ከጥቅምት 12 ቀን እስከ 21 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ንኡስ አንቀጽ 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉባኤው ከጥቅምት 6 ቀን 201ዐ ዓ.ም. ጀምሮ የመንበረ ፓትርያርኩን አጠቃለይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤና ዓመታዊውን የቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ ለ15 ቀናት ወሳኝ በሆኑ የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡

1. ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በጉባኤው መክፈቻ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ ሕይወት የቃኘ፣ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን እድገትንና የሰላም አስፈላጊነትን በስፋት የገለጸ በመሆኑ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡
2. የሠላሳ ስድስተኛውን የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ ሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ አንዳንድ ማሻሻያ በማድረግ የጋራ መግለጫው የ2010 በጀት ዓመት ተግባር ሆኖ ያገለግል ዘንድ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
3. የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዓተ አምልኮ እስከ አሁን ድረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደኖረ ሁሉ አሁንም ከመንበረ ፓርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ተሰጥቷል፡፡
4. በመንበረ ፓትርያክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ሒሳብና በጀት መምሪያ ተዘጋጅቶ የቀረበው የ2010 ዓ.ም. በጀት የክፍያው ጣሪያ ተጠብቆ ሥራ ላይ እንዲውል ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
5. የአንድ ሀገር እድገትና መሠረታዊ ፍላጎት ግቡን ሊመታ የሚችለው የሃይማኖቱና የሞራል ስሜቱ የማይወቅሠውን በሚሠራ፣ በመልካም ሥነ ምግባር በታነጸ፣ የሥራን ክቡርነት በተረዳና እግዚአብሔርን መፍራት የጥበብ መጀመሪያ መሆኑን ባስተዋለ ትውልድ ተደግፎ ሲገኝ ስለሆነ፣ ኅብረተሰቡ ይህንኑ በመረዳት፣ በትዕግሥትና በመቻቻል፣ በመከባበርና በመናበብ፣ በመደማመጥና በመግባባት መንፈስ በአንድነት ተባብሮ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
6. የነገድ፣ የሃይማኖትና የጾታ ልዩነት ሳይኖር ለጋራ ህልውና ለጋራ ልማትና ለጋራ ብልጽግና ለሀገራችን ኢትዮጵያና ለጎረቤት አህጉር ብሩህ ተስፋ ሠንቆ እንደሚመጣ የተነገረለት የዐባይ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ፕሮጀክት ኢትዮጵያዊነቱን እያስመሰከረ ስለመጣ አሁንም የፕሮጀክቱ ሥራ ተጠናክሮ ለውጤት እስከሚበቃ ድረስ ሁሎችም ኢትዮጵያውያን አስፈላጊውን ድጋፍ በመለገስ እንዲተባበሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
7. ትውልድ ሁሉ የሙያና የሥነ አእምሮ ብቃቱን አሳድጎ ሥራ የመፍጠር ክሂሎቱን እንዲያረጋግጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አስተላልፏል፡፡
8. ዕቅድን በተግባር ለማረጋገጥ፣ ሠርቶ ለማግኘት፣ ውሎ ለመግባት፣ አድሮ ለመነሣት፣ ዘርቶ ለማምረት፣ ነግዶ ለማትረፍና በነፃነት ለመኖር ሰላም ያስፈልጋል፡፡ ስለዚህ ሀገራችን ኢትዮጵያ ለአፍሪካ አህጉር የነፃነት ምልክት እንደሆነች ሁሉ የሰላምና የጸጥታም ምልክት መሆን አለባት፤ ከዚህ አንጻር ሰሞኑን በተለያየ ምክንያት በወገኖቻችን መካከል የተከሠተው ግጭት ተወግዶ ሙሉ ሰላምን የማስፈኑ ሥርዐት ተፋጥኖ እንዲረጋገጥ፣ ከዚህም ጋር በግጭቱ ምክንያት ለተጎዱ ወገኖቻችን ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አህጉረ ስብከት የአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ባለው መዋቅር ብር 6,000,000 (ስድስት ሚሊዮን) የገንዘብ ድጋፍ እንዲደረግ፡፡ እንዲሁም ከጥቅምት 27 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ በመላ ሀገሪቱ ባሉት ገዳማትና አድባራት ለሁለት ሱባኤ ማለትም ለ14 ቀናት ያህል ጸሎተ ምሕላ እንዲደረግ ተወስኗል፡፡
