለው ሕይወት በውስጧ ለዘለዓለሙ በደስታና በክብር ይኖራሉ፤ እንግዲህ የእግዚአብሔር ቃል ይህን ሁሉ የተናገረው ለንጽሕትና ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን ነው፤ ዛሬ በዚህ ዐቢይ ጉባኤ እግዚአብሔር የሰበሰበን ኀይል ‹‹ልጆችሽን በአንቺ ውስጥ እሰበስባቸዋለሁ›› ብሎ ከዛሬ ሁለት ሺሕ ሰባት መቶ ዓመታት በፊት የተናገረው የእግዚአብሔር ቃል ነው፡፡ ዛሬ መባዉን፣ ቀዳምያቱን፣ በኵራቱን፣ ዐሥራቱን፤ ወይም በዘመናችን አነጋገር የሰበካ ጉባኤ አስተዋፅኦውን ከሩቅ አገር ይዘን ወደዚህ የመጣንበት ምክንያት ‹‹መባሽን ከሩቅ ይዘውልሽ ይመጣሉ›› የሚለው የእግዚአብሔር ቃል አስተምሮን ነው፤ ይህ ሕያውና የማይታበል ቃል ዛሬም በእኛ ውስጥ ሥራውን እየሠራ የሚገኝ በመሆኑና እኛም የቃሉ መሣሪያ ሆነን በመገኘታችን እጅግ፤ ደስ ሊለን ይገባል፡፡

በዓለም ውስጥ እጅግ ሀብታምና ኀያል የሆነ ማን ነው? ተብሎ ቢጠየቅ ትክክለኛ መልስ ሊሆን የሚችለው ቤተ ክርስቲያን ናት የሚለው መልስ ነው፡፡ እርግጥ ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሰዎች ኀይል ቀርቶ ለሰይጣንና ለሠራዊቱ እንኳ የማትበገር ኀያል ናት፤ በዚህም የእግዚአብሔር ቃል ‹‹ወአናቅጸ ሲኦል ኢይኄይልዋ፣ የሲኦል በረኞች ሰይጣንና ሠራዊቱ አያሸንፉአትም›› ብሎ ተናግሮላታል፤ ይህ ቃል የማይሸነፍ ኀያልና ንጹሕ የእግዚአብሔር ቃል ስለሆነ እነሆ ጠላቶቿ ሁሉ እየተሸነፉ እርስዋ ግን በድል አድራጊነት በዘመኑ ሁሉ ወደፊት እየገሠገሠች ከዘመናችን ደርሳለች፤ ወደፊትም በዚሁ ትቀጥላለች፡፡

በሌላም በኩል ቤተ ክርስቲያን እጅግ የበለጸገች ባለሀብት መሆንዋን የእግዚአብሔር ቃል ሲናገር “ወይበውእ ኀቤኪ ብዕለ አሕዛብ፤ የሕዝቡና የአሕዛቡ ብዕል ወዳንቺ ይገባል” ይላል፡፡ ቤተ ክርስቲያን ይህ ቃል መሠረተ ሀብቷ ሆኖ አስገዳጅ ምድራዊ ኀይል ሳይኖር በቃሉ ቀስቃሽነት ብቻ ሕዝበ እግዚአብሔር የሆኑ ክርስቲያኖች ያላቸውን በደስታ፣ በፈቃደኝነትና በልግስና ዐውደ ምሕረቷ ድረስ እየመጡ ከከበረው የወርቅ ጌጥ ጀምሮ ስጦታውን በየዐይነቱ ሲያፈሱላት ይኖራሉ፡፡ እንግዲህ ይህን ሁሉ በዐይናችን እየተመለከትን የምንገኝ እኛ ‹‹በአማን ኢይሔሱ ቃሎ ዘነበበ፣ በእውነት የተናገረውን ቃል አይዋሽም›› ብለን እርሱን ከማመስገን ጋር በቤተ ክርስቲያን ውስጥ ሆነን ልንፈጽመው የተሰጠንን ተልእኮ በደስታ፣ በፈቃደኝነት፣ በትጋትና በቅንነት ከመወጣት በቀር ሌላ ምን ሥራ ሊኖረን ይችላል፤ ከዚህ ተነሥተን ስናይ እግዚአብሔር ለቤተ ክርስቲያን የተናገረው ቃሉን እንዳላጠፈብን እናረጋግጣለን፡፡
በአንጻሩ ደግሞ እኛስ ቃላችንን አክብረናል፤ ወይስ አጥፈናል፤ የሚለውን መመርመር ከእኛ ይጠበቃል፡፡

