ከጥቅምት 11 ቀን እስከ 25 ቀን 2015 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉባኤው የመክፈቻውን ሥርዓተ ጸሎት ከፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2015ዓ.ም. ጀምሮ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሂድ ሰንብቷል፡፡ ምልአተ ጉባኤው ለቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊ እድገት ለሀገራችን ማኅበራዊና ልማታዊ ክንውን እንዲሁም ለመላው ሕዝባችን ሰላምና አንድነት ጠቃሚ የሆኑ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡

በዚሁ መሠረት፡-

  1. የዚሁ የጥቅምት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መከፈቱን በማስመልከት የተደመጠው የመክፈቻ ንግግር
  • የሕዝባችንና የቤተ ክርስቲያናችን ሰላም ተጠብቆ እንዲኖር ማድረግ እንዲቻል፣
  • በሀገራችን በሰሜኑ ክልል በተከሠተው ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው ስለተፈናቀሉና በአጠቃላይ በችግር ላይ ስለሚገኙ ወገኖቻችን መደረግ ስለሚገባው እገዛ፣
  • በቀጣይም የቤተ ክርስቲያናችንን ሁለንተናዊ እድገት ማስቀጠል በሚቻልበት ሁኔታ ላይ ያተኰረ በመሆኑ ምልአተ ጉባኤው በዚሁ ላይ በስፋት ተነጋግሮ ለተግባራዊነቱ የሚመለከታቸው ሁሉ የበኩላቸውን እንዲወጡ አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
  1. የ2015ዓ.ም. የመንበረ ፓትርያርክ ዓለም ዐቀፍ አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ ያሳለፈውን የጋራ መግለጫ በመመርመርና አስፈላጊ ማሻሻያዎችን በማድረግ የበጀት ዓመቱ የሥራ መመሪያ እንዲሆን ጉባኤው አጽድቋል፡፡
  2. የ2015ዓ.ም. የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ የዓመቱን በጀት ድልድል አስመልክቶ ጉባኤው በስፋት ከተነጋገረ በኋላ የቀረበውን በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡
  3. ከ2007ዓ.ም. ጀምሮ በሥራ ላይ የነበረውን ሕገ ቤተክርስቲያን ወቅቱን በዋጀ መልኩ በማስጠናት መልካም አስተዳደርን ሊያሰፍን በሚችል ሁኔታ ተሻሽሎ በቀረበው ረቂቅ ላይ በመነጋገር ማሻሻያዎችን በማድረግ ረቂቅ ደንቡን አጽድቋል፡፡ በሁሉም የቤተ ክርስቲያኒቱ መዋቅር በሥራ ላይ እንዲውል ወስኗል፡፡ የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ካህናትና ምእመናን የሚያጋጥሟቸው ችግሮች ቀኖና ቤተክርስቲያንን በጠበቀ መልኩ በመንፈሳዊ ዳኝነት መታየትና ፍትሕ ማግኘት እንዲችሉ ለማስቻል በባለሙያ ተዘጋጅቶ የቀረበው የመንፈሳዊ ፍ/ቤት ማቋቋሚያ ረቂቅ አዋጅ በምልአተ ጉባኤ ጸድቋል፡፡ ከዚሁ ጋር ለቤተ ክርስቲያኒቱ ማኅበራዊና መንፈሳዊ የሥራ ሂደት ጠቃሚ የሆኑ ልዩ ልዩ ረቂቅ ደንቦችን መርምሮ በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውሉ ወስኗል፡፡
  4. በቤተ ክርስቲያናችን ሕፃናትና አስተዳደግ ድርጅት አገልግሎት የሚገኘው ምግባረ ሠናይ ሆስፒታል በሙሉ ዐቅሙ አገልግሎት እንዲሰጥ ለማስቻል የማሻሻያ ሥራ እንዲሠራ በተጨማሪም በቤተ ክርስቲያናችን በምሥራቅ አፍሪካ ውስጥ የመጀመሪያ የሆነ ታላቅ ሆስፒታል እንዲገነባ የቀረበውን ጥናት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አጽድቋል፡፡
  5. በሀገራዊ ሰላምና አንድነት ላይ የተነጋገረው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሰላም ለሀገራችን ሕዝቦች አንድነትና ለቀጣይ በልማታዊ እድገት የበለጸገች ኢትዮጵያን ለማየት መሠረት መሆኑን ሁሉም ተገንዝቦ ሀገራዊ ዕርቀ ሰላም እንዲወርድ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን አቅርቧል፡፡

ከዚሁም ጋር ሀገራዊ ሉዓላዊነትን በሚዳፈር መልኩ እየታየ ያለውን የውጭ መንግሥታት ጣልቃ ገብነት እንዲቆም ጉባኤው አሳስቧል፡፡

  1. በሰሜኑ ሀገራችንም ሆነ በውጭው ዓለም አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናት የቤተ ክርስቲያናችን ማእከላዊ አሠራር ላይ እያሳዩት ያለው አካሄድ ለቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ ለሀገራዊ አንድነታችን መጠበቅ ሲባል እንደገና በሰከነ መንፈስ ታይቶ ወደነባሩ ማእከላዊ አስተዳደርና አሠራር እንዲመለሱ ጉባኤው ጥሪውን ያቀርባል፡፡
  2. በቤተ ክርስቲያናችን ስብከተ ወንጌል እንዲስፋፋ መልካም አስተዳደር በሁሉም አቅጣጫ እንዲሰፍን ሀገራዊ አንድነትና ሰላም ተጠናክሮ እንዲቀጥል አህጉረ ስብከት ከምንግዜውም በላይ ተጠናክረው እንዲሠሩ ለማስቻል ምልአተ ጉባኤው በሰፊው መክሮ ውሳኔ አሳልፏል፡፡
  3. የቤተ ክርስቲያኒቱ አእምሮኣዊ ሀብት ንብረትና የቱሪዝም ቅርሶቻችንን አስመልክቶ በቀረበው የባለሙያ ጥናት ላይ የተነጋገረው ምልአተ ጉባኤ ጥናቱን በማጽደቅ በተግባር እንዲተረጐም ወስኗል፡፡
  4. ሀገራችንን በልማት አሳድጎ ሕዝባችንን ከረኃብና ከድህነት ለማላቀቅ በማሰብ ግንባታው ከዓመታት በፊት ተጀምሮ በአሁኑ ጊዜ ግንባታውን ለማጠናቀቅ ሕዝባችን እየተረባረበ ያለበት የዐባይ ግድብ የመጨረሻው ምዕራፍ ላይ እስከሚደርስ በቤተ ክርስቲያናችንም ሆነ በሁሉም ዘንድ አስፈላጊው ድጋፍና ትብብር እንዲቀጥል ምልአተ ጉባኤው ጥሪ አቅርቧል፡፡
  5. እስከ አሁን ድረስ በቤተ ክርስቲያናችን የሚገኙ መንፈሳዊ ኮሌጆች ቊጥር ዝቅተኛ መሆኑን በመገንዘብና ለትምህርት አስፈላጊው ትኩረት እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ባስቀመጠው አቅጣጫ ተጨማሪ ከሦስት ያላነሱ መንፈሳዊ ኮሌጆች መጨመራቸው ሥራም መጀመራቸውን ጉባኤው ተመልክቶ ኮሌጆቹ በቀጣይም በዕቅድና የቤተ ክርስቲያኒቱን አስተምህሮ በጠበቀ መልኩ ተጠናክረው እንዲቀጥሉ አስገንዝቧል፡፡
  6. ልማት ለቤተ ክርስቲያናችን ብሎም ለሀገራችን እድገት ለሕዝባችን የኑሮ መሻሻል በእጅጉ አስተዋፅኦው የጐላ መሆኑን በመገንዘብ በቁልቢ ቅዱስ ገብርኤል ገዳም ዓመታዊ በዓላትን ለማክበር ለሚገኙ ምእመናን አገልግሎት ለመስጠት የሚያስችል መሠረታዊ ልማት ለመተግበር እንዲቻል ጉባኤው ተነጋግሮ ለተግባራዊነቱ የወደፊት አቅጣጫ አስቀምጧል፡፡
  7. ከቅርብ ዓመታት ወዲህ በሰሜኑ የሀገራችን ክፍል ተከሥ በነበረው ጦርነት ሀገራችንና ሕዝባችን ከፍተኛ ጉዳት እንደደረሰባቸው ቤተ ክርስቲያናችንም የዚህ ችግር ገፈት ቀማሽ ሆና ካህናቶቿና ምእመናን ተከታዮቿ ለሞትና ለስደት መዳረጋቸው አብያተ ክርስቲያናት መፍረሳቸውና መቃጠላቸው የሚታወቅ ነው፡፡ ሆኖም በአሁኑ ጊዜ ይኸው ጦርነት እንዲያበቃ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት እንዲጠበቅ ትኵረት ባደረገ መልኩ በደቡብ አፍሪካ የተደረሰውን ስምምነት ቤተ ክርስቲያናችን በእጅጉ የምትደግፈውና በተደረሰው ስምምነት መሠረት ሰላሙ ፍጻሜ እንዲያገኝ የበኩሏን አስተዋፅኦ የምታበረክት ሲሆን ሁሉም አካል ለሰላሙ መገኘት በትኵረት እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ በኦጽንዖት ያስገነዝባል፡፡ ይህ በቅዱስ ሲኖዶሱ ሁልጊዜም በጒጉት ሲጠበቅ፣ ጸሎት ሲጸለይበትና የሰላም ጥረት ሲደረግበት የቆየ በመሆኑ አሁንም በየአቅጣጫው ሀገራዊ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
  8. በየአህጉረ ስብከቱ ያለውን መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎት ክንውን የገመገመው ምልአተ ጉባኤ ለአብያተ ክርስቲያናት መልካም አስተዳደር እድገትና ለሰላም መስፈን ትኵረት በመስጠት በአንዳንድ አህጉረ ስብከት የብፁዓን አባቶች ዝውውርና ምደባ አድርጓል፡፡
  9. በመካከለኛው ምሥራቅ የሚገኙት የሶሪያ አንጾኪያ ሐዋርያዊት ቤተ ክርስቲያን የግብጽ አሌክሳንድርያ ኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያንና የአርመን ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን የቂልቅያ ሊባኖስ መንበር የሆኑት እነዚህ ሦስቱ አብያተ ክርስቲያናት በግብጽ ሀገር ከጥቅምት 8-10 በአውሮፓውያን አቈጣጠር ከኦክቶበር 18 እስከ 20 ድረስ ባካሄዱት የመሪዎች ጉባኤ በሰጡት መግለጫ በቅድሰት ሀገር ኢየሩሳሌም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ገዳም ይዞታችን አስመልክቶ የሰጡት አሳዛኝ መግለጫ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በትኵረት ተመልክቶታል፡፡

