ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል በተባለውን የሰው መግደልና መፈናቀል እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥተዋል
ነሐሴ 11 ቀን 2010 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ኦርቶዶከስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በኢትዮጵያ በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል በተባለውን የሰው መግደልና መፈናቀል እንዲቆም ቅዱስ ሲኖዶስ መግለጫ ሰጥተዋል፣ ሲኖዶሱ በኢትዮጵያ ሶማሌ ለተፈናቀሉ ወገኖቻችን ከጠቅላይ ቤተ ክህነት 4 ሚሊዮን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት 4 ሚሊዮን ብር ርዳታ እንዲሰጥ የተወሰነውን ቅዱስነታቸው ገልጸዋል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትኖሩ፣ የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች ሆይ!!
ሀገራችን ኢትዮጵያ ከቅድመ ታሪክ ዘመን አንሥቶ ህልውናዋ፣ ታሪክዋ፣ ገናናነትዋ ታላቅነትዋና ሥልጣኔዋ በዓለም ዘንድ የታወቀ ታላቅና አኵሪ ሀገር ናት፤ ለታላቅነትዋ ዐቢይ አስተዋፅኦ ካበረከቱት መካከል በፈሪሀ እግዚአብሔርና በአምልኮተ እግዚአብሔር የተገነባ፣ ስለ ሃይማኖቱና ስለ አንድነቱ ፍንክች ሳይል በአንድነትና በጽናት የቆመ ሕዝብ ያላት መሆኑ ነው፡፡ በዚህ የሃይማኖት ሥርጸት የዜጎች የማይበጠስ አንድነትና ማኅበራዊ መስተጋብር ጸጋ ሀገሪቱ ከውጭ ወራሪዎች የሚሰነዘርባትን ማንኛውንም ጥቃት በሚገባ እየመከተች እስካሁን በኀያልነት ዘልቃለች፡፡
በዚህም የዓለም ሁሉ ጸሐፍትና ምሁራን ብቸኛ የሆነ አንጸባራቂ ታሪኳን ማንነትዋንና ነፃነትዋን በደማቅ ቀለም ጽፈውላታል፣ በቀላሉ ተዝቆና ተተንትኖ የማያልቅ ሃይማኖታዊና ሀገራዊ ታሪኳ በዓለምና በአፍሪካ ጎልቶ ሊወጣ የቻለው ሕዝቦቿ በሃይማኖት፣ በዘር፣ በቀለም፣ በመልከዐ ምድር፣ በባህልና በጥቃቅን ምክንያቶች ለሚፈጠሩ ልዩነቶች ቦታ ሳይሰጡ ዘላቂና የጋራ ጥቅማቸውን ለሚያረጋግጥ ሀገራዊ አንድነት ከማንም በፊት ቅድሚያ ሰጥተው እንደ ችቦና እንደ ነዶ አንድ ላይ በመቆማቸው እንደሆነ ታሪካችን አፍ አውጥቶ ይናገራል፡፡ በተለይም በሃያ አንደኛው መቶ ክፍለ ዘመን ሀገራችን ኢትዮጵያ ለምሥራቅ አፍሪካ አልፎም ለመላው አፍሪካና ለመላው የዓለም ጥቍር ሕዝቦች ተምሳሌት የሚሆን አንጻባራቂ የልማት፣ የአንድነትና የመልካም አስተዳዳር ስኬት ታረጋግጣለች ብሎ የዓለም ሕዝብ ተስፋ በጣለባት ወቅት፣ ዜጎች ለታሪካቸው፣ ለባህላቸውና ለሃይማኖታቸው የማይመጥን ሰብእና እንደዚሁም በዓለም ሕዝብ ፊት ኀፍረትና ፀፀት የሚያስከትል ተግባር እንዳይፈጽሙ በእጅጉ መጠንቀቅ አለባቸው፤
