ሚያዝያ 24 ቀን 2013 ዓ.ም ቅዱስነታቸው የትንሣኤ በዓልን አስመልክተው የሰጡት ቃለ ምዕዳንና ቡራኬ

በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤

በሀገራችን በኢትዮጵያ በገጠርና በከተማ የምትኖሩ፤
ከሀገር ውጭ በተለያዩ አህጉር የምትገኙ፤
የሀገራችንን ዳር ድንበር ለመጠበቅና ለማስከበር በየጠረፉ የቆማችሁ፤
በሕመም ምክንያት በየጸበሉና በየሆስፒታሉ ያላችሁ፤እንዲሁም የሕግ ታራሚዎች ሆናችሁ በየማረሚያ ቤቱ የምትገኙ ኢትዮጵያውያንና ኢትዮጵያት ሁሉ፤

እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሰን አደረሳችሁ። የትንሣኤ በኲር፣ የሰላም መበሥር የሆነው ጌታችን አምላካችንና መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እንኳን ለብርሃነ ትንሣኤው በሰላም አደረሳችሁ፡፡
“ወመጽአ እግዚእ ኢየሱስ ወቆመ ማእከሌሆሙ ወይቤሎሙ ሰላም ለክሙ
ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ መጣ በመካከላቸውም ቆሞ ሰላም ለእናንተ ይሁን አላቸው።”
(ዮሐ. 2ዐ፥19)፡፡

ይህ ቃል ቅዱሳን ሐዋርያት በኢየሩሳሌም ከተማ፣ቀራንዮ በተባለው ስፍራ በጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ላይ በሆነው ነገር ሁሉ በኀዘንም በፍርሀትም ተውጠው በተዘጋ ቤት ውስጥ ሳሉ የተነገረ ቃለ ሰላም ነው፡፡ ጌታችን ኢየሱስ ክርስቶስ እሑድ እኩለ ሌሊት በኀይለ መለኮቱ ሞትንና መቃብርን ድል አድርጎ ከተነሣ በኋላ ለማርያም መግደላዊትና ለሌሎች ቅዱሳት አንስት በመጀመሪያ ተገልጾአል፡፡ ቀጥሎም በኤማሁስ ለሁለት ደቀ መዛመርቱ ተገልጾላቸዋል& በዚህ ቀን አመሻሹ ላይ ደግሞ ሐዋርያት በጽርሐ ጽዮን ሳሉ በሩም መስኮቱም እንደተዘጋ በአምላክነቱ ኀይል ገብቶ በድንገት በመካከላቸው በመገኘት “ሰላም ለእናንተ ይሁን” ሲል የኋላ ኋላ የሕይወት ኀይል፣ የትንሣኤ ኀይል፣ የሰላም ኀይል አሸናፊ መሆኑን አብሥሮአቸዋል፡፡ አምላካችን ኢየሱስ ክርስቶስ ከትንሣኤው በኋላ ለደቀ መዛሙርቱ ያሰማው ዐቢይ ኀይለ ቃል ሰላም ለእናንተ ይሁን የሚለው አጽናኝ ቃል ነው፡፡

በእርግጥም በዚያች ቀውጠኛ ሳምንት ለሐዋርያት ከሰላም የበለጠ የሚያስፈልጋቸው ሌላ ነገር አልነበረም፤ ምክንያቱም ቅዱሳን ሐዋርያት ሰላም ከማጣታቸው የተነሣ ዕለታዊ ተግባራቸው ከመቋረጡም በላይ ሕይወታቸውም ከባድ ሥጋት ላይ በመውደቁ በአንድ ቤት በመሰባሰብ በሩንም መስኮቱንም ክርችም አድርገው በመዝጋት ራሳቸውን መሠወር መርጠዋል፡፡ ታድያ በዚህ ጊዜ ነበረ የሰላም ባለቤት የሆነው መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዚህ መጣ በዚህ ገባ ሳይባል መስኮቱና በሩ እንደተዘጋ ድንገት በመካከላቸው ተገኝቶ የሰላምን ቃል ያሰማቸው ቅዱሳን ሐዋርያትም አጥተውት የነበረውን የሰላም ድምፅ በመስማታቸው እጅግ ደስ አላቸው፤ ፍርሀታቸው ተወገደላቸው፤ ፍጹም ሰላምና ነፃነትም በውስጣቸው አበራ& የተማመኑበት ጌታ ሞትና መቃብር ይዘው የማያስቀሩት መሆኑን በተግባር ሲያዩ ጭንቀቱና ሥጋቱ ሁሉ ስፍራውን ለቀቀ፤ በምትኩም ደስታው፣ በጌታ መታመኑና ሰላሙ ውስጣቸውን ሞላው፤ ነገሮች በቅጽበት ተለዋውጠዋልና የተዘጋውን በር ራሳቸው ከፈቱት፤ ከዚህ ቀን ጀምሮ የጌታን ትንሣኤ ለመመስከርና ለዓለም ሁሉ ለማድረስ አንድ ብለው ጒዞውን ለመጀመር በልበ ሙሉነት ዝግጁ ሆኑ፤ የጌታችን መሰቀል መሞትና መነሣት በመመስከሩና በማስተማሩ ረገድ በዚህ ዓለም ሊገድባቸው የሚችል ኀይል እንደማይኖር እርግጠኞች ሆኑ፤ በአካላቸው ላይ ሊቃጣ የሚችል መከራ ሁሉ ከቊጥር ላለማስገባት በሕሊናቸው ደመደሙ፤ በሂደትም ይህንን በተግባር አሳዩ፣ ይህንን ሁሉ ድፍረትና ቈራጥነት የሰጣቸው ሌላ ሳይሆን የትንሣኤው ኀይል እንደ ነበልባለ እሳት ግሎ በልቡናቸው ውስጥ በመቀጣጠሉ ነበር፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

ከጌታችን ትንሣኤ በፊት የነበረው ፍርሐትና ሥጋት ዛሬም ከዓለማችን አልወጣም፤ ዛሬም ሰዎች ውስጣዊም ሆነ ውጫዊ ሕይወታቸው በፍርሀት በጭንቀትና በሥጋት እንደተከበበ ነው፡፡ ዛሬም ልክ ሐዋርያት እንደነበሩበት ዝግ ቤት ቤታቸውን የዘጉ፣ አሊያም ጥለው የሸሹ፣በመካከላቸውም ሕይወታቸውን ያጡ፣ሕይወታቸው ቢተርፍም የሚላስ፣ የሚቀመስ፣ የሚጐረስ፣ የሚለበስ፣ ያጡ ብዙ ናቸው፡፡ ከዚህ አኳያ ሰዎች ነንና ይህ ለምን ሆነ ብለን ልንጠይቅ ተፈጥሮና ሃይማኖት ያስገድዱናል፤ መልሱ ግን አንድና አጭር ነው፡፡ እሱም ሰላም በመጥፋቱ ነው፡፡ ይህንን ሰላም ያጣነው በሌላ ሳይሆን በእኛው በራሳችን ነው፤ መፍትሔ የሌለው ነገር ያለ ይመስል ቁጭ ብለን በአንድነትና በጋራ ተወያይተን ችግራችንን መፍታት አቅቶን ያመጣነው ጣጣ ነው፡፡ እንግዲህ እግዚአብሔር የሰጠንን ብሩህ አእምሮ ተጠቅመን የራሳችንን ችግር በራሳችን መፍታት ካልቻልን በማንም ይሁን በማን ብናመካኝ የሚቀበለን አናገኝም፤ እግዚአብሔር እንደሆነ በተፈጥሮም ሆነ በቅዱስ መጽሐፉ የሰላም መገኛዋና መጠበቂያዋ ዕርቅና ይቅርታ እንደሆነ ባለማወላወል ነግሮናል፡፡ እሱ ያለውን የማንቀበል ከሆነ እኛን በሚቀጣበት ሥልጣኑ ቀጥቶ በኀይለ መለኮቱ ሰላሙን ለድሆቹ ፍጡራን ያጐናጽፋል&ይህ የእግዚአብሔር አሠራር ስለሆነ እሱም አያልፈውም እኛም አናስቀረውም፤ ነገር ግን ቅዱስ መጽሐፍ እንደሚመክረን እሱ ሳይፈርድብን በይቅርታና በዕርቅ እኛው በእኛው ላይ ብንፈርድ ትልቅ ጥበብና ብልኅነት ነው&አሁንም የእኛ ቀን የጨለመ ቢመስልም ለእግዚአብሔር ቀኑ ሁሉ አይጨልምምና ኢትዮጵያውያን ልጆቻችንና ወገኖቻችን እባካችሁ ሁሉን ነገር እርግፍ አድርገን በመተው ለዕርቅና ለሰላም፣ ለይቅርታና ለአንድነት፣ ለእኩልነትና ለወንድማማችነት ያለ ማቋረጥ ብንተጋ መልካምና ጣፋጭ የሕይወት እሸት እንቀምሳለን፡፡

የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት፤

የሰው ልፋት ምንም ቢበዛ እግዚአብሔር ካልፈቀደው የሚሆን እንዳልሆነ የምንዘነጋው አይደለም፤ እግዚአብሔርን ፊት ለፊታችን አድርገን የማንሠራው ሥራ ሁሉ ብላሽ እንደሆነ የምንገነዘበው እግዚአብሔርን ከፊት ለፊታችን ገለል አድርገን ለብቻችን የሮጥንባቸው የዓመታት ጒዞ የት እንዳደረሱን በአእምሮአችን አስተውለናል& በዓይናችንም አይተናል፣ በጆሮአችን ሰምተናል፤ ከእግዚአብሔር ኮብልለን ማምለጥ እንደማንችልም ከኛ በላይ ሌላ ምስክር አያስፈልገንም&ለእኛ ያሉን ተመራጭና ብቸኛ ዕድሎች እግዚአብሔርንና ሰላም፣አንድነትና እኩልነት፣ ዕርቅና ይቅርታ ብቻ ናቸው፡፡ ከዚህ ውጭ ምንም ተመራጭ ዕድል የለንም&ጌታችንም በትንሣኤው ዕለት ሰላሙን በቃለ ብሥራት ያበሠረን ከሰላም የተሻለ እኛን የሚጠቅም ሌላ አማራጭ እንደሌለ ስለሚያውቅ ነው፡፡

በመጨረሻም በዓለ ትንሣኤውን ስናከብር በሰላም ዕጦት ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በየመጠለያው የሚገኙ ልጆቻችንና ወገኖቻችንን በመመገብ፣ በማጠጣትና&በማልበስ ከኛ ጋር የፋሲካውን በዓል በመጽናናት እንዲያሳልፉ ሁሉም ሕዝበ ክርስቲያን የበኩሉን ድጋፍ እንዲያደርግ፣ ከዚህ ጐን ለጐንም ሰላም እንዲሰፍን የሰላም ኀይሎች ሁሉ የበኩላቸውን ጥረት እንዲያደርጉ፣እግዚአብሔርንም ለሰላማችን መረጋገጥ መለኮታዊ ሥራውን እንዲሠራ እንድንማፀነው አባታዊና መንፈሳዊ መልእክታችንን በእግዚአብሔር ስም እናስተላልፋለን፡፡

መልካም በዓለ ትንሣኤ ያድርግልን!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦችዋን ይባርክ!
ወስብሐት ለእግዚአብሔር