ከሚያዝያ 24 ቀን እስከ 29 ቀን 2010 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜያት እንዲሆን በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ አምስት ንኡስ አንቀጽ 164 በተደነገገው መሠረት ቅዱስ ሲኖዶስ የዘንድሮውን የርክበ ካህናት ጉባኤ በማስመልከት የስብሰባው መክፈቻ ሥርዓተ ጸሎት ከተፈጸመበት ከበዓሉ ዋዜማ ከሚያዝያ 23 ቀን 2010 ዓ.ም. ጀምሮ እስከ ሚያዝያ 29 ቀን 2010 ዓ.ም. ለአንድ ሱባኤ ያህል ባደረገው ስብሰባ ለሀገራችንና ለቤተ ክርስቲያናችን የሚበጁ ጠቀሜታ ያላቸውን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡ ከውሳኔዎቹም መካከል ዋና ዋናዎቹ የሚከተሉት ናቸው፡፡
1. ለጉባኤው በቀረበው አጀንዳ ተራ ቊጥር 1 የተገለጸውን በተመለከተ፤ የጉባኤው መክፈቻ ንግግር፣ ትምህርትና መመሪያ የቤተ ክርስቲያኒቱንና የሀገሪቱን ሁለተናዊ ገጽታ የዳሰሰ፣ መንፈሳዊና ማኅበራዊ አገልግሎትን የሚገነባ ተልዕኮ ያለው በመሆኑ ምልአተ ጉባኤው በበሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል።
2. ከግንቦት ወር 2009 ዓ.ም. እስከ ሚያስዝያ 20 ቀን 2010 ዓ.ም. ድረስ በቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤና በቋሚ ሲኖዶስ የተላለፉ ውሳኔዎች በቅዱስ ሲኖዶስ ዋና ጸሓፊ አማካይነት ቀርበው ምልአተ ጉባኤው በአፈጻጸማቸው ዙሪያ ከተወያየ በኋላ አስፈላጊውን መመሪያ በመስጠት ተቀብሎ አጽድቆታል፡፡
3. በተለያየ ምክንያት የሥራ ዝውውር እንዲደረግላቸው ጥያቄ ያቀረቡ አንዳንድ ሊቃነ ጳጳሳትና ጳጳሳት የጥያቄያቸው አስፈላጊነት በቅዱስ ሲኖዶስ ከተጠና በኋላ ዝውውሩ ተፈጽሞላቸዋል፤
4. እናት አባታቸው ሙተውባቸው ሰብሳቢ ያጡ ሕፃናትን እያሳደገና እያስተማረ ለቁም ነገር ያበቃ ዘንድ ቀደም ሲል ቤተ ክርስቲያኒቱ ያቋቋመችው የሕፃናትና ቤተሰብ ጉዳይ ድርጅት፣ ከሀገር ውስጥና ከውጭ ሀገር ርዳታ ለጋሾች ጋር ያለውን የቅርብ ግንኙነት በበለጠ እያጠናከረ ሥራውን ይቀጥል ዘንድ ምልአተ ጉባኤው መመሪያን ሰጥቷል፤
5. የኢትዮጵያ ፌደራላዊ ዲሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ ጠቅላይ ሚኒስትር ክቡር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከተሠየሙበት ጊዜ ጀምሮ እያደረጉት ያለው ታሪካዊ ንግግር፣ ሀገራዊ አንድነትን፣ ፍቅርና ትሕትናን የሚያስተምር፣ ሰላምንና መረጋጋትን የሚያበሥር፣ የሩቁንና የቅርቡን የሚያስተባብር መንግሥታዊ ኀላፊነት የተሞላበት መልእክት በመሆኑ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በአክብሮት ተቀብሎታል፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በየክልሉ እየተዘዋወሩ በወንድማማች ሕዝቦች መካከል የተፈጠረው መቃቃር ይቅርታ ባልተለየው መንፈስ ተወግዶ ሰላምና መረጋጋት እንዲሰፍን መመሪያ ከመስጠት ጋር እያደረጉት ያለውን ከፍተኛ ጥረት ቅዱስ ሲኖዶስ በሙሉ ልብ ደግፎታል፤ የጥረቱም አካል በመሆን የበኩሉን ድርሻ እንደሚያበረክት ምልአተ ጉባኤው ተስማምቷል፡፡
6. ሀገራችን ኢትዮጵያን ለመጎብኘት የመጡት ክቡር የእስራኤል ሀገር ፕሬዚዳንት ሪቨን ሪቢሊን የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ስብሰባ በሚጀመርበት ሚያዝያ 24 ቀን 2010 ዓ.ም. በፓትርያርኬቱ ተገኝተው ለመጀመሪያ ጊዜ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንን ጎብኝተዋል፡፡ በዚህ ጊዜም ስለ ዴር ሡልጣን ገዳማችን ሁኔታ ለ30 ደቂቃ ያህል የጋራ ውይይት ካደረግን በኋላ በኢየሩሳሌም ያሉት ገዳማት በሙሉ እንደሚታደሱ፣ በተለይም አሁን በቅርቡ የመፍረስ አደጋ የደረሰበት የቅዱስ ሚካኤል ቤተ ክርስቲያን በቅርቡ እንደሚታደስ የቃል ተስፋ በመስጠት አረጋግጠውልናል፡፡
7. እግዚአብሔርን መፍራት የመጀመሪያው ጥበብ እንደሆነ እየተገነዘበ የመጣው ወጣቱ ትውልድ፤ ሀገሩንና ሃይማኖቱን፣ ባህሉንና ቋንቋውን፣ ሥርዓቱንና ትውፊቱን ከመጠበቅ ጋር ሥራ የመፍጠር ክሂሎቱን በበለጠ አጎልብቶ ሀገሩን እንዲያለማ ቅዱስ ሲኖዶስ አደራውን ጥሎበታል፡፡
8. የታላቁ ሕዳሴ ግድብ መሠረት ከተጣለበት ጊዜ ጀምሮ ቤተ ክርስቲያናችን የግንባታው ሥራ ማከናወኛ የሚሆን ገንዘብ እንዲያዋጣ ሕዝቡን ከማስተባበር ደረጃ ጀምሮ አስፈላጊውን የገንዘብ ድጋፍ ሁሉ ከመለገስ ወደኋላ ያለችበት ጊዜ እንደሌለ ቢታወቅም፣ የማጠናቀቂያው የደወል ድምፅ እስካልተሰማ ድረስ የማስተባበሩ ሥራም ሆነ የእርዳታ ገንዘብ አሰባሰቡ ተግባር እንዲቀጥል ማድረግ ሀገራዊ ግዴታ መሆኑን ትገነዘባለች፡፡

ከዚህ አንጻር የግድቡን ሥራ ለማጠናቀቅ ሁሉም ኅብረተሰብ የጋራ ኀላፊነት ያለበት መሆኑን በመገንዘብና በውል በመረዳት የርዳታ እጁን እንዲዘረጋ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥሪውን ያስተላልፋል፡፡ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ከዚህ በላይ በተገለጹትና በሌሎችም መንፈሳዊና ማኅበራዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ አስፈላጊዎቹን በመወሰን ስብሰባውን በጸሎት አጠናቋል፡፡

ወስብሐት ለእግዚአብሔር፤ አሜን፡፡