መስከረም 16 ቀን የ2006 ዓ.ም. የመስቀል ደመራ በዓል

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፣ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣ በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ በቅዱስ ደሙ ፈሳሽነት ከኀጢአት፣ ከሞተ ነፍስና ከሲኦል ግዞት ነፃ አድርጎ ያዳነን ጌታችን፣ አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ!!

‹‹መስቀል ዓለም የዳነበት የእግዚአብሔር ኀይልና ጥበብ ነው፤››
(1ቆሮ.1÷18-24)

የተወደዳችሁና የተከበራችሁ በመላ ኢትዮጵያና በተለያዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን ሆይ፡-

እኛ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማንያን፣ መስቀልን በታላቅ ድምቀት የምናከብርበት ዋናው ምክንያት፤ መስቀል ሰዎችን ለድኅነት፣ ዲያብሎስን ለሽንፈት ያበቃ የእግዚአብሔር ኀይልና ጥበብ በመሆኑ ነው፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን፣ ከሰው ልጅ ውድቀት ጀምሮ እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ድረስ በነበረው ዘመን፣ በኀጢአት ምክንያት ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ በሰው ላይ የሰለጠኑበት፣ ዲያብሎስ ኀጢአትን መሣርያ አድርጎ፣ በሞት አቀባይነት፣ ሰውን በሲኦል ውስጥ አጉሮ ያሠቃየበት ዘመን ነበረ፤ ሰው ለዚህ ዐይነቱ መከራ የተዳረገበት ምክንያት፣ የፈጣሪውን ትእዛዝ ተላልፎ በሠራው ኀጢአት በደለኛ ሆኖ በመገኘቱ ነው፤ በዚህም ተግባሩ እግዚአብሔር ተለየው፤ እግዚአብሔር ሰውን ሲለየው፣ ለሠራው ኀጢአት ቅጣት የሚሆን የሞት ፍርድም ፈርዶ ነው፤ ስለሆነም ሰው የተፈረደበት ጥፋተኛ በመሆኑ፣ ከፈጣሪው ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት አልነበረውም፤ ጠባቂ የሌላቸው በጎች፣ ለተኲላ ንጥቂያ የተጋለጡ እንደሚሆኑ ሁሉ፣ ሰውም እግዚአብሔር ሲለየው፣ ለዲያብሎስ የመከራ ግዛት የተጋለጠ ሆነ፤ ከአዳም ውድቀት እስከ ስቅለተ ክርስቶስ ባሉት ዘመናት፣ ሰው ሁሉ በፍዳ ኀጢአት እየተሰቃየ በዲያብሎስ ከተማ በሲኦል ውስጥ ግዞተኛ ሆኖ ቁም ስቅሉን አየ፤ (1ጴጥ. 3÷18-19 )

ይሁንና እግዚአብሔር ሰውን ካጋጠመው መከራ አንድ ቀን እንደሚገላግለው በነቢያት አድሮ ትንቢት ሲያናግር፣ ምሳሌ ሲያስመስል፣ ሱባዔ ሲያስቈጥር ቆይቶ ዘመኑ በደረሰ ጊዜ፣ በሰው ላይ የተላለፈውን ፍርድ ወደ ራሱ አዙሮ፣ ሕጉ የጣለውን የሞት ቅጣት እሱ ራሱ ለመቀበል፤በመስቀል ላይ ተሰቅሎ መሥዋዕት ሆነ፤ በመሥዋዕትነቱም ሰውን ከፍዳ ኀጢአትና ከሞተ ነፍስ ነፃ አወጣው፤ ቅዱስ ጳውሎስ በሮሜ መልእክቱ እንደጻፈው፡- በፊት የተሠራውን ኀጢአት ለመተውና በእርሱ የሚያምኑትንም በኋላ ከሚመጣው ኀጢአት ለማዳን እግዚአብሔር፣ በልጁ በኢየሱስ ክርስቶስ ደም ማመንን የኀጢአት ማስተሥረያ አድርጎ አቆመው፤ ብሎአል፡፡ (ሮሜ 3÷25-26)

