• Amharic  
  • English  
የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽ/ቤት
  • ቀዳሚ ገጽ
  • የኢ/ኦ/ተ/ቤ
    • የኢትዮጵያ መንበረ ፓትርያርክ እና ሐዋርያዊ የሥልጣነ ክህነት ትውፊት
    • ሃይማኖተ እግዚአብሔር በኢትዮጵያ
  • ልዩ ጽ/ቤት
    • የብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ ልዩ ጽሕፈት ቤት
    • የቅ/ሲኖዶስ ውሳኔዎች
    • የሀገር ውስጥ ሐዋርያዊ አገልግሎቶች
    • የውጭ አህጉር ሐዋርያዊ ጒዞ
  • ቃለ በረከት
  • ዜና መዋእል
  • ያግኙን
  • Menu Menu

ዜና መዋእል

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን 6ኛ ፓትርያርክ ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በፓትርያርክነት መምራት ከጀመሩ እነሆ 10 ዓመታት ተቈጠሩ፡፡

ቅዱስነታቸው ባለፉት 10 ዓመታት የአገልግሎት ዘመናቸው የቤተ ክርስቲያናችንን አገልግሎት የሚያጠናክሩና የሚያስፋፉ፣ መጠነ ሰፊ ተግባራት አከናውነዋል፡፡ ከእነዚህ እጅግ መሠረታዊና ጠቃሚ ተግባራት መካከል ቤተ ክርስቲያናችን መረጃዎችን ለሕዝበ ክርስቲያኑ ማስተላለፍ የምትችልበት የቴሌቪዥን ጣቢያ ባለቤት የሆነችበት የአገልግሎት ዘርፍ አንዱና በቀዳሚነት የሚጠቀስ ታሪካዊ ክንውን ነው፡፡

ቅዱስነታቸው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን በፓትርያርክነት መምራት በጀመሩ ማግስት ጥብቅ መመሪያ ካስተላለፉባቸው ጉዳዮች መካከልን በቤተ ክርስቲያን የሚስተዋለው የሙስና ተግባር ከሥሩ ተነቅሎ እንዲጣልና ቤተ ክርስቲያናችን ወደ ቀደመ ልዕልናዋ የምትመለስበት የፀረ ሙስና ሥራዎች ተጠናክረው እንዲከናወኑ የሰጡት አባታዊ መመሪያና አገልግሎቷ ሁሉ ዘመኑን በዋጀ መልኩ በመሪ ዕቅድ የሚከወንበት ሥርዐት እንዲዘረጋ ያስተላለፉት ታሪካዊ መልእክት በብዙዎች ዘንድ ተቀባይነት ያገኘ መልእክት ነበር፡፡

ይሁንና በሙስና ተግባራት ዙሪያ የሰጡት መመሪያ ከሙስናዊ አሠራሩ ሥር መስደድና ውስብስብነት አንጻር ፍሬ ማፍራት ባይችልም በመሪ ዕቅድ ዙሪያ የሰጡት መመሪያ ከብዙ ፈተናና እልህ አስጨራሽ ትግል በኋላ በተቋም ደረጃ እውን መሆን የሚችልበት ሁኔታ መፈጠር በመቻሉ በመሪ ዕቅድ ዝግጅት አሠራርና አተገባበር ዙሪያ በተደጋጋሚ በቅዱስ ሲኖዶስ ውይይት ሲደረግበት ከቆየ በኋላ እነሆ ተግባራዊ መሆን የሚችልበት ሁኔታ ተፈጥሮ የመሪ ዕቅድ ትግበራ ጽ/ቤት በመምሪያ ደረጃ ተዋቅሮ ወደ ሥራ የገባበት ሁኔታ እውን ሆኗል፡፡ የመሪ ዕቅድ ትግበራ በተቋም ደረጃ የሚመራበትን ሁኔታ በማመቻቸትም ወደ ዝርዝር ሥራው መግባት ተችሏል፡፡
የብፁዕ ወቅዱስነታቸው ዘመነ ሢመት በርካታ ስኬቶችና መከራዎችን ያሳለፈና በማሳለፍ ላይ ያለ ዘመነ ሢመት ነው፡፡ ይሁንና በቅዱስነታቸው ጸሎት፣ በቅዱስ ሲኖዶስ ያላሰለሰ ጥረትና ትዕግሥትን የተላበሰ የሥራ መመሪያ በርካታ ስኬታማ ሥራዎች ተከናውነዋል፡፡ ከሁሉም ሥራዎች በጒልሕነቱና ቤተ ክርስቲያንን ከሁለት መከፈል የታደገውና ቅዱስነታቸው ወደ ፓትርያርክነት ከመምጣታቸው በፊት ጀምሮ በግላቸውና በቅዱስ ሲኖዶስ ደረጃ ከፍተኛ ጥረት ሲያደርጉበት የነበረው ሁለቱ ሲኖዶሶችን ወደ አንድ ለማምጣት በተደረገው ጥረት በውጪ የነበረው ቅዱስ ሲኖዶስ ወደ ሀገር ቤት በመግባት አንድነቱ የተፈጠረውም በቅዱስነታቸው ዘመነ ሲመት በኢ.ፌ.ድ.ሪ. ጠቅላይ ሚኒስቴር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ድጋፍ ጭምር ነው፡፡

