የካቲት 29 ቀን 2013 ዓ.ም የዓብይ ጾምን መግባት በማስመልከት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገር ውስጥና በመላው ዓለም የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት በሙሉመልካም ስጦታ ሁሉ ገንዘቡ የሆነ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥራ ሦስት ዓመተ ምሕረት የጌታችን የአምላካችንና የመድኀኒታችን የኢየሱስ ክርስቶስ መዋዕለ ጾም በሰላም አደረሳችሁ!!
“ኦሆ በልዎ ለእግዚአብሔር ወእንብየ በልዎ ለሰይጣን ወይጐይይ እምኔክሙ
እንግዲህ ለእግዚአብሔር እሺ በሉት፤ ሰይጣንን ግን እንቢ በሉት ከእናንተም ይሸሻል።”
(ያዕ. 4፥7)
ሐዋርያው ቅዱስ ያዕቆብ በዚህ መልእክቱ እግዚአብሔርን እሽ እንድንል፥ ሰይጣንን ግን እምቢ እንድንል ያስተማረን ያለምክንያት አልነበረም፤ እኛ ሰዎች ከክብር ወደ ኀሣር፤ ከማግኘት ወደማጣት የወረድንበት ክ ጠላት እሱ ስለሆነ እንጂ፤ቀዳማዊ አዳም ለእግዚአብሔር መታዘዝን ቸል ብሎ ወይም ትቶ ለሰይጣን የታዘዘ ቀን ነበረ የሰው ልጅ ጸጋውን ሁሉ ያጣው፤ ያን ጊዜ ሰው ሰይጣንን እምቢ ብሎ ለእግዚአብሔር ቢታዘዝ ኖሮ በሰው ላይ የደረሰው ውድቀት አይከሠትም ነበር፡፡ ሰይጣን ሰውን የጣለው በመብል ምክንያት እንደነበረ ቅዱስ መጽሐፍ የሚነግረን እውነታ ነው፤ሰውን አስጐምጅተው ወደ ስሕተት ከሚጥሉ ነገሮች አንዱ መብል እንደሆነም እናውቃለን፡፡
ዲያብሎስ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስን ለመፈተን የተጠቀመው ስልትም እንደዚሁ መብል ነበረ፡፡ ነገር ግን ክብር ለእርሱ ይሁንና ዲያብሎስ፡-
• በስስዕት ቢመጣበት በትዕግሥት፣
• በትዕቢት ቢመጣበት በትሕትና፣
• በፍቅረ ንዋይ ቢመጣበት በጸሊአ ንዋይ ድል ስላደረገው ተስፋ በመቊረጥ ትቶት እንደ ሄደ ከቅዱስ መጽሐፍ እንረዳለን፡፡
ይህ ሁናቴ የሚያመለክተን እውነታ ቢኖር ሰው በዲያብሎስ የሚሸነፈው በፈቃደ ሥጋው ዝንባሌ መሆኑ ነው፤ዲያብሎስ ለቀዳማዊ አዳምም ሆነ ለዳግማዊ አዳም የዘረጋቸው የጥፋት ወጥመዶች ከላይ የተጠቀሱት ፈቃዳተ ሥጋ ናቸው፡፡ ቀዳማዊ አዳምን ለእሱ ታዛዥ በማድረግ ድል ያደረገበትም ይኸው ፈቃደ ሥጋ ነው፤ በአንጻሩ ደግሞ ዳግማዊ አዳም እሱን ድል ያደረገበት ይህን ፈቃደ ሥጋ ባለመቀበል ነው፡፡ከዚህ አኳያ ዲያብሎስ ሰውን ለመጣል የሚጠቀምበት መሣሪያ ፈቃደ ሥጋ ከሆነ ለፈቃደ ሥጋ ባለመሸነፍ ዲያብሎስን በብርቱ መቃወም ይኖርብናል። በአንጻሩ ደግሞ ለእግዚአብሔር በታማኝነት መታዘዝ ይኖርብናል ማለት ነው፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
የጌታችንን ጾም በማሰብ የምንጾመው ይህ ዐቢይ ጾም ዋና ዐላማው ዲያብሎስን በመቃወም ለእግዚአብሔር ለመታዘዝና ለመገዛት ነው፤የዲያብሎስ ውጊያ ለብዙዎቻችን ላይገባን ይችላል፡፡ ነገር ግን ላስተዋለው እጅግ በጣም ቀላል ነው፤ ይኸውም ፈቃደ ሥጋችንን ለመፈጸም ብለን የማይገባውን ነገር ለማድረግ ስንጐመጅ ያን መልእክት የዲያብሎስ ውጊያ መሆኑን ማወቅ እንችላለን፤ታድያ በዚህ ጊዜ የእኛ አቅዋም ሊሆን የሚገባው መቃወም ብቻ ነው፡፡