ጌታችን በዚህ በመስቀሉ ላይ በፈጸመው መሥዋዕትነት ምክንያት፣ ያለፈው ኀጢአትም ሆነ የኋላው ኀጢአት የሚደመሰስበት ሁኔታ ተፈጠረ፤ ከዚህ በኋላ ኀጢአትም፣ ሞትም፣ ዲያብሎስም ተሸንፈው ባዶአቸውን ቀሩ፤ ለሰው ከእግዚአብሔር መለየትና መቀጣት ዋና መንሥኤው ለእግዚአብሔር አለመታዘዝ ነው፤ አለመታዘዝ የኀጢአት ምንጭ ሆነ፤ ኀጢአትም ሰውን ለፍርድ አጋለጠ፣ ፍርድም ለሞት የኀይል ምንጭ ሆነ፤ ሞትም በበኩሉ ለዲያብሎስ ከተማ ለሲኦል በኀጢአተኞች መሞላት ዋና ምክንያት ሆነ፤ አሁን ግን ክርስቶስ ለኀጢአተኞች ቤዛ ሆኖ በሰዎች ፈንታ በመስቀል ላይ በመሠዋቱ፣ የሰውን የኀጢአት ዕዳ ራሱ ከፈለና ሰውን ከኀጢአት ዕዳ ነፃ አደረገው፤ በዚህም የኀጢአትና የሞት ግንኙነት ተቋረጠ፤ ዲያብሎስም ከሰረ፤ ምክንያቱም በክርስቶስ ሞት ኀጢአት ተደመሰሰ፤ ኀጢአት ሲደመሰስ፣ ሰውም ከፍርድ ነፃ ሆነ፤ ሞት ይዞ የሚያቀርበውን ሲያጣ፤ ሲኦል የሚውጠውን አጣ፣ ዲያብሎስም ከሰረ፤ ማለትም ድል ሆነ፤ ተሸነፈ፤ መስቀል ያስገኘልን ድል ይህንን ነው፤ ለዚህም ነው መስቀል ሞዐ፤ ሞት ተሞአ፤ ወዲያብሎስ ወድቀ፤ መስቀል ድል አደረገ፤ ሞት ድል ሆነ፤ ዲያብሎስም ወደቀ፤ ብለው ቅዱሳት መጻሕፍት የምሥራቹን የሚነግሩን፤ (1ቆሮ.15÷54-57፤ ኤፌ.2÷16፤ ተሰ. 2÷14-15) እግዚአብሔር በዚህ ምክንያት ሰውን ታረቀው፤ ሰው ቀድሞ ከውድቀቱ በፊት የነበረውን ጸጋና ክብር ተመልሶለት ከእርሱ ጋር ኅብረት እንዲኖረው ፈቀደ፤ ኅብረቱም በእምነት፣ በጥምቀትና በቅዱስ ቊርባን ምሥጢር እንዲፈጸም አደረገ፤ ኀጢአት በዚህ ሲወገድ ሀብተ ጸጋ መጣ፣ ሀብተ ጸጋ ሲመጣ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ኅብረት ተመሠረተ፣ ሞተ ነፍስ ተሻረ፣ የሲኦል በር ተሰባበረ፣ ዲያብሎስም ባዶውን ቀረ፤ ሰው ግን ዘለዓለማዊ ሕይወትና ክብርን ተቀዳጀ፤ ስለሆነም በመስቀሉ ላይ በተፈጸመው የመሥዋዕትነት ኀይል በኀጢአታችን ከሚመጣብን ሞተ ነፍስና ከኵነኔ ሲኦል ድነናል፤ መስቀል የእግዚአብሔር ኀይልና ጥበብ ነው ብለን የምናምነውም በዚህ ኀይልና ጥበብ በመዳናችን ነው፤ መስቀልን ስናከብር በዋነኛነት የምናስበው፣ ክርስቶስንና የእርሱ የደም መሥዋዕትነትን ነው፤ ታላቁ ምሥጢርና የመዳኛችን አስኳልም ያለው በእርሱ ደም ውስጥ ነው፤ ይሁንና ደሙ የፈሰሰበት ትእምርተ መስቀልም ትልቅ ክብር ያለው ነው፤

