በቅዱስነታቸው ዘመነ ፓትርያርክነት የተላለፉ በታሪክ የሚዘከሩ መመሪያዎች፤
ሀ. የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን መሪ ዕቅድ
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በእግዚአብሔር ቅዱስ ፈቃድ በፓትርያርክነት ተሹመው ርእሰ መንበርነቱን እንደያዙ ባስተላፉት የመጀመርያው የቅዱስ ሲኖዶስ ጉባኤ የመክፈቻ አባታዊ መልእክታቸው ቤተ ክርስቲያንዋ እንደተቋም ከማእከል ጀምሮ በደረጃ እስከ አጥቢያ ቤተ ክርስቲያናት ድረስ የሚወርድ ዘመናዊና የተጠና መሪ ዕቅድ ሊኖራት ይገባል የሚል ነበረ፡፡ በዚህ የቅዱስነታቸው ገዢ ሐሳብ ቅዱስ ሲኖዶሱም በመስማማቱ የቅዱስ ሲኖዶስ አባላት ሊቃነ ጳጳሳት የሚገኙበት ኮሚቴ ተሰይሞ አጠቃላይ የቤተ ክርስቲያንዋ ሁለንተናዊ ችግሮች በሚገባ እንዲጠና ያደረጉ ሲሆን እነሆ በአሁኑ ጊዜ የቅዱነታቸው ሐሳብ ተቀባይነት አግኝቶና ፍሬ አፍርቶ የመሪ ዕቅድ መምሪያ ተከፍቶና በጽ/ቤት ደረጃ ተዋቅሮ ሥራውን በማከናወን ላይ ነው፡፡ ይህ ከማእከል ጀምሮ ቤተ ክርስቲያንዋን የሚመጥን መሪ ዕቅድ ሊኖራት ይገባል የሚል ሐሳብም ሆነ በጽ/ቤት ደረጃ እንዲቋቋም የተደረገው በብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ዘመነ ፕትርክና በመሆኑ ቅዱስነታቸው በተቋም ደረጃ ለመልካም አስተዳደር መስፈንና ለግልጽነትና ተጠያቂነት አሠራር ሥርዐት መዘርጋት ያላቸውን ምጡቅ ራእይ በተግባር ያረጋገጠ ውጤታማ የሥራ አፈጻጸም ነው፡፡
ለ. የሀብትና ንብረት አያያዝና ቍጥጥርን በተመለከተ፣
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት ሥልጣነ ፓትርያርክነቱን በያዙ ማግሥት የሰጡት መመሪያ ቢኖር የቤተ ክርስቲያንዋ ሀብትና ንብረት በአግባቡና ዘመኑ በሚፈቅደው መልኩ መያዝ አለበት፣ ሀብት ንብረት ከብክነት ነጻ በሆነ መንገድ በዘመናዊ አሠራር መመራት አለበት፣ ከአጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ጀምሮ እስከ ጠቅላይ ቤተ ክህነት ድረስ ያለው የሒሳብ አሠራር ፈቃድ ባላቸው በውጭ ኦዲተሮች ጭምር በየዓመቱ መመርመር አለባቸው የሚል ሐሳብ ወደ ቅዱስ ሲኖዶስ በማቅረብ ቢያንስ በማእከል ደረጃ ተግባራዊ እንዲሆን አድርገዋል፡፡ ከዚህ በመነሣትም የጠቅላይ ቤተ ክህነት ሒሳብ በየዓመቱ በውጭ ኦዲተሮች እንዲመረመርና ሥራው ተጠናክሮ እንዲቀጥል የተደረገው በቅዱስነታቸው ከፍተኛ ጥረት በመሆኑ ሌላው የሥራቸው ውጤትነው፡፡
ሐ. የሒሳብ አያያዝና የሥነ ምግባር መስፈን በተመለከተ፣
ብፁዕ ወቅዱስ አቡነ ማትያስ ቀዳማዊ ፓትርያርክ ርእሰ ሊቃነ ጳጳሳት ዘኢትዮጵያ ሊቀ ጳጳስ ዘአክሱም ወዕጨጌ ዘመንበረ ተክለ ሃይማኖት በመጀመርያው የሲኖዶስ መክፈቻ ንግግራቸው በአጽንዖት ካቀረቡት መሪ ሐሳብ አንዱ ቤተ ክርስቲያንዋ ከማእከል እስከ አጥቢያ አብያተ ክርስቲያናት ድረስ ከሙስና መላቀቅና ፍትሓዊ አሠራር መስፈን አለባት የሚል ነው፡፡ በመሆኑም ችግሩ የቤተ ክርስቲያን ብቻ ሳይሆን የሀገራችን ብሎም የመላው ዓለም ችግር በመሆኑ ይህንን የጥፋት መንገድ (ሙስና) በቤተ ክርስቲያን ደረጃ በስፋት የሚስተዋል ችግር መሆኑን በመግለጽ ቤተ ክርስቲያን ወደቀደመ ልዕልናዋ መመለስ ትችል ዘንድ ግብረ ሙስናን የሚፀየፍ መዋቅር መዘርጋት እንዳለበት አመልክተዋል፡፡ ከዚህ በተጨማሪም በተለያዩ ጊዜያት በግልጽ በአደባባይ ወጥተው፣ በዐበይት ጉባኤያት፣ በየዐውደ ምሕረቱ… በማስተማር ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን ሙስናን እንዲፀየፍ በተደጋጋሚ አስተምረዋል፡፡ መመሪያም ሰጥተዋል፡፡
የቤተ ክርስቲያናችን ጠንቅ የሆነው የጥፋት መንገድ (ሙስና) ከቤተ ክርስቲያናችን በዚህ ቅጽበት ይጠፋል ባይባልም ቅሉ የፀረ ሙስና ትግሉን በይፋ፣ በአዋጅና፣ በመመሪያ ደረጃ በተደጋጋሚ በማስተላለፍ ቅዱስነታቸው ለሥነ ምግባር መጠበቅ፣ ለቤተ ክርስቲያን አሠራር ግልጽነትና ተጠያቂነት መስፈን፣ ያላቸውን ጠንካራ አቋም አሳይተዋል፡፡ የሒሳብ አሠራሩም ከነጠላ የሒሳብ አያያዝ (ሲንግል ኢንትሪ) ወደ ሁለትዮሽ የሒብ አያያዝ (ደብል ኢንትሪ) እንዲለወጥ አድርገዋል፡፡