መስከረም 16 ቀን 2008 ዓ/ም የመስቀል ደመራ በዓል (የእስክንድርያ ፓትርያርክ መገኘት ጋር)
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
“ወደምሰሰ ለነ መጽሐፈ ዕዳነ በሥርዐቱ እምእድውነ ወአእተቶ እማእከሌነ ወቀነዎ በመስቀሉ —
በእኛ ላይ የነበረውን የሚቃወመንንም በትእዛዝ የተጻፈውን የእዳ ጽሕፈት ደመሰሰው፡፡ እርሱንም በመስቀል ጠርቆ ከመንገድ አስወግዶታል” (ቆላ. 2፥14)።
የተወደዳችሁ በዚህ በዓል ላይ የተገኛችሁ ሁሉ፤
እንኳን ለጌታችንና ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ መስቀል በሰላም አደረሳችሁ
በቅድስት ቤተ ክርስቲያን ከሚከበሩት ታላላቅ በዓላት አንዱ በዓለ መስቀል ሲሆን ስለ መስቀል መናገር ማለት ስለ ሰው ልጅ የድኅነት ታሪክ መናገር ነው፡፡ መስቀሉ የመዳናችን ብቻ ሳይሆን የሕይወትና የድል አድራጊነት ምልክታችንም ነውና፡፡ በመስቀሉ ዕርቅና ሰላም፣ ነፃነትና ተስፋ ይሰበካሉ፤ ቅዱስ መስቀል ዕርቅ የተፈጸመበት አደባባይ፣ አማናዊው የሐዲስ ኪዳን መሥዋዕት የተሠዋበት መንበር ነው፡፡ በመስቀሉ ጌታችን በሰው ላይ የተፈረደውንና የሕይወት ዕንቅፋት የነበረውን ሞትን በራሱ መሣሪያ አቅርቦ ከመንገድ ያስወገደበት፣ እርሱ ጌታችን የሕይወት ንጉሥ ሆኖ የነገሠበት ዙፋን ነው፡፡የተቀደሰ ነው የምንለውም በክርስቶስ ደም የተቀደሰ ስለሆነ ነው፡፡
ጌታችን እኛን ከሰይጣን ቍራኝነት ነፃ ያወጣን፤ ወደራሱ ያቀረበን፣ ጠብን እንድናሳድድ ጥላቻን እንድናስወግድ፣ከጥፋት እንድንድን ያደረገን በመስቀሉ ስለ ሆነ ይህ በዓል ለእኛ የድኅነታች ማስታወሻ አድርገን እናከብረዋለን፤ ከቅዱሳት መጻሕፍትና ከታሪክ እንደምንረዳው ጌታችንን የሰቀሉት አይሁድና የወቅቱ መሪዎች ከሙታን መነሣቱ ስለቈጫቸው የተሰቀለበትን መስቀል ዓለም እንዳያስታውሰው ቀበሩት፡፡ ይሁን እንጂ በመስቀሉ የተፈጸመውን ድኀነትና ፍቅር መቅበር ስላልቻሉ፤ፍቅሩ በልባቸው የታተመው ክርስቲያኖች በንግሥት እሌኒ መሪነት ከሦስት መቶ ዓመት በኋላ ቅዱስ መስቀሉን ከተቀበረበት አወጡት፡፡ አስቀድሞ በመስቀሉ የተገኘውን ድኅነትና ሰላም፣ የተገለጸው ፍቅር፣ የተደመሰሰው የዕዳ ጽሕፈት፣ የተወገደው ጥላቻና ሞት በሰው ልጅ ሕይወት ውስጥ ዋና ጉዳዮች ስለሆኑ በክርስቲያኖች ዘንድ መስቀሉን ማክበር ተቋርጦ ዐያውቅም፡፡ እኛም በሀገራችን በአንድነትና በፍቅር ሁነን ጥንታዊ ትውፊቱን በጠበቀ መልኩ በዓለ መስቀሉን በአደባባይ ወጥተን ደመራ ደምረን እያከበርን እንገኛለን፡፡
የዘንድሮውን የ2008 ዓ/ም በዓለ መስቀል ልዩ የሚያደርገው ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ታዋድሮስ ዳግማዊ የእስክንድርያ ፖፕና የመንበረ ማርቆስ ፓትርያርክ ከግብጽ ሀገር በመምጣት በመካከላችን መገኘታቸውና በዓለ መስቀሉ በዩኔስኮ የዓለም ቅርስ ሁኖ በተመዘገበበት ማግስት መሆኑ ነው፡፡