ከኢትዮጵያ ሰንደቅ ዐላማ በስተጀርባ ያለው ትልቅ መልእክት የኢትዮጵያ ሕዝብ ነፃነትና ሉዓላዊነት ነው፤ ሆኖም የኢትዮጵያውያንን ነፃነትና ሉዓላዊነት በውክልና የተሸከመው ሰንደቅ ዐላማም ልዩ ክብር አለው፤ እንደዚሁም ሁሉ በክርስቶስ ደም የተገኘው ዕርቅና ድኅነት በስተጀርባው ያዘለና የዳንንበት ደሙም የፈሰሰው በእርሱ ላይ መሆኑን የሚያስታውሰንና የሚያሳስበን ትእምርተ መስቀልም ከፍ ያለ ክብር የሚገባው በመሆኑ እናከብረዋለን፤ መስቀል በክርስትና ሃይማኖት ጠላቶች ተቀብሮ ደብዛው እንዲጠፋ የተደረገው ሤራ እንዲከሽፍ የሆነበትም ዋና ምክንያት፣ መስቀል በዓለም ላይ የክርስቶስን መሥዋዕትነትና አዳኝነት እንዲመሰክርና እንዲያሳስብ ተፈልጎ ነው፤ ስለዚህ ትእምርተ መስቀሉን ባየን ቊጥር የክርሰቶስን መሥዋዕትነትና ድኅነታችንን እናስባለን፤ እናስታውሳለንም፡፡

ስናስበውም ቀላል በሆነ ነገር ሳይሆን፣ ለታላቅ የአዳኝነት ምሥጢሩ በሚገባ፣ በታላቅ ሃይማኖታዊ ሥነ ሥርዐትና በታላቅ ድምቀት መሆን ይገባዋል፣ መስቀል በክርስትና ሃይማኖት ጠላቶች ከተቀበረ በኋላ፣ በንግሥት ዕሌኒ መንፈሳዊ ጥረት ከተቀበረበት ጒድጓድ የወጣበትን ታሪክ ለማስታወስ፣ እኛ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖች በየዓመቱ መስከረም 17 ቀን ከፍ ባለ ሥነ ሥርዐትና በታላቅ ድምቀት እናከብረዋለን፤ እግዚአብሔር በመጀመሪያ ሰውን ከረቀቀ ጭንቅላት ጋር ፈጠረው፤ ሰውም ከእግዚአብሔር በተሰጠው አእምሮ እየተመራመረና እየተራቀቀ አሁን በዐይናችን የምናያቸውን የጥበብ ውጤቶች ሠራ፤ ከዚህ አኳያ ሰውን ለመርዳት የሚያገለግል መልካም የጥበብ ሥራ ሁሉ የእግዚአብሔር ጥበብ ነው ብሎ መቀበል እውነት እንጂ ስሕተት አይሆንም፤ ዓለም በየጊዜው የሚያጋጥሙአትን ችግሮች ከእግዚአብሔር በተገኘ ጥበብ መከላከል ኀጢአት አይደለም፡፡

ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ እግዚአብሔር ለሰዎች በሰጠው የሕክምና ጥበብ በዓለም አስከፊ የሆነውን የኤች አይ ቪ ቫይረስን መቀነስ የሚያስችል የዕድሜ ማራዘሚያ መድኀኒት መገኘቱ መልካም ነው፤ በሌላ በኩል ደግሞ ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖቻችን ፈጣሪን በማመንና በመማፀን፣ እግዚአብሔር የመፈወስ ኀይልን ባሳደረበት በቅዱስ ጸበል እየተጠቀሙ ፈውስ ማግኘቱ የእግዚአብሔር የምሕረት ስጦታ ነው፤ ስለሆነም ከቫይረሱ ጋር የሚኖሩ ወገኖቻችን፣ መድኀኒቱና ጸበሉ ሰውን ለማዳን ከእግዚአብሔር የተሰጡ መሆናቸውን አምነው ሁለቱንም በመውሰድ በሽታውን ቢከላከሉ ኀጢአት አይሆንባቸውም፡፡