እንደሚታወቀው ሁሉ በመንፈሳዊው ዓለም ካልሆነ በቀር እኩያት ፍትወታት ባየሉበት በዚህ ዓለም እንከን የለሽ ሥራና ሠሪ ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም፤ በመሆኑም ስላለፈው እንከን ስናቀነቅን የወደፊቱ ዕድል እንዳያመልጠን ሁሉንም ነገር በይቅርታና በፍቅር ማለፍ አማራጭ የሌለው ጥበብ እንደሆነ ኢትዮጵያውያን ሁሉ በውል ሊገነዘቡት ይገባል፣ሀገራችን ኢትዮጵያ በጥቍሮች ዓለም፣ በአፍሪካና ይልቁንም በምሥራቅ አፍሪካ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሆና እንድትታይ ያደረጋት ምሥጢር የሃይማኖቷ ጸጋና የሕዝቦችዋ አንድነት እንደሆነ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ፣ በተለይም ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎችና ወጣት ልጆቻችን ከልብ እንድትገነዘቡት አጥብቀን እንመክራለን፤
ታላቅና ገናና የሆነች ኢትዮጵያ በአንድነቷ እንደ ታፈረች፣ እንደተከበረችና ኀያል እንደሆነች እንደጥንቱ እንድትቀጥል የማይፈልግ ኢትዮጵያዊ እንደሌለ በእርግጠኝነት እናውቃለን፡፡ ነገር ግን መንገዱን ስተን ወደ ገደል እንዳንገባ በማስተዋልና በአርቆ አሳቢነት መጓዝ ይገባናል፤ በዚህ ዙሪያ የሃይማኖት መሪዎች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ ምሁራንና አርቲስቶች ያለመታከት ሌት ተቀን መሥራት ይኖርባችኋል፤ ወጣት ልጆቻችንም በማኅበራዊ ሚዲያ ቅስቀሳ፣ በአፍራሽ የቅንብር ወሬና በስሜት ሳትሸነፉ የነገዋን ኢትዮጵያ ብሩህ ተስፋ ከወዲሁ በመመልከት ከሁሉም በላይ ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት በጽናት እንድትቆሙ በሚወዳችሁና በምትወዱት በእግዚአብሔር ስም አጥብቀን አደራ እንላችኋለን፡፡
የተወደዳችሁና የተከበራችሁ የኢትዮጵያ ሕዝቦች!! ለዚህች ሀገር መነሻም መገስገሻም ሆና ሁሉንም ኢትዮጵያዊ በእኩልነት እያስተናገደች የኖረችና ያለች የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን እንደሆነች ማንም ኢትዮጵያዊ አይስተውም፣ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያናችን ለሀገሪቱ የሃይማኖት፣ የባህል፣ የቅርስ፣ የዕውቀት፣ የሥነ ጽሑፍ፣ የሥነ ጥበብ፣ የመቻቻልና የአብሮነት ጒልላት የሆነች፣ በማንም ይሁን በማን ላይ እጅዋን ጭና የማታውቅ፣ ሁሉንም በሰላምና በፍቅር እንደዚሁም በእናትነት መንፈስ የምትመለከት ቤተ ክርስቲያን ናት፡፡ ይሁን እንጂ በአሁኑ ጊዜ በእርስዋ ላይ እየተሠነዘረ ያለው አሳፋሪ፣ ዘግናኝና አሠቃቂ ድርጊት የናት ጡት ነካሽ የሚያስብል፣ ሊደረግ ቀርቶ ሊታሰብ የማይችል፣ በእግዚአብሔር አምናለሁ የሚል ቀርቶ ሃይማኖት የለሽ ፍጡር የማይፈጽመው ድርጊት በኢትዮጵያ ሶማሌ፣ በባሌ፣ በሻሸመኔ፣ በጣና በለስና በሌሎችም አካባቢዎች ተፈጽሞአል፡፡