ሌላውና በቅዱስነታቸው ዘመነ ሢመት ሀገራችን ከገጠማት ጠንካራ ኀዘን መካከል በሊቢያ በአይኤስ አሸባሪዎች የተገደሉት ኢትዮጰያውያን ወገኖቻችን ኀዘን በግንባር ቀደምትነት የሚጠቀስ ሲሆን በሀገራችን ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች የተከሠተው ህውከትና በህውከቱ ምክንያት ሕይወታቸውን ያጡ ክርስቲያን ወገኖችን የተቃጠሉ አብያተ ክርስቲያናትና በግፍ የተገደሉ ካህናት አሠቃቂ ህልፈትና የኮረና ቫይረስ ወረርሽኝ መከሠት በቅዱስነታቸው ዘመነ ሢመት የተከሠቱ ፈታኝ ችግሮች የነበሩ ቢሆንም በቅዱስነታቸው ጸሎትና በቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔ ልዩ ልዩ የፀረ ኮረና ቫይረስ ሥራዎች ተከናውነው ቫይረሱ ትርጒም ያለው ጉዳት ሳያደርስ የመከራው ጊዜ አልፏል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በቅዱስነታቸው ዘመነ ሢመት የቤተ ክርስቲያችን አሠራሮች በተለይም የሂሳብ አያያዝ ሥርዐቱ የዘመነበት በውጭ ኦዲተሮች ጭምር መመርመር የጀመረበት ዘመን ሲሆን በተለያዩ ምክንያቶች ወደ ውጪ የወጡ ጥንታዊያን ቅርሶችም ወደ ሀገር ቤት የተመለሱበት ዘመን ነበር፡፡ በሌላ በኩልም በተቋም ደረጃ በቤተ ክርስቲያን ደረጃ በርካታ የልማት ሥራዎች የተሠሩበት አህጉረ ስብከት የተጠናከሩበትና በቅዱስነታቸው አንብሮተ እድ በርካታ ጳጳሳት የተሾሙበት፥ የውጭ አህጉረ ስብከት የተጠናከሩበትና በዐረብ ሀገራት ጭምር አብያተ ክርስቲያናት መታነጽ የጀመሩበት ስኬታማ ዘመን ሆኖ በታሪክ ተመዝግቧል፡፡

በዚህ በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዜና መዋዕል መጽሐፍ ከቅዱስነታቸው የሕይወት ታሪክ ጀምሮ በቅዱስነታቸው የተከናወኑ በርካታ ተግባራት ተዘርዝረው ቀርበዋል፡፡ ይህ መጽሐፍ 15 ርእሶችን መሠረት በማድረግ የተዘጋጀ ሲሆን የቅዱስነታቸው ልደት፣ ምንኲስና፣ ጵጵስናና ፕትርክና ላይ ያተኮሩ ግለ ታሪኮች፣ የቅዱስነታቸው ዘመነ ሢመት ዋና ዋና ክንውኖች ቅዱስነታቸው ያስተላለፏቸው አባታዊና ታሪካዊ መልእክቶችን ጨምሮ ጠቃሚ መረጃዎች ተካተውበት ተዘጋጅቷል፡፡