ከዚህም ጋር የእናቶችን ሞትና ሥቃይ ለመቀነስ ታስቦ በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን እናቶችን በእርግዝና እና በወሊድ ጊዜ የመርዳት ሕክምና፣ እግዚአብሔር እናቶችን ለማዳን ብሎ የገለጸው ጥበብ እንደሆነ መገንዘቡ ብልህነት ነው፡፡ በተለይም በነፍስ አባትነት የጥበቃ ሥራ የተሠማሩ ቀሳውስትና መምህራን፣ እንዲሁም ሰባክያነ ወንጌል፣ ሕዝቡን በሚያስተምሩበት ጊዜ፣ እናቶች የተለመደው የሃይማኖታችን እምነትና ጸበል እየጠጡና እየተቀቡ፣ እንዲሁም የሚወዷትን እናታችን ቅድስት ድንግል ማርያምን እየተማጸኑ፣ በሕክምና እየተረዱ ቢወልዱ በእግዚአብሔር የተወደደና የተፈቀደ ቅዱስ ተግባር መሆኑን በማስተማርና በማስረዳት፣ እናቶችን በወሊድ ከመሞት የመቀነስ መርሐ ግብሩ እንዲሳካ በሰፊው እንዲሠሩ ያስፈልጋል፡፡

የእግዚአብሔር ዐላማ ምን ጊዜውም ሰውን በሁለመናው ማዳን እንደሆነ እናውቃለን፤ በመሆኑም የእርሱ መልእክተኞች የሆን ሁላችን ሰው የሚድንበትን ሁሉ የማስተማርና የማስረዳት ግዴታና ኀላፊነት እንዳለብን መዘንጋት የለብንም፤ የመስቀል ምሥጢርም መዳንና ማዳን ነውና፣ አሁንም የማዳን ሥራውን ያለመታከት ማስተማር አለብን፤ ማስተዋልና ትጋት፣ ፍቅርና ስምምነት፣ መከባበርና መረዳዳት፣ መቻቻልና መተማመን ምንጊዜም መሣሪያዎቻችን እናድርጋቸው፤ ኢትዮጵያውያን አባቶቻችን ሃይማኖትና ቋንቋ፤ ብሔርና ባህል ሳይለያያቸውና ሳይነጣጥላቸው፤ ለዚህ ዓይነቱ ስሜትም ሳይበገሩ፣ ሁሉም እንደ መስቀል ችቦ አንድ ሆነው የዚህችን ሀገር አንድነትና ነፃነት፣ ታሪክና ሉዓላዊነት ጠብቀው ያስረከቡን በፍቅር፣ በስምምነትና በአንድነት መሥዋዕትነትን እየከፈሉና በኅብረት እየሠሩ ነው፤ ስለሆነም ከጥንት ጀምሮ ተጠብቆ የቆየውን የሕዝባችን አንድነት፣ በሃይማኖት የመቻቻልና የመከባበር፣ ተስማምቶና ተጋግዞ በፍቅር የመኖር ልዩ ጸጋችን፣ ከሀገራችን አልፎ ለዓለም ሁሉ መልካም አርኣያ እንዲሆን፣ እንደዚሁም በመላ ሀገራችን ተቀጣጥሎ የሚገኘው ልማታችንን ከሚፈለገው ግብ ለማድረስ ዋናውና መሠረታዊ ግብአት ሆኖ የሚያገለግለን ስለሆነ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን እንደ ዐይን ብሌን ልንጠብቀው ይገባል፡፡ ይህ የሆነ እንደሆነ ሀገራችን ከድህነትና ከጒስቊልና ተላቃ ከበለጸጉ የዓለማችን ሀገሮች እኩል የምትሰለፍበት ጊዜ እንዲመጣ በጒጉት እንጠብቃለን በብርቱም እንጸልያለን፡፡ ይህ እንዲሆንም ጠንክረን እንሥራ፤ በማለት ለመላ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት መልእክታችንን አደራ ጭምር እናስተላልፋለን ፡፡ መልካም የመስቀል በዓል ያድርግልን ፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ይቀድስ፡፡አሜን፡፡

የ2006 ዓ.ም ዘመን መለወጫ በዓል መስከረም 1 ቀን 2006 ዓ.ም

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠር፥ በከተማ፥ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትኖሩ፣ የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፣
በሕመም ምክንያት በየሆስፒታሉ ያላችሁ፣ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፣

የዘመናት ፈጣሪ እግዚአብሔር አምላካችን፣ እንኳን ከሁለት ሺ አምስት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማቴዎስ ወደ ሁለት ሺሕ ስድሰት ዓመተ ምሕረት ዘመነ ማርቆስ በሰላም አደረሳችሁ!