ይህ ዘግናኝና አሳፋሪ ድርጊት ቅዱስ ሲኖዶስን ብቻ ሳይሆን መላ ኢትዮጵያውያንን ያሸማቀቀ ድርጊት ነው፤ በዚህ አሳዛኝና አሠቃቂ ድርጊት ለጊዜው የታወቁት ዘጠኝ አብያተ ክርስቲያናት ከነሙሉ ንብረታቸውና ሀብታቸው በቃጠሎና በዝርፊያ ወድመዋል፤ የሀገረ ስብከቱ መንበረ ጵጵስና፣ ጽ/ቤቱና መኪናው፣ እንደዚሁም የቤተክርስቲያኗ ት/ቤቶች ሙሉ በሙሉ ተቃጥለዋል፤ ንብረታቸውም ተዘርፈዋል፡፡ ለጊዜው የታወቁ አምስት ካህናት በአሠቃቂ ሁኔታ ተገድለዋል፣ ሰባት ካህናትም በጽኑ ተደብድበው ሞተዋል ከተባሉ በኋላ ተርፈው በሕክምና እየተረዱ ይገኛሉ፤ ገና ቊጥራቸው ያልታወቀ ምእመናንም በተመሳሳይ ሁኔታ ተገድዋል፣ ተደብድበዋልም ሀብታቸውና ንብረታቸውም ተዘርፎአል፡፡ ይህ ኢሰብኣዊ የሆነ አሠቃቂ የጭካኔ ድርጊት በኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ የተፈጸመ ሳይሆን በሌሎች አብያተ ሃይማኖትም እንደተፈጸመ ለማወቅ ተችሎአል፡፡ በመሆኑም በቤተ ክርስቲያንና በዜጎች ላይ የደረሰው ጉዳት እጅግ ከባድ ከመሆኑ አንጻር ሁኔታውን በሀገር ውስጥም ሆነ ከሀገር ውጭ ያለው ኢትዮጵያዊ ሁሉ ለወገን ደራሽ ወገን ነውና በተቻለው ሁሉ የተቸገሩትን፣ የሚላስ፣ የሚቀመስ እንዲሁም የሚለበስ ያጡትን ወገኖችን ለመርዳት የበኩሉን በማድረግ እንዲረባረብ፣ የፈረሱትንና የተቃጠሉትን አብያተ ክርስቲያናት እንደገና መልሶ ለመሥራት በሚደረገው ርብርብ አስፈላጊውን ድጋፍ እንዲያደርግ ቤተ ክርስቲያናችን በእግዚአብሔር ስም ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡
በመጨረሻም፡ የዜጎች ደኅንነት፣ የሀገር ሰላምና አንድነት የሚጠበቀው ገደብ የለሽ መብትና ነፃነት በመስጠት ብቻ ሳይሆን የሕግን የበላይነት በማስፈንና ሥነ ሥርዐትን በማስጠበቅ እንደሆነ ጥርጥር የለውም፤ ይሁንና መንግሥት ለብሔራዊ መግባባት ሲል የሚከተለው ከመጠን ያለፈ ትዕግሥት የሀገሪቷን አንድነትና የዜጎችዋን ደኅንነት በከባድ ሁኔታ እየሸረሸረ ስለሆነ ሳይውል ሳያድር የዜጎችን የመኖር ዋስትና፣ የሃይማኖትን ልዕልና በሕጉ መሠረት በመጠበቅ ፀጥታውን እንዲያስከብር፣ ኦርቶዶሳዊት ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ትማፀናለች፤ እንደዚሁም ተፎካካሪ የፖለቲካ ኀይሎችና ሕዝቡም ከሁሉ በፊት ለሀገር አንድነትና ለዜጎች ደኅንነት ቅድሚያ ሰጥታችሁ እንድትሠሩ፣ ወጣት ልጆቻችንም በስሜት ተገፋፍታችሁ በወገን ላይ መጨከንን ከዛሬ ጀምሮ እርም ብላችሁ እንድታቆሙ፣ መንግሥት፣ የሃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች የሚሏችሁን ብቻ እየሰማችሁ ሀገር የምታድግበትን አንድነትዋ የሚጠበቅበትንና ሰላምዋ የሚጠናከርበትን ሥራ ብቻ ለመሥራት በማስተዋል እንድትተጉ አባታዊ መልእክታችንን በድጋሚ በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን