ነሐሴ 1 ቀን 2010 ዓ.ም. የጾመ ፍልሰታ ሙሉ ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገር የምትገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ምእመናን ወምእመናት በሙሉ እግዚአብሔር አምላካችን እንኳን ለሁለት ሺሕ ዐሥር ዓመተ ምሕረት የቅድስት ድንግል ማርያም ተዝካረ ጾም በሰላም አደረሳችሁ፡፡

“ወአፅገቦሙ እምበረከቱ ለርኁባን
የተራቡትን ከበረከቱ አጠገባቸው፤”
(ሉቃ. 1፥53)

ይህ ቃል፤ መንፈሰ እግዚአብሔር በቅድስት ድንግል ማርያም ልሳን በኩል ያስተላለፈው መለኮታዊ ቃል ነው፡፡ የቃሉ መሠረታዊ መልእክት በድንግል ማርያም ማሕፀን ካደረው ከጌታችን ከመድኀኒታችንና ከአምላካችን ከኢየሱስ ክርስቶስ ነገረ አድኅኖ ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው፤ ረኃብ የሚለው ቃል ሰፋ ተደርጎ ሲታይ በረኃበ ሥጋ ላይ ብቻ ሳይሆን በሰው ልጅም ሆነ በሌሎች ሕያዋን ፍጡራን የሚከሠት የመሠረታዊ ፍላጎት ዕጥረትን የሚገልጽ ነው፡፡ ይህም የዕውቀት፣ የጤና፣ የመንፈሳዊ ሕይወት፣ የሞራል፣ የሰላም አለመረጋጋትን የሚያከስትሉ የህልውና ጣዕም ዕጥረቶችን በሙሉ ሊያመለክት ይችላል ማለት ነው፡፡

በተለይም በአምሳለ እግዚአብሔርና፣ በአርኣያ እግዚአብሔር የተፈጠረውና ሕያው መንፈስ ያለው የሰው ልጅ ከመንፈሳዊ ሕይወት ርቆ ከእግዚአብሔር ጋር ያለውን ግንኝነት ሲያቋርጥ ከባድ የሆነ መንፈሳዊና ሞራላዊ ረኃብ ያጠቃዋል፡፡ ይህ ዐይነቱ ረኃብ ከሁሉም የባሰ ጎጂ ረኃብ ነው፤ ሰው በአምላኩ እስካመነ ድረስ በጸሎትና በሃይማኖት ፈጣሪውን ተማፅኖ በፈጣሪ በረከት ተግባሩ ሰምሮለት ረኃበ ሥጋንና ሌሎች መሰል ዕጥረቶችን ሊያስወግድ ይችላል፡፡ ከእግዚአብሔር በመለየቱ የሚያጋጥመው ረኃበ ነፍስ ግን በዚህ ዓለም ባለበት ጊዜ ጎልቶ ባይታይም በወዲያኛው ዓለም የከፋ ረኃበ ነፍስ ያገኘዋል፤ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ “እናንተ አሁን የምትራቡ ብፁዓን ናችሁ ትጠግባላችሁና፤ እናንተ አሁን የጠገባችሁ ወዮላችሁ ትራባላችሁና” ሲል ያስተማረው ረኃበ ሥጋውን ከፅጋበ ነፍስ፣ ፅጋበ ሥጋን፣ ከረኃበ ነፍስ አዟዙሮ በማነፃጸር እንደሆነ መረዳት ይቻላል፡፡ ከዚህ አኳያ ሲታይ ከረኃበ ሥጋ ይልቅ ረኃበ ነፍስ እጅግ በጣም ከባድ እንደሆነ እናስተውላለን፤ በሌላ በኩል ረኃብ ማለት የእግዚአብሔርን ቃል ያለመስማት እንደሆነ ሲያመለክት እግዚአብሔር በነቢዩ አድሮ “ረኃብሰ ኢሰሚዐ ቃለ እግዚአብሔር፣ ረኃብ ማለት የእግዚአብሔርን ቃል ያለመስማት ነው ብሎአል” ከዚህ አንጻር መንፈስ ቅዱስ ባደረባት እግዚአብሔር ወልድ ማሕፀኗን መንበረ መንግሥት ባደረገላት በቅድስት ድንግል ማርያም ልሳን የተጠቀሰው ረኃብና ጽጋብ የትኛው ነው ብለን ብንጠይቅ መልሱ ከባድ አይሆንም፤ እግዚአብሔር የፍጥረቱን ረኃበ ሥጋ የማይሻ ሩኅሩኅ አባትና ፈጣሪ ቢሆንም ከሥጋዊ ይልቅ ለመንፈሳዊ፣ ከጊዜያዊ ይልቅ ለዘለዓለማዊ ሕይወት እንደሚያደላ የታወቀ ነው፤ ለሰው ልጅ ሁሉ ቤዛ ይሆን ዘንድ ወደዚህ ዓለም የመጣበት መሠረታዊ ዐላማም ይኸው ነው፤ ከዚህ አኳያ ከላይ የተጠቀሰው በረከት ከበረከተ ሥጋ በላይ የሆነ በረከተ ነፍስን የሚያመለክት ነው፡፡

