ከጥቅምት 11 ቀን እስከ 24 ቀን 2012 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 ድንጋጌ መሠረት ከጥቅምት 12 እስከ ጥቅምት 24 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ የተካሄደውን የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አስመልከቶ የተሰጠ መግለጫ፤
1. ለቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የመክፈቻ ንግግር ሆኖ ለምልአተ ጉባኤው የቀረበው መልእክት በቀጣይ በቤተ ክርስቲያናችን ለሚከናወነው መንፈሳዊውም ሆነ ማህበራዊ ተልእኮ ጠቃሚነቱ የጐላ በመሆኑ ጉባኤው የሥራ መመሪያ አድርጎ ተቀብሎታል፡፡
2. የሀገር ሰላምን ጉዳይ አስመልክቶ በአሁኑ ጊዜ በአገራችን ኢትዮጵያ እየታየ ያለው የሰው ሕይወት መጥፋትና የዜጎች ንብረት መውደም፣ ቅዱስ ሲኖዶሱን በእጅጉ ያሳዘነ ሲሆን፣ መንግሥት ለጉዳዩ ትኵረት ሰጥቶ ሰላምን እንዲያስከብር፣ የዜጎች ደህንነት እንዲጠበቅ እንዲያደርግ፣ የተፈናቀሉትም ወደቀያቸው እንዲመለሱና ለጠፋው ንብረታቸው ማቋቋሚያ እንዲደረግላቸው፣ በተለይም በክርስቲያኖችና በአብያተ ክርስቲያናት ላይ እየደረሰ ያለው ስደትና መከራ ጐልቶ እየታየ በመሆኑ የጥፋቱ መልእክተኞችን መንግሥት በሕግ እንዲጠየቁ እንዲያደርግ ቅዱስ ሲኖዶስ እያሳሰበ መንግሥትም ለሕዝቡ ብርቱ የበኩሉን ጥበቃ እንዲያደርግ፣
3. በቤተ ክርስቲያናችን የሚከናወነውን መንፈሳዊም ይሁን ማኅበራዊ ተግባራት በአግባቡ ማስተላለፍ እንዲቻል የቤተ ክርስቲያኒቱ የሕዝብ ግንኙነት በመምሪያ ደረጃ እንዲቋቋም፣
4. በአገራችን በተለያዩ ክልሎች የተለያዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች በብዛት እንደሚገኙ ይታወቃል፡፡ በመሆኑም የቤተ ክርስቲያኒቱን ተከታዮች በቋንቋቸው ማስተማርና ማገልገል እንዲቻል በየአህጉረ ስብከቶቹ የሚገኙ የአብነት ት/ቤቶችን ማጠናከር ከልዩ ልዩ ቋንቋ ተናጋሪዎች አገልጋዮችን ማፍራት እንዲቻል ለት/ቤቶቹ ማጠናከሪያ የሚሆን ቋሚ በጀት እንዲመደብ፣ በቀጣይም በሁሉም አፍ መፍቻ ቋንቋ በማእከል ማሠልጠኛ እንዲቋቋም፤
5. የአገራችን ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በሀገራችንና በአፍሪካ ጭምር ያበረከቱት የሰላም ተልእኮ አስመልክቶ ዓለም ዐቀፍ የኖቤል ተሸላሚ መሆናቸው፣ በተለይም ለአገራችን ኢትዮጵያ ከፍተኛ ዕውቅና ያስገኘላት ቀድሞም የነበረ ክብሯን አጒልቶ ያሳየ በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ አድናቆቱን ገልጿል፡፡ ለወደፊቱም ለአገራችን እድገትና ብልጽግና በመንግሥት በኩል ለሚሠራው ማኅበራዊና ልማታዊ ሥራ ቤተ ክርስቲያናችን አስፈላጊውን ድጋፍ በማድረግ ትቀጥላለች፡፡
6. አገራችን ኢትዮጵያ በጀመረችው የልማት አቅጣጫ በስፋት ለማስቀጠልና በተለይም ዜጎችን ከድህነት ለማላቀቅ በእጅጉ ተስፋ የተጣለበት የዐባይ ግድብ በተያዘው የግንባታ ሥራ ተፋጥኖ ግድቡ እንዲጠናቀቅና ሥራ እንዲጀምር ለማስቻል መላው የአገራችን ሕዝቦች አስፈላጊውን እገዛ በማድረግ እንዲቀጥሉ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፡፡
7. የቤተ ክርስቲያናችንን አጠቃላይ መሪ ዕቅድ በተመለከተ ቀደም ሲል በቅዱስ ሲኖዶስ በተወሰነው መሠረት በጠቅላይ ቤተ ክህነቱ በኩል ወደተግባር እየተገባ መሆኑን ጉባኤው ከቀረበው ሪፖርት አዳምጧል፡፡ በቀጣይም ሥራው ተፋጥኖ እንዲቀጥልና ከካህናት ከምእመናን ከወጣቱም ጭምር የሚቀርቡ ወቅታዊ አቤቱታዎች በመሪ ዕቅዱ እየተጠኑ አፋጣኝ ምላሽ እንዲሰጥ ተወስኗል፡፡
8. በግንቦቱ ርክበ ካህናት በቤተ ክርስቲያናችን የተቋቋመው አገራዊ የሰላምና የዕርቅ ኮሚቴ የ4 ወራት ሪፖርት ለጉባኤው አቅርቧል፡፡ ኮሚቴውም ያከናወነው የሰላም ተልእኮ ጉባኤው በአድናቆት ተቀብሎ በቀጣይም ኮሚቴው ከሀገር ሽማግሌዎች፣ ከምሁራንና ከወጣቶች የተውጣጡ አባላትን አካቶ የሰላምና የዕርቅ ሥራውን አጠናክሮ እንዲቀጥል በማሳሰብ፣ ለዚህም የሚሆን አስፈላጊ በጀት መድቧል፡፡
9. በአገራችን በኢትዮጵያ በኦሮምያ ክልል በሚገኙ ወገኖቻችን ላይ በደረሰው የሰው ሕይወት መጥፋትና ስደት ላይ በመነጋገር በጣም ለተቸገሩ ወገኖች በጊዜያዊነት የሚደርስ ምግብና አልባሳት ለማቅረብ እንዲቻል አስፈላጊውን ገንዘብ እንዲመደብ፣ በቀጣይም በክልሉ ይህንን ችግር እየተከታተለ ዘለቄታዊ ርዳታ የሚያሰባስብ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተወስኗል፡፡