“ወሠርዐ ዕድሜሁ ወዓመታቲሁ መጠነ ይነብሩ በዘየኀሥሥዎ ለእግዚአብሔር
እግዚአብሔር፣ እርሱን ፈልገው ያገኙት ዘንድ፣ ሰዎች የሚኖሩባቸውን
የዕድሜና የዘመናት መጠን ሠራ።”
(የሐዋ.ሥራ 17÷26-27)

አምላካችን እግዚአብሔር፣ ለፍጡራን ከሰጣቸው መልካም ስጦታዎች መካከል፣ የዘመን ስጦታ የመጀመሪያውን ደረጃ ይይዛል፤ ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚነግረን፣ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት፣ ፍጥረታትን ውብ አድርጎ ሲፈጥር፣ ዘመናትንና ዕለታትን ለመለየት ያስችሉ ዘንድ፣ ብርሃናትን በሰማይ ጠፈር ፈጥሮአል፤ (ዘፍ.1÷14-19) ከዚያን ጊዜ ጀምሮ፣ የሰው ልጅ፣ በብርሃን ዑደት እየታገዘ፣ ዘመናትን፣ ወቅቶችን ፣ወራትንና ዕለታትን ለይቶ በማወቁ፣ መርሐ ግብር እያወጣ፣ ለሥራው አፈጻጸም ይጠቀምባቸዋል፤ በመሆኑም፣ ዘመናት፣ ለሥራችን የሚሰጡት ግብአት፣ ከፍ ያለ ሆኖ ይታያል፤ እግዚአብሔር፣ ዘመናትን በሰዓታት፣ በቀናት፣ በወራት በወቅቶችና በዓመታት፣ ከፋፍሎ የፈጠረበት ዋና ምክንያት፣ በእነርሱ መለኪያነት፣ ዐቅደን፣ አልመንና ጠንክረን በመሥራት፣ ራሳችንን፣ ቤተ ሰባችንን፣ ሀገራችንንና በአጠቃላይ ዓለማችንን፣ ለኑሮ የተመቸች፣ ውብና ለም አድርገን እንድንከባከብና እንድንጠብቅ ነው፡፡ (ዘፍ.2÷15)

የዘመን ጸጋ፣ በሥጋዊ ሕይወታችን ብቻ ሳይሆን፣ በመንፈሳዊ ሕይወታችንም ከፍተኛ ትርጒም አለው፤ የእግዚአብሔር ቃል፣ ከፍ ብሎ እንደነገረን፣ ዘመናት፣ እግዚአብሔርን ፈልገን ለማግኘት የሚያስችሉን መሣሪያዎች ናቸው፤ ይህም ማለት፣ እያንዳንዱ ዓመት፣ በሰው አእምሮ ውስጥ ጥሎት የሚያልፍ፣ ተግባራዊ ትምህርትና ዕውቀት አለ፤ ከዚህ አኳያ፣ ሰው፣ በየዓመቱ ከሚቀስመው ሰፊ ግንዛቤ፣ ዕውቀቱን እያሰፋ፣ ወደ ተሻለ ማስተዋል ይሸጋገራል፤ ጤናማ ማስተዋልን ሲያገኝ፣ ፈጣሪውን ወደ መፈለግና ወደ መከተል፣ ፍጹም ሰው ወደ መሆንም ይደርሳል፤ በዚህ ምክንያት፣ ዘመን፣ ሰው፣ ፈጣሪውን እንዲያውቅ የሚያስችል፣ የማብቃት ጸጋ አለው ማለት ነው፤ (የሐዋ.ሥራ 17÷26-27)

