ጥቅምት 8 ቀን 2014 ዓ.ም 40ኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኀላፊ፣ የአርሲ ሀገረ ስብከት እና የምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ፣ የሲዳማ ክልል፣ የጌዴኦ አማሮና ቡርጂ ዞኖች አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ጽ/ቤት የየመምሪያውና የየድርጅቱ ኀላፊዎች፣
ከሀገር ውስጥና ከውጭ አህጉር የመጣችሁ የየሀገረ ስብከቱ ሥራ አስኪያጆች፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት የየክፍሉ ኀላፊዎች፣
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣
ከሁሉም አህጉረ ስብከት የመጣችሁ ተወካዮች በአጠቃላይ፤ የተበታተኑትን የሚሰበስብ፣ የተራራቁትን የሚያቀራርብ እግዚአብሔር አምላካችን ከልዩ ልዩ አጽናፈ ዓለም የመጣችሁትንና ከዚህ ከቅርብ የቆየነውን በአንድነት አሰባስቦ ስላገናኘን ክብርና ምስጋና ለአምላካችን እናቀርባለን።

“ወአናቅጸ ሲኦል ኢይኄይልዋ ወኢያንቀለቅልዋ፤
የሲኦል በሮች አይበረቱባትም፤ አያናዋውጧትምም።”
(ማቴ. 16፥18)

ይህን አረፍተ ነገር ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ኀይልና ጽናት አስመልክቶ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ያስተማረን ትምህርት ነው፤ አረፍተ ነገሩ እንደሚያመለክተው ቤተ ክርስቲያን ፈተና የሚያበዙባት ፈታኞች እንደማይለዩዋት ነው፤ ፈተናውን የሚያመጡባት አካላት በስም ባይጠሩም በተግባራቸው የሲኦል በሮች ተብለው ስለ ተጠቀሱ ሞትና መቃብር እንደዚሁም የእነሱ ዘበኞች የሆኑ ሠራዊተ አጋንንት እንደሆኑ መረዳቱ አያዳግትም፤ ጌታችን የቤተ ክርስቲያን ፈታኞች እስከ ዓለም ፍጻሜ ድረስ በሙሉ ዐቅማቸው ቤተ ክርስቲያንን ቢታገሏትም ሊያሸንፏት ግን አይችሉም ማለቱ በራእየ ዮሐንስ እንደተገለጸው መቃብር በትንሣኤ ዘጉባኤ፣ ሠራዊተ አጋንንት ደግሞ በደመ በግዑ በመጨረሻ የሚሸነፉና ከነካቴው የሚወገዱ መሆናቸውን ለመግለጽ እንደሆነ እናስተውላለን፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላትነ ክቡራን የጉባኤው ታዳሚዎች
ሊቀ ኖሎት በሆነው በአምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ስም የተቋቋመውና የተሰበሰበው ይህ ዓለም ዐቀፍ ጉባኤ፣ የሲኦል በሮች የማያናውጧትን ቤተ ክርስቲያን ለመጠበቅ እንደሆነ ሁላችንም የምንገነዘበው ነው፤ ቤተ ክርስቲያን ለሁለት ሺሕ ዘመናት ያህል በመከራ እየተፈተነች እስካሁን ድረስ ከዕለት ወደ ዕለት እየሰፋችና ሁሉንም እያዳረሰች የመጓዟ ምሥጢር መድኀኒታችን ከላይ የገባላትን ቃል ኪዳን ሊቀለብስ የሚችል ኀይል በሰማይም ይሁን በምድር የሌለ በመሆኑ እንደሆነ አንዘነጋውም፤ ይሁን እንጂ ዋናውና ላዕላዊው ጠባቂ እሱ መሆኑ እንደተጠበቀ ሆኖ እኛም የጥበቃው ተሳታፊዎች አድርጎ ሹሞናልና አደራ ጭምር ያለበት የጥበቃ ተልእኮና ኀላፊነት አለብን፡፡ በዚህም “አማልክት አንትሙ ወደቂቀ ልዑል ኲልክሙ፤ እናንተ አማልክት ናችሁ፤ ሁላችሁም የልዑል ልጆች ናችሁ” ብሎ ያናገረው የጸጋ አምላክነት በእኛ ላይ እንዴት ተፈጻሚ እንደሆነ ማጤኑ ተገቢ ነው፤ ከዚህ አንጻር በአሁኑ ጊዜ የቤተ ክርስቲያን ፈተና በምን ደረጃ ላይ ይገኛል?በየአካባቢው የሚገኙ ኖሎትስ ቤተ ክርስቲያንን ለመጠበቅ ያደረጉት ጥረት ምን ይመስላል? ለወደፊቱስ የቤተ ክርስቲያንን ፈተና ለማቅለል ምን ማድረግ ይገባል? የሚሉትን መሪ ሐሳቦች በማንሣት ይህ ጉባኤ የማየት ኀላፊነት አለበት፡፡

ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ክቡራን የጉባኤው ታዳሚዎች፣
ቤተ ክርስቲያን በአየር የተንሳፈፈች ነገር ሳትሆን በማኅበረ አማንያን ልቡና ውስጥ ተጠልላ የምትገኝ መንፈሳዊት መንግሥተ እግዚአብሔር ናት፤ ይህም ባሕርይዋ ከአማንያን ህልውና ጋር ያቀራኛታል፤ አማንያንም ያለ ሀገር ህልውና ስለሌላቸው ቤተ ክርስቲያን በተከታዮቿ አማካኝነት ከሀገር ሰላም ጋር ትተሳሰራለች፣ ይህ ብቻም አይደለም፤ የዓለሙን ሰላምና ፍቅር አስተማሪ፣ ሰባኪና ተምሳሌት በመሆን የሰው ልጆችን ሁሉ የመጠበቅ ኀላፊነትም አለባት፤ ይህንም ስታደርግ እንደ እናትም እንደ መምህርም እንደ ሽማግሌም ማእከላዊት ሆኖ ሥራዋን በለብዎ ማከናወን እንዳለባት ይታወቃል፡፡ ይሁንና ቤተ ክርስቲያናችን በአሁኑ ጊዜ በፈተና ተከባ፣ ልጆችዋም እርስ በርስ እየተጣሉ እንደሚገኙ ዓለም ሁሉ የሚያውቀው ነው፤ እነዚህ ወገኖቻችን ቤተ ክርስቲያን ልጆቼ ብላ የተቀበለቻቸው፣ በልጅነት ያከበረቻቸውና ለእግዚአብሔር መንግሥት ዕጩ ያደረገቻቸው፣ ያም ባይሆን በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠሩ ክቡራን ሰዎች ናቸው፤ ቤተ ክርስቲያን በዚህም በዚያም ያሉ ሁሉ ልጆቿ ናቸውና ስለነሱ ይገዳታል፤ ይሰማታል፣ ያሳስባታልም፤ በመሆኑም ብትችል መክራና አስተምራ፣ ገሥጻና ተቈጥታ፣ ካልሆነም ልባዊ የሆነ ጸሎት ወደ እግዚአብሔር በማቅረብ ከእርስ በርስ ጠብ ተላቅቀው በአንድነት፣ በሰላምና በፍቅር እንዲኖሩ በጸሎትና በምሕላ ፈጣሪን መማፀን አለባት፤ ይህን ስናደርግ የኖላዊነት ኀላፊነታችንን በአግባቡ እየተወጣን ነው ማለት እንችላለን፤ በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ በሚያስተላልፈው ቀኖናዊ መልእክት ገዳማቱ አድባራቱና አብያተ ክርስቲያናቱ በጸሎትና በምሕላ ተጠምደው ስለ ሕዝብ ስለ ምእመናንና ስለሀገር ደኅንነት አጥብቀው ፈጣሪን እንዲማፀኑ በዚህ ጉባኤ ፊት አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

በመጨረሻም አርባኛው ዓለም ዐቀፍ የሰበካ መንፈሳዊ ጠቅላላ ጉባኤ በዛሬው ዕለት ተከፍቶ በፈቃደ እግዚአብሔር የተጀመረ መሆኑን እናበሥራለን፡፡

እግዚአብሔር የተባረከ የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።