በአሁኑ ጊዜ ያለው የቤተ ክርስቲያናችን ገቢ በቂ ነው ባይባልም ቤተ ክርስቲያናችን በሰበካ ጉባኤ መደራጀት ስትጀምር ገቢዋ በመቶ ሺሕ ብር ደረጃ የነበረው ዛሬ ወደመቶ ሚሊዮኖች መድረሱ በሀገር ዐቀፍ ደረጃ አጠቃላይ ሲታይ ደግሞ ወደ ቢሊዮኖች መድረሱ ትልቅ እድገት ነው፤ ነገር ግን የምእመናን እድገትስ የት ነው ያለው የሚለውን አይተነዋል ወይ?፤ በዚህ በኩል ያለው እድገት የኋልዮሽ መሆኑ የማያውቅስ በመካከላችን ይኖር ይሆን? ይህን ችግር በሚገባ ተገንዝበንና በቁጭት ተነሣሥተን ነገሩን ለመቀልበስ ያደረግነው ሙከራስ ይኖር ይሆን? ለዚህ ጥያቄአችን ከዚህ ጉባኤ መልስ እንፈልጋለን ፡፡

መቼም ቢሆን ተልእኮአችን ሰማያዊ እንጂ ምድራዊ እንዳይደለ ሁላችንም እናውቃለን፤ ሰማያዊውና ታላቁን ተልእኮአችን በተገቢው ሁኔታ ለመወጣት ከኅሊና መቈርቈር ጀምሮ እስከ ኅልፈተ ሕይወት የሚዘልቅ የመሥዋዕትነት ዋጋ እንደሚጠይቅ ምንጊዜም አንዘነጋውም፤ ይህ መሥዋዕትነት ብዙዎቹ የሃይማኖት መስተጋድላን አባቶቻችን ያለፉበት ስለሆነ ለኛ ለቤተ ክርስቲያን ልጆች አዲስ አይሆንም፡፡ ይሁንና እኛ ባለንበት በአሁኑ ዘመን ከፍተኛ መሥዋዕትነትን እየጠየቀን ያለው የደምና የሕይወት መሥዋዕትነት ሳይሆን ራስን የመካድ ወይም ያልተገባ ጥቅምን የመጸየፍና ኀላፊነትን በሚገባ ለመወጣት የመነሣሣት ጉዳይ ነው፡፡

ቤተ ክርስቲያናችንን ከሌሎች አብያተ ክርስቲያናት ጋር ስናነጻጽር በቊጥር እጅግ የላቀ የውሉደ ክህነት ብዝኅነት ያላት ስትሆን ‹‹ታላቁን የቅዱስ ወንጌል ተልእኮን›› ለውሉደ ሰብእ በማዳረስ ረገድ ያለን ውጤት ግን አናሳ ነው ማለት ይቻላል፡፡ ባሕርን አቋርጦ፣ ድንበርን ተሻግሮ፣ እስከ ጽንፈ ምድር ተጒዞ፣ አስተምሮና ያላመነውን፣ አሳምኖ የቤተ ክርስቲያን ልጅ ማድረጉ ይቅርና በሀገር ውስጥ ያሉትን ወገኖች በቤተ ክርስቲያን ውስጥ አሰባስቦ ምእመናንን ማብዛት ብዙ ያልተሄደበት እንደሆነ ማወቅ አለብን፡፡

ከሁሉም በላይ የሚያስቈጨው ደግሞ ትናንት ቤተ ክርስቲያን “ሀብተ ወልድና ስመ ክርስትና” ሰጥታ በአባልነት የተቀበለቻቸው ልጆችዋ ዛሬ እናት ቤተ ክርስቲያናቸውን እየካዱ ወደሌላው ጎራ የመቀላቀሉ ጉዳይ እጅግ በጣም እየናረ መምጣቱን ነው፡፡