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቼ፤

እግዚአብሔር እኛን ሲፈጥር ዐላማ አለው፤ ተቀዳሚ ዐላማውም፣ በተፈጥሮ የተሰጠንን ዕውቀት ተጠቅመን፣ እርሱን እንድናውቅ፣ እርሱን እንድናምን፣ እርሱን እንድናመልክና ለእርሱ እንድንታዘዝ፣ በእርሱም የዘለዓለም ሕይወትና ክብር እንድናገኝ ነው፤ (ሮሜ.1÷19-21፤ ዮሐ. 20÷31)፤ በምድራዊው ኑሮአችንም እንዳንቸገር፣ ልዩ ልዩ ሀብት ያላትን ምድር ፈጥሮ ሰጥቶናል፤ ይሁንና፣ ምድራችን፣ በማሕፀንዋ የተሸከመችውን ልዩ ልዩ ጥሬ ሀብት፣ መልክና ጣዕም እንዲኖረው አድርጎ ወደ ጥቅም የመለወጡ ኀላፊነት፣ ለእኛ አስረክቦአል፤ ይህም፣ እግዚአብሔር፣ እኛን የሥራው ተሳታፊዎች የማድረግ ዐላማ ያለው መሆኑን የሚያረጋግጥ ነው፡፡

እግዚአብሔር፣ የሥራ ሁሉ ጀማሪ ከመሆኑም ሌላ፣ሁሌም ሲሠራ የሚኖር፣ሥራ ወዳድ አምላክ ነው፤ (ዮሐ. 5÷17) የእኛንም አካል ለሥራ የተመቸ አድርጎ መፍጠሩ፣ የሥራው ተሳታፊዎች እንድንሆን ብሎ እንደሆነ ልናስተውል ይገባል፤ ስለለሆነም፣ እኛ፣ ታታሪ ሠራተኞች በሆን ቍጥር፣የእግዚአብሔር ተባባሪዎች እንሆናለን፤ ከሥራ በራቅን ቍጥር ደግሞ፣ ከእግዚአብሔር ጋር ላለመተባበር እየከጀልን እንደሆነ፣ መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ አንጸር፣ እያንዳንዱ ሰው፣ ዘመን አልፎ ዘመን ሲተካ፣ በኅሊናው ማቃጨል ያለበት ዐቢይ ነገር፣ በሥጋዊም ሆነ በመንፈሳዊ ኀላፊነቴ ምን ሠራሁ? ምንስ ቀረኝ? በአዲሱ ዓመትስ ምን ሠርቼ ከእግዚአብሔር ጋር ተባባሪ ልሁን የሚለውን ነው፤ ሥራ መሥራት ማለት፣ ከእግዚአብሔር ጋር መተባበር ማለት ነውና፤ እያንዳንዱ ሰው፣ ይህንን አስተሳሰብ አንግቦ፣ አዲሱን ዘመን በአዲስ መንፈስ ከተቀበለው፣ እውነትም ዘመኑን በሥራ ወደ አዲስነት ይለውጣል፡፡ ዐይነተ ብዙ በሆነ የተፈጥሮ ጸጋ የታደለችው ሀገራችን ኢትዮጵያ፣ በተፈጥሮ ጸጋ የጎደላት የሌለ ብቻ ሳይሆን፣ ከሁሉም የበለጠና የተሻለ ሀብት ያላት ሀገር ናት፤ ነገር ግን፣ በሀገራችን ከርሠ ምድርና ገጸ ምድር ተከማችቶ የሚገኘውን ሀብት፣ ጠንክረን በመሥራት ወደ ጥቅም መለወጥ እየቻልን፣ የሌላውን ትርፍራፊ ለመለቃቀም በሚል የተሳሳተ ግንዛቤ፣ መተኪያ የማናገኝላቸውን ልጆቻችን፣ በየአቅጫው እየተጎዱብን ነው፤ ወጣት ልጆቻችን፣ ለአደጋ በተጋለጠ ሁኔታ፣ በሕገ ወጥ መንገድ፣ ከውድ ሀገራቸው እየወጡ በየአካባቢው ወድቀው እየቀሩ ናቸው፤ ይህን አሳዛኝ ሁኔታ ለማስቆም፣ ሕዝቡ በርትቶ በማስተማርና በመሥራት፣ ልጆቹን ከአሠቃቂ ኀልፈተ ሕይወት ማዳን አለበት፡፡

