ጥር 11 ቀን 2014 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን በማስመልከት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት በተወካያቸው ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል።

ጥር 11 ቀን 2014 ዓ.ም የጥምቀት በዓልን በማስመልከት በጃንሜዳ ባሕረ ጥምቀት በተወካያቸው በብፁዕ ዶ/ር አቡነ አረጋዊ በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን መንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት የውጭ ጉዳይና የቅዱስ ፓትርያርኩ ልዩ ጽ/ቤት የበላይ ኀላፊ ሊቀ ጳጳስ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል።

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ብፁዕ አቡነ ያሬድ የመንበረ ፓትርያርክ ዋና ጠቅላይ ሥራ አስኪያጅ፣የሰበካ ጉባኤ ማደራጃ መምሪያ የበላይ ኀላፊና የአርሲና ምሥራቅ ጎጃም አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፣
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሐፊ፣ የሲዳማ፣ የጌድኦ የአማሮና የቡርጂ አህጉረ ስብከት ሊቀጳጳስ፣
ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፣
ክቡራን ሚኒስትሮች፣
የተከበራችሁ የመንግሥት ልዩ ልዩ ባለ ሥልጣናት፣
ክቡራን አምባሳደሮችና ኮር ዲፕሎማቶች፣
ክቡራን የቤተ ክርስቲያናችን የየመምሪያውና የድርጅት ኀላፊዎች፣
የአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ኀላፊዎች፣የተከበራችሁ ሊቃውንተ ቤተ ክርስቲያን፣
የአዲስ አበባ ገዳማትና አድባራት አስተዳዳሪዎች፣ ወጣት የሰንበት ት/ቤት ልጆቻችን፣
የተወደዳችሁ የፓሊስና የፀጥታ አካላት፣
በአጠቃላይ በዚህ ታላቅ የጥምቀተ ክርስቶስ በዓል የተገኛችሁ ምእመናንና ምእመናት በሙሉ፤

በንስሓ መንፈስ ወደ እርሱ የሚቀርቡትን በማየ ጥምቀት በማንጻት ከፍዳ ኀጢአት ነፃ የሚያደርግ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ አራት ዓመተ ምሕረት በዓለ ጥምቀት በሰላም አደረሳችሁ።

“ነስሑ እስመ ቀርበት መንግሥተ ሰማያት
መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ፤”
(ማቴ. 3÷1)፤

ይህንን ቃለ ቅዱስ ወንጌል፣ አጥማቂው ቅዱስ ዮሐንስና ተጠማቂው ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የትምህርታቸው ርእስ አድርገው ያስተማሩበት ቃለ ብሥራት ነው፡፡ ትምህርቱ የመንግሥተ ሰማያት መግቢያ በር ንስሓ እንደሆነ በዋናነት ያመለክታል፡፡ መንግሥተ ሰማያት ማለት በሰማያትም በምድርም በአጠቃላይ በትዕይንተ ዓለማት ሁሉ በምልአት የምትገኝ የእግዚአብሔር ሥልጣን ናት፤ ጌታችንም ሆነ ቅዱስ ዮሐንስ “መንግሥተ ሰማያት ቀርባለችና ንስሓ ግቡ” የሚለውን አረፍተ ነገር የትምህርታቸው ዋና ርእስ አድርገው ማስተማራቸው፣ የእግዚአብሔር ሥልጣን በተነሳሕያንንና በኢተነሣሕያን ላይ ለይታ ልትፈርድ መዘጋጀቷን ለማመልከት እንደሆነ እንገነዘባለን፡፡ መጥምቁ ቅዱስ ዮሐንስ ይህንን ግልጽ ሲያደርግ “እነሆ ምሣር በዛፎች ላይ ተቀምጦአል፤ መልካም ፍሬ የማያፈራው ሁሉ ይቈረጣል፤ ወደ እሳትም ይጣላል” ካለ በኋላ “እንግዲህ ለንስሓ የሚገባ ፍሬ አድርጉ” በማለት የንስሓን አስፈላጊነት ያስገነዝባል፡፡ ይህ የንስሓ ጥሪ ለተወሰኑ ሰዎች ሳይሆን ለመላው የሰው ዘር የተላለፈ አምላካዊ ጥሪ ነው፡፡ ምክንያቱም የሰው ዘር በአጠቃላይ በኀጢአት አረም የተዋጠ ሆኖ ስለተገኘ፣ ከዚህ አረም ነፃ ለመሆን በእግዚአብሔር ፊት የመጀመሪያው ተግባር ንስሓ መግባት ስለሆነ ነው፡፡ የትምህርቱ ዋና ዐላማ ሰዎች አምነውና በንስሓ ተራምደው ወደ ጥምቀት ሲደርሱ የእግዚአብሔር ሥልጣን ልትቀበላቸው ዝግጁ ናት የሚለውን መልእክት በዋናነት ማስተላለፍ ነው፡፡ ጌታችን ሲጠመቅ ሰማይ መከፈቱ ይህንን የሚያረጋግጥ ነው፡፡ የእግዚአብሔር ሥልጣን በንስሓ ታድሰው ለሚቀርቡና ለሚጠመቁ ምእመናን ያዘጋጀችው ሰማያዊ ርስት ማደልን ብቻ ሳይሆን፣ የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን መብትንም ጭምር ለመስጠት ነው፡፡ “ይህ ልጄ ነው” የሚለው አምላካዊ ድምጽም ይህንን ያመሠጥራል፡፡ “ለተቀበሉት ሁሉ ግን የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን ሥልጣንን ሰጣቸው” ተብሎ ተነግሮናልና፡፡

የተወደዳችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች ምእመናንና ምእመናት፤

የበዓለ ጥምቀት ዐቢይ ጥሪ፣ ሰማያዊ ርስትንና የእግዚአብሔር ልጅ የመሆን መብትን ለማግኘት በእምነት ገብታችሁ፣ በንስሓ ተራምዳችሁ በጥምቀት ሀብተ ንጽሐን ተጐናጸፉ የሚል ነው፡፡ እዚህ ላይ እኛ ልንወስደው የሚገባን ትልቅ ኀላፊነት እንዴት ንስሓ እንግባ? የሚለውን ነው፡፡ ትምህርቱን በትክክል ተቀብለን ለተግባራዊነቱ በቈራጥነት ከተነሣን፣ ንስሓ መግባት የሚያስፈልገን መሆኑን ለማወቅ የማያወላውል ዘዴ አለን፡፡ እርሱም “ሰዎች ሊያደርጉላችሁ የምትፈልጉትን ሁሉ እናንተም እንዲሁ አድርጉላቸው” የሚል ነው፡፡ ይህ ትምህርት ጌታችን ያስተማረው፣ ዓለም በሙሉ “ወርቃማ ሕግ” ብሎ የተቀበለው ነው፡፡ ከዚህ የበለጠ የኀጢአትና የጽድቅ መመዘኛ የሚሆን ሚዛን የለም፡፡ ይህንን ሚዛን በቀጥታ ወደ ራሳችን አእምሮ አስገብተን ከመዘን፣ በአኛ ላይ ሊደረግብን የማንፈልገውን በሌላ ወንድም ላይ እንዳደረግን፣ አእምሮአችን በዝርዝር ይነግረናል፡፡ በዚህ ጊዜ አእምሮአችን የመሰከረብንን ጥፋት ተቀብለን መጸጸትና ንስሓ መግባት ከአኛ ይጠበቃል፡፡ ከዚህ አንጻር አእምሮውን ጠይቆ ከኀጢአት ንጹሕ ነህ የተባለ እዚህ መካከላችን ይኖር ይሆን? የሚለውን ብንጠይቅ ፍጹም ንጹሕ ሆኖ የሚገኝ ያለ አይመስለንም፡፡ ከተገኘም ቅዱስ መጽሐፍ አይቀበለውም፡፡ ለምን ቢባል? ለአንዲት ሰዓት ስንኳ ከስሕተት የማንነፃ ድኩማን ስለሆንን ነው፡፡ ቅዱስ ዮሐንስ በመልእክቱ ይህንን በተመለከተ ሲያስተምረን ”አልበደልንም የምንል ከሆነ እግዚአብሔርን ውሸተኛ እናደርገዋለን፡፡ ቃሉም በኛ ውስጥ የለም”ይላል፡፡ እንግዲያውስ ሁላችንም በድለናል ማለት ነው፡፡ እግዚአብሔርም፣ አእምሮአችንም በዚህ ተስማምተው አዎን ነው መልሳቸው፡፡ ይህ ከሆነ ዘንድ ሁላችንም ንስሓ መግባት ግዴታችን ነው።

የተከበራችሁ የበዓሉ ተሳታፊዎች ምእመናንና ምእመናት!ንስሓ በሰውና በእግዚአብሔር፣ በሰውና በሰው መካከል እውነተኛ ሰላምንና ዘላቂ ፍቅርን የሚገነባ  የሕሊና መሐንዲስ ነው፡፡ ሰላምና ፍቅር ከሰው ልጆች እየራቀ የመጣው በንስሓ የታጀበ እምነት መከተል ባለመቻላችን እንደሆነ ንጹሕ ልቡና ላለው ሁሉ የተደበቀ ምሥጢር አይደለም፡፡ ከዚህ አኳያ በሀገራችን ውስጥ ላለው ወቅታዊ ሁኔታም ፈውሱ በንስሓ የታጀበ፣ ከእግዚአብሔርና ከሰው ጋር የሚያስታርቅ ሃይማኖትን ገንዘብ አድርጎ መመላለስ የግድ ሆኖ ይገኛል፡፡ ትክክለኛ ንስሓ በራስ ላይ እንጂ በሌላ ላይ መፍረድን አይፈቅድም፡፡ ሁሉም ራሱን ፈትሾ በራሱ ላይ መፍረድ ከጀመረ፣ ያኔ ያማረ ውጤት ይገኛል፡፡ ወደ ፍጹም ሰላም የሚያደርስ መንገድ ያኔ ወለል ብሎ ይታያል፡፡ ስለዚህ ክርስቲያኖች በሕይወት ዘመናችን ሁሉ በራሳችን ላይ እየፈረድንና በንስሓ እየታደስን ልንኖር የሃይማኖታችን መርሕ እንደሚያስገድድ ተገንዝበን ንስሓ በመግባት ወደ ሰከነ አእምሮአችን ልንመለስ ይገባል።

በመጨረሻም ከበዓለ ጥምቀት አስተምህሮ እንዳስተዋልነው፣ በአበው ብሂልም “መተው ነገሬን ከተተው” እንደሚባለው በንስሓ መንፈስ ቅራኔን፣ ጥላቻን፣ በቀልንንና ቂምን እርግፍ አድርገን በመተው ለሰላም የሚደረገውን ጥረት በመደገፍ ለሀገራችን አንድነትና ለሕዝባችን ደኅንነት የሚበጀውን ሥራ እንድንሠራ ለሁሉም ኢትዮጵያውያን መንፈሳዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን።

በዓሉን የደስታ፣ ዘመኑም የሰላም ያድርግልን፤
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ ይቀድስ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።