ከጥቅምት 11 ቀን እስከ 18 ቀን 2014 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ከኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ የተሰጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉባኤው የመክፈቻው ሥርዐተ ጸሎት ከፈጸመበት ከጥቅምት 11 ቀን 2014 ዓ.ም. ጀምሮ የተለመደውን ዓመታዊ መደበኛ ስብሰባ ሲያካሄድ ሰንብቶ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚበጁ ማኅበራዊና መንፈሳዊ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡
በዚሁ መሠረት፡-
1. የ2014 ዓ.ም. የጥቅምቱ ቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ መክፈቻ መልእክት አሁን በሀገራችን እየታየ ባለው ጦርነት እና የእርስ በርስ ግጭት ላይ ያተከረ ሲሆን፡-

• ጦርነቱ በወንድማማቾች መካከል እየተደረገ ያለና ኀዘኑን የከፋ ያደረገው መሆኑ፣
• በዚሁ ጦርነትና ግጭት በርካታ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ለሞት ለስደትና ለረኃብ መዳረጋቸው፣
• በዚህም ምክንያት በሀገሪቱ እየታየ ያለው የኑሮ ውድነት ሀገራዊ ልማት ላይ እያደረሰ ያለው ተጽዕኖ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ይህ ጦርነትና ግጭት ተወግዶ በሀገሪቱ ሰላምና አንድነት እንዲሰፍን ከሁሉም በላይ ወደ እግዚአብሔር በመጸለይ ይቅርታ ምሕረት መጠየቅ አስፈላጊ በመሆኑ ጉባኤው ይህንኑ መልእክት ተቀብሎ በመላ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ተግባራዊ እንዲሆን ወስኗል፡፡

2. በሀገራችን በኢትዮጵያ አሁን ያለው የሰላም ዕጦትና ጦርነት ወደፊትም ሊያስከትል የሚችለው ችግር ከፍተኛ መሆኑ ስለታመነበት በተቻለ ዐቅም ዜጎች ሁሉ ለሀገራዊው አንድነትና ሰላም መገኘት ዘብ እንዲቆሙ የየበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

3. በዚሁ ሀገራዊ የሰላም ዕጦት እየተደረገ ያለውን ጦርነት ምክንያት አድርገው ከሀገር ውጭ የሚገኙ አንዳንድ አብያተ ክርስቲያናትና ካህናት ሀገራዊ ሰላም ላይ ጥላ በሚያጠላ ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነትን በሚያፈርስ መልኩ ቅስቀሳ ማድረጋቸው ከቤተ ክርስቲያንና የቤተ ክርስቲያን አገልጋዮች ነን ከሚሉ በፍጹም የማይጠበቅ ሆኖ አግኝቶታል፡፡ በመሆኑም በአውስትራልያ፣ በካናዳ፣ በአውሮፓና በአሜሪካ ሁነው በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ስም እየፈጸሙ ካለው ሀገራዊና ሕዝባዊ አንድነት ከሚያደፈርስ ተግባራቸው እንዲቈጠቡ ቅዱስ ሲኖዶስ እያሳሰበ አሁንም ወደ ሰላሙና አንድነቱ እንዲመለሱ ጥሪውን ያቀርባል፡፡ ይህንንም የሰላም ተልእኮ የሚያስፈጽም በውጭው ዓለም የሚገኙ ብፁዓን አባቶች የሚመሩት የጋራ የሰላም ልኡክ እንዲቋቋም ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

4. በሀገራችን በኢትዮጵያ በተከሠተው ጦርነት ምክንያት ከቀያቸው ለተፈናቀሉና በተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር ለደረሰባቸው ወገኖቻችን እርዳታ እንዲሆን ብር 50,000,000 (ኃምሳ ሚሊየን ብር) በቤተ ክርስቲያናችን ስም ችግሩ ለደረሰባቸው ወገኖች እንዲሰጥ ቅዱስ ሲኖዶስ ወስኗል፡፡