የምእመናን ፍልሰት በየጊዜው እየጨመረ የመሄዱ መነሻ ምሥጢር ምንድን ነው? የሚለውን ጥያቄ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ልታጤነው ይገባል፤ በዚህ ዙሪያ የሚታየው ክፍተት ፈጣን ምላሽ በመስጠት መግቻ ካላበጀንለት ነገ ከባድ የሃይማኖትና የታሪክ ወቀሳ ማስከተሉ እንደማይቀር ልብ እንበል፡፡ ለመሆኑ ምእመናን ከቤተ ክርስቲያናችን እየወጡ ወደ ሌላ ካምብ ለመግባት ለምን መረጡ?
• የሚያስተምራቸው ካህን አጥተው ነው?
• የቤተ ክርስቲያናችን ትምህርተ ሃይማኖት ክፍተት ኖሮት ነው?
• የቤተ ክርስቲያናችን አስተዳደር የማያረካ ሆኖ ነው?
• የካህን እጥረት ስላለ ነው?
• ወይስ ሌሎች ከእኛ የተሻሉ ሆነው ስለተገኙ ነው?

የዚህ ሁሉ መልስ በእያንዳንዳችን ኅሊና ውስጥ ቊልጭ ብሎ ስለሚታወቅ የጥያቄው መልስ ለእናንተው ሰጥተናል፡፡ ይሁን እንጂ ይህ ዐቢይ ጉባኤ በሁለት ዐበይት የቤተ ክርስቲያን ጉዳዮች ላይ ትኲረት ሰጥቶ እንዲነጋገርባቸው ሳንጠቁም አናልፍም ይኸውም፡-
• ምእመናንን የመጠበቅ ተልእኮ በሚገባ እየተወጣን አይደለምና ባዶአችንን ከመቅረታችን በፊት ለተደራጀና ለድንበር የለሽ ትምህርተ ወንጌል ብንነሣ፤
• የአስተዳደር ሥራችን ለምእመናን ኅሊና ዕንቅፋት እየሆነ ነውና የሃይማኖቱን መርሕ ጠብቀን አስተዳደራችን የሕግ የበላይነትን ያረጋገጠ፣ ግልጽ፣ ተአማኒና ተጠያቂነትን ያሰፈነ የምእመናንን ልብ የሚያረካ፣ ምእመናን በቤተ ክርስቲያናቸው ኵራት እንዲሰማቸው የሚያስችል አሠራር ብናረጋግጥ ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ እንችላለን፤
• ይህ ሲሆን ነው የሰበካ ጉባኤ ዐላማ ግቡን የሚመታው በእርግጠኝነት ለመናገር እንደ ጌታችን አስተምህሮ ሕፃናትን፣ ወጣቶችንና ዐዋቂዎችን በአግባቡ ጠብቃ የምትኖር ቤተ ክርስቲያን ለሃይማኖት ቅሰጣ አትጋለጥም ፡፡

ስለሆነም የሰበካ ጉባኤ ዋና ምንጭ ምእመናን መሆናቸውን ዐውቀን በዚህ ዙሪያ በሰፊው እንሥራ፤ ቢቻል አሁን አለን ከምንለው የላቀ የምእመናን ቊጥር በበለጠ ለማሳደግ ከፍተኛ ጥረት ማድረግ፣ ባይሆን ደግሞ ባለበት ጠብቆ ለማቆየት በርትተን መሥራት ይጠበቅብናል ፡፡

በመጨረሻም፡ ይህ ዓለም አቀፋዊ የቤተ ክርስቲያን ጉባኤ ከየአቅጣጫው የሚቀርቡትን ሪፖርቶች በመገምገም፣ ለበጀት ዓመቱ ሥራችን መሠረት የሚሆኑ የዕቅድ አመላካች አስተያየቶችና ሐሳቦችን በማስቀመጥ፣ እንደዚሁም የሀገራችንን የሕዳሴ ጒዞ በተያዘለት መርሐ ግብር መሠረት ግቡን እንዲመታ ሕዝቡን ለማነሣሣት ቃል በመግባት የሚጠበቅበትን ሁሉ እንዲያደርግ መልእክታችንን በቤተ ክርስቲያን ስም እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ፣ ይቀድስ አሜን፡፡ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፡፡