ከጥቅምት 12 እስከ 21 ቀን 2006 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቊጥር 164 በተደነገገው መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የመክፈቻው ሥርዐተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2006 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ጥቅምት 21 ቀን 2006 ዓ.ም. ድረስ ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባን በማካሄድ፤ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለኅብረተሰቡ የሚጠቅመውን፤ ለሀገርና ለዓለም ሰላም የሚበጀውን አጀንዳ በማመቻቸት በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ የሚከተለውን ውሳኔ አሳልፏል፤

1. የ32ኛው አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ውሳኔና የጋራ መግለጫ በምልአተ ጉባኤ የ2006 ዓ.ም. የሥራ መመሪያ እንዲሆን ጸድቋል፤

2. ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ጽ/ቤት ድረስ በባለሙያዎች ተጠንቶ የቀረበውና በስላይድ የታየው የሥራ መዋቅር ወደታች ወርዶ በካህናት፣ በምእመናንና በሰንበት ትምህር ቤት ወጣቶች በውይይት ዳብሮ በሚገባ ተጠንቶና ተስተካክሎ ለቋሚ ሲኖዶስ እንዲቀርብና ቋሚ ሲኖዶሱም አይቶና ተመልክቶ በሥራ ላይ እንዲያውል ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፤

3. ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በልማት ዘርፍ ዙሪያ የምታደርገው እንቅስቃሴ በማእከልም ሆነ በየአህጉረ ስብከቱ በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፤

4. የአብነት ትምህርት ቤቶችንና የካህናት ማሠልጠኛ ማዕከላትን፤ በጥንታዊነታቸውና በታሪክ መዘክርነታቸው ዕውቅና ያላቸውን ገዳማት፤ ወላጅ አልባ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት እየተማሩ የሚያድጉበትንና ሴቶች መነኰሳዪያት በምናኔ የሚኖሩባቸውን ገዳማት በበለጠ እንዲጠናከሩ ማድረግ የታመነበት ስለሆነ፤ ለዚሁ አገልግሎት የሚውል በጀት በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር ተጠንቶ ይቀርብ ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል መመሪያን ሰጥቷል፤ አሁንም በድጋሚ መመሪያውን አጽንቷል፤

5. የዓለምን ሰላም፤ ፍቅር አንድነትን ጠብቆ መገኘት የሁሉም ዜጎች ኀላፊነት ስለሆነ ሁሉም ኅብረተሰብ አንድነትን ፈጥሮ አሁን በሀገራችን እየታየ ያለውን አክራሪነትና ጽንፈኝነትን በመቃወም ሰላምን የማስፈን ግዴታውን እንዲወጣ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤

6. ከሀገራችን ውጭ ወደ ውጭው ዓለም ሕጋዊ ባልሆነ መንገድ የሚደረገው ፍልሰት የዜጎችን ሕይወት እየቀጠፈ በሀገርም ላይ ከፍተኛ ቀውስ እያስከተለ መሆኑ ስለሚታወቅ የችግሩን አስከፊነት ኅብረተሰቡ እንዲያውቀው በቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊው ትምህርት እንዲሰጥ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፤

7. የእናቶችና የዕጓለ ማውታ ሕፃናት፣ የአረጋውያንና የአረጋውያት፤ የሁሎችም ፍላጎት ተሟልቶ መኖር ይቻል ዘንድ ኅብረተሰቡ ትኵረት እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤

8. ሀገራችን ኢትዮጵያ ከኤች አይ ቪ ኤድስ በሽታ፣ ከድንቊርና፣ ከድህነትና ኋላ ቀርነት ተላቅቃ ዓለም ወደ ደረሰበት መድረስ የምትችለው ማንኛውም ወገን ተቻችሎና ተከባብሮ ለሰላምና ለልማት ሥራ ሲነሣሣ ስለሆነ፤ ይኸው ታውቆ ሁሉም የየበኩሉን ድርሻ እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡

9. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን በርካታ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ ሥነ ሥዕልና ኪነ ጥበብ ቅርሶችና ሀብቶች ባለቤት መሆንዋ የታወቀ ስለሆነ፤ የእነዚህ የቤተ ክርስቲያኒቱ የዜማ መጻሕፍት፣ የትርጓሜ መጻሕፍት፣ የሕንጻዎች፣ የቋንቋ በአጠቃላይም ብሔራዊው የአእምሮ ንብረት ባለቤትነት መብቷ በሕግ ይከበር ዘንድ በቅርስ ጥበቃና ምዝገባ በቤተ መጻሕፍት ወመዘክር መምሪያ ተከታታይነት ጉዳዩ ለሚመለከተው የፍትሕ አካል ቀርቦ ውሳኔን እንዲያገኝ፤

10. የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኵስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የሢመተ ፓትርያርክነት በዓል እንደ ቀደሙት ቅዱሳን ፓትርያርኮች የተሾሙበት ዕለት በየዓመቱ የካቲት 24 ቀን እንዲከበር የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወስኗል፤

11. ስለ ኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ታሪካዊነትና ቀዳሚነት ሁሉም ሰው መጻፍ ሲገባው እውነት ያልሆነውን በማስመሰል የሚነገረውን፣ የሚጻፈውን እውነታውንና ትክክለኛውን አስተካክሎ ለሕዝብ ለትውልደ ትውልድ ማስተላለፍ እንዲቻል መነሻ ይሆን ዘንድ በብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የኮሚቴ አባልነት ተጠንቶ የቀረበውን ጽሑፍ ምልአተ ጉባኤው በንባብ ሰምቶ ጉዳዩ ወደ ሊቃውንት ጉባኤ ቀርቦ የሊቃውንት ጉባኤውም ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊነትና ታሪካዊነት አብራርቶ፣ አስፍቶና አጒልቶ ለ2006 ዓ.ም. ለርክበ ካህናት ጉባኤ እንዲያቀርብ ወስኗል፤

12. የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የቅዱስ ፍሬምናጦስ አባ ሰላማ ከሣቴ ብርሃን መንፈሳዊ ኮሌጅ፣ የሰዋስወ ብርሃን ቅዱስ ጳውሎስ መንፈሳዊ ኮሌጅ የሦስቱም የቤተ ክርስቲያኒቱ መንፈሳውያን ኮሌጆች በጀታቸው ተጠቃልሎ ወደ ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ ገቢ እየሆነ በጀታቸውንም ጠቅላይ ቤተ ክህነቱ እየበጀተ እንዲከፍል ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ወስኗል፤ ከዚህም ጋር በቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅ ሥር የሚተዳደረው ከኮሌጁ ጋር ተያይዞ የሚገኘው አዲሱ ትልቁ ሕንጻ በጠቅላይ ቤተ ክህነት ቤቶችና ሕንጻዎች፤ አስተዳደርና ልማት ድርጅት ሥር ሁኖ የሕንጻዎቹ ወርኃዊ የኪራይ ገቢም በሕጋዊ መንገድ እንዲሰበሰብ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፤

13. የቤቶችና ሕንጻዎች አስተዳደር ድርጅትን በተመለከተ በሚፈርሱ ቤቶች ምትክ ቸል ሳይባል በትጋትና በንቃት የመልሶ ማልማቱ የሕንጻ ግንባታን ለማካሄድ የሚያግዝ ገንዘብ ማግኘት እንዲቻል ለየአህጉረ ስብከት፣ ለአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናትና በጠቅላይ ቤተ ክህነት ሥር ላሉ የልማት ድርጅቶች የአክስዮን ሽያጭ እንዲደረግ ተወስኗል፤

14. ቤተ ክርስቲያኒቱ በሥሯ ያሉ ምእመናኖቿን በትክክል ቈጥራ መመዝገብ እንድትችል በሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ በኩል ቅጽ ተዘጋጅቶ በየአንዳንዱ ሀገረ ስብከት ኀላፊነት ቈጠራው በየአህጉረ ስብከቱ እንዲካሄድ ተወስኗል፤
15. ስለ ሰንበት ት/ቤቶች ውስጠ ደንብ ተጠንቶ የቀረበው መመሪያ ጸድቆ በሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፤