5. የሀገራችንን ቀጣይ የእድገት ደረጃ በእጅጉ ከፍ ያደርጋል የሕዝቦችን አኗኗር በመቀየር ከድህነት ያወጣል በሚል ታስቦበት ከዓመታት በፊት ግንባታው የተጀመረው የሕዳሴ ግድብ እየተጠናቀቀ ያለበት ምዕራፍ ላይ መድረሱና 2ኛ ሙሌት መከናወኑ ለሀገራችን ለኢትዮጵያ ትልቅ የድል ምዕራፍ በመሆኑ ቅዱስ ሲኖዶስ አድንቋል፡፡ በቀጣይም ለመጨረሻው የድል ምዕራፍ ለመድረስ መላው ኢትዮጵያውያን በጒልበት በገንዘባቸውም በሐሳብም ጭምር ድጋፋቸውን እንዲያደርጉ ቅዱስ ሲኖዶስ አሳስቧል፡፡

6. በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን የሚገኙ መንፈሳውያን ኮሌጆችን አሁን ቤተ ክርስቲያኒቱ ከደረሰችበት የእድገት ደረጃ ጋር ለማመጣጠንና ተጨማሪ ኮሌጆች በማስፈለጉ በደቡብ ክልል የሚገኙ ሁለት ካህናት ማሠልናዎች ወደ መንፈሳዊ ኮሌጅ እንዲያድጉ አስፈላጊውም በጀት እንዲመደብላቸው ጉባኤው ወስኗል፡፡

7. ለመንበረ ፓትርያርክና ለየአህጉረ ስብከት የሚያገለግል የ2014 ዓ.ም. ዓመታዊ በጀት ከመንበረ ፓትርያርክ ጠቅላይ ጽ/ቤት ተደልድሎ በቀረበው መሠረት ዝርዝሩን ተመልክቶ በጀቱ እንዲጸድቅ በማድረግ በሥራ ላይ እንዲውል ጉባኤው ወስኗል፡፡

8. የ4ዐኛው አጠቃላይ የሰበካ መንፈሳዊ ጉባኤ የጋራ መግለጫ ላይ የተነጋገረው ጉባኤ በመግለጫው ላይ በመወያየት አንዳንድ ማሻሻያዎችን በማድረግ እና በማጽደቅ የ2014 ዓ.ም. በጀት ዓመት የሥራ መመሪያ እንዲሆን ጉባኤው ወስኗል፡፡

9. በሀገራችን በኢትዮጵያ የተደረገው 6ኛ ሀገራዊ ምርጫ ነፃና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ መከናወኑና በተለይም ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር ሆነው በመመረጣቸው የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የተሰማውን ደስታ እየገለጸ፤ ቀጣዩ ሀገራዊ ሥራቸውም ለሀገርና ለወገን የሚጠቅም የተሳካ የአመራር ዘመን እንዲሆንላቸው በሥራቸውም እግዚአብሔር አብሮአቸው እንዲሆን ቤተ ክርስቲያን ትጸልያለች፡፡

በአጠቃላይ ቅዱስ ሲኖዶስ በጉባኤ በሰነበተባቸው ቀናት ስለ አብነት ት/ቤቶች እና ስብከተ ወንጌል መስፋፋት፣ ስለ ሰንበት ት/ቤቶች መጠናከር ስለ ሀገራዊ ሰላምና አንድነት ሰፊ ምክክርና ውይይት ያደረገ ከመሆኑም በላይ በሀገራችን በተከሠተው የሰላም ዕጦት የደረሰው ጦርነት ረኃብና የጤና ማጣት አብቅቶ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ ለሰባት ቀናት ጸሎት ያደረገ ሲሆን በቀጣይም መላው ካህናትና ምእመናን ስለ ሀገራችን ሰላምና አንድነት እንዲጸልዩ ቅዱስ ሲኖዶስ አጥብቆ አሳስቧል፡፡

በመጨረሻም ቅዱስ ሲኖዶስ ለ8 ቀናት ሲያከናውን የቆየውን የጥቅምቱ 2014 ዓ.ም. የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ስብሰባ ዛሬ ጥቅምት 18 ቀን 2014 ዓ.ም. በጸሎት ዘግቷል፡፡

እግዚአብሔር አምላክ ለሀገራችን ሰላሙን
ለመላው ሕዝባችን አንድነቱን ይስጥልን፤ አሜን፡፡