9. በውጭ ሀገር ከሚኖሩት አባቶች ጋር ቀደም ሲል ተጀምሮ የነበረው ዕርቀ ሰላም አሁንም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔን አሳልፎአል፡፡
10. በቃለ ዐዋዲው የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ መሠረት የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ እምነት ተከታዮች የሆኑት ወጣቶች በየአጥቢያ ቤተ ክርስያናቸው በሰንበት ትምህርት ቤት ተደራጅተው በየሰበካ ጉባኤው አመራር ሰጭነት እንዲማሩ ምልአተ ጉባኤው አመራርን ሰጥቷል፡፡
11. በምሥራቅ ሸዋ ሀገረ ስብከት የሚገኘው የዝዋይ ሐመረ ብርሃን ቅዱስ ገብርኤል ገዳም የካህናት ማሠልጠኛ ተቋም ወደ ኮሌጅ ደረጃ ማደግ ያስችለው ዘንድ ከክፍሉ ሊቀ ጳጳስ የቀረበውን ፕሮፖዛል ጉባኤው ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
12. በኢትየጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም መንፈሳዊ ማሠልጠኛ አቋቁመው ለሚንቀሳቀሱ የተለያዩ ማኅበራት የሚያገለግል እስካሁን ድረስ የተዘጋጀ የማኅበራት ማደራጃ ደንብ የሌለ በመሆኑ ለወደፊቱ ሕገ ቤተ ክርስቲያኑንና ቃለ ዓዋዲውን መሠረት ያደረገ የማኅበራት ማደራጃ ደንብ በሕግ ባለሙያዎች እንዲዘጋጅ ጉባኤው ተስማምቶ ወስኗል፡፡
13. በጋሻው ደሳለኝ የተባለ ግለሰብ በቤተ ክርስቲያኒቱ ውስጥ ለበርካታ ዓመታት ለምእመናን ሲያስተላልፍ የነበረው የክህደት ትምህርት በመረጃ ተሰብስቦ ችግሩ ለቅዱስ ኖዶስ ከቀረበ በኀላ ከ15/02/2010 ዓ.ም. ጀምሮ የክሕደት ትምህርቱን በማውገዝ ከቤተ ክርስቲያናችን እንዲለይ ተደርጓል፣ በቤተ ክርስቲያችንም ስም እንዳያስተምር ተወግዟል፡፡
14. በተመሳሳይ መልኩም በአሜሪካን ሀገር በዋሺንግተን ዲ.ሲ. የሚያገለግሉት አባ መዓዛ ክርስቶስ በየነ እያስተማሩ ያለው የክሕደት ትምህርት ለቅዱስ ሲኖዶስ በመረጃ ቀርቦ የተረጋገጠባቸው ስለሆነ ሥልጣነ ክህነታቸው ተይዟል፤ ያሉበትን ቤተ ክርስቲያን ጨምሮ በማናቸውም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አገልግሎት እንዳይሰጡ ታግደዋል፡፡
15. ወልደ አብ በሚል ርእስ፤ ገብረ መድኅን በተባለ ግለሰብ የተጻፈው የክህደትና የኑፋቄ ትምህርት የቅብዐትንና የጸጋን የክሕደት ትምህርት የሚያስፋፋ በመሆኑ ካህናትን ከካህናት ምእመናንን ከምእመናን የሚያጋጭ ከመሆኑ ጋር፤ ከቤተ ክርስቲያንም አልፎ በሀገራችን ሁከት ለማስነሣት ታስቦ የተዘጋጀ ሆኖ ስለተገኘ፣ መጽሐፉ ከማናቸውም አገልግሎት እንዲለይ ተወግዟል፡፡
16. ለገዳማት መተዳደሪያ እንዲሆን የተዘጋጀው ደንብ ረቂቁ ተስተካክሎ የቀረበ በመሆኑ በሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
17. ተሐድሶ እየተባለ የሚጠራው የኑፋቄ እምነት ማኀበር ራሱን ኦርቶዶክሳዊ በማስመሰል የቤተ ክርስቲያኒቱን ህልውና እየተፈታተነ ከማስቸገሩ የተነሣ ቅዱስ ሲኖዶስ ቀደም ሲል ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ በየአህጉረ ስብከቱ ተቋቁሞ የመከላከልና ቤተ ክርስቲያኒቱን የመጠበቅ ሥራ እንዲያከናውን ውሳኔን መስጠቱ የሚታወስ ነው፡፡

አሁንም ከቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር እስከ አህጉረ ስብከት ባለው መዋቅር የተቋቋመው ፀረ ተሐድሶ ኮሚቴ ተጠናክሮ የመከላከሉን ሥራ እንዲቀጥል ቅዱስ ሲኖዶስ አመራር ሰጥቷል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ከዚህ በላይ በተገለጹትና በሌሎችም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ አስፈላጊውን መመሪያ ከሰጠ በኋላ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቆአል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ለሕዝባችን ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!