የካቲት 9 ቀን 2018 ዓ.ም. ቅዱስነታቸው የዐቢይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ አስተላልፈዋል
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ ኣሐዱ አምላክ ኣሜን !!
በሀገር ውስጥና በልዩ ልዩ ክፍለ ዓለማት የምትገኙ ሕዝበ ክርስቲያን በሙሉ፡-
በመዋዕለ ጾሙ ሰይጣንንና መስሓቲ ተግባሩን ድል በማድረግ ድል እንድንነሣ ያደረገን ጌታችን ኣምላካችንና መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዓሥራ ስምንት ዓመተ ምሕረት ጾመ ኣርብዓ በሰላም ኣደረሰን ኣደረሳችሁ!
‹‹ወልበሱ ወልታ እግዚአብሔር በዘትክሉ ተቃውሞቶ ለመናግንተ ሰይጣን፤
የሰይጣንን ሽንገላ መቃወም ትችሉ ዘንድ የእግዚአብሔርን ጋሻ ልበሱ›› (ኤፌ.፮፥፲፩)፤
እኛ ሰዎች ቀዋሚና ምሕረት የለሽ ጠላት እንዳለን እናውቃለን፤ ይህ ጠላት ሰይጣን፣ ዲያብሎስ፣ክፉ መንፈስ፣ ርኩስ መንፈስ ተብሎ እንደሚጠራም ቅዱስ መጽሓፍ ነግሮናል፤ዲያብሎስ ከጥንት ጀምሮ በክፉ ሽንገላው ሰዎችን ሲጥል ኖሮኣል፤ ኣሁንም ከዚህ ክፉ ተግባሩ ኣልታቀበም፤ ለወደፊቱም ይታቀባል ተብሎ ኣይጠበቅም፤ ጌታችን በዚህ ዓለም በሥጋ በተገለጠ ጊዜም ይህ ክፉና ርኩስ መንፈስ በሽንገላ ቃሉ ጌታችንን ሊጥል ያልተሳካ ሙከራ ኣድርጎኣል፡፡ ርኩሱ መንፈስ ጾም መንፈሳዊ ኃይልን እንደሚያቀዳጅ ያውቃልና፣ጌታችን ምንም ሳይበላና ሳይጠጣ ኣርባ ቀንና ኣርባ ሌሊት መጾሙን ተመልክቶ፣በሽንገላ ቃሉ ሊጥለው ሙከራ ኣድርጎኣል፤ይህንን ያደረገበት ዋና ምክንያትም ጾም መንፈሳዊ ኃይል መሆኑን በውል ያውቃልና በጾም ኃይል ከእጄ ያመልጣል ብሎ በማሰቡ ነው፤ ይሁን እንጂ ሰይጣን የሰውን ደካማ ጠባይ በመጠቀም ያስለመደው ሽንገላ፣በተዋሕዶ ሰውም ኣምላክም በሆነው ጌታችን ላይ ሊሳካለት ባለመቻሉ ተሸንፎና ተስፋ ቆርጦ ሊሄድ ችሎኣል፡፡
የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን!
የጌታችን ድል ኣድራጊነት ያስተማረን ብዙ ነገር ኣለ፤በዚህ ተግባራዊ ትምህርቱ እኛ ጥንተ ጠላታችን ዲያብሎስን ድል የምናደርግባቸው ሁለት መሳሪያዎችን በዋናነት ኣሳይቶናል፤ እነሱም የእግዚአብሔርን ጋሻ መልበስና በጾም መንፈሳዊ ኃይልን መቀዳጀት ናቸው፡፡ ሁሌም እንደምንማረው በውስጣችን ሁለት ተቃራኒ ነገሮች ኣሉ፤ እነሱም ፍትወተ ሥጋና ፍትወተ መንፈስ ናቸው፤ እነኝህ ሁለት ነገሮች ኣንዱ ላንዱ ፍጹም ተቃራኒ መሆናቸውን ቅዱስ መጽሓፍ እንዲህ በማለት ያስረዳል፡-‹‹ እስመ ሥጋኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ መንፈስ፤ ወመንፈስኒ ይፈቱ ዘኢይፈቱ ሥጋ፤ ወይትኣበዩ በበይናቲሆሙ ከመ ኢትግበሩ ዘትፈቅዱ፤ ወባሕቱ እብለክሙ በመንፈስ ሑሩ ወፍትወተ ሥጋክሙ ኢትግበሩ፣ማለትም ሥጋ መንፈስ የማይወደውን ይወዳል፤ መንፈስም ሥጋ የማይወደውን ይወዳል፤እርስ በርሳቸውም ይቀዋወማሉ፤ስለዚህም የምትወዱትን ልታደርጉ ኣትችሉም፤ ነገር ግን እላለሁ በመንፈስ ተመላለሱ የሥጋን ምኞት ግን ከቶ ኣትፈጽሙ››(ገላ.፭÷፲፮‐፲፰)፡፡
