ከግንቦት 16 ቀን እስከ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ መደበኛ ስብሰባ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቊጥር 164 በተደነገገው መሠረት ምልአተ ጉኤው የዘንድሮውን መደበኛ የርክበ ካህናት ስብሰባ የጉባኤው መክፈቻ ሥርዐተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከግንቦት 16 ቀን 2008 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሰኔ 1 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ ለ16 ቀናት ያህል ባደረገው ጉባኤ ጠቀሜታ ባላቸው የአጀንዳ ነጥቦች ተወያይቶ ውሳኔዎችን አሳልፎአል፡፡ ከእነዚህም መካከል የሚከተሉት በዋናነት የሚጠቀሱ ናቸው፡፡
1. የ2008 ዓ.ም. የርክበ ካህናት ጉባኤን በተመለከተ ቅዱስ ፓትርያርኩ ያደረጉት የመክፈቻ ንግግር እንዳበቃ ጉባኤው ሥራውን ቀጥሏል፡፡
2. የቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ዓመታዊ ሪፖርት በጽሑፍ ቀርቦ ጉባኤው ካዳመጠ በኋላ በሪፖርቱ ላይ ውይይት በማድረግ ለወደፊቱ የሚወሰኑት ሁሉ የአፈጻጸም ችግር እንዳይደርስባቸው ክትትል ይደረግ ዘንድ ተወስኗል፤
3. እስከአሁን እየተሠራበት ያለው ቃለ ዐዋዲ የቤተ ክርስቲያናችን መተዳደሪያ ደንብ ወቅቱን ባገናዘበ መልኩ እንዲሻሻል በተሰጠው መመሪያ መሠረት የተዘጋጀው ረቂቅ ቀርቦ ምልአተ ጉባኤው ከተነጋገረበትና ከታየ በኋላ የረቂቁ ዝግጅት በቋሚ ሲኖዶስ ታይቶ እንዲታተም ተወስኗል፤
4. ስለቅዱስ ፓትርያርክ እንደራሴ አስፈላጊነት ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተነጋገረ በኋላ የእንደራሴ አስፈላጊነት በምን ዐይነት ሕግ ላይ ተመሥርቶ መመረጥ አለበት የሚለውን በማጥናት ለጥቅምቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ የሚያቀርብ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ያሉበት ሰባት አባላት እንዲመረጡ ተደርጓል፤
5. ተፈጥሮ ባስከተለው ድርቅ ምክንያት በየመጠለያው ለሚገኙ ወገኖች የዕለት ደራሽ ርዳታ፤ ለተፈናቀሉ ወገኖችም ለመልሶ ማቋቋሚያ አገልግሎት የሚውል የገንዘብና የቊሳቍስ ርዳታ ይደረግ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን ጥሪዋን ታስተላልፋለች፤ የድርሻዋንም አስተዋፅኦ አድርጋለች፤
6. በቅድስት ሀገር ኢየሩሳሌም ለኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ገዳማት የሚያገለግል ሕንጻ መገንባት ይቻል ዘንድ ቦታ እንዲሰጥ ከገዳሙ ማኅበረ መነኮሳት የቀረበውን ጥያቄ ምልአተ ጉባኤው የተቀበለው ስለሆነ፤ በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር በኩል ቦታ ተፈልጎ እንዲሰጥ ተወስኗል፤
7. ቅዱስ ሲኖዶስ በየአህጉረ ስብከቱ ክፍት በሆኑ መንበረ ጵጵስናዎች ብቁ የሆኑ ኤጲስ ቆጶሳትን መርጦ ለመሾም ባለው ዕቅድ መሠረት፤
• ፈተናውንና መሰናክሉን ሁሉ አልፈው ዕውቅና ያገኙትን
• በብሔር ዐቀፍና በዓለም ዐቀፍ ትምህርት የበሰሉትን፤
• የወቅቱንም ችግር ይፈታሉ ተብለው እምነት የተጣለባቸውንና የሚጣልባቸውን፤