16. በጉጂ ዞን ነገሌ ቦረናና የሲዳማ ዞን አህጉረ ስብከትን በተመለከተ በሁለት ተከፍለው ያለመግባባት ችግር ፈጥረዋል በሚል የተነሣው ሁከት ዓመታትን ካስቈጠረ በኋላ ችግሩን የፈጠሩት የሁለቱም ወገኖች ጉዳዩ በዕርቅ እንዲፈጸም ጥያቄ በማቅረባቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የዕርቀ ሰላሙን ሂደት የተቀበለ በመሆኑ ከቦታው ላይ ተገኝተው ዕርቀ ሰላሙን የሚያወርዱ ብፁዓን አባቶችን ሰይሟል፤ (ሀ) ብፁዕ አቡነ ማትያስ የካናዳ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ (ለ) ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳትና የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ (ሐ) ብፁዕ አቡነ ሉቃስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊና በክልል ትግራይ የምዕራብ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በመሆን ስምምነቱንና ዕርቀ ሰላሙን አስፈጽመው የመጨረሻ የዕርቁን ሰነድ ለጉባኤው እንዲያቀርቡ ተወስኗል፤

17. የጣና ቂርቆስ ገዳም አንጡራ ሀብት የሆነው መስቀለ ያሬድ ተሰርቆ ወደ ውጭ ተወስዶ ከቆየ በኋላ ወደሀገሩ ተመልሶ በመንበረ ፓትርያርክ ቤተ መጻሕፍት ወመዘክር ስለሚገኝ ገዳሙ መስቀሉ እንዲሰጠው በጽሑፍ በመጠየቁ ምልአተ ጉባኤው እንዲሰጥ ወስኗል፤

18. የብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ጳውሎስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ልዩ ልዩ ፎቶ ግራፎች፣ መጻሕፍትና የተለያዩ ንዋያተ ቅድሳትና አልባሳት የመሳሰሉትን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ኀላፊነት ወስዶ ኑዛዜም ካለ ሁሉንም እየመረመረና እያጣራ ለየሚመለከታቸው እንዲሰጥ ይደረግ ዘንድ ምልአተ ጉባኤው ወስኗል፤

19. ቤተ ክርስቲያናችን ወደፊት የምታከናውነውን ማኅበራዊና መንፈሳዊ አገልግሎት በዕቅድ የሚመራ እንዲሆን ለማስቻል በግንቦቱ ርክበ ካህናት ጉባኤ 2005 ዓ.ም. ተቋቁሞ የነበረው ኮሚቴ ያዘጋጀውን ጥናት ለጉባኤው አቅርቦ ጉባኤው ማብራሪያውን ካዳመጠ በኋላ ኰሚቴው ያላለቁ ሥራዎችን እንዲቀጥል በማለት መመሪያን ሰጥቷል፡፡

20. በጥንታዊቷ፣ በታሪካዊቷ በርእሰ አድባራት ወገዳማት አክሱም ጽዮን ቤተ ክርስቲያን ዐውደ ምሕረት በመሠራት ላይ ያለው ቤተ መጻሕፍት ወመዘክሩ ግንባታን አስመልክቶ ከዐቢይ ኮሚቴው በቀረበው ሪፖርት ላይ በመነጋገር በቀጣይ የገቢ ማሰባሰቢያ ስልቶችን ያስቀመጠ ከመሆኑም በላይ ለጊዜው ለተቋራጩ ብር 5,000,000 (አምስት ሚሊዮን ብር) እንዲሰጠውና የቆመው የግንባታ ሥራ እንዲቀጥል ወስኗል፤

21. በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተጠንቶ እንዲቀርብ ስለታዘዘው የማኅበረ ቅዱሳን ደንብ ደንቡን እንዲያጠና የተመደበው ኮሚቴ ጥናቱ ለጊዜው ያልደረሰለት መሆኑን ስለገለጸ ለግንቦት ርክበ ካህናት 2006 ዓ.ም. ጥናቱ ተጠናቆ ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ እንዲቀርብ ጉባኤው ትእዛዝ ሰጥቷል፤

22. የቅድስት ሥላሴ መንፈሳዊ ኮሌጅን በተመለከተ ኮሌጁን ማጠናከር አስፈላጊ ሆኖ በመገኘቱ ለኮሌጁ ዋና ዲን እንዲሾም ጉባኤው ውሳኔን አሳልፏል፤

