ጥቅምት 12 ቀን 2006 ዓ.ም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ቸርነት ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን፣ ሁላችንንም ከምናገለግልበት ሀገረ ስብከት አሰባስቦ፣ ከዚህ ቅዱስ ጉባኤ በአንድነት ስላገናኘን ከሁሉ በፊት እርሱን እናመሰግናለን፡፡
“ወይእዜኒ አዕብይዋ ወአብድርዋ ለትምህርተ ተስፋክሙ
አሁንም ተስፋ መንግሥተ ሰማያት ያላት ትምህርተ ወንጌልን ውደዷት፤ ከፍ ከፍም አድርጓት።”
(ዕብ. 12፥5)
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት
የዛሬው ጉባኤያችን፣ በፍትሕ መንፈሳዊ በተደነገገው መሠረት፣ ወቅታዊ የሆኑ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮችን በማንሣት ለመወያየትና፣ መንፈስ ቅዱስ በሚገልጽልን መንፈሳዊ ጥበብ እየተመራን፣ መፍትሄ ማግኘት ያለባቸው ጉዳዮች፣ መፍትሄ እንዲያገኙ ለማድረግ እንደሆነ ሁላችሁም ታውቃላችሁ፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ፣ በአሁኑ ጊዜ በጥልቀት፣ በማስተዋልና የኀላፊነት መንፈስ በተላበሰ ወኔ፣ አጥብቆ ሊወያይባቸውና ሊወስንባቸው፣ ከውሳኔ በኋላም ለተግባራዊነታቸው ሊረባረብባቸው የሚገቡ፣ በርከት ያሉ ጉዳዮች እንዳሉ ግልጽ ነው፡፡
ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ቤተ ክርስቲያንን በሐዋርያት ላይ ሲመሠርት፣ በእነርሱ ሥልጣነ ክህነት አማካኝነት፣ ቃሉን ወደ ዓለም ሁሉ ለማዳረስ እንደሆነ አንሥተውም፣ ቅዱሳን ሐዋርያትም፣ በሥልጣነ ክህነት እኛን ተክተዋል በመሆኑም እኛ ሊቃነ ጳጳሳት፣ የሐዋርያት የሆነውን ሁሉ ለመፈጸምና ለማስፈጸም፣ የእነርሱን ሥልጣን ወራሾች ሆነን በመንፈስ ቅዱስ ተሰይመናል፡፡ የቅዱሳን ሐዋርያት ተቀዳሚ ተልእኮ፣ በድንበር ሳይገደቡ፣ ስብከተ ወንጌልን ለዓለም ሁሉ ማስተማር ነው የሐዋርያት ቀዳሚ ተግባር ይህ ከሆነ፣ የኛም ቊጥር አንድ ሥራ ስብከተ ወንጌልን ማስፋፋት ነው።
ከትንሹ የሥልጣነ ክህነት ሹም ጀምሮ እስከ ትልቁ የቤተ ክርስቲያን ባለሥልጣን ያለው ሁሉ፣ ለስብከተ ወንጌል መስፋፋት ተልእኮ በንቃት፣ በሙሉ ዕውቀት፣ በተነሣሽነት፣ በፍጹም ፈቃደኝነት እንዲነሣሣና እንዲሰለፍ በማድረግ ረገድ፣ የሚጠበቀውን ያህል ተሠርቶአል ማለት ያስቸግራል በየትም ሀገር የማይገኝ ቊጥሩ እጅግ በርካታ የሆነ ካህን ያላት ቤተ ክርስቲያናችን በጥምቀት ወልዳ፣ በሥጋ ወደሙ አሳድጋ፣ ገብረ ሥላሴ፥ ገብረ እግዚአብሔር፥ ወልደ ማርያም፣ ገብረ ሚካኤል ብላ የሰየመቻቸው ልጆችዋ፣ ከጒያዋ እየተነጠቁ ወደ ሌላ ካምፕ ሲወሰዱ እርስዋ የወላድ መኻን የሆነችበት፣ ያልወለዱና ያላሳደጉ ባለ ብዙ ቤተሰብ የሆኑበት ክሥተት እያጋጠመ ነው፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ ባለው ኀላፊነት፣ የታሪክ ተወቃሽ እንዳይሆን፣ ለዚህ መሠረታዊና ወቅታዊ ጉዳይ፣ ፈጣን፣ አስተማማኝና ዘላቂ መፍትሄ ሊፈልግለት ይገባል