ክርስቶስ ሰው ከመሆኑ በፊት በዓለም ሁሉ ተንሰራፍቶ የነበረውና መድኀኒት ያልተገኘለት የምግብ ረኃብ ሳይሆን የመንፈሰ ልደትና የመንፈሰ ሕይወት ዕጦት ነው፤ ይህ ዕጦት ነው ረኃብ ተብሎ የተገለጸው፣ ቅዱስ ገብርኤል ሊያበሥር የመጣውም መንፈሳዊ በረከትን፣ እርሱም ከእግዚአብሔር ጋር በሐዲስ ልደት መገናኘትን፣ ለሰው ልጅ ሁሉ የሚናኝበት ዕድል ከእግዚአብሔር የተዘጋጀ መሆኑን በቅድስት ድንግል ማርያም በረከት በኩል ሊያበሥር ነው፤ የበረከቱ መጀመሪያ ቅድስት ድንግል ማርያም መሆኗን ለማሳየትም እግዘአብሔር ካንቺ ጋር ነው በማለት ገልጾታል፡፡ እንግዲህ ትልቁ ረኃብ እግዚአብሔርን ማጣት፣ ትልቁ በረከት ደግሞ እግዚአብሔርን ማግኘት እንደሆነ ከዚህ መረዳት ይቻላል፤ ከቅድስት ድንግል ማርያም በፊት የነበረው ዘመን ዓመተ ፍዳ ፣ ዓመተ ኵነኔ በመሆኑ በእነዚያ ዘመናት የነበረው ትውልድ ሁሉ ከረኃበ ሥጋ ይልቅ መንፈሳዊ ረኃብ ያጠቃው ነበረ፤ በምድራዊ ሕይወቱም በአምልኮ ጣዖት፣ በክሕደት፣ በብልሹ ሥነ ምግባር፣ በቀቢጸ ተስፋ፣ በጽልመተ አእምሮ የተዋጠ፣ በሰማያዊ ሕይወቱም በኵነኔ ነፍስ በግዞት ከሰይጣን ሠራዊት ጋር በሥቃይ የሚማቅቅ ነበረ፤ ይህ ሁሉ በግዙፉ ዓለም ከሚታወቀው ረኃበ ሥጋ የባሰ ነበረ፤ ቅድስት ድንግል ማርያም በመንፈስ ቅዱስ ተሞልታ የተናገረችው ረኃብ እሱ ነው፤ በረከቱም በማሕፀኗ የተሸከመችው ምሉአ ጸጋ ኢየሱስ ክርስቶስ ነው፤ ከበረከቱ አጠገባቸው የተባሉትም በእሱ አምነው የተጠመቁ፣ በደሙ ነጽተው ከሱ ጋር የተዋሐዱ ናቸው፤ ይህንን ያደረጉ ምእመናን ከእግዚአብሔር ጋር በትክክል ተገናኝተዋል፤ በረከቱም በምልአት አድሮባቸዋል፡፡ ምድራዊ ረኃብ እንኳ ቢያጋጥማቸው በሰማያዊ ተስፋ ተሞልተው ሁሌም እንደጠገቡ፤ በሰማያዊውም ዓለም ከእርሱ ጋር ነግሠው ከብረው በደስታ ይኖራሉ።