23. ገዳማቱን መልሶ ማቋቋምና ማጠናከር ብሎም በነበሩበት ሁኔታ አደራጅቶ ሥራቸውን መቀጠል ይችሉ ዘንድ የሚያመለክት በመምሪያው በኩል ሰፊ ጥናት የተደረገ በመሆኑ ገዳማቱ የሚገኙትም በየአህጉረ ስብከቱ ስለሆነና ብፁዓን አበው የሌሉበት ጥናትም አጥጋቢ ውጤት ስለማይኖረው የተወሰኑ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ከመምሪያው ተጠሪ ጋር ተገናኝተው ገዳማቱ እንዴት መቋቋምና መልማት እንዳለባቸው ጥናት ይደረግበት በሚለው ጉባኤው ተስማምቶ ጠለቅ ያለ ሐሳብ ከነመፍትሔው አጥንተው ለግንቦቱ 2006 ዓ.ም. ርክበ ካህናት ዓመታዊ ጉባኤ እንዲያቀርቡ፤ (1) ብፁዕ አቡነ ኤጲፋንዮስ የምዕራብ ሸዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን (2) ብፁዕ አቡነ ሳሙኤል የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽን ሊቀ ጳጳስና የሕንጻዎችና ቤቶች አስተዳደር ድርጅት የበላይ ኀላፊን (3) ብፁዕ አቡነ ቀሌምንጦስ የከምባታ ሐዲያና ጉራጌ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስን በመምረጥ ምልአተ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተስማምቶ ወስኖአል፡፡

24. የመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ሕንጻ ከጊዜ ብዛት የተነሣ ውኃ በማስገባቱ እድሳት የሚያስፈልገው ስለሆነ የእድሳቱም ጥናት በመቅረቡ የካቴድራሉ ሕንጿ የቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንና የሀገር ቅርስ እንዲሁም የቱሪስቶች መዳረሻ በመሆኑ የውስጥና የውጭ ቁመናውን እንደያዘ በጥንቃቄ እድሳቱ እንዲደረግ ጉባኤው ወስኗል፤

25. በውጭ ሀገር ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም ወደፊት እንዲቀጥልና የቤተ ክርስቲያኒቱ አንድነት እንዲጠናከር ጉባኤ ተስማምቷል፤

26. በውጭው ዓለም ገለልተኛ አብያተ ክርስቲያናት ነን በሚል የሚገኙ ወገኖች ወደ እናት ቤተ ክርስቲያናቸው እንዲመለሱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ጥሪውን አቅርቧል፤

27. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ጥንታዊትና ታሪካዊት እንደመሆኗ ሁሉ በቀጣይም አጠቃላይ ማኅበራዊም ሆነ መንፈሳዊ ሥራዎቿን በመሪ ዕቅድ በመምራት ሙስናና የመልካም አስተዳደር እጦትም ከሥሩ መቅረፍ እንዲቻል በባለሙያዎች የተጠናውን የመሪ ዕቅድ ዘገባ በመገምገም በቀጣይ ዕቅዱ ዳብሮ በሥራ መተርጐም በሚቻልበት ሁኔታ ተዘጋጅቶ እንዲቀርብ ጉባኤው መመሪያ ሰጥቷል፤

28. አሁን ያለው ሕገ ቤተ ክርስቲያን ተሻሽሎ እንዲቀርብ በተወሰነው መሠረት የተሻሻለው ረቂቅ ሕገ ቤተ ክርስቲያን የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት እንዲመለከቱት ረቂቁ የታደለ ሲሆን እንዲሁም በሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ታይቶና ሐሳብ ተሰጥቶበት በ2006 ዓ.ም. በግንቦት ርክበ ካህናት ውይይት እንዲካሄድበት ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፤

ቅዱስ ሲኖዶስ ከላይ በተገለጹትና በሌሎችም መንፈሳውያንና ማኅበራውያን ጉዳዮች ላይ ለዐሥር ቀናት ያህል ሲወያይ ሰንብቶ አስፈላጊውን በመወሰን መደበኛ ስብሰባውን በዛሬው ዕለት በጸሎት አጠናቅቋል፡፡

ቸሩ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን፣ ለሕዝባችን፣ ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ምሕረቱንና ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ይባርከን፤ ይቀድሰን፤ አሜን፡፡

ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ቸርነት ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን፣ ሁላችንንም ከምናገለግልበት ሀገረ ስብከት አሰባስቦ፣ ከዚህ ቅዱስ ጉባኤ በአንድነት ስላገናኘን ከሁሉ በፊት እርሱን እናመሰግናለን፡፡

“ወይእዜኒ አዕብይዋ ወአብድርዋ ለትምህርተ ተስፋክሙ
አሁንም ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ያላት ትምህርተ ወንጌልን ውደዷት፤ ከፍ ከፍም አድርጓት።”
(ዕብ. 12፥5)