ሃይማኖታችንና ሀገራችንን የምንወድ ኢትዮጵያውያን ሁሉ፣ በሀገራችን ሥር ሰዶ የቆየውን ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ችግር በመቅረፍ፣ በማኅበራዊ ኑሮው የተስተካከለና በኢኮኖሚው የበለጸገ ማኅበረሰብ ለመፍጠር በሚደረገው ርብርቦሽ፣ ሁላችንም ኢትዮጵያውያን በመቻቻል፣ በመከባበር፣ በመፈቃቀር፣ በስምምነትና በመመካከር መሥራት፣ ተቀዳሚ ዐላማችን ማድረግ አለብን፤ ከሁሉም በላይ፣ የተጀመሩም ሆኑ ለወደፊት የሚጀመሩ የልማት ሥራዎች፣ ፍጻሜ አግኝተው፣ ሀገራችንን በልማት የመለወጥ ሕልማችንን እውን ሊያደርግ የሚችል፣ ሰላማችን በአስተማማኝ ሁኔታ የተጠበቀ እስከሆነ ድረስ ብቻ መሆኑን፣ እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ፣ ለአፍታ እንኳ ሊዘነጋው አይገባም፡፡ በመሆኑም፣ ሁላችንም ኢትዮያውያንና ኢትዮጵያውያት፣ በዘር፣ በሃይማኖት፣ በቋንቋ በአካባቢ ሳንለያይ የእድገታችን ዋስትና የሆነው ሰላማችንን፣ በንቃት መጠበቅ አለብን፡፡

የሀገር ደኅንነትና ልማት ከሚረጋግጥባቸው አንዱ፣ በአካል፣ በአእምሮና በአስተሳሰብ ጭምር፣ ሙሉ ጤናማ የሆነ ማኅበረ ሰብእ ሲኖረን ነው፤ ስለሆነም፣ በሀገራችን፣ በእርግዝናም ሆነ በወሊድ ጊዜ፣ የጤና ባለሙያ ተገቢ እንክብካቤና እገዛ ባለማግኘት፣ ለሞት አደጋ የሚጋለጡ እናቶችና ሕፃናት፣ በርከት ያሉ እንደሆነ ይታወቃል፤ ይህን ለመቀነስና ለመከላከል ታስቦ፣ በሀገራችን እየተካሄደ ያለውን የእናቶችና የሕፃናት የጤና እንክብካቤ፣ የተሳካ ይሆን ዘንድ ሁሉም ሕዝባችን ሊደግፈውና በመርሐ ግብሩ ተጠቃሚ ሊሆን ይገባል፤ ሕክምና ማለት ጥበብ ማለት ነው፤ ጥበብን ደግሞ አጽንተን እንድንከተላትና እንድንጠቀምባት፣ እግዚአብሔር ያዘዘን በመሆኑ፣ በባለሙያና በሕክምና ጥበብ እየተረዱ፣ በጤና ተቅዋም መውለድ እግዚአብሔር የፈቀደውና የሚወደው ነው፤ በተለይም፣ እናቶቻችን፣ የጉዳዩን አሳሳቢነት ተገንዝበው፣ በየአካባቢያቸው በሚገኙ የጤና ተቅዋማት እየተገኙ፣ በጤና ባለሙያ ድጋፍና ርዳታ በመውለድ፣ ጤንነታቸውን መጠበቅ ይኖርባቸዋል፡፡

በመጨረሻም፣ በአዲሱ ዓመት፣ ሕዝባችን ሁሉ፣ በማኅበራዊና በኢኮኖሚያዊ ኑሮው የበለጸገ፣ በዕውቀትና በማስተዋል የተካነ፣ ጤንነቱና ሰላሙ የተጠበቀ ይሆን ዘንድ፣ በተሰማራበት የሥራ መስክ ጠንክሮ በመሥራት፣ ሀገሩን ያለማ ዘንድ፣ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር አዲሱን ዘመን ይባርክልን ይቀድስልን አሜን!