ታኅሣሥ 29 ቀን 2009 ዓ.ም የልደት በዓል ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤ ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤ እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያውያት፤

እኛን ለማዳን በለበሰው ሥጋ በቤተ ልሔም ተወልዶ በመካከላችን የተገኘው፣ በመለኮታዊ ባሕርዩ የማይወሰነው አካላዊ ቃል እግዚአብሔር ወልድ ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት በዓለ ልደቱ በሰላም አደረሳችሁ!!

“ወበዘርዕከ ይትባረኩ ኵሎሙ አሕዛበ ምድር
የምድር አሕዛብ ሁሉ በዘርህ ይባረካሉ።”
(ዘፍ 22፥18)

በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው በረከት የመልካም ነገር ሁሉ ምንጭ ነው፤ እግዚአብሔር በጥንተ ፍጥረት ለሰው ልጅ የሰጠው የመጀመሪያው ጸጋ ብዝኀ በረከት ነው፡፡ ቅዱስ መጽሐፍ ይህንን አስመልክቶ እንዲህ ይላል “እግዚአብሔርም ባረካቸው፤ እንዲህም አላቸው፤ ብዙ ተባዙ ምድርንም ሙሉአት፤ ግዙአትም፤ የባሕርን ዓሣዎችና የሰማይን ወፎች በምድር ላይ የሚንቀሳቀሱትንም ሁሉ ግዙአቸው” ይላል፤ (ዘፍ. 1፥28)፡፡ ለሰው የተሰጠው በረከት በኀጢአት ምክንያት መሰናክል ቢገጥመውም፣ እግዚአብሔር በፍጡሩ ጨርሶ አይጨክንምና ሙሉና ፍጹም የሆነው በረከት እንደገና ተመልሶ ለሰው ልጅ እንዴት እንደሚሰጥ ለበረከት በጠራቸውና በመረጣቸው ቅዱሳን አበው አማካይነት ሲያስታውቅ ኖሮአል፡፡ በተለይም የበረከት አባት ተብሎ በሚታወቀው በአብርሃም ዘር በኩል መጻኢው በረከት እውን እንደሚሆን “በዘርህ የምድር አሕዛብ ሁሉ ይባረካሉ” ተብሎ በእግዚአብሔር አንደበት በማያሻማ ሁኔታ ተነግሮ ነበር፡፡ ከእውነተኛው በረከት ተራቊታ የቆየችው ዓለመ – ሰብእ፣ እግዚአብሔር በራሱ ቃል የገባላት ዘላቂውና እውነተኛው በረከት እስኪመለስላት ድረስ ለአምስት ሺሕ አምስት መቶ ዓመታት በተስፋ ስትጠባበቅ ቆይታለች፡፡

የተናገረውን የማያስቀር እግዚአብሔር በረከቱን ለሕዝቡ የሚያድልበት ጊዜ ሲደርስ ቅዱስ መንፈሱን ባሳደረባት ቅድስት እናት በኤልሳቤጥ አንደበት የበረከቱ ሙዳይ ቅድስት ድንግል ማርያም፣ በረከቱ ኢየሱስ ክርስቶስ መሆኑንና በረከቱን ለምድር አሕዛብ ሁሉ ሊያድል እንደመጣ “ከሴቶች ሁሉ ተለይተሸ አንቺ የተባረክሽ ነሽ የማሕፀንሽ ፍሬም የተባረከ ነው” ሲል የምሥራቹን ለዓለም አሰማ (ሉቃ 1፥41-43)፡፡ ቀዳማዊ የሆነ እግዚአብሔር ወልድ በድንግል ማርያም ማሕፀን ውስጥ ዘጠኝ ወር ከአምስት ቀን በፅንስ ቆይቶ የዛሬ ሁለት ሺሕ ዘጠኝ ዓመተ ምሕረት ታኅሣሥ ሃያ ዘጠኝ ቀን በቤተ ልሔም ተወለደ ጌታችን በተወለደ ጊዜ የሰማይ ሠራዊት ማለትም መላእክትና የመላእክት አለቆች “ወናሁ ተወልደ ለክሙ መድኅን ዘውእቱ እግዚእ ቡሩክ — እነሆ መድኅን ተወልዶላችኋል፤ ይኸውም ቡሩክ የሆነ ጌታ ነው” በማለት የሕፃኑን ማንነት ከገለጹ በኋላ “በሰማያት ለእግዚአብሔር ክብር ይሁን፤ በምድርም ሰላም ይሁን፤ ለሰውም በጎ ፈቃዱ ይደረግለት” እያሉ የተወለደው ሕፃን ለሰው ልጅ የሚያስገኘውን ሰላምና መልካም በረከት በመግለጽ ደስታቸውን በቃለ መዝሙር በቤተ ልሔም ዙሪያ አስተጋብተዋል፡፡