እነኝህ የውስጣችን ጠባዮች በዚህ ደረጃ እርስ በርስ የሚቃረኑ መሆናቸው ለምናስተውላቸው በግልጽ የሚታወቁ ናቸው፤ ከዚህ ኣንጻር ሰይጣን ይህንን ክፍተት ተጠቅሞ የሥጋችንን ፍላጎት እንድንከተል ይገፋፋናል፤ መሳሪያዎቹ ደግሞ ፍቅረ መባልዕት፣ ፍቅረ ንዋይና ፍቅረ ሢመት ናቸው፤ ይህም በመሆኑ ነው ሰይጣን፣ በነዚህ ጌታችንን ሊሸነግለው የሞከረ፤ይሁንና ጌታችን እነኝህን የሽንገላ መሳሪያዎች ሰባብሮ ጥሎኣቸዋል፤የጣላቸውም በጾምና በእግዚአብሔር ቃል ነው፤
ጾም መጾም ማለት ከፍቅረ መባልዕት፣ ከፍቅረ ንዋይና ከፍቅረ ሢመት ፍላጎት ጨርሶ መራቅ ማለት ነው፤ ይህንን ኣደረግን ማለት ደግሞ ሥጋችን የማይወደውን፣መንፈሳችን ግን የሚወደውን ነገር ኣደረግን ማለት ነው፤ ይህ ሲሆን ሰይጣን ከሰረ፤ ድልም ሆነ ማለት ነው፤ በዚህ መንፈሳዊ ኃይል ዲያብሎስ ተሸንፎና ተስፋ ቆርጦ ይሄዳል፡፡ ከዚህ ኣኳያ እኛም በቃለ እግዚአብሔር እየተመራን የምንጾምበት ምክንያት የሥጋችንን ፍላጎት በመግራት ለነፍሳችን ፍላጎት ለማደርና በዚህ ኃይለ መንፈስ ሰይጣንን በማሸነፍ የእግዚአብሔር ቤተ ሰብ ለመሆን ነው፡፡
የተከበራችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን!
የጾም ዋና ዓላማ ሥጋዊ ፍላጎትን መግራት፣ በምትኩ ደግሞ መንፈሳዊ ፍላጎትን ማጐልበት እንደሆነ ተነግሮናል፤በመሆኑም ይህንን መርሕ ጠብቀን መጾም ግዴታችን ይሆናል፤ ዛሬ ባለንበት ዓለም ሥጋዊ ፍላጎታችን ያየለበት፣መንፈሳዊ ፍላጎታችን ግን የተዳከመበት ዘመን ላይ እንገኛለን፤ ከፍቅር ይልቅ ጥላቻ፣ ከኣንድነት ይልቅ መለያየት፣ ከመራራት ይልቅ ጭካኔ፣ ከእምነት ይልቅ ክሕደትና ኣስመሳይነት በዓለማችን ላይ የበላይነቱን ይዞ መገኘቱ ለዚህ ማሳያ ነው፤ የተወደዳችሁ ሕዝበ ክርስቲያን ልጆቻችን! ይሁንና ዓለም ቢሰማም ባይሰማም፣ ሓቁም ጠቃሚውም የመንፈስን ፍላጎት ማጐልበት ስለሆነ የመንፈስ ፍሬዎች የሆኑትን ማለትም፣ ፍቅርን ሰላምን፣ ኣንድነትን፣ ርኅራኄንና፣ ሃይማኖትን፣ ማስፈን ምርጫችን ልናደርግ ይገባል፤ ቤተክርስቲያንም እንድንጾም የምታስተምረን እነዚህን ለመተግበር ጾም ፍቱን መሳሪያ ሆኖ ስለሚገኝ ነው፡፡
ከዚህ ኣንጻር የጾም ዓላማውና ግቡ ጽኑዕ ሃይማኖትን፣ እውነተኛ ፍቅርን፣ ዘላቂ ሰላምን፣ ልባዊ ኣንድነትን፣ የማይናወጽ ፍትሕንና እኩልነትን፣ ወሰን የሌለው ርኅራኄን በውስጣችን፣ ብሎም በዓለማችን ማሥረጽ እንደሆነ በውል ተገንዝበን ጾሙን መጾም ይገባል፤ልንለብሳቸው የሚገቡ እነዚህ የመንፈስ ፍሬዎች የእግዚአብሔር ጋሻዎች ናቸውና፡፡ ይህንን ካደረግን እንደ ጌታችን የሰይጣንን ሽንገላ በጣጥሰን በመጣል በኣስተማማኝ ሁኔታ ድል ማድረግ እንችላለን፤ የተጠራነውም ለዚሁ ነው፡፡
በመጨረሻም፡-
የሕዝባችንና የሀገራችን የራስ ምታት ሆኖ የሚገኘውን ያለመግባባት ዝንባሌ ለመቅረፍ ከልብ በመጸለይ፣ እንደዚሁም የተራቡትን በማጒረስ፣ የታረዙትን በማልበስ፣ የተጠሙትን በማጠጣት፣ የተጣሉትን በማስታረቅ፣ ፍትሕ ለተነፈጉትም እውነተኛ ፍትሕን በመስጠት፣ መዋዕለ ጾሙን እንድንጾመው በእግዚአብሔር ስም ኣባታዊ መልእክታችንን እናስተላልፋለን፡፡
“እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ”
ወስብሓት ለእግዚአብሔር ኣሜን!
አባ ማትያስ ቀዳማዊ
ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጰሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአኲስም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለሃይማኖት፣
የካቲት ፱ ቀን ፳፻፲፰
አዲስ አበባ ኢትዮጵያ