በልዩ ልዩ ምክንያቶች ለኅትመት ሳይበቃ የቆየው የቅዱስነታቸው ዜና መዋዕል መጽሐፍ የቅዱስነታቸውን 10ኛ ዓመት ዘመነ ሢመት ምክንያት በማድረግ በተቋቋመው የመጽሐፍ ዝግጅት ዐቢይ ኮሚቴ አማካኝነት የተዘጋጀ ሲሆን ዜና መዋዕሉ አስተማሪ፣ መረጃ ሰጪ፣ ለምርምርና ለታሪክ የሚሆኑ በርካታ ጽሑፎች የተካተቱበት ሆኖ መዘጋጀት ይችል ዘንድ ከፍተኛ ጥረት ተደርጓል፡፡ ዝግጅቱ የተዋጣለት ስኬታማና ሥርዐተ ቤተ ክርስቲያንን የጠበቀ መሆን ይችል ዘንድም የመጽሐፉ ሙሉ ዝግጅት እና የሥነ ጽሑፉ ይዘት በቤተ ክርስቲያናችን ሊቃውንት ጉባኤ መምሪያ በኩል ታርሞና ተመርምሮ እንዲታተም ተደርጓል፡፡

በአጠቃላይ ይህ ታሪካዊ መጽሐፍ ተቋማዊ ይዘት ኖሮት መዘጋጀት ይችል ዘንድ አዘጋጅ ኮሚቴው ከፍተኛ ጥረት አድርጓል፡፡ አንባቢያንም ጠቃሚ መረጃ፣ የሚያገኙበት ዕድል ተፈጥሯል ተብሎ ይታመናል፡፡ መጽሐፉ በዝግጅትና በሥነ ጽሑፍ ይዘቱ ጠንከር ያለ መልእክቶቹን በመረጃ በማስደገፍ ደረጃ በርካታ ሰነዶችና ፎቶግራፎች የተካተቱበት እንዲሆንም ጥረት ተደርጓል፡፡ መጽሐፉ ለታሪክና ለምርምር ጠቃሚ እንዲሆን ከማድረግ በተጨማሪ የውጪ ሀገር ዜጎች አስፈላጊውን መረጃ በቀላሉ ማግኘት የሚችሉበትን ሁኔታ መፍጠር ይቻል ዘንድ የመጽሐፉ ዋና ዋና መልእክቶች የተዳሰሱባቸው ዝግጅቶች በእንግሊዝኛ ቋንቋ እንዲተረጐሙ በማድረግ በመጽሐፉ ውስጥ እንዲካተት ተደርጓል፡፡

የመጽሐፉ ይዘትም ሳቢ፣ ማራኪና ቤተ ክርስቲያናችንን የሚመጥን መሆን ይችል ዘንድ በገጽ ቅንብር ሥራው በኅትመት ግብአቶች ጥራትና ውበት እንዲሁም በኅትመት ጥራቱ ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ ተደርጎ እንዲታተም ተደርጓል፡፡ በመሆኑም አንባቢያንና የታሪክ ተመራማሪዎች መጽሐፉን በቋሚ ሰነድነት የሚጠቀሙበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡ አሁን ያለንበትን ዘመን ታሳቢ በማድረግም መጽሐፉ በቤተ ክርስቲያኒቱ የቴክኖሎጂ ግብአቶች ማለትም በቤተ ክርስቲያኒቱ የማኅበራዊ ድኅረ ገጾች የሚጫንበት እና በሶፍት ኮፒ ደረጃ ተደራሽ የሚሆንበት ሁኔታ ተፈጥሯል፡፡

መልካም ንባብ ይሁንልን፡፡

በፌስቡክ ያግኙን

© Ethiopian Orthodox Tewahedo Church | Website by atbiya.com
  • Link to Facebook
Scroll to top Scroll to top Scroll to top