ቅዱስ ሲኖዶስ በሥሩ ያሉትን በጎች መጠበቅ ብቻ ሳይሆን፣ ድንበር የለሽ ስብከትና ትምህርት በማካሄድ፣ ከዛሬ ጀምሮ በየዓመቱ በርከት ያሉ በጎችን የማርባትና የመጠበቅ ሥራ ሊያሠራው የሚችል አሠራር መቀየስ ይገባዋል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ፣ ሐዋርያትን በመምህርነት ወደ ዓለም ሲልክ፣ በቅድሚያ አስተምሮ፣ አሳምኖ፣ አሠልጥኖ፣ መከራ እንደሚኖርም ገልጾ ነው፡፡ እኛም ለስብከተ ወንጌል የምናሰማራቸውና የምንሾማቸው ዲያቆናት፣ ቀሳውስትም ሆኑ ኤጲስ ቆጶሳት በተለምዶ የተሾሙ ሳይሆኑ፣ ጌታችን እንዳዘዘው የተማሩ፣ የሠለጠኑ፣ ነገሩ የገባቸውና መከራውን ለመቀበል የተዘጋጁ ሊሆኑ ይገባል
ይህንም ግንዛቤ በሥዩማነ ቤተ ክርስቲያን አእምሮ ለማሳደር የአብነት ትምህርት ቤቶቻችን፣ የማሠልጠኛዎቻችንና የከፍተኛ ትምሀርት ተቋሞቻችን በብዛትም፣ በጥራትም በአደረጃጀትም ተማሪውን በትክክል ለመለወጥና ለመቅረጽ በሚያስችል አዲስ አሠራር፣ ማስተካከልና ማብቃት አለብን እነዚህ የትምህርት ተቅዋማት ሰባክያንና መምህራን የሚፈልቁባቸው የሃይማኖታችን ምንጮች ናቸው ምንጩ ድፍርስ ከሆነ የጠማው መንገደኛ ውኃ ለመጠጣት ይቸገራል ጥሩ ምንጭ ከሆነ ግን የጠማው ብቻ ሳይሆን ያልጠማው መንገደኛም ቢሆን በውሀው ጥራት ከመጎምጀቱ የተነሣ ሳይቀምሰው አያልፍም፡፡
ቤተ ክርስቲያናችን የሃይማኖት እንከን ሳይኖራት፣ ሙያ ሳያንሳት፣ ተቈርቋሪ ምእመናን እያሏት በአያያዝና በአመራር ምክንያት የምትወቀሥበትና ልጆችዋን የምታጣበት ታሪክ መገታት አለበት፣ ይህንንም በወሳኝ መልኩ ለማስተካከል ቅዱስ ሲኖዶስ የትምህርት ቤቶቻችንን ትንሣኤ የሚያበሥር፣ እድገታቸውንና ጥራታቸውን የሚያፋጥን ጠንካራ መሠረት ዛሬ ማስቀመጥ ይኖርበታል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
ከጌታችን አሠራር አብነት ወስደን ስናይ፣ መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርሰቶስ፣ ሐዋርያትን ወደ ዓለም ሲያሰማራ፣ ቀዋሚ ሀብት እንዲኖራቸው አልፈቀደም፣ ሆኖም ምግብ፣ ልብስና መጠጥ ለሥጋዊ ሕይወት ህልውና እንደሚያስፈልጋቸው በመግለጽ “ለሠራተኛ ደመወዝ ይገባዋል” ብሎ ከማስተማሩም በላይ፣ ይህን የምግብ አቅርቦት ካስተማሩዋቸው አማንያን ማግኘት፣ እንዳለባቸው በማብራራት “ያቀረቡላችሁን ብሉ” ብሎ አዞአል፡፡ (ሉቃ. 10፥7-9)
ከላይ እንደተጠቀሰው የቤተ ክርስቲያናችን ምእመናን እኛ የሚፈለገውን ያህል ተደራጅተን፣ መስለን ሳይሆን ሆነን፣ በሁሉም ነገር ተዘጋጅተን ባለማስተማራችን የሚጠበቅባቸውን ዐሥራት፣ በኵራትና ቀዳምያት በሕጉ መሠረት እየሰጡ ነው ባይባልም፣ በተለያየ መልኩ ለቤተ ክርስቲያን የሚሰጡትን ስጦታ፣ ዘመኑ በሚፈቅደው የፋይናንስ አያያዝና ቊጥጥር ባለመያዛችን፣ ለቤተ ክርስቲያን ሥራ ከሚውል ይልቅ በየመንገዱ እየተንጠባጠበ፣ ወፎች የሚለቃቅሙት እንደሚበዛ፣ ፍጹም የማካይድ ሐቅ ነው በሌላ በኩል፣ በአድልዎና ከወገንተኝነት ሙሉ በሙሉ ያልተላቀቀው አስተዳደራችን፣ የቤተ ክርስቲያናችን ታላቅነትና ተሰሚነትን ክፉኛ እየጎዳው መሆኑ፣ አሌ ልንለው አይገባም፡፡
ስለሆነም በፋይናንስ አያያዝና በመልካም አስተዳደር ዙሪያም ይህ ጉባኤ ጥበብ ማስተዋል ያልተለየው፣ የማፍረስ ሳይሆን የመገንባት ግብ ያለው ራእይ አንግቦ ሥር ነቀል የሆነ የፍጹም እድገት ለውጥ ማምጣት የሚያስችለውን አሠራር መቀየስ ይገባዋል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