እነዚሁ አብያተ ክርስቲያናት በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም የቤተ ክርስቲያናችን በሆነ የይዞታ ላይ የሰጡት የተሳሳተ መግለጫ የቤተ ክርስቲያናችንና የሀገራችንን ኢትዮጵያ ክብር የሚነካ ስለሆነ ጉባኤው በእጅጉ ተቃውሞታል፡፡ አብያተ ክርስቲያናቱም የሰጡትን መግለጫ መልሰው እንዲያጤኑትና የማረሚያ መግለጫ እንዲሰጡ የኢፌዲሪ መንግሥትም በጉዳዩ ጥብቅ ክትትል እንዲያደርግበት ጉባኤው ጥሪውን አቅርቧል፡፡

  1. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከጥቅምት 21-27/2015 ዓ.ም. ድረስ ለሰባት ዕለታት ለምሥጢራተ ቤተ ክርስቲያን ማስፈጸሚያ ባዘጋጀው የአንድ ሱባዔ የጸሎት ሳምንት፡-
    • ለሀገራችንና ብሎም ለዓለማችን ፍጹም ሰላም፣
    • ለሕዝቦች አንድነትና ሰላማዊ ኑሮ መገኘት፣
    • በጦርነት ምክንያት ከቄያቸው ለተፈናቀሉና
    • በልዩ ልዩ ወረርሽኝ በሽታ ለተያዙ ምሕረትና ጤና እንዲያገኙ፣

እንዲሁም በጦርነትና በማንኛውም አጋጣሚ ውድ ሕይወታቸውን ያጡ ወገኖቻችን ዕረፍተ ነፍስን እንዲሰጣቸው ሁሉን ቻይ ወደሆነው እግዚአብሔር በሱባዔ የሰነበተ ሲሆን በቀጣይም ለሀገራችንና ለሕዝባችን ፍጹም ሰላም መገኘት መላው ካህናትና ምእመናን በጸሎት እንዲተጉ ጉባኤው አሳስቧል፡፡

በመጨረሻም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በስብሰባ በሰነበተባቸው ዕለታት በቤተ ክርስቲያናችን የአጭርና የረጅም ጊዜ ዕቅድ ላይ በስፋት በመነጋገር መንፈሳዊ አገልግሎቱ ተጠናክሮ እንዲቀጥል ልማታዊው ተግባር ትኵረት ተሰጥቶት እንዲከናወን ለኅብረተሰቡ ሊደረግ የሚገባው ማኅበራዊ ጉዳዮች አስፈላጊው ክትትል እንዳይለያቸው በተለይም በሀገራዊ ሰላምና አንድነት ላይ በሁሉም አካባቢዎች የተጠናከረ ሥራ እንዲሠራ በማስገንዘብ ከጥቅምት 11 ቀን 2015 እስከ ጥቅምት 25 ድረስ ሲያካሂድ የቆየውን ጉባኤ በዛሬው ዕለት በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ፤

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