በዚሁ አጋጣሚ ብፁዕ ወቅዱስ ፖፕ ታዋድሮስ ዳግማዊ ጥሪያችንን ተቀብለው በመምጣታቸው የተሰማኝን ደስታ እየገለጽኩ በድጋሚ እንኳን ደኅና መጡ እላለሁ፡፡ እንደሚታወቀው በኢትዮጵያና በግብጽ መካከል ለብዙ ዘመናት የቆየ ግንኙነት ያለሲሆን፣ ግንኙነቱ በእግዚአብሔር ፈቃድና በተፈጥሮ ላይ የተመሠረተ ነው፡፡ ይህ ግንኙነት ቆይቶ ወደማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ሃይማኖታዊ ግንኙነት እያደገ አሁን ያለበት ደረጃ ላይ ደርሷል፡፡ ቀደም ሲል እንደተባለው ግንኙነቱ የተመሠረተው በተፈጥሮ ላይ ስለሆነ ወደፊትም አይቋረጥም፡፡ ለዚህ አንዱ ምሳሌ የዐባይ ወንዝ ነው፡፡ ይህ በቅዱሳት መጻሕፍት ሳይቀር ስሙ የተጠቀሰው ታላቁ ወንዝ ለዘመናት ሁለቱን ሀገሮች እያጠጣ ይገኛል፡፡
በአሁኑ ጊዜ ኢትዮጵያውያን ከራሳቸው አልፎ ለጎረቤት ሀገሮች ሳይቀር የሚጠቅም ግድብ እየሠሩ ይገኛሉ፡፡ የግድቡ መገንባትም በማንም ላይ ጒዳት እንማያደርስ በዓለም ዐቀፍ ባለሙያዎችም ጭምር መረጋገጡ ሁላችንም ያስደሰተ ጉዳይ ሆኗል፡፡ በወንድም ላይ ጒዳት ሳያደርሱ ራስን መጥቀም ደግሞ ወገናችን የሆነው የግብጽ ሕዝብ ብቻ ሳይሆን ፈጣሪንም የሚያስደስት የሥነ ልቦና ነፃነትን የሚሰጥ ሰላማዊ ተግባር ነው፡፡ ከዚህ ባሻገር የመስቀል በዓልን ስናከብር ፍቅርን ወዳጅነት እንደምንዘክር ሁሉ የቅዱስነታቸውም በመካከላችን መገኘት ለሁለቱ ሀገሮች ሕዝቦች የወደፊት ትብብር ብቻ ሳይሆን የሃይማኖት አባቶች ለዓለም ሰላምና ደኅንነት ለምናሰማው የጋራ ድምፅ ከፍተኛ አስተዋፅኦ ይኖረዋል፡፡ በተለይ በአሁኑ ጊዜ ባለ መቻቻል፣ በጽንፈኝነት፣ በሕገ ወጥ የሰዎች ዝውውር፣ በስደት፣ በእርስ በእርስ ጦርነት፣ በአየር ንብረት ለውጥ፣ እና በመሳሰሉት ተፈጥሯዊና ሰው ሠራሽ ችግሮች የሰው ልጅ ሕይወት ለአደጋ በተጋለጠባቸው የዓለማችን ክፍሎች መፍትሔ ለመስጠት የሚመለከታቸ ሁሉ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፡፡
በቅርቡ ከሀገራቸው የወጡ የኢትዮጵያና የግብጽ ወጣቶች የዚሁ ችግር ሰማዕታት ሲሆኑ የሁለቱም ሀገሮች አባቶች ተመሳሳይ መልእክትን ለዓለም አስተላልፈዋል፡፡ ኢትዮጵያውያንና ግብጻውያንም በችግርና በደስታ ያለቸውን አንድነት ገልጸዋል፡፡ ከወራት በፊት ቅዱስነታቸው ባስተላለፉልን ጥሪ መሠረት ከብፁዓን አባቶች ጋር በመሆን ግብጽን የጎብኝን ሲሆን አሁን ደግሞ እኛ ባቀረብንላቸው ጥሪ መሠረት ወደ ሀገራችን መጥተው በመካከላችን ተገኝተዋል፡፡ ቅዱስነታቸው በኢትዮጵያ የሚኖራቸው ቆይታ ታሪካዊ እንደ ሚሆንና የሁለቱን ሀገሮች መልካም ግኑኝነት የበለጠ እንደሚያጠናክር ጽኑ እምነት አለን፡፡
በዓሉን የሰላምና የፍቅር ያድርግልን፣ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይጠብቃችሁ፣ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