በአንጻሩ ደግሞ ለእግዚአብሔርም ለሰውም የሚበጅ፤ለሊናም ጸጸት የሌለው ሥራ እንድንሠራ ሊናችንም ቤተ ክርስቲያንም ሲነግሩን፣ አእምሮአችንም ሲቀበለው ያ ነገር በቀጥታ የእግዚአብሔር መልእክት መሆኑን ተገንዝበን እሱን መፈጸም ነው፤ለእግዚአብሔር መታዘዝ ማለትም ይኸው ነው፤ በሌላ አገላለጽ፣ እግዚአብሔር በቅዱስ መጽሐፍ አድርጉ ያለንን ማድረግ አታድርጉ ያለንን አለማድረግ ነው፤ ይህም ማለት ለእግዚአብሔር መገዛት ማለት እንደሆነ ማስተዋል ይገባል፤ መታዘዝም ማለት ይኸው ነው፤ይህ ነገር በሕይወታችን ዘመን ሁሉ እንደ ዐይን ብሌን ልንጠብቀውና ልንፈጽመው ይገባናል፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤
ዲያብሎስን መቃወም በአንጻሩ ደግሞ ለእግዚአብሔር መታዘዝ የዘወትር ተግባራችን ቢሆንም በተለይም በጾም ወቅት በብርቱ ልንፈጽመው ስለሚገባ ፈቃደ ሥጋን በማድከም፣ ፈቃደ ነፍስን ግን በማጐልበት እንጾማለን፤ በመሆኑም በአሁኑ ጊዜ አብዝተን ልንሠራው ከሚገባን ፈቃደ ነፍስ፣ ሰላም፣ ፍቅር፣ ስምምነት፣ ይቅር ባይነት፣ መታዘዝ፣ መተጋገዝ፣ መራራት ካለው ከፍሎ ለሌለው መስጠት የሚሉት በዋናነት የሚታዩ ናቸው፡፡ ምክንያቱም በሀገራችን በተከሠተው ችግር መንሥኤነት ብዙ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ለረኃብ፤ ለእርዛት፤ ለመፈናቀል መዳረጋቸውን በብዙ መልኩ እየሰማን ነው፤ እያየንም ነው፤ችግሩ እኛን ብቻ ሳይሆን የዓለም ማበረ ሰብንም እያሳሰበ እንደሆነ እያየን ነው፡፡ በመሠረቱ ይህ መከራ ሊከሠትብን የቻለው በውስጣችን ፍቅርና ሰላም በመጥፋቱ ስለሆነና አሁንም መፍትሔው በእኛው እጅ ስለሆነ ነገሮች በሰላምና በፍቅር እልባት እንዲያገኙ ሁሉም ወገን ያላሰለሰ ጥረት ማድረግ ይኖርበታል፡፡ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በየአቅጣጫው ያሉ የተቸገሩ ወገኖቻችንን ለመርዳትና ለማገዝ እጆቻችን በርራኄ ሊዘረጉ ይገባል፡፡ በዚህ መንፈስ ተቃኝተን ጾምን የምንጾም ከሆነ በእርግጥም ለእግዚአብሔር ታዝዘናል ማለት ነው፡፡
በመጨረሻም፤ ከሁሉ በፊት የሰው ሕይወት በቀጣይነት እንዳይጎዳ፣ አብያተ ክርስቲያናት እንዳይደፈሩ፣ ንዋየ ቅድሳትና ቅርሶች እንዳይዘረ መንግሥት ድርጊቱን በማስቆም ለሁሉም የሕግ ከለላ እንዲያደርግላቸው ሕዝቡ የሃይማኖት ተቅዋማትና በጎ አድራጊዎችም በችግር ያሉ ወገኖችን በመደገፍ የበኩላቸውን ርዳታ እንዲያደርጉ፣ መንፈሳዊና አባታዊ ጥሪያችንን እያስተላለፍን በጎ አድራጊዎች ሁሉ ለእግዚአብሔር እና ለሰብኣዊ ፍጡር ሲሉ በከፍተኛ ችግር ላይ የወደቁትን ወገኖች ሁሉ ሕይወት እንዲያተርፉ በእግዚአብሔር ስም እንማፀናለን፣ እናሳስባለን፡፡
እግዚአብሔር አምላካችን ወርኀ ጾሙን አስፈጽሞ ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም ያድርሰን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤
ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን።