ሚያዝያ 15 ቀን 2007 ዓ/ም፡ በመንበረ ጸባኦት ቅድስት ሥላሴ ካቴድራል ጸሎተ ፍትሐት
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
“ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡየ ዘበሰማያት
በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ።”
(ማቴ. 10፥32)
ቤተ ክርስቲያን ከተመሠረተችበት ጊዜ ጀምሮ መሥዋዕትነት አብሯት የኖረ ታሪክ ነው፡፡ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያንም በልዩ ልዩ ዘመናት ልጆቿ በግፍ ተገድለው ሰማዕትነትን ተቀብለዋል፡፡ በስድስተኛው ክፍለ ዘመን በናግራን፣ በዘጠነኛው ክፍለ ዘመን በዮዲት ጉዲት፣ በዐሥራ አምስኛው ክፍለ ዘመን በግራኝ አሕመድ፣ በዐሥራ ዘጠነኛውና ሃያኛው ክፍለ ዘመን በውጭ ወራሪ ኀይሎች በርካታ የሰማዕትነት ታሪኮች አልፈዋል፡፡
ይሁን እንጂ በሁሉም ዘመን የተነሡባት አሳዳጆችና ገዳዮች ከነታሪካቸው ሲጠፉ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን በአምላኳ ጥበቃና በልጆቿ ጽናት ሰማዕታቷን አክብራ ለሰው ልጅ መንፈሳዊ ሀብትን እያደለች አሁንም አለች ወደፊትም ትኖራለች፡፡ ዛሬ እነዚህ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ወጣቶች በጠባቡ በር ተጒዘው ሰማዕትነት ተቀብለው ወደ መንግሥተ ሰማያት የገቡ የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን የክርስትና እምነት ጽኑ ምስክሮች ናቸው፡፡
የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስም ለእነዚህ ልጆቻችን ቀኖና ቤተ ክርስቲያን በሚፈቅደው መሠረት የሚገባውን የሰማዕትነት ቀኖና ሥነ ሥርዐት በቅርቡ በማከናወን ለመላው ዓለም ያሳውቃል፡፡ ስለዚህ የክርስቶስ ቤተ ሰቦች የሆናችሁ ክርስቲያኖች ሁሉ በዚህ አረመኔያዊ ወንጀል ሳትደናገጡ አሸባሪነትን በአንድነት ሆናችሁ በማውገዝና በመከላከል የተጀመረውን ተቃውሞ ትርጒም ባለውና አፋጣኝ በሆነ መንገድ ልንፈጽመው እንደሚገባ ማሳሰብ እንወዳለን፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን!
ለአሸባሪነት ሃይማኖት የለውም፣ በዕውቀትና በበሳል አእምሮ የሚከናወን ተግባርም አይደለም፣ የድርጊቱ ፈጻሚዎችም የተረጋጋ ሥነ ልቡና ያላቸው ሊሆኑ አይችሉም፡፡ ብሶት ያለባቸው ሰዎች እንደሚያደርጉት ያለ የነፃነት ትግልም አይደለም፡፡ ነገር ግን በፍጹም ራስ ወዳድነትና ጭካኔ ላይ የተመሠረተ አስነዋሪ ወንጀል ነው፡፡ የአይ ኤስ አሸባሪዎች የፈጸሙት ወንጀል የሃያ አንደኛው ክፍለ ዘመን ትውልድ አስተሳሰብን የማይወክልና የሰውን ልጅ ተፈጥሮኣዊ ባሕርይ የጣሰ ተግባር ነው፡፡
ይህንን አስነዋሪ ግፍ ክርስቲያኖችና የሌላ እምነት ተከታዮች ብቻ ሳይሆኑ ሰው የሆነ ፍጡር ሁሉ ሊያወግዘውና ሊጸየፈው የሚገባ ተግባር ነው፡፡እነዚህ ሰዎች የፈጸሙት ተግባር በራሳቸው ላይ ቢፈጸምና በጤናማ ሥነ ልቡና ቢያዩት ኖሮ በወጣቶቻችን ላይ በፈጸሙት ተግባር ልክ እንኳ ቢከፈላቸው እንደማይበቃ አድርገው በራሳቸው ላይ ይፈርዱ ነበር፡፡
ዛሬ የሰው ልጅ በተፈጥሮ ለሚመስሉት ወገኖቹ ሕይወት፣ ደኅንነት፣ ምቾትና ሰላም ደፋ ቀና በሚልበት ዓለም ከሰው የተፈጠሩ የማይመስሉ አረመኔዎች ክቡር የሆነ የሰውን ልጅ ነፍስ ኢሰብኣዊ በሆነ መንገድ ሲቀጥፉ መታየት ምን የሚሉት እምነት ነው? ይህን አስነዋሪና ከሰው ተራ የሚያወጣቸውን ተግባርስ የወጣቶቹ ወላጆች ሳይቀሩ ዓለም ሁሉ በሚመለከተው ሚዲያ ማሳየትስ ምን የሚሉት ጭካኔ ነው? የሰውን ልጅ የቀድሞ ታሪክ አጥፍቶ አዲስ የግፍና የኢሰብኣዊነት ታሪክ ለመሥራት መጣጣርስ ምን የሚሉት አስተሳሰብ ነው?
ስለዚህ አይ ኤስን ጨምሮ በሰብኣዊ ፍጡር ሉዓላዊ ክብር ላይ የተቃጣ የአሸባሪነት ወንጀል ያለምንም ቅድመ ሁኔታ ከምድራችን ሊወገድ የሚገባው እኩይ ግብር ነው፡፡ ከዚህ አንጻር ራሳቸውን አይ ኤስ ብለው የሚጠሩት አሸባሪዎች ከዕውቀትና ከሃይማኖት የወጡ፣ የልማትና የሰው ልጅ ሰላማዊ ሕይወት ሥጋቶች የሆኑ ቡድኖች በመሆናቸው ዓለም በአንድነት ተባብሮ ሊያስቆማቸው ይገባል፣ ምናልባት ቡድኑን በገንዘብና በልዩ ልዩ መንገድ ድጋፍ የሚያደርጉ ግለሰቦችና ተቋማት ካሉም የጥፋት ተባባሪ ከመሆን ሊታቀቡ ይገባል፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም ለፈጸሙት ወንጀል በነፍሳቸውና በኅሊናቸው ከሚመጣባቸው ዘለዓለማዊ ፍርድ ይድኑ ዘንድ ንስሓ እንዲገቡ ጥሪዋን ታስተላልፋለች፡፡
የተወደዳችሁ የመንፈስ ቅዱስ ልጆቻችን ምእመናንና ምእመናት!
ቀደም ሲል እንደገለጽነው በመንፈሳዊ ሕይወት ከምናገኘው ዋጋ ሁሉ የሰማዕትነት ዋጋ ተወዳዳሪ የለውም፣ በፍትሕ መንፈሳዊ ‹‹ወሰማዕታትሰ እሉ እሙንቱ ዘይቤ ክርስቶስ በእንቲኣሆሙ ዘሰ አምነኒ በቅድመ ሰብእ አነኒ አአምኖ በቅድመ አቡየ ዘበሰማያት፣ ወለእመ ተሳተፍክምዎሙ በጊዜ ኀዘናቲሆሙ ይከውን ለክሙ ስምዕ በእንተ ጻሕቀ ኅሊናክሙ –ሰማዕታት ማለት እኔን በሰው ፊት ያመነኝን ሰው እኔም በሰማያዊ አባቴ ፊት አምነዋለሁ ብሎ ክርስቶስ ስለእነርሱ የተናገረላቸው ናቸው፡፡ እነዚህን በመከራቸው ጊዜ ብትመስሏው ስለቊርጥ ሓሳባችሁ ሰማዕትነት ይቈጠርላችኋል» የተባለላቸው ናቸው።
“ሰማዕታት እንደ እግዚአብሔር ፈቃድ መከራን የሚቀበሉ፣ መልካም እያደረጉ ነፍሳቸውን ለታመነ ፈጣሪ የሰጡ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡” (1ኛ ጴጥ. 4፥19)፤ ሰማዕታት ኀላፊ ጠፊ የሆነውን የዚህን ዓለም ጣዕም ትተው ስለእግዚአብሔር መንግሥት እና ፍቅር ታማኝ ሆነው በስለትና በእሳት ፊት በጽናት የቆሙ የእምነት አርበኞች ናቸው፤ ሰማዕታት ለሃይማኖታቸው ታማኞች ለመድኀኒታችን ለኢየሱስ ክርስቶስ ስም ደማቅ ምስክሮች ናቸው።
ሰማዕታት በቅዱሳት መጻሕፍት “ሥጋን የሚገድሉትን ነፍስን ግን መግደል የማይቻላቸውን አትፍሩ፤ ይልቁንስ ነፍስንም ሥጋንም በገሃነም ሊያጠፋ የሚቻለውን ፍሩ፤” (ማቴ 10፥28) የሚለውን ቃል ተቀብለው ምርጫቸው እግዚአብሔር መሆኑን በአደባባይ ያሳዩ ክርስቲያኖች ናቸው፡፡ሰማዕታት የጥበብ መጀመሪያ እግዚአብሔርን መፍራት ነው በተባለው መሠረት የመንግሥተ ሰማያትን የክብር አክሊል በጥበብ ጀምረው በደማቸው ምስክርነት የተቀዳጁ ናቸው፡፡
ክብራቸውም አቡቀለምሲስ ዮሐንስ በራእዩ ምዕ 20 ቁጥር 4 “ዙፋኖችንም አየሁ፤ በእርሱ ላይ ለተቀመጡትም ዳኝነት ተሰጣቸው፣ ስለኢየሱስም ምስክርና ስለ እግዚአብሔር ቃል ራሶቻቸው የተቈረጡባቸውን ሰዎች … አየሁ” ብሎ እንደተናገረው በእግዚአብሔር መንግሥት የማያልፍ አክሊልና የፍርድ ዙፋን የተዘጋጀላቸው ናቸው፡፡
ስለዚህ የእነዚህ ወጣቶች ልጆቻችን ቤተሰቦች የሰማዕታት ቤተ ሰቦች በመሆናችሁ ልትጽናኑ ይገባል፡፡ ቅድስት ቤተ ክርስቲያንም በደሙ የመሠረታት ወልደ እግዚአብሔር የልጆቿን ነፍስ በክብር እንዲቀበል ትጸልያለች፡፡ ልዑል እግዚአብሔር አምላካችን የልጆቻንን ነፍስ በክብር ያሳርፍልን፣ ለመላው ዓለም ሰላምንና መረጋጋትን ለቤተ ክርስቲያንና ለሰማዕታቱ ቤተ ሰቦች መጽናናትና ብርታትን ይስጥልን፡፡
ወስብሐት ለእግዚብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!