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን፤

የቅድስት ድግል ማርያም በዓለ ፍልሰታን በማሰብ፣ በይቅርታ፣ በምሕረት፣ በጸሎት፣ በአምልኮት፣ በስግደት፣ ቅዱስ ቊርባንን በመቀበል፣ የምንጾመው ጾም ዋና ዐላማው ከእግዚአብሔር ጋር ለመገናኘት ነው፤ ምክንያቱም ከእግዚአብሔር ጋር ግንኑነት ሲኖረን የሚጐድለን ነገር እንደሌለ እናውቃለንና፤ ቅዱሳን ሐዋርያት በዚህ ወቅት ጾመው እግዚአብሔርንም ቅድስት ድንግል ማርያምንም አግኝተዋል፤ እኛም እግዚአብሔርንም ቅድስት ድንግል ማርያምንም ለማግኘት እንጾማለን እናገኛቸውማለን ለዚህም ምስክራችን ግዙፉ ንጻሬ ዐይን ሳይሆን ረቂቁ ንጻሬ መንፈስ ነው፤ ፈጣሪዋን የምትከተል መንፈስ ምን ጊዜም ነፃና ደስተኛ ናት፤ ስለዚህ ይህንን ጾም ወጣት ሽማግሌ፣ ሕፃን ዐዋቂ ሳይባል ሁሉም እግዚአብሔርንና ቅድስት ድንግል ማርያምን በመሻት ፍቅርንና መታዘዝን፣ ሰላምንና አንድነትን እንደ ሸማ በመጎናጸፍ ሁሉም ሊጾመው ይገባል፡፡ ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ እየታየ ያለው ተስፋ ሰጭ የሆነ የሀገራችን ሰላምና የመግባባት መንፈስ ሥር እንዲሰድ አጥብቀን ወደ ፈጣሪ የምንጮኽበት ጾም ሊሆን ይገባል፡፡ በተለይም በሰው ሠራሽ ምክንያቶች ከቀያቸው የተፈናቀሉና ጕዳት የደረሰባቸው ወገኖችን እንደዚሁም በሌላ ምክንያት የኑሮ እጥረት ያጠቃቸው ድሆችን ካለን ከፍለን በመመገብና በማልበስ ለእግዚአብሔር እንታዘዝ፤ ለወገኖቻችንም እንድረስ ፡፡

የዘንድሮ የጾመ ማርያም ሱባዔን ልዩ የሚያደርገው ለረጅም ጊዜ ተለያይተው የቆዩ የቤተ ክርስቲያናችን አባቶች መከፋፈሉ ቀርቶ በሰላምና በአንድነት ሆነው ሃይማኖታቸውን ሕዝባቸውንና ሀገራቸውን ለማገልገል በተስማሙበት ማግስት፣ እንደዚሁም ዓለም ከተፈጠረ ጀምሮ በአንድነት የነበሩትና ተለያይተው የማያውቁት የኢትዮጵያና የኤርትራ ሕዝቦች በሰላም ለሰላም ተባብረው ለመኖር ቃል በገቡበት ታሪካዊ ወቅት ላይ የሚጾም ጾም መሆኑ ነው፤ ይህ ለሕዝባችን ለሀገራችን ለሃይማኖታችን የተሰጠ ታላቅ አምላካዊ በረከት ነው፤ ይህ የሰላም የፍቅርና የአንድነት በረከት በከፍተኛ ጥንቃቄ ልንጠብቀው ይገባናል፤ ከእንግዲህ ወዲህ የሚፈናቀል ሕይወቱንም ሆነ ንብረቱን የሚያጣ ሰው እንዳይኖር፣ ያለፈው ይብቃ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ ተወልዶ ያደገባትና እናት ሀገሬ ናት ብሎ የሚኮራባት ኢትዮጵያ የሥጋት አገር እንዳትሆንበት አጥብቀን እንሥራ፣ እንጸልይ፣ እናስተምር ሁሉም ኢትዮጵያዊ ከሰላም፣ ከፍቅር፣ ከአንድነት፣ ይቅር ይቅር ከመባባል የተሻለ አጀንዳ እንደሌለ ዐውቆ ሰላም የየቀኑ ሳይሆን የየሰዓቱ አጀንዳ አድርጎ እንዲሠራ ከአደራ ጋር መንፈሳዊና አባታዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም ጾም ያድርግልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