ከግንቦት 21-30 ቀን 2005 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቊጥር 164 ላይ ከበዐለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ እንዲካሄድ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከግንቦት 21-30 ቀን 2005 ዓ.ም. ተካሂዷል፡፡ ይህ ጉባኤ የርክበ ካህናት ጉባኤ ተብሎ የሚታወቅ ሲሆን፤ ከላይ በተጠቀሰው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን እንደተገለጸው ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት በቤተ ክርስቲያን ያለውን አጠቃላይ መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ጉዳዮችን በማየት በመንፈስ ቅዱስ መሪነት ታላላቅ ውሳኔዎችን የሚወስኑበት ዐቢይ ጉባኤ ነው፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ በቤተ ክርስቲያናችን ውስጥ ያሉትን ወቅታዊና ነባራዊ ጉዳዮችን ለመመርመርና ለመገምገም ባለው ሐዋርያዊ ኀላፊነት ለቅድስት ቤተ ክርስቲያን መንፈሳዊ ተልእኮ አፈጻጸም ዕንቅፋት ናቸው ብሎ ያመነባቸውን ጉዳዮች በአጀንዳ ቀርጾ፣ በስፋትና በጥልቀት ተወያይቶ ውሳኔ ሰጥቶባቸዋል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን በምድር ላይ ያለች የእግዚአብሔር መንግሥት ማእከል፣ በባሕርይዋም ንጽሕትና ቅድስት ብትሆንም ኀጢአትና ስሕተት በነገሠበት ዓለም ያለች በመሆንዋ ከእርስዋ መሠረታዊ ባሕርይ ጋር የማይስማሙ ተግባራት እንዳይጋቡባት የመጀመሪያው ጥበቃ በብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ላይ ያረፈ ነው፡፡

በተለይም የአሁኑ ዓላማችን ጥበብ ባፈራው የአሠራር ዕውቀት በየቀኑ በለውጥ ጎዳና በሚራመድበት ጊዜ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንም ከዓለሙ በተሻለና በበለጠ በመንፈሳዊና በአእምሮኣዊ ጥበብ ሕዝበ ክርስቲያኑን መምራት፣ ማስተማርና ማገልገል ይጠበቅባታል፡፡ በቤተ ክርስቲያናችን እነዚህን የተቀደሱ ተግባራት በሥራ ለመተርጐም ወቅታዊ ዕንቅፋት ሊሆኑ የሚችሉ ነገሮች ምን ምን ናቸው? በማለት ቅዱስ ሲኖዶስ በጥልቀት ተመልክቶአል፡፡ በዚህ መሠረት ጉባኤው ብዙ ውይይት ካደረገ በኋላ የሚከተሉትን ዐበይት ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡

1. በየሥራ ዘርፉ እየተከሠተ ያለው የመልካም አስተዳደርን ችግር በተለይም ብልሹ አስተዳደርና አሠራር፣ ዘመኑን ያልዋጀና ጥራት የጎደለው የፋይናንስ አያያዝ፣ እንደዚሁም ለሙስናና ለብክነት የተጋለጡ አሠራሮች ሁሉ ወሳኝ በሆነ መልኩ ለመቅረፍና ለማድረቅ፣ ከዚህም ጋር ቤተ ክርስቲያናችን በመሪ ዕቅድ መሥራት የምትችልበትን አሠራር ለመቀየስ፣ ቅዱስ ሲኖዶስ፡- ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት፣ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣ ምሁራን ምእመናን የሚገኙበት ዐቢይ ኮሚቴ ተቋቁሞ ጉዳዩን የማጣራትና የማጥናት ሥራውን እንዲቀጥል ተስማምቶ በአንድ ድምፅ ወስኖአል፡፡

2. የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ለሌሎች አህጉረ ስብከት በመልካም አስተዳደርና በፋይናንስ አያያዝ፣ እንደዚሁም በስብከተ ወንጌልና በአገልግሎት አሰጣጥ ለሌሎች አህጉረ ስብከት በሞዴልነት የሚጠቀስ ሀገረ ስብከት መሆን ስለሚገባው በአንድ ሀገረ ስብከት፣ በአንድ የቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ እንዲመራ፣ እንደዚሁም በመልካም አስተዳደር፣ በፋይናንስ አያያዝና በሰው ኀይል አመዳደብ የሕግ የበላይነትን አክብሮ እንዲሠራ አስፈላጊውን ክትትል ሁሉ በቋሚ ሲኖዶስና በመንበረ ፓትርያርኩ ጥብቅ ክትትል እንዲደረግ፤

3. የቤተ ክርስቲያናችን የሕይወት ምንጭ የሆነውን የስብከተ ወንጌል ትምህርት በሰው ኀይል፣ በሚድያም ጭምር እየታገዘ በመላው ዓለም ላሉ የቤተ ክርስቲያናችን ተከታዮች ትምህርቱን በጥራትና በጥልቀት ይሰጥ ዘንድ አስፈጻሚው አካል ጠንከር ያለ ሥራ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ድምፅ ወስኗል፡፡

4. የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ምርጫ በየሦስት ዓመቱ እንዲካሄድ ሕገ ቤተ ክርስቲያን ባስቀመጠው ድንጋጌ መሠረት፡ ብፁዕ አቡነ ማቴዎስ የወላይታ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅ፤ እንዲሁም ብፁዕ አቡነ ሉቃስ፡ የሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ አድርጎ ቅዱስ ሲኖዶስ መርጦአቸዋል፡፡

5. ብፁዕ አቡነ እስጢፋኖስ የጅማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ በአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ፤ እንደዚሁም የምሥራቅና ሰሜን አዲስ አበባ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ብፁዕ አቡነ ዳንኤል በኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ገዳማት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡

6. በመካከለኛው ምሥራቅና በሌሎች የዓለም ክፍሎች ለሥራ ፍለጋ በሕገ ወጥ መንገድ በሚሄዱ ልጆቻችንና ወገኖቻችን ላይ እየደረሰ ያለውን ዘግናኝ ድርጊት ለማስቆም መንግሥት እያደረገ ያለው ጥረት ቤተ ክርስቲያናችን በሙሉ ልብ እንደምትደግፈውና ለስኬቱም የበኩሏን እንደምትወጣ፣ ለዚህም በየደረጃው ያሉ መምህራን፣ ካህናትና ሰባክያን ሁሉ የዚህን ጎጂነት ደጋግመው በማስረዳትና በማስተማር ሕዝቡ ግንዛቤ እንዲኖረው ጠንክረው እንዲያስተምሩ ቅዱስ ሲኖዶስ መመሪያ ሰጥቷል፡፡

7. የሀገራችን ሕዝቦች ከድህነትና ከኋላ ቀርነት ተላቀው መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች ጋር እኩል ለማሰለፍ በሚደረገው ሁለንተናዊ የልማት ተግባር ቤተ ክርስቲያናችን ከሕዝቡና ከመንግሥት ጎን በመሆን የሚጠበቅባትን ሁሉ እንደምታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ አረጋግጧል፡፡

8. ኢትዮጵያ ሀገራችን በሀገር ውስጥ፣ በምሥራቅ አፍሪካ፣ በመላ አፍሪካ ከዚያም በመላው ዓለም ሰላም እንዲሰፍን፣ የሰው ልጅ እኩልነትና መብት እንዲከበር፣ ፍትሓዊ የሆነ የሀብት አጠቃቀም እንዲኖር፣ የአየር መዛባትን ለመቋቋም የአረንጓዴ ልማት ሀብት እንዲስፋፋ የምታደርገውን ያላሰለሰ ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በእጅጉ እያደነቀ የሀገሪቱን መልካም ዝናና በጎ ገጽታ ለመጠበቅ የበኩሉን ጠንክሮ እንደሚሠራ አረጋግጦአል፡፡

9. በሀገራችን የዕድገት ሂደት ከፍተኛ ሚና ይጫወታል ተብሎ በመገንባት የሚገኘው ታላቁ የሕዳሴ ግድብ ሥራው ተጠናቅቆ ጥቅም ላይ እስኪውል ድረስ ቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ እንደማታቋርጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ያረጋግጣል፡፡

10. ሀገራችን ኢትዮጵያ በጤናው ዘርፍ የኅብረተ ሰቡን ጤንነት ለመጠበቅ በተለይም በሀገር ዐቀፍ ደረጃ ለእናቶችና ለሕፃናት እየተደረገ ያለው ልዩ የጤና እንክብካቤ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቤተ ክርስቲያናችን ኅብረተሰቡን ከማስተማርና የጉዳዩን ጠቃሚነት ከማስረዳት ባሻገር ለመርሐ ግብሩ መሳካት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደምታደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ ይገልጻል፡፡

11. ከሀገር ውጭ ከሚገኙ የቤተ ክርስቲያን አባቶች ጋር የተጀመረው የሰላም ውይይት በተለያዩ ምክንያቶች እስካሁን የሚፈለገውን የአንድነት ውጤት ባያስገኝም የቤተ ክርስቲያናችን አንድነትና ሰላም ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሀገራችን እንዲሁም ለሕዝባችን ያለው ትርጒም የላቀ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ስለሚገነዘብ ሁኔታዎች ተመቻችተው የሰላም ውይይቱ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኖአል፡፡

12. ቅዱስ ሲኖዶስ የቤተ ክርስቲያኒቱን መንፈሳዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ማኅበራዊ ተልእኮ ዘመኑ በሚጠይቀው ጥበብና ዕውቀት እየቃኘ ለሃይማኖት፣ ለሀገርና ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማበርከት የሚገባውን ሁሉ በብቃት ለመሥራት ከምንም ጊዜ በላይ የተዘጋጀ መሆኑን ሕዝበ ክርስቲያኑ ተገንዝቦ እርሱም የበኩሉን ሥራ በቅን መንፈስ እንዲወጣ አበክሮ አሳስቧል፡፡

የቤተ ክርስቲያናችን የመጨረሻ ውሳኔ ሰጭ የሆነው ቅዱስ ሲኖዶስ በየጊዜው የሚያስተላልፋቸው ውሳኔዎችና መመሪያዎች ሁሉ ተፈጻሚነት ኖሮአቸው ጥሩ ውጤት ሊያስገኙ የሚችሉት በሁሉም ደረጃና አካባቢ የሚገኙ የቤተ ክርስቲያናችን ካህናትና ምእመናን ለቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ተግባራዊነት በሙሉ ልባቸው ሲሰለፉ እንደሆነ የቅዱስ ሲኖዶስ እምነት ነው፡፡

ስለሆነም ለእናት ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ክብርና ሉዓላዊነት መጠበቅ፣ ለህልውናዋ መቀጠልና ለዕድገትዋ መስፋፋት የሚቈረቈሩ የቤተ ክርስቲያናችን አገልጋዮችና ተከታዮች በሙሉ ቅዱስ ሲኖዶስ የሚያሳልፋቸውን ውሳኔዎችና መመሪያዎች ለመተግበር አስፈላጊውን ትብብር ሁሉ እንዲያደርጉ በአጽንዖት በማሳሰብ ለዐሥር ቀናት ያህል ሲካሄድ የሰነበተውን ጉባኤ ዛሬ ግንቦት 30 ቀን 2005 ዓ.ም. በጸሎት አጠናቅቆአል፡፡

እግዚአብሔር ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችንንና ሀገራችን ኢትዮጵያን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ አሜን!!