10. የጌዴኦና ቡርጂ ዞኖች እስከ አሁን ድረስ በሲዳማ ሀገረ ስብከት ሥር ሆነው መንፈሳዊውን አገልግሎት ሲያገኙና ሲተዳደሩ የቆየ ቢሆንም በአሁኑ ጊዜ ራሱን ችሎ ሀገረ ስብከት እንዲሆንላቸው የአካባቢው ነዋሪዎች ባቀረቡት ጥያቄ መሠረት ራሱን የቻለ ሀገረ ስብከት እንዲሆን ተወስኗል፡፡
11. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን እና በሩሲያ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን ሞስኮ መንበረ ፓትርያርክ መካከል ሊኖር ስለሚገባው ግንኙነት በተመለከተ ከቤተ ክርስቲያናችን የውጭ ግኑኝነት መምሪያ በቀረበ ሪፖርት ላይ ጉባኤው ተነጋግሮ በሁለቱ አብያተ ክርስቲያናት የነበረው ጥንታዊ ግንኙነት ወደፊትም ተጠናክሮ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
12. በስዊድን ሀገር ሶደርቴሌ ከተማን ማእከል ያደረገ የቅዱስ አግናጥዮስ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ሴሚናሪ በመላው አውሮፓ ለሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ምእመናን እና አገልጋይ ካህናት ስለ ቅድስት ቤተ ክርስቲያናችን ጥንታዊ የአብነት ትምህርትና ዘመናዊ የኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ነገረ መለኮት ሥልጠና የሚሰጥ ከፍተኛ የትምህርት ማእከል በመሆኑ በቤተ ክርስቲያናችን ስም ዕውቅና እንዲያኝ ተወስኗል፡፡ አገልግሎቱን በስፋትና በብቃት እንዲያከናውን በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም የዕውቅና ደብዳቤ እንዲደርሰውም የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ወስኗል፡፡
13. የ2012 ዓ.ም በጀት ዓመት የመንበረ ፓትርያርክ አጠቃላይ በጀት አስመልክቶ ከበጀትና ሂሣብ መምሪያ በቀረበው ዕቅድ ላይ በመነጋገር የቀረበው በጀት ላይ ማሻሻያ በማድረግ የ2012 ዓ.ም. በጀት በማጽደቅ በሥራ ላይ እንዲውል ተወስኗል፡፡
14. በአሁኑ ጊዜ በአገራችን በተለያዩ አካባቢዎች እየታየ ያለው ችግር እንዲያበቃ እግዚአብሔር አምላክ ምሕረቱን እንዲሰጠን የተጀመረው ሱባኤ እንዲቀጥል ተወስኗል፡፡
ጥንታዊትና ኦርቶዶክሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን ከጥንት ጀምሮ የአገር ባለውለታ እንደመሆኗ ሁሉ ወደፊትም በአገራችን ኢትዮጵያ በመንግሥትና በሕዝቡ ትብብር ለአገር አንድነትና ለዜጎች መብት መከበር፣ ለሰው ልጆች እኩልነት ለሚደረገው አገራዊ ጥረት የበኩሏን አስተዋፅኦ ከማድረግ አትቈጠብም፡፡ ሆኖም ለዚሁ አገራዊ ስኬት ከሁሉም በላይ በዜጎች መካከል መከባበርና ሰላማዊ አንድነት መኖር ቅድሚያ ሊሰጠው የሚገባ መሆኑን ቅዱስ ሲኖዶስ ያምናል፡፡ ስለዚህ ኢትዮጵያውያን ልጆቻችን ሁሉ በአሁኑ ጊዜ ለአገራዊ አንድነታችን ሰላም ቅድሚያ የሚሰጠው መሆኑን አምናችሁ በአንድነት በሰላምና ተከባብሮ በጋራ ለመኖር፣ ለመሥራትም ሆነ ሠርቶ ለመበልጸግ አገራዊ አንድነታችሁን እንድታጠናክሩ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያቀርባል፡፡
የአገራችን መንግሥትም የአገር ሰላም፣ የዜጎች ደኅንነትና በሰላም ወጥቶ መግባት ቅድሚያ የሚሰጠው ተግባር መሆኑን፣ ክቡር የሆነው የሰው ልጅ ሕይወት በምንም መልኩ በከንቱ መጥፋት የሌለበት መሆኑን ተገንዝቦ፣ ሰላምን የማስከበሩን፣ አገር የመጠበቁንና ዜጎችን በአገራቸው በእኩልነት ተሳስበው የሚኖሩበትን መንገድ በመቀየስ መንግሥታዊ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም ከጥቅምት 11 እስከ 24 ቀን ለ13 ቀናት በቤተ ክርስቲያናችን መንፈሳዊና ማኅበራዊ እንዲሁም አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሲነጋገር የቆየው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በሰላም ተጠናቅቆ በዛሬው ቀን በጸሎት ተዘግቷል፡፡ እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን!