ሚያዝያ 27 ቀን እስከ 30 ቀን 2007 ዓ.ም የተካሄደው ቅዱስ ሲኖዶስ ውሳኔዎች፡፡

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በፍትሕ መንፈሳዊ አንቀጽ 5 ቍጥር 164 ላይ በተደነገገው ቀኖና ቤተ ክርስቲያን መሠረት የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ በዓመት ሁለት ጊዜ ይካሄዳል፡፡ ከሁለቱ አንዱ ከጌታችን ከአምላካችንና ከመድኀኒታችን ከኢየሱስ ክርስቶስ በዓለ ትንሣኤ በኋላ በሃያ አምስተኛው ቀን በዕለተ ረቡዕ የሚውለው የርክበ ካህናት ጉባኤ ነው፡፡

በመሆኑም የርክበ ካህናቱ የቅዱስ ሲኖዶስ ምልአተ ጉባኤ ሚያዝያ 27 ቀን ከሰዓት በኋላ በጸሎት ተከፍቶአል፡፡ በመቀጠልም ሚያዝያ 28 ቀን 2007 ዓ.ም. መደበኛ ስብሰባውን በጸሎትና በብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ የመክፈቻ ንግግር ተጀምሮ ለሦስት ቀናት ሲካሄድ ሰንብቶአል፤ ልዩ ልዩ ውሳኔዎችንና መመሪያዎችንም አስተላልፎአል፡፡

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ ለአራት ቀናት ያህል ባካሄደው ቀኖናዊ ጉባኤ፤ ለቤተ ክርስቲያናችንና ለሀገራችን የሚጠቅሙትን፤ ለልማትና ለሰላም የሚበጁትን፤ ከሀገር ውጭ ለሚገኙና በሀገር ውስጥ ላሉ ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችን ሁለንተናዊ ሕይወት መጠበቅ የሚያስችሉትን ርእሰ ጉዳዮች በማንሣት በስፋትና በጥልቀት አይቶ የሚከተሉትን ውሳኔዎች አሳልፎአል፡፡

1. ብፁዕ ወቅዱስ ፓትርያርክ በጉባኤው መክፈቻ ያደረጉት ታሪካዊ ንግግር የቤተ ክርስቲያንን ሁለንተናዊ ሕይወት የቃኘ የሀገራችን እድገትንና የሰላም አስፈላጊነትን በስፋት የገለጸ በመሆኑ ጉባኤው በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡
2. ምልአተ ጉባኤው በቅዱስ ሲኖዶስ ጽ/ቤት ተዘጋጅቶ የቀረበውን ዓመታዊ የሥራ መግለጫ ሪፖርት አዳምጦ አንዳንድ ማስተካከያዎችን በማድረግ በሙሉ ድምፅ ተቀብሎታል፡፡
3. ምንም ጥፋትና በደል ሳይኖርባቸው ክርስቲያኖች በመሆናቸው ብቻ በሊቢያ ሀገር አይ ኤስ በተባለ የአሸባሪዎች ቡድን በግፍና በሚዘገንን ሁኔታ የተገደሉ ኢትዮጵያውያን ክርስቲያኖችንና የግብጽ ኦርቶዶክስ ክርስቲያኖችን በተመለከተ ቋሚ ሲኖዶስ ቀደም ሲል በሟቾቹ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ተወያይቶ ባቀረበው ሐሳብ መሠረት ምልአተ ጉባኤው ያለውን ሁኔታ በጥልቀት ከተረዳ በኋላ ሟቾቹ የዘመኑ ሰማዕት እንዲባሉ ተስማምቶ ወስኗል፡፡
4. እንዲሁም እንደ ኢትዮጵያውያን አቆጣጠር ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ የተሠዉት 30 የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች ልጆቻችን እና እንደ አውሮፓውያን አቈጣጠር የካቲት 15 ቀን 2015 ዓ.ም. በሊቢያ የተሠዉት 21 የኮፕቲክ ኦርቶዶክስ ቤተ ክርስቲያን አባላት ክርስቲያኖች በሁለቱም አብያተ ክርስቲያናት ሲኖዶስ የሰማዕትነት ክብር የተሰጣቸው ስለሆነ፣ የሁለቱ አኃት አብያተ ክርስቲያናት የ21ኛው ክፍለ ዘመን ሰማዕታት ተብለው በአንድነት እንዲታሰቡ ቅዱስ ሲኖዶስ ተስማምቷል፡፡
5. በልዩ ልዩ ምክንያት ከኢትዮጵያ ሀገራቸው ወጥተው በባዕድ ሀገር የሚገኙትንና ወደ ሀገራቸው በመመለስ ላይ ያሉትን ኢትዮጵያውያን ወገኖቻችንን ከማንኛውም ጥቃት ለመከላከልና ለማቋቋም ቤተ ክርስቲያናችን መንግሥት ከሚያደርገው ጥረት በመቀናጀት አስፈላጊውን ሁሉ እንድታደርግ፣ ይህን በተመለከተ ጉዳዩን የሚከታተል ኮሚቴ የቤተ ክርስቲያናችን የልማትና ክርስቲያናዊ ተራድኦ ኮሚሽንም ርዳታ ሰጪዎችን በማስተባበር ኀላፊነቱን ወስዶ በንቃትና በትጋት አንዲሠራ ጉባኤው ወስኖአል፡፡
6. ሀገራችን ኢትዮጵያ በአሁኑ ጊዜ አምስተኛውን ሀገራዊ ምርጫ ለማከናወን በሂደት ላይ መሆኗን ቅዱስ ሲኖዶስ አውስቶ ምርጫው ሰላማዊና ፍትሐዊ ሆኖ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ቤተ ክርስቲያናችን በጸሎት እንድትተጋ ጉባኤው መልእክቱን አስተላልፏል፡፡
7. ኢትዮጵያ ሀገራችን ለብዙ ዘመናት ተጭኖአት ከቆየ የድህነት አረንቋ በተጨማሪ የእርስ በርስ ግጭት ጥሎባት ባለፈው ጠባሳ ክፉኛ የተጎዳች ብትሆንም በተገኘው ሰላም ምክንያት ባሳለፍናቸው ዓመታት እየታዩ ያሉ የልማትና የዕድገት፣ የእኩልነትና የአንድነት እመርታዎች የሰላምን ጠቃሚነት ከምንም ጊዜ በላይ መገንዘብ የተቻለበት ስለሆነ፤ መላው የኢትዮጵያ ሕዝብ ከምንም በላይ ሰላሙንና አንድነቱን አጽንቶ በመያዝ ሀገሩን ከአሸባሪዎችና ከጽንፈኞች ጥቃት ነቅቶ እንዲጠብቅ ቅዱስ ሲኖዶስ በአጽንዖት ያሳስባል፤
8. ሀገራችን ኢትዮጵያ የቴክኖሎጂና የካፒታል እጥረት እንደዚሁም በሀገር ውስጥ ሠርቶ የመበልጸግ ግንዛቤ ማነስ ካልሆነ በቀር በተፈጥሮ ሀብትም ሆነ በማናቸውም መመዘኛ ከሌላው የተሻለች እንደሆነች የታወቀ ስለሆነ፤ ወጣቶች ልጆቻችን ወደሰው ሀገር እየኮበለሉ ራሳቸውን ለአደጋ ከሚያጋልጡ በሀገራቸው ሠርተው የተሻለ ኑሮ እንዲኖሩ ኅብረተሰቡም ይህንን ከግንዛቤ ውስጥ አስገብቶ በሰፊው እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ መልእክቱን አስተላልፏል፤
9. ለሀገራችንና ለሕዝቦቻችን ችግሮች ቍልፍ መፍትሔ ሊሆን የሚችለው ልማትን በማጠናከርና እድገትን በማረጋጋጥ ድህነትን ማስወገድ ስለሆነ ሕዝባችን ይህን ከልብ ተቀብሎ በየአቅጣጫው የተጀመሩትን የልማት ሥራዎች በመደገፍ ሀገሪቱን መካከለኛ ገቢ ካላቸው ሀገሮች እኩል ለማሰለፍ የሚደረገውን ሀገራዊ ርብርቦሽ ለማሳካት በርትቶ እንዲሠራ ቅዱስ ሲኖዶስ ያሳስባል፤
10. በመላ ሀገሪቱ የሚገኙ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ አብያተ ክርስቲያናት በየቤተ ክርስቲያኑ ዙሪያ ሁሉ የአረንጓዴ ልማትና የራስ አገዝ ልማት በማካሄድ ልማትን እንዲያፋጥኑ ቅዱስ ሲኖዶስ ጥብቅ መመሪያ አስተላልፎአል፡፡
11. በውጭ ሀገር ከሚገኙ አባቶች ጋር ተጀምሮ የነበረው የዕርቀ ሰላም ድርድር ለሀገራችን ልማትና ለሕዝባችን አንድነት የሚሰጠው ጥቅም የማይናቅ ስለሆነ የቤተ ክርስቲያናችን በር ለሰላምና ለዕርቅ ክፍት መሆኑን ምልአተ ጉባኤው ገልጿል፡፡

ቅዱስ ሲኖዶስ ከዚህ በላይ በተገለጹትና በሌሎችም መንፈሳዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች ላይ ሲወያይ ሰንብቶ ስብሰባውን በጸሎት አጠናቅቆአል፡፡ እግዚአብሔር አምላካችን ለሀገራችን ለሕዝባችንና ለዓለሙ ሁሉ ሰላሙን፣ ምሕረቱንና ፍቅር አንድነቱን ይስጥልን፤ እግዚአብሔር ይባርካችሁ ይቀድሳችሁ አሜን፡፡