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት

የዛሬው ጉባኤያችን፣ በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት፣ ወቅታዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮችን በማንሣት ለመወያየትና፣ መንፈስ ቅዱስ በሚገልጽልን መንፈሳዊ ጥበብ እየተመራን፣ መፍትሄ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች፣ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሆነ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ በአሁኑ ጊዜ በጥልቀት፣ በማስተዋልና የኀላፊነት መንፈስ በተላበሰ ወኔ፣ አጥብቆ ሊወያይባቸውና ሊወስንባቸው፣ ከውሳኔ በኋላም ለተግባራዊነታቸው ሊረባረብባቸው የሚገቡ፣ በርከት ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡

ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቤተ ክርስቲያንን በሐዋርያት ላይ ሲመሠርት፣ በእነርሱ ሥልጣነ ክህነት አማካኝነት፣ ቃሉን ወደ ዓለም ሁሉ ለማዳረስ እንደሆነ አንሥተውም፣ ቅዱሳን ሐዋርያትም፣ በሥልጣነ ክህነት እኛን ተክተዋል በመሆኑም እኛ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሐዋርያት የሆነውን ሁሉ ለመፈጸምና ለማስፈጸም፣ የእነርሱን ሥልጣን ወራሾች ሆነን በመንፈስ ቅዱስ ተሰይመናል፡፡ የቅዱሳን ሐዋርያት ተቀዳሚ ተልእኮ፣ በድንበር ሳይገደቡ፣ ስብከተ ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ማስተማር ነው የሐዋርያት ቀዳሚ ተግባር ይህ ከሆነ፣ የኛም ቊጥር አንድ ሥራ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ነው።

ከትንሹ የሥልጣነ ክህነት ሹም ጀምሮ እስከ ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣን ያለው ሁሉ፣ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ተልእኮ በንቃት፣ በሙሉ ዕውቀት፣ በተነሣሽነት፣ በፍጹም ፈቃደኝነት እንዲነሣሣና እንዲሰለፍ በማድረግ ረገድ፣ የሚጠበቀውን ያህል ተሠርቶአል ማለት ያስቸግራል በየትም ሀገር የማይገኝ ቊጥሩ እጅግ በርካታ የሆነ ካህን ያላት ቤተ ክርስቲያናችን በጥምቀት ወልዳ፣ በሥጋ ወደሙ አሳድጋ፣ ገብረ ሥላሴ፥ ገብረ እግዚአብሔር፥ ወልደ ማርያም፣ ገብረ ሚካኤል ብላ የሰየመቻቸው ልጆችዋ፣ ከጒያዋ እየተነጠቁ ወደ ሌላ ካምፕ ሲወሰዱ እርስዋ የወላድ መኻን የሆነችበት፣ ያልወለዱና ያላሳደጉ ባለ ብዙ ቤተሰብ የሆኑበት ክሥተት እያጋጠመ ነው፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ ባለው ኀላፊነት፣ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን፣ ለዚህ መሠረታዊና ወቅታዊ ጉዳይ፣ ፈጣን፣ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ ሊፈልግለት ይገባል

ቅዱስ ሲኖዶስ በሥሩ ያሉትን በጎች መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ድንበር የለሽ ስብከትና ትምህርት በማካሄድ፣ ከዛሬ ጀምሮ በየዓመቱ በርከት ያሉ በጎችን የማርባትና የመጠበቅ ሥራ ሊያሠራው የሚችል አሠራር መቀየስ ይገባዋል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሐዋርያትን በመምህርነት ወደ ዓለም ሲልክ፣ በቅድሚያ አስተምሮ፣ አሳምኖ፣ አሠልጥኖ፣ መከራ እንደሚኖርም ገልጾ ነው፡፡ እኛም ለስብከተ ወንጌል የምናሰማራቸውና የምንሾማቸው ዲያቆናት፣ ቀሳውስትም ሆኑ ኤጲስ ቆጶሳት በተለምዶ የተሾሙ ሳይሆኑ፣ ጌታችን እንዳዘዘው የተማሩ፣ የሠለጠኑ፣ ነገሩ የገባቸውና መከራውን ለመቀበል የተዘጋጁ ሊሆኑ ይገባል