ከሰው ወገንም ቅድስት ድንግል ማርያም፣ ከእርስዋ ጋር የነበሩ ወገኖች፣ እንደዚሁም በአካባቢው የነበሩ የከብት እረኞች በመላእክት የምስጋና መዝሙር ተሳታፊዎች ነበሩ፡፡ (ሉቃ. 2፥8-20) እንግዲህ ከጥንት ጀምሮ በአበው ሲነገርና ሲጠበቅ የነበረው የበረከት ተስፋ በቃልም፣ በመልእክትም፣ በሐሳብም፣ በምሥጢርም ተፋልሶ ሳያጋጥመው፣ ከላይ ጀምሮ እስከ ታች ፍሰቱና ምሥጢሩ ተጠብቆ በተነገረው መሠረት ተፈጽሞ መገኘቱ፣ የክርስትና ሃይማኖት ምን ያህል አምላካዊ የሆነ ጽኑ መሠረት እንዳለው ያረጋግጣል ፡፡ የክርስትና ሃይማኖት መሠረቱ “ባርኮ እባርከከ፤ መባረክን እባርክሃለሁ” ከሚል ተነሥቶ፣ “የአባቴ ቡሩካን መንግሥተ ሰማያትን ትወርሱ ዘንድ ወደኔ ኑ!” በሚል የሚጠናቀቅ፣ መነሻውና መድረሻው በረከት የሆነ ሃይማኖት ነው፡፡ የክርስትና ሃይማኖት “ለሰላሙም ፍጻሜ የለውም” ከሚል ተነሥቶ “በምድርም ሰላም ይሁን” በሚል ተንደርድሮ፣ በምስጋና፣ በክብርና በሰላም፣ በማያልፍም ሕይወት ዘለዓለማዊነቱን የሚያውጅ ሃይማኖት ነው፡፡

መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በተወለደበት ዕለት ከወደላይ የተላለፈው ዐቢይ መልእክት ሰላምና በረከት በምድር ላይ ሆነ የሚል እንደሆነ ማስተዋል አለብን፡፡ ታላቁ ሊቅና ኢትዮጵያዊው አባት ቅዱስ ያሬድ ስለዚህ በረከት ሲናገር “ በእንተ ልደቱ ለክርስቶስ አድባር ኮኑ ኅብስተ ሕይወት፤ወዕፀወ ገዳምኒ ፈረዩ አስካለ በረከት፤ ወማየ ባሕርኒ ኮነት ሐሊበ ወመዓረ፤ ማለትም ክርስቶስ በተወለደ ጊዜ ተራሮች የሕይወት እንጀራ ሆኑ፤ የበረሓ ዛፎችም የበረከት እሸትን አፈሩ፤ የባሕር ውኃም ወተትና ማር ሆነች” ይላል፡፡ የቅዱስ ያሬድ ቃለ ዝማሬ ሕያዋኑም ግዑዛኑም ሁሉ በልደተ ክርስቶስ ምክንያት በበረከት እንደ ተንበሸበሹ ይመሰክራል፡፡ ከዚህ አኳያ በበዓለ ልደተ ክርስቶስ የሚበላ እንጀራና የሚጠጣ ውኃ አጥቶ በረኃብና በጥም ተጐሳቊሎ የዋለ አልነበረም ብቻ ሳይሆን፤ እንጀራውም ወተቱም ማሩም ፍጥረቱ ሁሉ እንደ ፈለገው እየተመገበ በሰላምና በደስታ ቀኑን ሁሉ ማሳለፉን እንገነዘባለን፡፡ የልደተ ክርስቶስ በረከት ገደብ የለሽ መሆኑን ያወቅን የኢየሱስ ክርስቶስ ተከታዮች ነን የምንል ክርስቲያኖች በዚህ ቀን ርቦትና ጠምቶት፣ አዝኖና ተክዞ የሚውል ሰው እንዳይኖር ያለውን በማካፈልና በጋራ በመመገብ የታረዘውን በማልበስ የታመመውን በመጠየቅ የበዓሉን ሃይማኖታዊና ሥነ ምግባራዊ ገጽታ መጠበቅና ማስጠበቅ ይኖርብናል፡፡ በዓለ ልደተ ክርስቶስ የበረከት ቀን ከመሆኑም ሌላ የዕርቅ፣ የእኩልነትና የአንድነት በዓልም ነው፡፡ ከብዙ ጊዜ መለያየትና መራራቅ በኋላ፣ ፈጣሪ የሰዎችን ሥጋ አካሉ አድርጎ በሰዎች መካከል በአካል መገኘት ከዕርቅ ሁሉ የበለጠ ዕርቅ መሆኑን መዘንጋት የለበትም፡፡ በዕለተ ልደተ ክርስቶስ መላእክትና ሰዎች ፈጣሪያቸው በተወለደበት ዙሪያ ተሰባስበው በእኩልነትና በአንድነት ሲዘምሩና ሲያመሰግኑ ማየትና መስማትም የፍጡራንን እኩልነትና አንድነት ያረጋገጠ ሌላው ክሥተት ነበረ፡፡

ሰማያውያንና ምድራውያን ለሰው ልጅ ህልውና ወሳኝ የሆነውን ‹‹ ሰላም በምድር ይሁን›› እያሉ በአንድ ቃል መዘመራቸውም ለሰማያውያኑም ሆነ ለምድራውያኑ ከሰላም የበለጠ ትልቅ ጸጋ የሌለ መሆኑ የሚያስገነዝብ ነበረ፡፡ እንዲህም ስለሆነ ከልደተ ክርስቶስ ያልተማርነው ትምርት የለም ማለት ይቻላል። እግዚአብሔር በልደተ ክርስቶስ ዕለት ያስተማረን ብቻ አጥብቀን ብንይዝና ይህንኑ ብንፈጽም ከበቂ በላይ ነው ቢባል ፍጹም እውነት ነው፡፡ ተራራው ሁሉ የሕይወት እንጀራ ሆነ፤ የበረሓ ዛፍ ሁሉ የበረከት እሸት ሆነ፤ የባሕር ውኃም ማርና ወተት ሆነች ተብሎ ሲነገር በዓለ ልደተ ክርስቶስ የልማት፣ የእድገትና፣ የብልጽግና አስተማሪ መሆኑን ያስገነዝባል፡፡ ከዚህ አንጻር ዛሬም ቤተ ክርስቲያን የምታስተምረው ተራራው ይልማ፣በረሓው በደን ይሸፈን፣ ውኃው ከብክለት ድኖ ለምግብነት የሚያገለግሉ ሕይወታውያን ፍጡራን በብዛት ይኑሩበት የሚለው በልማትና በበረከት የተሞላው የልደተ ክርስቶስ አስተምህሮ ነው፤ ሕዝበ ክርስቲያኑ ይህንን አምላካዊ አስተምህሮ በምልአት ተቀብሎ ወደ ልማት ከተሰማራ በዚያው መጠን በረከቱን በገፍ ያፍሳል፡፡ ከዚህም ጋር “የሺሕ ፍልጥ ማሰሪያው ልጥ›› እንደሚባለው የሁሉም ማሰሪያ ሰላም ስለሆነ የድሮ ነጋዴ ለንግድ ሲወጣ ሥንቁን በትከሻው ተሸክሞ እንደሚጓዝ ሁሉ፣ ዛሬም የልማት ነጋዴ ሕዝባችን ሰላምን በልቡ ቋጥሮ መጓዝ ይኖርበታል፡፡ ሁሉም ችግሮች ከሰላም በታች መሆናቸውን ሁሉም ማኅበረሰባችን መገንዘብ አለበት፤ ሁሉም ለአንድነት፣ ለእኩልነት፣ ለፍትሕ፣ ለወንድማማችነት፣ ለመተማመንና ለመከባበር መስፈን የማያወላውል አቋም ሊይዝ ይገባል፡፡ የቀደሙት አባቶቻችን ኢትዮጵያን ታላቅ ሀገር እንድትሆን ያበቋት አንድነታቸውን ጠብቀው በጋራ ስለሠሩ ነው፤ ያለ አንድነት ታላቅነትም፣ ኀያልነትም፣ ልማትና እድገትም፣ ፈጽሞ እንደማይገኝ ሳይታለም የተፈታ ነውና ሕዝባችን ይህንን በውል ማጤን ይኖርበታል፡፡

በመጨረሻም፡ ከላይ ለመግለ,, እንደተሞከረው የክርስቶስ መወለድ ዋና ዐላማ መለያየትና መቃቃርን፣ መነታረክንና፣ በጥላቻ ዐይን መተያየትን አስወግዶ በምትኩ ዕርቅን፣ ዘላቂ ሰላምና አንድነትን በሰው ሁሉ አእምሮ ውስጥ ማስፈን እንደሆነ እናውቃለን፡፡ በመሆኑም ይህ ነገረ ሕይወት ከተሰበከባቸው የዓለማችን ሀገራት ኢትዮጵያ ቀዳሚዋ ሀገር እንደመሆኗ መጠን፣ በእግዚአብሔር ከተሰጣት የቅድሚያ ኀላፊነት አንጻር በሀገር ውስጥ ብቻ ሳይሆን በዓለም ዐቀፍ ደረጃም ሁሉ፣ እንደ ድሮው ደማቁ የአንድነት ታሪኳና ተደናቂው ሥልጣኔዋ፣ እንደዚሁም ጽኑ ሰላምዋና ልማቷ ጠብቃ በማስጠበቅ አስተማሪነትዋ ጎልቶ እንዲወጣ “ችግሮች ሁሉ ከሰላም በታች ናቸው” የሚለውን ጠንካራ የሰላም አስተሳሰብ መርሕ በማድረግ ሁሉም በአንድነት፣ በኀላፊነት፣ በቅንነትና በተቈርቋሪነት ሀገሩን እንዲጠብቅና እንዲያለማ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም የልደት በዓል ያድርግልን እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝባችንን ይባርክልን ወስብሐት ለእግዚአብሔር አሜን፡፡