በዘመናዊ የአመራር ጥበብ እይታ፣ ከመልካም አስተዳደር አንዱና ምናልባትም ዋነኛው መስፈርት፣ አሳታፊነት እንደሆነ ግልጽ ነው በመሆኑም ቅዱስ ሲኖዶስ፣ ለለውጥና ለተሻለ እድገት የሚወስናቸው፣ ሀገር ዐቀፍና ታላላቅ የቤተ ክርስቲያናችን ጉዳዮች የየክፍሉ ኀላፊዎችን፣ ሊቃውንቱን፣ የምእመናን ተወካዮችን፣ የካህናት ተወካዮችን፣ የወጣቶች ተወካዮችን በማሳተፍ ወይም በሌላ አባባል የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላትን እያሳተፈ፣ ሐሳባቸውንም እያዳመጠ ቢሠራ፣ በመጨረሻም ባለው ሐዋርያዊ ሥልጣን በዚህ ጉባኤ አጽድቆ ሥራ ላይ ቢያውል ይበልጥ ብዙ ደጋፊና ረዳት፣ እንዲሁም ከዳር እስከ ዳር ብዙ ተቀባይነት ሊያገኝ ይችላል
ቅዱስ ሲኖዶስ ይህን ሳያደርግ፣ ሁሉንም ነገር፣ ብቻው ሆኖ የሚሠራና የሚወስን ከሆነ፣ የሕዝቡና የካህኑ ድጋፍ ይቀንስበታል በትክክል መግባባትም አይቻልም ለበጎ ተብሎ የተደረገው ነገር ሁሉ በሌላ አባባል ተገልብጦ እየተተረጐመ የሚረዳም የሚያስረዳም ስለማይኖር፣ በአዙሪት ማዕበል ከመንጓለል በቀር፣ የምናመጣው ለውጥ ይኖራል ብሎ መገምት ያዳግታል
ስለሆነም ሕዝቡንና ካህናቱን እንደዚሁም ባለ ድርሻ አካላትን እያሳተፉ መሥራትና መወሰን፣ የአሉባልተኞችን ሤራ የሚያከሽፍ እንደሆነ ዐውቀን በተግባር ልንጠቀምበት ይገባል፡፡
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤
ሃይማኖትን ማስፋፋት፣ መማርም ሆነ ማስተማር፣ ሀብት ማግኘትም ሆነ በሰላም ማስተዳደር የመሳሰሉ ሁሉ፣ በአግባቡ ሊከናወኑ የሚችሉ፣ በሀገር ውስጥ ባሉ ሕዝቦች መካከል፣ እኩልነት፣ መከባበር፣ መቻቻል፣ መተማመን መፈቃቀር፣ መስማማት፣ አንድነት፣ ፍጹምና አስተማማኝ የሆነ ሰላም ሲሰፍን ነው አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ በቅዱስ ወንጌል አስተምህሮ መሠረት እነኝህን ጠብቆ በማስጠበቅ ረገድ ኀላፊነቱን የሰጠ በቤተ ክርስቲያን በኩል ለቅዱስ ሲኖዶስ ነው፡፡
ስለሆነም ሁላችንም የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ችግሮችን በውይይትና በውይይት ብቻ በጋራ የመፍታት ባህል መደገፍና በማጎልበት መሥራት አለብን እንደዚሁም በሀገራችን እየተከናወነ ያለውን የሰላም፣ የእኩልነት፣ የመቻቻል፣ የመከባበር፣ የመተማመን፣ የወንድማማችነት፣ የልማትና የእድገት ጅምር ሊፈታተኑ የሚችሉ የአክራሪነት፣ የአሸባሪነትና የጽንፈኝነት ተግባራትን በማውገዝ፣ የክርስቶስ መልእክት የሆነውን ሰላምና እኩልነት፣ መከባበርና መቻቻል፣ አብሮ መልማትና ማደግ ብቻ ለሕዝቡ በየቀኑ ልንሰብክና ልናስተምር ይገባል፡፡
በመጨረሻም ይህ መንፈስ ቅዱሳዊና ሐዋርያዊ ዐቢይ ጉባኤ፣ ቤተ ክርስቲያንን የሚያስፋፋ፣ ማኅበረ ካህናቱንና ማኅበረ ምእመናኑን የሚያስደስት፣ በሁሉም የቤተ ክርስቲያናችን ተከታይ ዘንድ በናፍቆት የሚጠበቀውን የለውጥና የእድገት ጎዳና የሚከፍት፣ እንዲሆን በመመኘት፣ ንግግሬን እደመድማለሁ፡፡
እግዚአብሔር ጉባኤያችንን ይባርክ ይቀድስ
ሀገራችንን ኢትዮጵያ ይጠብቅልን
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።