ይህንም ግንዛቤ በሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን አእምሮ ለማሳደር የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን፣ የማሠልጠኛዎቻችንና የከፍተኛ ትምሀርት ተቋሞቻችን በብዛትም፣ በጥራትም በአደረጃጀትም ተማሪውን በትክክል ለመለወጥና ለመቅረጽ በሚያስችል አዲስ አሠራር፣ ማስተካከልና ማብቃት አለብን እነዚህ የትምህርት ተቅዋማት ሰባክያንና መምህራን የሚፈልቁባቸው የሃይማኖታችን ምንጮች ናቸው ምንጩ ድፍርስ ከሆነ የጠማው መንገደኛ ውኃ ለመጠጣት ይቸገራል ጥሩ ምንጭ ከሆነ ግን የጠማው ብቻ ሳይሆን ያልጠማው መንገደኛም ቢሆን በውሀው ጥራት ከመጎምጀቱ የተነሣ ሳይቀምሰው አያልፍም፡፡

ቤተ ክርስቲያናችን የሃይማኖት እንከን ሳይኖራት፣ ሙያ ሳያንሳት፣ ተቈርቋሪ ምእመናን እያሏት በአያያዝና በአመራር ምክንያት የምትወቀሥበትና ልጆችዋን የምታጣበት ታሪክ መገታት አለበት፣ ይህንንም በወሳኝ መልኩ ለማስተካከል ቅዱስ ሲኖዶስ የትምህርት ቤቶቻችንን ትንሣኤ የሚያበሥር፣ እድገታቸውንና ጥራታቸውን የሚያፋጥን ጠንካራ መሠረት ዛሬ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ከጌታችን አሠራር አብነት ወስደን ስናይ፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ፣ ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሲያሰማራ፣ ቀዋሚ ሀብት እንዲኖራቸው አልፈቀደም፣ ሆኖም ምግብ፣ ልብስና መጠጥ ለሥጋዊ ሕይወት ህልውና እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ “ለሠራተኛ ደመወዝ ይገባዋል” ብሎ ከማስተማሩም በላይ፣ ይህን የምግብ አቅርቦት ካስተማሩዋቸው አማንያን ማግኘት፣ እንዳለባቸው በማብራራት “ያቀረቡላችሁን ብሉ” ብሎ አዞአል፡፡ (ሉቃ. 10፥7-9)

ከላይ እንደተጠቀሰው የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን እኛ የሚፈለገውን ያህል ተደራጅተን፣ መስለን ሳይሆን ሆነን፣ በሁሉም ነገር ተዘጋጅተን ባለማስተማራችን የሚጠበቅባቸውን ዐሥራት፣ በኵራትና ቀዳምያት በሕጉ መሠረት እየሰጡ ነው ባይባልም፣ በተለያየ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ስጦታ፣ ዘመኑ በሚፈቅደው የፋይናንስ አያያዝና ቊጥጥር ባለመያዛችን፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥራ ከሚውል ይልቅ በየመንገዱ እየተንጠባጠበ፣ ወፎች የሚለቃቅሙት እንደሚበዛ፣ ፍጹም የማካይድ ሐቅ ነው በሌላ በኩል፣ በአድልዎና ከወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቀው አስተዳደራችን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅነትና ተሰሚነትን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑ፣ አሌ ልንለው አይገባም፡፡

ስለሆነም በፋይናንስ አያያዝና በመልካም አስተዳደር ዙሪያም ይህ ጉባኤ ጥበብ ማስተዋል ያልተለየው፣ የማፍረስ ሳይሆን የመገንባት ግብ ያለው ራእይ አንግቦ ሥር ነቀል የሆነ የፍጹም እድገት ለውጥ ማምጣት የሚያስችለውን አሠራር መቀየስ ይገባዋል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

በዘመናዊ የአመራር ጥበብ እይታ፣ ከመልካም አስተዳደር አንዱና ምናልባትም ዋነኛው መስፈርት፣ አሳታፊነት እንደሆነ ግልጽ ነው በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለለውጥና ለተሻለ እድገት የሚወስናቸው፣ ሀገር ዐቀፍና ታላላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች የየክፍሉ ኀላፊዎችን፣ ሊቃውንቱን፣ የምእመናን ተወካዮችን፣ የካህናት ተወካዮችን፣ የወጣቶች ተወካዮችን በማሳተፍ ወይም በሌላ አባባል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ፣ ሐሳባቸውንም እያዳመጠ ቢሠራ፣ በመጨረሻም ባለው ሐዋርያዊ ሥልጣን በዚህ ጉባኤ አጽድቆ ሥራ ላይ ቢያውል ይበልጥ ብዙ ደጋፊና ረዳት፣ እንዲሁም ከዳር እስከ ዳር ብዙ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል

ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ሳያደርግ፣ ሁሉንም ነገር፣ ብቻው ሆኖ የሚሠራና የሚወስን ከሆነ፣ የሕዝቡና የካህኑ ድጋፍ ይቀንስበታል በትክክል መግባባትም አይቻልም ለበጎ ተብሎ የተደረገው ነገር ሁሉ በሌላ አባባል ተገልብጦ እየተተረጐመ የሚረዳም የሚያስረዳም ስለማይኖር፣ በአዙሪት ማዕበል ከመንጓለል በቀር፣ የምናመጣው ለውጥ ይኖራል ብሎ መገምት ያዳግታል

ስለሆነም ሕዝቡንና ካህናቱን እንደዚሁም ባለ ድርሻ አካላትን እያሳተፉ መሥራትና መወሰን፣ የአሉባልተኞችን ሤራ የሚያከሽፍ እንደሆነ ዐውቀን በተግባር ልንጠቀምበት ይገባል፡፡

ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

ሃይማኖትን ማስፋፋት፣ መማርም ሆነ ማስተማር፣ ሀብት ማግኘትም ሆነ በሰላም ማስተዳደር የመሳሰሉ ሁሉ፣ በአግባቡ ሊከናወኑ የሚችሉ፣ በሀገር ውስጥ ባሉ ሕዝቦች መካከል፣ እኩልነት፣ መከባበር፣ መቻቻል፣ መተማመን መፈቃቀር፣ መስማማት፣ አንድነት፣ ፍጹምና አስተማማኝ የሆነ ሰላም ሲሰፍን ነው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ መሠረት እነኝህን ጠብቆ በማስጠበቅ ረገድ ኀላፊነቱን የሰጠ በቤተ ክርስቲያን በኩል ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡

ስለሆነም ሁላችንም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ችግሮችን በውይይትና በውይይት ብቻ በጋራ የመፍታት ባህል መደገፍና በማጎልበት መሥራት አለብን እንደዚሁም በሀገራችን እየተከናወነ ያለውን የሰላም፣ የእኩልነት፣ የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመተማመን፣ የወንድማማችነት፣ የልማትና የእድገት ጅምር ሊፈታተኑ የሚችሉ የአክራሪነት፣ የአሸባሪነትና የጽንፈኝነት ተግባራትን በማውገዝ፣ የክርስቶስ መልእክት የሆነውን ሰላምና እኩልነት፣ መከባበርና መቻቻል፣ አብሮ መልማትና ማደግ ብቻ ለሕዝቡ በየቀኑ ልንሰብክና ልናስተምር ይገባል፡፡

በመጨረሻም ይህ መንፈስ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ ዐቢይ ጉባኤ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስፋፋ፣ ማኅበረ ካህናቱንና ማኅበረ ምእመናኑን የሚያስደስት፣ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ተከታይ ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቀውን የለውጥና የእድገት ጎዳና የሚከፍት፣ እንዲሆን በመመኘት፣ ንግግሬን እደመድማለሁ፡፡

እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ ይቀድስ
ሀገራችንን ኢትዮጵያ ይጠብቅልን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።

32ኛው የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የሰበካ ዓመታዊ ጉባኤ ከጥቅምት 4 እስከ 11 ቀን 2ዐዐ6 ዓ.ም. አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

“ከሁሉ በፊት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትና በቤተ ክርስቲያናችን የአመራር አካላት በሙሉ እንደተለመደው ሁሉ የቤተ ክርስቲያናችንን ጥሪ አክብራችሁ እንኳን በደኅና መጣችሁ፡፡

ይህ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ መደበኛ ጉባኤ ከተመሠረተበት ጊዜ ጀምሮ በአዲስ አበባ ርእሰ ከተማ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር በዓመት አንድ ጊዜ እየተሰበሰብን በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት በአጠቃላይም በሁለንተናዊ እድገት ላይ እየተወያየን የሚጠበቅብንን ግዳጅ ስንወጣ እነሆ! ዛሬ ለሠላሳ ሁለተኛው መደበኛ ስብሰባ ለመድረስ በቅተናል፡፡

በቃለ ዐዋዲው የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ እየታገዘ ሰበካ ጉባኤ አስተዳዳር ከሚሠራው የስብከተ ወንጌል ክፍል አንዱ አካል እንደሆነ ይታወቃል፡፡ ከዚህ አንጻር የቤተ ክርስቲያናችን የደም ሥር የሆነውን የስብከተ ወንጌሉን ተግባር ከመቼውም ጊዜ በበለጠ ማሳደግ ይጠበቅብናል፣ ለማስረጃም ያህል አንድ ሰው ሕይወት የምትሰጠው ነፍሱ ከተለየች በዓለም ላይ የመኖር ተስፋ ስለሌለው የሚጠብቀው ዕድል ወደ ዐፈርነት መለወጥ ብቻ ነው፡፡

እንደዚሁ ሁሉ ቤተ ክርስቲያናችን ከአጥቢያ ቤተ ክርስቲያን እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ ባለው መዋቅር በስብከተ ወንጌል ካልተጠናከረች የሚጠበቅባትን ያህል አበርክታለች ለማለት አያስደፍርም፣ እንግዲህ ይህ ታሪካዊ ጉባኤ ቤተ ክርስቲያኒቱን ሲጠብቅ እንደቆየ ሁሉ አሁንም የስብከተ ወንጌሉን ተግባር ለማጠናከር መቀጠል አለበት ስንል ቢያንስ ሦስት ዐበይት ነጥቦችን መጥቀስ ያስፈልጋል፡፡

ስብከተ ወንጌልን በተመለከተ፡- የስብከተ ወንጌል ሠራተኞች ብቃት ባላቸውና በሠለጠኑ መምህራን በተደገፈ የወንጌል ትምህርት መሠልጠን አለባቸው፡፡ እነዚህ ለተልእኮ የሚፋጠኑ አስተማሪዎች የቈራጥነት መንፈስ ያልተለያቸው፣ የተቈርቋሪነት ባሕርይ ያደረባቸው መሆን አለባቸው፡፡

የገንዘብ (ፋይናንስ) አስተዳደር ሁኔታን በተመለከተ፡- የፋይናንስ ዐቅምን ማጠናከር የስብከተ ወንጌሉን ተግባር በበለጠ ማፋጠን ያስችላል፡፡ የፋይንስ ዐቅም ባልጎለበተበት ሁኔታ የሥራውን ድኅንነት ለመቈጣጠርም ሆነ ሂደቱን ለማፋጠን አስቸጋሪ እንደሚሆን ስለሚታወቅ ነው፡፡ ስለዚህ ሌሎች አብያተ ክርስቲያናት በአሠራር እየቀደሙ የሚታዩት ተከታዮቻቸው የሚከፍሉትን የአስተዋፅኦ ገንዘብ በማጎልበት እንደሆነ ከጉባኤው አመለካከት ይሠወራል ብለን ባንገምትም በበኩላችንም ሕዝበ ክርስቲያኑን ጠንክረን ማስተማርና ማስተባበር ይጠበቅብናል፡፡

መልካም አስተዳደርን በሚመለከት፡- ኀላፊነት ሐቀኝነትና ተጠያቂነት የተሞላበት መልካም አስተዳደር ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት እስከ መንበረ ፓትርያርክ ድረስ እንዲሰፍን ማድረግ ተገቢነቱ አያጠያይቅም፡፡ መልካም አስተዳደር ከሌለ ሁሉም ነገር ከንቱ እንደሆነ እናምናለን፡፡ በቅዱስ መጽሐፋችንም ሲነገር የኖረ አሁንም እየተነገረ ያለ ስለሆነ ለመልካም አስተዳዳር መስፈን ምዕራፍ ከፋች በሆነችው ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ዙሪያ ልናደርገው የሚገባንን ምግባረ ሠናይ ሁሉ በመፈጸምና በማስፈጸም ለቤተ ክርስቲያናችን ያለንን ደጀንነት መግለጽ ይጠበቅበናል፡፡
ስለዚህ በዚህ ታሪካዊ ጉባኤ ላይ የተገኛችሁት፡- የየሀገረ ስብከቱ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች፣ የየአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ተወካዮች፣ በአጠቃላይም የጉባኤው ተሳታፊዎች ሁላችሁ ይህ ዓመታዊ የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ መደበኛ ጉባኤ ለግብ እንዲበቃ፣ የምታደርጉት ጥረት እንዲሳካ እንጸልያለን፡፡

እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ፡፡”