የቅዱስ ሲኖዶስ የሰላም ልኡካን ሽኝት ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም
ሐምሌ 10 ቀን 2010 ዓ.ም የኢትዮጵያ ኦርቶዶስክ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ አሜሪካ ለሚጓዙ የዕርቀ ሰላም ልኡካን ሽኝት አድርጓል፡፡
በሽኝቱ መርሐ-ግብር ላይ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቀ ጳጳስ ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት አባታዊ መልእክትና መመሪያን ሰጥተዋል፡፡
ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ለዚህ ዕርቀ ሰላም ሂደት የበኩሏን ጥረት ስታደርግ መቆየቷን አስታውሰው ዛሬም ቅዱስ ሲኖዶስ በሁሉም መንገድ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀው የዕርቀ ሰላሙ ሂደት ወደ ፍጻሜ ማምራት እንዳለበት አበክረው አስታውቀዋል። ቅዱስነታቸው በአባቶች መካከል መከፋፈል ከመፈጠሩ በፊት የነበረውን ሰላምና አንድነት አስታውሰው “ሰላምና ፍቅር ለሁሉም ጥሩ ነው” ካሉ በኋላ “ያለፈውን ሁሉ ረስተን ወደ ጥንት አንድነታችንና ወደ ጥንት ፍቅራችን፣ ወደ ጥንት መንፈሳዊ ሕይወታችን እንድንመለስ እግዚአብሔር ይርዳን” በማለት ልባዊ ምኞታቸውን ገልጸዋል።
በተጨማሪም “ሰላም በእጃችን ሳለች አትታወቅም ከእጃችን ከወጣች በኋላ እንጂ” በማለት የተናገሩት ቅዱስነታቸው “ቤተ ክርስቲያን የሰላም ቤት ናት፣ ቤተ ክርስቲያን የሰላም ምንጭ ናት፣ ቤተ ክርስቲያን የመለያየትና የመከፋፈል ምክንያት አይደለችም” በማለት በአባቶች መካከል የተፈጠረው መለያየት የቤተ ክርስቲያን ባሕርይ አለመሆኑን በአጽንዖት ገልጸዋል። አያይዘውም “የቤተ ክርስቲያን ሥራ ሰላም፣ ፍቅርና አንድነት መመሥረት ሆኖ ቤተ ክርስቲያንን ማገልገል፣ አገርን መጠበቅና ትምህርት ማስተማር ነው” በማለት የቤተ ክርስቲያን አገልጋይ አባቶች ካህናትና ምእመናን ለሰላም፣ ለፍቅርና ለአንድነት እንዲሠሩ መልእክታቸውን አስተላልፈዋል።
ብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትም በቅዱስ ፓትርያርኩ የተላለፈውን መልእክት በመጋራት ቅዱስነታቸው አስቀድሞ ጀምረውት የነበረው ዕርቀ ሰላም ዛሬም በቅዱስነታቸው ዘመን ለፍጻሜ መቅረቡ ዕደለኛነታቸውን ጠቅሰው በየራሳቸው እይታ ዕርቀ ሰላሙ ከመቼውም ጊዜ ይልቅ ዛሬ ዕውን ሊሆን የሚችልበት ወቅት ላይ መድረሱን ገልጸዋል። ልኡካኑም ይህ የዕርቀ ሰላም ሂደት በጥሩ መንገድ እየተጓዘ የመጣ መሆኑን በማስታወስ ከፍጻሜ ላይ ደርሶ የቤተ ክርስቲያንን ሰላምና የአባቶችን አንድነት በቅርቡ ማየት እንድንችል የቅዱስነታቸውና የብፁዓን አባቶች ድጋፍና ጸሎት እንዳይለያቸው ተማጽነዋል።
የዕርቀ ሰላም ኮሚቴ አባላትም ላቀረቡት የዕርቀ ሰላም ጥያቄ ከቅዱስ ፓትርያርኩና ከቅዱስ ሲኖዶስ ላገኙት አዎንታዊ መልስና ቀና ትብብር ምስጋናቸውን ገልጸው የተጀመረው ዕርቀ ሰላም በመልካም ፍጻሜ እንዲቋጭ አሁንም ድጋፋቸውና ጸሎታቸው እንዳይለያቸው ተማጽነዋል።