ግንቦት 18 ቀን 2013 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ መርቆሬዎስ 4ኛው ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ፤
ብፁዕ አቡነ ያሬድ የመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ዋና ሥራ አስኪያጅና የአርሲሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዕ አቡነ ዮሴፍ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊና የሲዳማ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ፤
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፡-

የምሕረት አባት፣ የሰላም አለቃ የሆነው እግዚአብሔር አምላካችን ለዓመታዊው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ስላደረሰን በስሙ ልንወያይም ስላበቃን ክብርና ምስጋና ሁሉን ለሚችል ለኀያሉ አምላካችን ለእግዚአብሔር ይሁን፡፡

“ወተጸመዱ ለጸሎት ኵሎ ጊዜ በእንተ ኩሎሙ ቅዱሳን
ስለ ቅዱሳን ሁሉ ዘወትር ለጸሎት የተጠመዳችሁ ሁኑ”
(ኤፌ. 6፥18)

ከእግዚአብሔር ጋር የሚያገናኘን የቤተ ክርስቲያናችንና የሃይማኖታችን ቊልፍ፣ የግንኙነት መሣርያ ጸሎት እንደሆነ ለጥያቄ የሚቀርብ አይደለም፡፡እግዚአብሔር በሁሉም ያለና የሚገኝ ምሉእ አምላክ ነው፡፡ እግዚአብሔር ሁሉንም ያውቃል፣ ያያልም፡፡ ነገሮች ከመሆናቸው ወይም ከመታሰባቸው በፊት ሳይቀር ድንበርና ወሰን በሌለው ዕውቀቱ ያውቃል፡፡ ይሁንና ቢያውቅም ለፍጡራን ሁሉ በተለይም አእምሮና ለብዎ ላላቸው መላእክትና ሰዎች የተሰጣቸውን ብሩህ አእምሮ ተጠቅመው የሚበጃቸውን በራሳቸው እንዲመርጡና እንዲወስኑ ፍጹም ነፃነትን አጎናጽፎአቸዋል፡፡

ሰዎችም ሆኑ መላእክት ይህንን ነፃነት ተጠቅመው ያለ ምንም ተጽዕኖ ሲወስኑ በውሳኔአቸው ላይ እግዚአብሔር ተጽዕኖ አያደርግም፡፡ ውሳኔአቸውን ተከትሎ በሚመጣው ውጤት ግን ይጠይቃል፣ ዳኝነትም ይሰጣል፡፡ የመላእክትም ሆነ የሰዎች ውድቀት ሊከሠት የቻለው በዚህ ነፃ ምርጫና ውሳኔ እንደሆነ ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረን እውነት ነው፡፡ ዛሬም በዓለም እየሆነ ያለው ይኸው እውነት ነው፡፡ ሰው የከፋ ኀጢኣትን ለመፈጸም ሲሮጥ ምክርና ትምህርት ከመስጠት ባለፈ እግዚአብሔር በነገሩ ጣልቃ ገብቶ ሲያስቆም አናይም፡፡ “አቅረብኩ ለከ እሳተ ወማየ ደይ እዴከ ኀበ ዘፈቀድከ — እሳትንና ውኃን አቅርቤልሃለሁ፤ እጅህን ወደ ፈለግኸው ክተት” የሚለውም ይህንን እውነታ ያመለክታል፡፡ ከዚህ አንጻር ሰው መከራዎችንና ፈተናዎችን እየሳበና እየጎተተ የሚያመጣቸው በራሱ ነጻ ምርጫና ውሳኔ እንጂ በሌላ ተጽዕኖ እንዳይደለ እናስተውላለን፡፡ የርኩሳን መናፍስት ተጽዕኖ እንዳለ የምናይበት ጊዜ ቢኖር እንኳ መግቢያቸው የሰው ነፃ ዝንባሌ እንደሆነ በአዳምና በሔዋን ያየነው እውነት ነው፡፡ከዚህ ሌላ ደግሞ ሰዎች በሌሎች ምክንያቶች ሲፈተኑና መከራ ላይ ሲወድቁ የምናየው እውነት ነው፤ ከዚህም አኳያ በቃየን ምክንያት አቤል ሕይወቱን ሲያጣ እንመለከታለን፡፡ ስለዚህ ሰዎች በኀጢአት ምክንያት ከወደቁ በኋላ በራሳቸው ምርጫና ውሳኔ ወይም በሌላ ወገን ግፊት ፈተና ላይ ሲወድቁ እናያለን፡፡

ብፁዕ ወቅዱስ አባታችን፤ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳት የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት፤