• ለተልእኮ የሚፋጠኑትን መነኰሳት በመመርመር፣ በማጥናትና በማጣራት ውጤቱን እስከ ሰኔ 30 ቀን 2008 ዓ.ም. ድረስ የሚያቀርብ አስመራጭ ኮሚቴ እንዲቋቋም ተደርጓል፤
8. የብፁዓን አበው ሊቃነ ጳጳሳትን ምደባ በተመለከተ (ሀ) ብፁዕ አባ ያሬድ ሊቀ ጳጳስ የኢትዮጵያ ሱማሌ ሀገረ ስብከት ሥራን እንደያዙ በአርሲ ሀገረ ስብከት (ለ) ብፁዕ አባ እንጦንስ ሊቀ ጳጳስ በምዕራብ ሐረርጌ ሀገረ ስብከት (ሐ)ብፁዕ አባ ያዕቆብ ሊቀ ጳጳስ በደቡብና ምዕራብ አፍሪካ አህጉረ ስብከት፤ (መ) ብፁዕ አባ እንድርያስ ሊቀ ጳጳስ የሊቃውንት ጉባኤ የበላይ ኀላፊነቱን ሥራ እንደያዙ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል የበላይ ኀላፊ በመሆን ተመድበው እንዲሠሩ ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
9. በውጭ ላሉት አህጉረ ስብከት ጥናት ተደርጎ በቋሚነት የሚሠሩ አባቶች እስከሚመደቡ ድረስ፤
ሀ/ ሰሜን፣ ሰሜን ምሥራቅና ሰሜን ምዕራብ አውሮፓ አህጉረ ስብከት፤ ለጊዜው በብፁዕ አባ ሙሴ የደቡብ ምዕራብና የደቡብ ምሥራቅ አውሮፓ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
ለ/ አውስትራልያ ሀገረ ስብከት፤ በብፁዕ አባ ሄኖክ የምዕራብ ወለጋና የአሶሳ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
ሐ/ ምሥራቅ አፍሪካ ኬንያና ጅቡቲ አህጉረ ስብከት፤ በብፁዕ አባ ዳንኤል የድሬዳዋ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ፤
መ/ ምሥራቅ አፍሪካ ሰሜን ሱዳንና ግብጽ አህጉረ ስብከት፤ በብፁዕ አባ ሉቃስ በክልል ትግራይ ዞን ወልቃይት ጸገዴ ሰቲት ሑመራ ሀገረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ሆኖ በተጨማሪም የትንሣኤ ዘጉባኤ ማተሚያ ቤት የበላይ ኀላፊ ሆነው እንዲሠሩ፤
ሠ/ ደቡብ ሱዳን ሀገረ ስብከት፤ በብፁዕ አባ እስጢፋኖስ የጅማ፣ የኢሉባቦርና ጋምቤላ አህጉረ ስብከት ሊቀ ጳጳስ ተደርቦ እንዲሠራ ሲል ምልአተ ጉባኤው በአንድ ድምፅ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
10. በውጭ አህጉረ ስብከት ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ጋር ያለው የሰላሙ ንግግር ይቀጥል ዘንድ ሰላም ለማንኛውም መሠረት መሆኑ ታምኖበት ይህንኑ ሰላም ለማምጣት አስፈላጊው ጥረት ሁሉ እንዲደረግ፤
11. ስለ አዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ረዳት ሊቀ ጳጳስ ምደባ ጉዳይ ቅዱስ ሲኖዶስ ከተወያየ በኋላ በሕገ ቤተ ክርስቲያን አንቀጽ 50 መሠረት ብፁዕ አባ ሕዝቅኤል በያዙት የሀገረ ስብከት ሥራቸው ላይ ደርበው እስከ ጥቅምት 2009 ዓ.ም. ድረስ የፓትርያርክ ረዳት ሊቀ ጳጳስ ሆነው እንዲሠሩ ተስማምቷል፤
12. በየሦስት ዓመቱ የሚደረገው የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅና የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ምርጫ ካሉት ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት መካከል በማወዳደር፡- (ሀ) ብፁዕ አባ ዲዮስቆሮስ ሊቀ ጳጳስ የጠቅላይ ቤተ ክህነት ዋና ሥራ አስኪያጅ፣ (ለ) ብፁዕ አባ ሳዊሮስ ሊቀ ጳጳስ የቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ ሆነው ለሚቀጥሉት ሦስት ዓመታት እንዲሠሩ በቅዱስ ሲኖዶስ ተመርጠዋል፡፡
13. በሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ኀላፊነት በቤተ ክርስቲያናችን እየተረዱ የሚያድጉ ዕጓለ ማውታ ሕፃናት በየአህጉረ ስብከቱ መኖራቸው የሚታወቅ ነው፤ ይኸው የሕፃናትና የቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት ዕጓለ ማውታ ሕፃናትን በማሳደግና በማስተማር ረገድ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን ታላቅ አለኝታ ስለሆነ እስከ አሁን ከነበረው ይዘት በበለጠ ተጠናክሮ እንዲቀጥል በቅዱስ ሲኖዶስ ተወስኗል፤
14. የቤተ ክርስቲያናችን እምነትና ሥርዐተ አምልኮ እስካሁን ድረስ ተከብሮና ተጠብቆ እንደኖረ ሁሉ አሁንም ከመንበረ ፓትርያርክ እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ያለው የመንፈሳዊና የማኅበራዊ አገልግሎት መዋቅር በበለጠ ተጠናክሮ ይቀጥል ዘንድ መመሪያ ተሰጥቶአል፤
15. በቤተ ክርስቲያኒቱ ማእከላዊ አስተዳደር ቀልጣፋና ቅንነት የሰፈነበት አሠራር እንዲኖር፤ በየደረጃው የተዘረጉትም የልማት አውታሮች የበለጠ ውጤት እንዲኖራቸው ለማስቻል፤ ከመንበረ ፓትርያርክ ሥራ አስኪያጅ ጀምሮ ሁሎችም የየአህጉረ ስብከቱ ብፁዓን ሊቃነ ጳጳሳት ኀላፊነት ያለባቸው ስለሆነ ተከታትለው እየሠሩ እንዲያሠሩ ተወስኗል፤
16. በመከናወን ላይ ለሚገኘው የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ፕሮጀክት አጀማመር ሁሉም ኅብረተሰብ እጁን ሲዘረጋ እንደቆየ ሁሉ፤ አሁንም ለፕሮጀክቱ አፈጻጸም መላው ኅብረተሰብ የበኩሉን ድርሻ ይፈጽም ዘንድ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤
17. ከሀገራችን ኢትዮጵያ ውጭ ባሉት አንዳንድ አህጉር እየደረሰ ያለውን የተፈጥሮና ሰው ሠራሽ ችግር በጀሮአችን እንሰማለን፤ በዓይናችንም እናያለን፣ ለማስረጃም ያህል፤ በመሬት መንቀጥቀጥ፣ በጎርፍ ማጥለቅለቅና በሰደድ እሳት ዘግናኝ አደጋ የሚደርስ ኅልፈተ ሕይወት፤ በእርስ በርስ የውስጥ ጦርነት የደረሰውና እየደረሰ ያለው ዕልቂት፤ የእግዚአብሔርን ህልውና በሚፈታተኑ አንዳንድ ግለሰቦች ግንዛቤ ጒድለት እየደረሰ ያለው የጦርነት አደጋ፤ በየብስ በውቅያኖሶችና በሰማይ ላይ በሚበሩ አውሮፕላኖች የሚደርሰው ዘግናኝ ዕልቂትና የመሳሰሉት ከሚጠቁሰት መካከል ናቸው፤
ስለዚህ እግዚአብሔር አምላየካችን ጉዳት ለደረሰባቸው መጽናናትን መረጋጋትን እንዲሰጥልን ቅን ልቡና፣ ትሑት ሰብእና ለሚጎድልባቸው የኅብረተሰብ ክፍሎችም ትዕግሥቱን፣ ርኅራኄውን እንዲያበዛልን እንጸልያለን፡፡ ከሁሉም በላይ ለሀገራችንና ለሕዝቦቿ የሚፈለገውን ሰላምና አንድነት እንዲሁም የልማት ውጤት ማምጣት እንዲቻል ሁሉም ኅብረተሰብ ተግባብቶ፣ ተፋቅሮና ተከባብሮ በአንድነት መንፈስ መነሣሣት እንደሚያስፈልገው ቅዱስ ሲኖዶስ አበክሮ ያሳስባል፡፡
በመጨረሻም በሀገራችን ጎልቶ የሚታየው ድኅነት እንዲወገድ የተራበው፣ የተጠማው፣ የታረዘው፣ መሠረታዊ ፍላጎቱ ተሟልቶለት እንዲኖር፣ በሀገራችን ኢትዮጵያ በዓለሙም ሁሉ ሰላም እንዲሰፍን ቅዱስ ሲኖዶስ በመጸለይ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ፤ ይቀድስ፤ ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤አሜን!