ሚያዝያ 14 ቀን 2007 ዓ.ም. በሊቢያ አይኤስ በተባለው አሸባሪ ቡድን በግፍ ስለተገደሉት ኢትዮጵያውያን በመስቀል አደባባይ በተደረገው ሰላማዊ ሰልፍ ላይ ቅዱስነታቸው የሚከተለውን አስተላልፈዋል፡፡
በስመ አብ ወወልድ ወመንፈስ ቅዱስ አሐዱ አምላክ፤
ሚያዝያ 11 ቀን 2007 ዓ/ም ራሱን አይ ኤስ በማለት የሚጠራው ሰብኣዊ ርኅራኄ የሌለው አሸባሪ ቡድን በወገኖቻችን ላይ ያደረሰውን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ከሰማንበት ቀንና ሰዓት ጀምሮ በአምላካችን ዘንድ የወገኖቻችን ደም በከንቱ እንዳይቀር ልብን በሚሰብር ኀዘን በጸሎት በማሰብ ላይ እንገኛለን፡፡ ይህ በሰብኣዊ ፍጡር ይፈጸማል ተብሎ የማይታሰብ ድርጊት አሳሳቢና ፍጹም ጭካኔ የተመላው በመሆኑ ከኀዘናችንና ሰማዕታቱን በጸሎት ከማሰብ በተጨማሪ ወጣቶቹ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች መሆናቸውን ስለተረዳን ስለጌታችን ስምና ስለቀናች ሃይማኖት፣ ስለ እግዚአብሔርም ፍቅር ዐላውያን በቅጣት የሚያሠቃዩትን ክርስቲያናዊ ቸል አትበሉ ተብሎ በዲድስቅልያ በተደነገገው ቀኖና መሠረት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ቅዱስ ሲኖዶስ በተደጋጋሚ ልዩ ልዩ መግለጫዎች በማውጣት፣ ቅድስት ቤተ ክርስቲያን ልታደርግ የሚገባትን ሃይማኖታዊና ቀኖናዊ ሥርዐት በማከናወን ላይ ትገኛለች፡፡
በሁሉም ዘንድ እንደሚታወቀው የሁሉም ሃይማኖቶች ተልእኮ ሰውን ማዳን እንጂ ሰውን መግደል እንዳይደለ ቢታመንም ንጹሓን ዜጎችን በሃይማኖት ምክንያት በአሠቃቂ ግድያ የመግደል ወንጀል በዓለማችን መታየት ከጀመረ ሰነባብቶአል፡፡ ኢትዮያውያን ወገኖቻችንም በተለያየ ጊዜና በተለያየ አካባቢ የዚህ ዐይነቱ ግድያ ሰለባ መሆናቸው አልቀረም፡፡ ከዚህ አንጻር በዚህ ሰሙን በሊቢያና በደቡብ አፍሪካ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን አማኞች በሆኑት ልጆቻችን ላይ የተፈጸመው አሠቃቂ ግድያ ከምንም ጊዜ በላይ ቤተ ክርስቲያናችንን፣ ሀገራችንንና ሕዝባችንን ያሳዘነና ያሳሰበ ጉዳይ ሆኖ ተገኝቶአል፡፡
የተፈጸመው አሠቃቂ ድርጊት በኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተ ክርስቲያን ላይ ብቻ ሳይሆን በሁሉም የዓለም ሃይማኖቶች ላይ የተቃጣ የወንጀል ተግባር መሆኑን በማመን መላው የሀገራችን ሕዝቦችና የሃይማኖት ተቅዋማት እንደዚሁም መላው የዓለም መንግሥታት ይህን ድርጊት በጽኑ መቃወምና ማውገዝ ይጠበቅባቸዋል፡፡ ቤተ ክርስቲያናችንም የተፈጸመውን ድርጊት ፈጽሞ ታወግዛለች ከመንግሥትና ከሕዝብ ጋር ተሰልፋም የሚጠበቅባትን ሁሉ ለማድረግ ዝግጁ መሆኗን ታረጋግጣለች፡፡
ቀደም ሲል በመግለጫችን እንደተነገረው የአሸባሪዎች የጥፋት ዕልቂት ሃይማኖትን፣ ቀለምን፣ ጾታንና አካባቢን ሳይለይ በአጠቃላይ በሰው ዘር ላይ የዘመተ የጥፋት ተልእኮ ስለሆነ ሁሉም የሃይማኖት መሪዎችና የፀረ ሽብር ተቅዋማት ለዓለማችን ሰላም መረጋገጥና ለሰው ልጆች በሕይወት የመኖር መብት መከበር ተባብረው እንዲሠሩ ቤተ ክርስቲያናችን በአጽንዖት ትጠይቃለች፤
የኢትዮጵያ መንግሥት ከዓለም ዐቀፍ ማኅበረ ሰብና ከየሀገሩ መንግሥታት ጋር በመሆን የሚያካሂደውን የፀረ ሽብር እንቅስቃሴ አጠናክሮ በመቀጠል የዜጎቻችን ሕይወት በአሸባሪዎች እንዳይቀጠፍ ከእስከ አሁኑ በበለጠ እንዲንቀሳቀስ፤ ሕዝቡም ከአሁን በፊት በበጎ ታሪካችን እንደሚታወቀው በሃይማኖትና በሌላው ሁሉ ሳንለያይ ጠብቀን ያቆየነውን በአንድነት፣ በፍቅርና በመቻቻል የመኖር ዕሴት አሁንም አጥብቀን በመያዝ የጋራ ጠላት የሆነውን ግብረ ሽብር በመመከት ራሱንና ሀገሩን ከአሸባሪዎች ነቅቶ እንዲጠብቅ ቤተ ክርስቲያናችን ታሳስባለች፤
የሟዋች ቤተሰቦች የሆናችሁ ወገኖቻችን ሁሉ በዚህ ግፍ የተሞላበት ጭካኔ የተገደሉት ልጆቻችን በዚህ ዓለም የመኖር ተስፋቸው ባጭሩ ቢቀጭም ጌታችን መድኀኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ የተገፉ መንግሥተ ሰማያትን ይናጠቋታል ማለትም ይወርሱአታል ባለው አምላካዊ ቃል መሠረት እግዚብሔር ዕንባቸውን አብሶ በመንግሥቱ የሚቀበላቸው መሆኑን ዐውቃችሁ፣ ቤተ ክርስቲያንም ለሰማዕታቱ የአንድ ሳምንት የጸሎተ ፍትሐት ያወጀች መሆኑንና ሰማዕታቱን በሚገባቸው ክብር ለማክበር የሚገባትን ሥርዐት የምታከናውን መሆኑን ተረድታችሁ ልትጽናኑ ይገባችኋል፡፡
ከዚሁ ጋር ለማሳሰብ የምንወደው ጉዳይ ማንኛውም ኢትዮጵያዊ ዜጋ በሕገ ወጥ መንገድ ከሀገር ከመውጣት፣ አስተማማኝ የሕይወትና የንብረት ዋስትና ወደሌለበት ሀገር ከመሄድ ተቈጥቦ በሀገሩ ሠርቶ ኑሮውን እንዲመራ ቤተ ክርስቲያን የምትመክር መሆኑን እናስገነዝባለን፤
ክቡራንና ክቡራት፡ የተወደዳችሁ የሀገራችን ሕዝቦች
ሞትን ለመጀመሪያ ጊዜ የቀመሰው አቤል የተገደለው በወንድሙ በቃየል እጅ ነበር፡፡ እግዚአብሔር አምላክ ግን በዐመፅና በክፋት ተመልቶ ወንድሙን አቤልን የገደለ ቃየልን ከነጥፋቱ እንዲሠወር አልፈቀደም፡፡ ይልቁንም ገዳዩን “ወንድምህ አቤል ወዴት ነው? አቤል ምን አደረገህ?” የወንድምህ የአቤል የደሙ ድምፅ ከምድር ወደ እኔ ይጮሃልና ብሎ ጠይቆታል፡፡ (ዘፍ 4፥10)
ስለዚህ ዛሬም በግፍና በጭካኔ የተመሉ አሸባሪዎች ከፈጣሪን ጥያቄና ፍርድ ፈጽመው እንደማያመልጡ እናምናለን፡፡ ምክንያቱም ፈጣሪ የወንድሙን ደም ያፈሰሰውን ቃየልን የወንድምህን ደም ከእጅህ ለመቀበል አፍዋን በከፈተች በምድር ላይ አንተ የተረገምህ ነህ፣ በምድር ላይ ኮብላይና ተቅበዝባዥ ትሆናለህ በማለት በቃየል ላይ ፈርዷልና ነው፡፡ ይህ አምላካዊ ፍርድ ዛሬም ወንድሞቻቸው የሚሆኑ የንጹሓን ወጣቶችን ሕይወት ያለርኀራኄ የቀጠፉ አሸባሪዎች ከዚህ ሰማያዊና ምድራዊ ፍርድ እንደማያመልጡ እምነታችን የጸና ነው፡፡ ስለዚህ እኛም በዛሬው ዕለት በወገኖቻችን የደረሰውን አሠቃቂ ወንጀል ልባችንን ስለነካው አቤል ወዴት አለ ብሎ የተገደለውን እንደፈለገው ፈጣሪ ወንድሞቻችን ወዴት አሉ ብለነን ሁላችንም ከመኖሪያ ቤታችን ከሥራችን ወጥተን ይህንን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ለመቃወምና ለማውገዝ ወደ አደባባይ መውጣታችን ሰውን በሚወድ በፈጣሪ ፊት የሚያስመሰግን ነው፡፡
ክቡራንና ክቡራት፥ የተወደዳችሁ የሀገራችን ሕዝቦች
ይህ በወገኖቻችን ላይ የደረሰውን አሠቃቂ የወንጀል ድርጊት ከሰው ልጅ ተፈጥሮኣዊ ተግባር የወጣ ደረቅ ወንጀል ስለሆነ፣ ልንቃወምና ልንመክት የምንችለው በጥልቀትና በተረጋጋ መንፈስ በመሆን በመላው ዓለም ካሉ ከፀረ ሽብረ ግብረ ኀይላት ጋር በመተባበር ስለሆነ በትዕግሥትና በጥበብ የሰው ልጅ ሉዓላዊ ክብር እንዳይጣስ በነፃነት ሊኖርባት በተሰጠችው ምድር የሕይወት ዋስትና እንዲኖረው ለማስቻል ሁሉም ነቅቶና ተግቶ ኀላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን፡፡
ወስብሐት ለእግዚብሔር እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቦቿን ይባርክ!