የምንኖርባት ዓለመ ሰብእ ከላይ በተጠቀሱት ምክንያቶች ምን ጊዜም ከመከራና ከፈተና ተለይታ አታውቅም፡፡ ይህ የማይቀር ነገር መሆኑን የሚያውቅ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ የሰጠን መርሕ ቢኖር፡- “ትግሁ ወጸልዩ ከመ ኢትባኡ ውስተ መንሱ ማለትም ወደ ፈተና እንዳትገቡ ተግታችሁ ጸልዩ” የሚለው ነው፡፡ ቅዱስ ጳውሎስም ጌታችንን ተከትሎ ዘወትር ስለ ቅዱሳን እንድንጸልይ አስተምሮናል፡፡ ከዚህ አንጻር ከመከራና ከፈተና ለመዳን የተሰጠን የመዳኛ ስልት ተግቶ መጸለይ ነው፤ ስንጸልይም ለራሳችን ብቻ ሳይሆን ለቅዱሳን ሁሉ ተግተን ዘወትር መጸለይ እንዳለብን ተነግሮናል፣ ኀላፊነትም አለብን፡፡ ቤተ ክርስቲያን በደመ ክርስቶስ አንጽታ ስለ ቀደሰቻቸው ምእመናን ልጆቿ ዘወትር ስትጸልይ የምትኖረውም ከዚህ የተነሣ ነው፡፡ ቤተ ክርስቲያን ቅዱሳን ስለሆኑ ምእመናን ብቻ ሳይሆን ስለ ዓለሙ ሁሉ ማለትም ስለ ሰማዩም፣ ስለ ምድሩም፣ ስለ እንስሳቱም፣ በአጠቃላይ ስለ ፍጥረት ሁሉ ትጸልያለች፡፡ ይሁንና በአሁኑ ጊዜ ደግሞ በሀገራችን፣ በሕዝባችንና በደመ ክርስቶስ በተቀደሱ ክርስቲያን ልጆቻችን ላይ ከበድ ያለ ፈተና እየተከሠተ ስለሆነ ከምንም ጊዜ በላይ ወደ እግዚአብሔር አጥብቀን ልንጸልይ፣ ልናለቅስና ልናዝን ይገባናል፡፡ገዳማትና አድባራት፣ መነኮሳትና ቀሳውስት፣ ዲያቆናትና ወጣቶች፣ ምእመናንና ምእመናት ፈተና ላይ ሲወድቁና መከራ ሲጸናባቸው ቅዱስ ሲኖዶስን በቀጥታ የሚመለከተው ስለሆነ የመፍትሔው አካል ሆኖ መሥራት ይጠበቅበታል፡፡ ይህንን የፈተና ጊዜ አይተን እንዳላየን፣ ሰምተን እንዳልሰማን በዝምታ የምናልፈው ከሆነ ለቤተ ክርስቲያናችን ጠባሳ ታሪክ መሆኑ አይቀርም፤ በእግዚአብሔርም ተጠያቂነትን ማስከተሉ አይቀርም፡፡ ምእመናን ልጆቻችንም በዚህ ጉባኤ ላይ አመኔታ እንዳያጡ በጣም መጠንቀቅ አለብን፡፡

ይህ ጉባኤ በሀገሪቱ በተለያዩ አካባቢዎች እየተጎዱ ለሚገኙት ምእመናንና ምእመናት እንደዚሁም በአጠቃላይ ያለ ፍትሕ እየተጎዱ ለሚገኙ ሰዎች መፍትሔ አምጪ አካል ሆኖ ከጎናቸው ሊቆም ይገባል፡፡ይህንንም ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በተሰጠው የጥበቃ ኀላፊነት መሠረት በጸሎት፣ በማስታረቅ፣ በቊሳቊስ ማለትም መጠልያ፣ ምግብ፣ መጠጥ፣ ልብስና መድኀኒት በማቅረብ ሊያከናውነው ይገባል፡፡ ይህ መሰሉ ቅዱስ ተግባር ለቤተ ክርስቲያናችን አዲስ ነገር ሳይሆን ስታደርገው የነበረና አሁንም እያደረገችው የሚገኝ ነው፡፡ የአሁኑ ከሌላው ጊዜ ልዩ የሚያደርገው ነገር ቢኖር የችግሩ ክብደትና ውስብስብነት ማየሉ ነው፡፡ ይሁን እንጂ ሕልም ተፈርቶ መተኛት እንደማይቀር ሁሉ ክብደቱን አይተን የምንሸሸው ሳይሆን የቤተ ክርስቲያናችን የውስጥ ዐቅምን በማየት የምእመናንን ትብብርና እገዛ በመጠየቅ፣ እንደዚሁም የዓለም አብያተ ክርስቲያናትና ልዩ ልዩ በጎ አድራጊዎችን በማስተባበር መከራውንና ፈተናውን መቋቋም ይኖርብናል፤ ለዚህም የዛሬ ሠላሳ ዓመት ገደማ የነበረው ዐይነት አሠራር ዘርግተን ብንሠራ ሰውን ከረኃብ እልቂት ማዳን እንችላለን፡፡ ስለሆነም ቅዱስ ሲኖዶስ በዚህ ዙርያ በሰፊው መክሮበት ውሳኔ እንዲያሳልፍ በዚህ የመክፈቻ ጉባኤ በአጽንዖት እናሳስባለን፡፡

በመጨረሻም፤ ለመንግሥትም ሆነ ለሁሉም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ እንደዚሁም ለመላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ማስተላለፍ የምንፈልገው የአደራ መልእክት ቢኖር፣ የሁሉም ነገር መሠረትና የችግሮቻችን ሁሉ መፍትሔ ሰላምና ሰላም ብቻ መሆኑን በመገንዘብ ለሰላም ሲባል አስፈላጊ የሆነ ዋጋ መክፈል እጅግ አስፈላጊ መሆኑ ነው፡፡ ዋስትና ያለው ሰላም በሀገራችን ሊረጋገጥ የሚችለው ደግሞ ሁሉም ባለድርሻ አካላት በጠረጴዛ ዙሪያ ተሰባስበው መወያየት፣ መግባባትና ሀገራዊ ስምምነትን መፈጸም ሲችሉ ነው፡፡ ስለሆነም ይህ ለነገ የማይባል፣ የህልውናችን ጥያቄ መልስ መሆኑን ዐውቀን ሁላችንም በዚህ መልካም ሥራ እንድንተባበር በእግዚአብሔር ስም አባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡

እግዚአብሔር የተባረከ የተቀደሰ ጉባኤ ያድርግልን
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ
ወስብሐት ለእግዚአብሔር